Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊእንደ አዲስ ለመቋቋም የመንግሥትን ውሳኔ የሚጠባበቀው የካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ በሠራተኞች ፍልሰት መቸገሩን...

  እንደ አዲስ ለመቋቋም የመንግሥትን ውሳኔ የሚጠባበቀው የካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ በሠራተኞች ፍልሰት መቸገሩን አስታወቀ

  ቀን:

  • የመስክ ተሽከርካሪዎች እጥረት በሥራዬ ላይ እንቅፋት ሆኖብኛል ብሏል

  ከተመሠረተ 71 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ፣ እንደ አዲስ ለመቋቋም ከስያሜ ጀምሮ ለውጥ የሚያደረግበትን ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ ለማፀደቅ እየተጠባበቀ ቢሆንም፣ ከፍተኛ የሠራተኞች ፍልሰት እዳስቸገረው አስታወቀ፡፡

  የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሱልጣን መሐመድ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ተቋሙ በሙሉ አቅሙ ለመሥራት የሚያስፈልገው የሰው ኃይል 600 ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጠናና የሥራ ልምድ ያካበቱ 250 ሠራተኞቹ ወደ ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ፈልሰውበታል፡፡ በቀሩት 350 ሠራተኞች የሚጠበቁበትን ሥራዎች ለመፈጸም ቢታገልም፣ ያሉትንም ለማቆየት የሚቻልባቸውን ማሻሻያዎች ማድረግ ግድ እንደሚል አቶ ሱልጣን አሳስበዋል፡፡

  ከሚለቁት ሠራተኞች ውስጥ አብዛኞቹ በሚከፈላቸው የወር ደመወዝ ዝቅተኛነት ምክንያት ለመልቀቅ እንደሚገደዱ በተደረጉ ውይይቶች ወቅት መረዳታቸውን ያስታወቁት አቶ ሱልጣን፣ ይሁንና ሁሉም ሠራተኞች ግን ተመሳሳይ ሥራ ወደሚሠሩና ከኤጀንሲው የተሻለ የደመወዝ ስኬልና ጥቅማ ጥቅም ወዳላቸው የመንግሥት ተቋማት ይሄዳሉ ብለዋል፡፡ እንደ ብሔራዊ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) እና እንደ ቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ያሉ መሥሪያ ቤቶች ከኤጀንሲው ጋር ተመሳሳይ ሥራ የሚያከናውኑ ቢሆኑም፣ ከካርታ ሥራዎች ይልቅ ከፍተኛ የደመወዝ ስኬል ስላላቸው ሠራተኞች እየለቀቁ እንደሚሄዱ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም ኤጀንሲው ተመጣጣኝ የደመወዝ ስኬል እንዲኖረው የሚያስችል ጥናት አጥንቶ ለመንግሥት ማቅረቡንም አቶ ሱልጣን ጠቁመዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪ ኤጀንሲው ለመስክ ሥራ የሚያስፈልጉትን ተሽከርካሪዎች በበቂ መጠን ማግኘት ካለመቻሉም በላይ፣ ያሉትም ቢሆኑ አብዛኞቹ ከ30 ዓመታት በላይ ያገለገሉ በመሆናቸው ጫና ውስጥ እንደከተቱት ተገልጿል፡፡ እንደ አቶ ሱልጣን ማብራሪያ፣ ተቋሙ ካሉት 20 የመስክ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 15 ያህሉ 30 ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ የተቀሩት አምስቱም ቢሆኑ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የተገኙ መሆናቸው ታውቋል፡፡ 

  እንዲህ ያሉ ችግሮቹን በመቅረፍ ዓለም የሚገኝበት ዘመናዊ የካርታ፣ የቅየሳ፣ የሪሞት ሴንሲንግ ሥራዎችን በማጠቃለል ዘመናዊ የመልከዓ ምድር መረጃዎችን (ጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን) በጥራትና በቅልጥፍና ለማቅረብ ከስያሜ ጀምሮ የአደረጃት ለውጥ ለማድረግ የሚያስችለውን የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ለማፀደቅ እየተጣበቀ ይገኛል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ ኤጀንሲው ተጠሪ ለሆነበት ለብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን አቅርቦ እንደታመነበትና የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያፀድቀው አቶ ሱልጣን እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

  85 በመቶ የአገሪቱን ክፍሎች የሚሸፍን 1፡ 50,000 መሥፈርት ካርታን ወደ 1፡25,000 ለማሻሻል እየሠራ እንደሚገኝ ያስታወቀው ኤጀንሲው፣ በአሁኑ ወቅት በአናሎግ ደረጃ የነበሩ የአገሪቱን ካርታዎች ወደ ዲጂታል መቀየር እንደቻለም አስታውቋል፡፡

  ከ71 ዓመታት በፊት በአሜሪካ መንግሥት እገዛ የተመሠረተው ኤጀንሲው ለመመሥረቱ ምክንያት የሆነውም በዓባይ ሸለቆ ውስጥ ይካሄዱ የነበሩ የጥናትና የቅየሳ ሥራዎች መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡ አሜሪካውያኑ ኤጀንሲው ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የሚያበቃውን የቅየሳና የካርታ ሥራ እንደሠሩም ይነገራል፡፡ ይሁንና በ1973 ዓ.ም. በአዋጅ በመቋቋም፣ በ1980 ዓ.ም. የተቋቋመበት አዋጅ መጠነኛ ማሻሻያ ተደርጎበት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በዚሁ አግባብ ከ30 ዓመታት በላይ የዘለቀው የካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ፣ በ2003 ዓ.ም. ባደረገው ጥናት መሠረት ማሻሻያዎች ሊደረጉለት እንደሚገባ አስታውቆ ነበር፡፡

  የካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት የልዩ ተግባር፣ ጠቅላላ መሠረታዊ ካርታዎችን ማምረት፣ የቅየሳ መቆጣጠሪያ ነጥቦችን ማስፋፋት፣ በተለያየ ወቅት የተነሱ የአየር ፎቶግራፎችንና የሳተላይት ምሥሎችንና ሌሎችንም ምርቶችና አገልግሎቶች እያቀረበ ይገኛል፡፡

   

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img