Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቻይና ፕሮጀክቶች ከ111 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

እ.ኤ.አ. ከ1970 ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገረው የቻይና መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እያደረገ ባለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለ57,555 ቋሚና ለ53,669 ጊዜያዊ፣ በአጠቃላይ ለ111,224 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ተጠቆመ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ሐሙስ ግንቦት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የቻይና ባለሀብቶች በ674 ፕሮጀክቶች ላይ በመሰማራት ከ3.86 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ እያፈሰሱ ነው፡፡

ሁለቱ አገሮች በንግድ ዘርፍ ለመተባበር የሚያስችል ስምምነት እ.ኤ.አ በ1996 የተፈራረሙ መሆኑን አቶ መለስ አስታውሰው፣ የንግድ ምጣኔውም እ.ኤ.አ. በ2004 357 ሚሊዮን ዶላር የነበረው እ.ኤ.አ. በ2015 ብቻ 6.37 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የሁለቱ አገሮች የንግድ ምጣኔ በየዓመቱ በአማካይ 22.2 በመቶ እያደገ ነው ብለዋል፡

ኢትዮጵያና ቻይና የልማትና የቴክኒክ ትብብር የተፈራረሙት እ.ኤ.አ. በ1971 እንደሆነ የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፣ የትብብር ዓይነቱና ስትራቴጂያዊ አጋርነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ የቻይና ኢኮኖሚ እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ብድር የመስጠት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን የገለጹት አቶ መለስ፣ ቻይና ከወለድ ነፃ ብድርና ዕርዳታ ብቻ ሳይሆን በገበያ ዋጋ የንግድ ብድር ወደ መስጠት እየተሸጋገረች በመሆኑ ኢትዮጵያም የዕድሉ ተጠቃሚ ሆናለች ብለዋል፡፡

ከቻይና በተገኘው የልማት ዕርዳታ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ ከእነዚህም መካከል የወረታ-ወልዲያ መንገድ፣ የዕድገት የክር ፋብሪካ፣ የሃሬ መስኖ ልማት፣ የአዲስ አበባ የቁጠባ ቤቶች ግንባታ፣ የኮል ፎስፌት የማዳበሪያ ፋብሪካ ማቋቋሚያ ጥናት፣ የአዲስ አበባ ቀለበት መንገድ፣ የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ጥናት፣ የወሎ ሠፈር-ጎተራ መንገድ ግንባታ፣ የሐዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የማሽነሪ ግዥ፣ የግብርና የቴክኒክና የሙያ ትምህርት የቁሳቁስ ዕርዳታ፣ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርና የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ተጠቃሾች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከግንቦት 13 ቀን 2017 ጀምሮ በቻይናና በሌሎች የእስያ አገሮች መሥራችነት እ.ኤ.አ. በ2012 የተቋቋመው ‹‹ኤዥያ ኢንፍራስትራክቸር ኢንቨስትመንት›› አባል በመሆኗ፣ ባንኩ አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ እንደሚሆንላት ተገልጿል፡፡

በቅርቡ ቻይና ተካሂዶ በነበረው ‹‹ቤልት ኤንድ ሮድ›› ፎረም ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በቆይታቸው ቻይና ውስጥ ከሚገኙ 17 ታላላቅ ኩባንያዎች ጋር የአንድ ለአንድ ውይይቶችን በማካሄድ፣ ስለኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ገለጻና ማብራሪያ መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች