የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 1/2009ን ተላልፈዋል በሚል ኅዳር 8 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋሉትና ላለፉት ሰባት ወራት በእስር ላይ የነበሩት፣ የቀድሞ አንድነት ለፍትሕና ዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) አመራር አቶ ዳንኤል ሺበሺና አቶ ኤልያስ ገብሩ (ጋዜጠኛ) ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
ተከሳሾቹ አዋጁን በመተላለፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕርምጃ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 1/2009 አንቀጽ 2(1) እና (2)ን መተላለፋቸውን፣ ከሳሽ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ካዲስኮ አካባቢ ተይዘው ሲፈተሹ፣ አቶ ዳንኤል ጥቁር ህዋዌ ሞባይል ስልክ ይዘው ተገኝተዋል፡፡ በጋዜጠኝነት ለበርካታ ዓመታት የሠራው አቶ ኤልያስ ደግሞ ሳምሰንግ ሞባይል ይዞ እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡
በአቶ ዳንኤል ሞባይል ስልክ ውስጥ ‹‹ተማምሏል ጎንደር›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ቪዲዮ፣ የግንቦት ሰባት አመራሮች ምሥልና ዓርማ የሌለው ሰንደቅ ዓላማ መገኘቱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ የአዋጁን አንቀጽ 12(1)ና መመርያ ቁጥር 1/2009 አንቀጽ 2(3) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ አቶ ዳንኤል፣ የኢሳት ቴሌቪዥንን ፕሮግራሞች ቪዲዮና ለቴሌቪዥን ጣቢያው የሰጡትን መግለጫ ሪፖርት በስልካቸው ውስጥ መገኘቱን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም አቶ ዳንኤል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የከለከላቸውን ድርጊቶች ተላልፈው በመገኘታቸው፣ ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት ማድረግ ወንጀልና የሽብርተኛ ድርጅቶች ሚዲያዎችን መከታተልና ሪፖርት ማድረግ ወንጀል መከሰሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡
አቶ ኤልያስ ሲፈተሽ በተገኘው የሳምሰንግ ሞባይሉ ውስጥ የኢሳት አመራሮች ምሥሎች፣ የሽብርተኛ ድርጅቶችን ሐሳብ የሚገልጹ ጽሑፎችና ምሥሎች መገኘታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ሌላው በሞባይሉ ውስጥ የተገኘው፣ ‹‹መለስ ብዙኃኑን የማጥፋት ሴራ፣ ትግሬን ታላቅ የማድረግ ቅዥት፣ ፀረ አማራ፣ የሁሉም ድክመት ተጠያቂ አማራ ነው ብሎ የሚያስብ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ተባብሮ ቡናን ብቻ ባለመሸጥ ማዕቀብ ቢጥል ለመቀሌ ዘይት መግዣና ለሕዝባችን ጥይት መግዣ… በመቸገር የሚንበረከክ ወያኔ እናያለን…›› የሚል መጣጥፍ መገኘቱን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም፣ ‹‹ጎንደር በወራሪው ሕወሓት ሠራዊት ተወረረች…፣ ትምህርት ከድል በኋላ፣ በትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደባችሁ ተማሪዎች እንዳትሄዱ…›› የሚሉና የትግራይ ክልል ከድሮው የሰፋ መሆኑን የሚያሳይ የካርታ ምሥልና ይዞታ መገኘቱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በመሆኑም መቻቻልንና አንድነትን የሚጎዳ ተግባር በመፈጸም ወንጀልና ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት በማድረግና በማስተዋወቅ ወንጀል ክስ መመሥረቱን ገልጿል፡፡
ተከሳሾቹ በጠበቃቸው አማካይነት ባቀረቡት ተቃውሞ አንድ ድርጊት ወንጀል ነው ለማለት ክልከላና የቅጣትን መጠን ማስቀመጥ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሕግ መርህ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይም ሆነ ማስፈጸሚያ መመርያም ላይ የተቀመጡ አንቀጾች የያዙት በአዋጁ የተከለከሉትን መተላለፍ እንደማይቻል ብቻ የሚገልጹ መሆኑን ተከሳሾቹ ገልጸው፣ በማመሳሰልና በማቀራረብ (አናሎጂ) አንድ ሰው ሊከሰስ እንደማይችል አስረድተዋል፡፡
ሌላው በአዋጁ መመርያ 1/2009 አንቀጽ 2(1) እና (2) ስር የነበሩት ክልከላዎች በመመርያ ሁለት ቀሪ የተደረጉ በመሆናቸውና ሕግ ወደኋላ ሄዶ ሊሠራ ስለማይችል ሊከሰሱ እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡
ክልከላ ወንጀል ካለመሆኑም ሌላ፣ እነሱ ደግሞ የተከለከሉትን ተላልፈዋል በሚል ከስድስት ወራት በላይ ስለታሰሩ በነፃ ሊሰናበቱ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ምላሽ እንዲሰጥ ሲጠይቀው፣ ‹‹ተከሳሾች ሕግ ጠቅሰው ስለተከራከሩ ምላሻችንን በጽሑፍ እናቅርብ›› በማለቱ፣ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ ለግንቦት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡