Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርበቆጠራ የተገኙት የኮንዶሚኒየም ቤቶች እንኳ ለዕጣ ይቅረቡልን እንጂ!

በቆጠራ የተገኙት የኮንዶሚኒየም ቤቶች እንኳ ለዕጣ ይቅረቡልን እንጂ!

ቀን:

በብሩክ ፈለቀ

የቤት ባለቤት እሆናለሁ በማለት ምዝገባ ያካሄዱ አዲስ አበቤዎች አሥራ ሦስት ዓመት ሊሞላቸው ምንም አልቀረውም፡፡ እነኚህ በሺዎች የሚቆጠሩ ተስፈኞች በየጊዜው የሚሰሙት ነገር ተስፋ የሚያስቆርጥ እንጂ፣ ወደተመኙት ቤታቸው ደጅ የሚያስጠጋ ሆኖ አላገኙትም፡፡

በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው ኑሮአቸውን እየገፉ ቢገኙም፣ ያኔ ሲመዘገቡ ካለሙት ውስጥ አንዱም እንደማይሆንላቸው ነፍሳቸው ብቻ ሳትሆን ነባራዊ እውነታዎች በገሃድ እያሳዩዋቸው ይገኛሉ፡፡

- Advertisement -

ያኔ ሲመዘገቡ ቤት የሚደርሳቸው ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን፣ ሥራቸውን፣ የትራንስፖርት ወጪያቸውን በማያዛባ ሁኔታ መሀል ከተማ መኖሪያቸውን እንደሚያደርጉ አልመው ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ቆመው ሲያዩት ሲያልሙት የነበረው በሙሉ ህልም ሆኖ ቀርቷል፡፡ በእርግጥም የሰው ፍላጎትና የቤቶቹ ግንባታ አቅም የተራራቀና ዕጣ ያልወጣላቸው ቢሆንም ከእነሱ በኋላ አዲስ አበባን የረገጡ፣ መኖሪያ ቤት ያላቸው፣ በልማት ተነሺዎች ስምና ለመጠባበቂያ ተብለው በተተው ቤቶች ላይ የእነሱን ዕድልና ህልም ነፍገው የቤት ባለቤት የሆኑ ሰዎችን ተመልክተዋል፡፡ ይህም ተስፋ መቁረጥ፣ በኑሮአቸው መንገፍገፍና የአዲስ አበቤነት ፋይዳን ዜሮ አድርጎባቸዋል፡፡

ያኔ ሲመዘገቡ እንደ አቅማቸው ነበር፡፡ በቤቶቹ ግንባታ ፍጥነትና አካሄድ ላይ ችግር በመከሰቱ የጊዜ ቆጣሪ ቆሞ አልጠበቃቸውምና ዋጋው ዛሬ ላይ እንደ አንዳንዶቹ አባባል ከ500 በመቶ በላይ ጨምሯል፡፡ ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው ቤቶች (Low Cost Houses) ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ታሳቢ ያደረገ ቢመስሉም ከአቅማቸው በላይ ሆነዋል፡፡

1997 ዓ.ም. ሲመዘገቡ የነበረው አካሄድ ቤቶቹ ተገንብተው ዕጣ ሲደርሳቸው 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ አከናውነው ቤታቸውን እንደሚረከቡ ነበር፡፡ በዚህም አካሄድ በመጀመሪያ ዙር አካባቢ የደረሳቸውን ወንድም እህቶች፣ ዘመዶችና ወዳጆች ሁሉ ቅድሚያ ክፍያውን የመክፈል አቅም እንዲያበጁ በባህላችን መሠረት ረድተናቸዋል፣ ዕቁብ ጥለንላቸዋል፣ የቤት ባለቤትም ሆነዋል፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የማኅበረሰቡ ክፍል የመጀመሪያውን አካሄድ የሚመርጥበት ምክንያትም አማራጮችን ስለሚሰጡት ነው፡፡ ይህ ማኅበረሰብ ትዳርና ልጆች አሉበት፡፡ የቤት ኪራይና አስቤዛ አለበት፡፡

በእርግጥም ዕለታዊ ኑሮውን ሸፍኖ መቆጠብ ከቻለ እሰየው፣ ካልሆነ ግን ዕጣው ሲደርሰው ከመሥሪያ ቤቱ ተበድሮ፣ በዘመድ ወዳጅ ተረድቶም ሆነ ዕቁብ ተጥሎለት የቤት ባለቤት ይሆን ነበር፡፡ ይህ ያልሆነለትና ከአሥር ዓመት በላይ የጠበቀ ዕድለ ቢስ  ግን የበፊቱ ዕድል ተሽሮበትና የውል ማሰር ፍልስፍናም በሉት አሠራር ባልተረጋገጠበት ሁኔታ፣ የውዴታ ግዴታ ውስጥ ለመግባት ተገደደ፡፡ የቻለም ከራሱም ከልጆቹም ጉሮሮ ነጥቆና ተስፋኛነቱ አሸንፎት ዘልቋል፡፡ መቆጠብ አቅቶትም የቤት ባለቤትነት ተስፋውን ያጣውም ቤቱ ይቁጠረው፡፡

አገሪቱ በያዘችው የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ምስቅልቅል ሒደት መሀል ደግሞ ግልጽና ጥረት ያለ መነሻ ሐሳብ የሌለው የ40/60 ፕሮጀክት መጀመሩ ደካማውን የ1997 ዓ.ም.  ተስፈኛ ተመዝጋቢ ኩምሽሽ ያደረገ ነበር፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የነባር የ20/80 ተመዝጋቢዎች እንረሳለን የሚል ፍርኃት ነበር፡፡ እውነትም በአሁኑ ጊዜ አሥራ ምናምን ዓመት ሲጠብቁ የነበሩ አዲስ አበቤዎች ሊሰጣቸው የሚገቡ ሁነኛ ቦታዎች በ40/60 ፕሮጀክት ተወረው እየተመለከትን ነው፡፡ የ20/80 ነባር ፕሮጀክቶች  ተገፍተው ምድረ በዳ በሆኑ የአዲስ አበባ ዳርቻዎች መጣላቸውን ዓይተናል፡፡ ይህን ድንጋጤና ፍራቻ አሜሪካ በጥገኝነት የገቡ ስደተኞች በዲቪ ሎተሪ የሄዱ ስደተኞችን ከሚመለከቱበት ሁኔታ ጋር የሚያነፃፅሩ ሰዎች እንደ ምቀኛ ሲቆጥሩት ይታያል፡፡ እውነታው ግን ዳቦ ለመግዛት የተሠለፉ ሰዎች ዳቦ ቤቱ ሲከፈት የሽያጩ አስተባባሪ ዕደላውን ከኋላ ከተሠለፉት ሰዎች ቢጀምር፣ ማንኛውም ከፊት ተሠልፎ የነበረ ሰው የሚሰማው ስሜት ይመስለኛል፡፡

የተለያዩ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መስተጋብሮች በተፈጠሩ ቁጥር የእነሱ ዕጣ ፈንታና የተስፋቸው መዳረሻ ሊሆኑ የሚችሉ ቤቶች ለሌሎች ሲተላለፉ መመልከትም ሕመም ሆኖባቸው ከርሟል፡፡ እንደ ዜጋ እነኚህ ነባር ተመዝጋቢዎች የመንግሥት ሠራተኛ፣ ነጋዴ፣ የቀን ሠራተኛ የፈለጉትን ቢሆኑም መለያቸው አንድ ያደርጋቸዋል፡፡ የአገሪቱ ዜጎች ናቸው፡፡ አገሪቱ ላይ የሚፈጠሩ የኑሮ ውድነት፣ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የፖለቲካ ውዝግብ፣ ወዘተ እኩል ይነካቸዋል፡፡

ለፖለቲካዊ ፋይዳ ሲባል ብቻ ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ ለመንግሥት ሠራተኛ፣ ለመከላከያ፣ ለፖሊስና ለመሳሰሉት በኮታ ቤቶች መታደላቸው ገለልተኛ ሆነን ብናስበው ሚዛናዊ የሆነ ፍርድ አይመልስም፡፡ በእርግጥም ነባር ተመዝጋቢ የነበሩና  በተፈጠሩ የኮታ ዕድሎችና ምክንያቶች የቤት ባለቤት የመሆን ዕድል የገጠማቸው ይኖራሉ፡፡ ብዙዎቹ የኮታውን ምክንያታዊነት ከነባር ተመዝጋቢዎች አንፃር ትክክል አለመሆን ቢመሰክሩም፣ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የኮታ ዕደላውን ተዓማኒነት የሚጠራጠሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

ወጣም ወረደም ባለፉት ዙሮች ዕጣ ያልደረሳቸው ነባር ተመዝጋቦዎች ቁጠባውን ያቋረጡትን ባይመለከትም ዕጣ ፈንታ መጨረሻ መገመት የሚከብድ ሆኗል፡፡ ባለፈው ሰሞን ቆመው የነበሩት የቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች በጀት ተፈቅዶላቸው መንቀሳቀስ መጀመራቸው ለተስፈኞች የተስፋ ጭላንጭል የሰጠ ቢሆንም፣ ማኅበረሰቡ ምንም ዓይነት  ግልጽ የሆነ መረጃ የለውም፡፡ ይህም ከቤተሰቡ ጉሮሮ እየነጠቀና ራሱ ከተጣመመ ጫማና ከነተበ ሸሚዝ፣ ልጆቹን በኤርገንዶ መጫሚያ ያለ ምሳ የሚልከው ነባር ተመዝጋቢ እስከ መቼ በተስፋ በማለት ቁጠባውን እንዳያቋርጥ (ያቋረጡትንም ቤቱ ይቁጠራቸው) የብዙዎች ፍራቻ ነው፡፡

የዚያን ሰሞን የቆጠራ ውጤት አወዛግቦ ቢያልፍም በዕጣ ከተላለፉ ቤቶች በፍተሻ ሰበብ የተገኙ ሦስት ሺሕ አካባቢ የሚጠጉና በሕገወጥነት የተያዙ ቤቶች በመጨረሻው ዙር ዕጣ አወጣጥ ላይ እንዳልገቡ ቢነገርም፣ ምን እንደታሰበላቸው ግልጽ አይደለም፡፡ የእነዚህ ቤቶች ባለ ዕድል መሆን ያለባቸው ደግሞ ነባር ተመዝጋቢዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም በሕግ አምላክ!! በቆጠራ የተገኙት የኮንዶምንየም ቤቶች እንኳ ለዕጣ ይቅረቡልን!!! የነባር ተመዝጋቢዎች ድምፅ ይሰማ!!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡      

                                                 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...