Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት የተፈጥሮ ማዕድን ውኃ ፋብሪካ በደብረ ብርሃን ሥራ ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በደብረ ብርሃን ከተማ ጫጫ አካባቢ በ30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባና በሰዓት 12 ሺሕ ጠርሙስ ውኃ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በ83 ሚሊዮን ብር ወጪ ተቋቁሞ ሥራ ጀመረ፡፡

ታምሬና ቤተሰቡ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤትነት የተቋቋመው ፋብሪካ፣ አልፋ የተፈጥሮ የማዕድን ውኃ የሚል ሥያሜ የተሰጠውን የታሸገ ውኃ በማምረት ገበያውን የተቀላቀለው ከጥቂት ቀናት በፊት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በ0.6 ሊትር፣ በአንድና በሁለት ሊትር በማሸግ የሚያቀርበው ውኃ ምንም ዓይነት ኬሚካልም እንደማይጨመርበትና የእጅ ንክኪ ሳይኖረው እንደሚመረት የአልፋ የተፈጥሮ ማዕድን ውኃ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ጣሰው አብተው አስታውቀዋል፡፡

አቶ ጣሰው እንዳሉት፣ ከአዲስ አበባ በ110 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ደብረ ብርሃን ከተማ አቅራቢያ፣ ጫጫ ከተባለው አካባቢ በሚገኘው የከርሰ ምድር ውኃ ላይ በተደረገ ጥናት ውኃው ከፍተኛ የጥራት ደረጃዎች ያሉትና በማዕድን ይዘቱም የዓለም የጤና ድርጅት መሥፈርቶችን በሚያሟላ ደረጃ አሟልቷል፡፡ በመሆኑም ለአዋቂዎች ብቻም ሳይሆን ለጨቅላ ሕፃናት ምግብ ማብሰያነት ጭምር መዋል የሚችል መሆኑ ተረጋግጦ፣ የጥራትና የተስማሚነት ምዘናዎችን በማለፍ ማረጋገጫ ከመንግሥት እንደተሰጠው አቶ ጣሰው ገልጸዋል፡፡

የአልፋ ማዕድን ውኃ የምርት ጥራትና ቁጥጥር ኃላፊ አቶ ወንድሙ ከበደ በበኩላቸው፣ የማዕድን ውኃ ክሎራይድን ጨምሮ ምንም ዓይነት ኬሚካል ሳይጨመርበት በዘመናዊ የውኃ ማጣሪያዎች ጥራቱ ተጠብቆ እንደሚመረት አብራርተዋል፡፡ እንደ አቶ ወንድሙ ገለጻ ከሆነ፣ ጥሬ ውኃው ከከርሰ ምድር ተስቦ ወደ ማጣሪያ የሚገባው ውኃ ከአክቲቭ ካርቦን ማጣሪያ ጀምሮ እስከ ኦዞን ማጣሪያ ድረስ ባለው ረዥም ሒደት ውስጥ በማለፍ ሙሉ ሙሉ የተጣራ የተፈጥሮ ውኃ እየተመረተ ይገኛል፡፡

የውኃ ማምረቻው የሚለቀው ጥቅም ላይ የዋለው ውኃም በአካባቢ ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ የማያስከትል መሆኑ ተረጋግጦ የሚለቀቅ ሲሆን፣ ንፁህ በመሆኑም በፋብሪካው አቅራቢያ ለሚገኙ ገበሬዎች አትክልትና ፍራፍሬ ማምረቻነት እንዲውል መታሰቡን አቶ ወንድሙ አብራርተዋል፡፡ ወደፊት ኩባንያው በአትክልትና ፍራፍሬ አምራችነት የመሰማራት ዕቅድ ያለው በመሆኑም ጥቅም ላይ የዋለውን ንፁህ ውኃ ዳግመኛ የመጠቀም ፍላጎት እንዳለውም አክለዋል፡፡

ለምርት ማሸጊያነት የሚጠቀምባቸውን የፕላስቲክ ጠርሙስ መሥሪያ ፕሪ-ፎርም እንዲሁም የጠርሙስ ክዳን ከአገር ውስጥ አምራቾች እንደሚያገኝ ያስታወቁት ኃላፊዎቹ፣ የምርት መግለጫ ኅትመቶችን ግን ከውጭ እንደሚያስመጣ ጠቅሰዋል፡፡

ፋብሪካው ችግር ከሆኑበት መካከል የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንዱ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ግን በጣም አሳሳቢ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ይሁንና ይህንን ችግር ለመቀነስ 800 ኪሎ ቮልት ኃይል ያለው ጄነሬተር ለመትከል መገደዱን አቶ ጣሰው ተናግረዋል፡፡

በ93 ሠራተኞች ሥራ የጀመረው አልፋ ውኃ በሙሉ አቅሙ በሦስት ፈረቃ ማምረት ሲጀምር በቀን 290 ሺሕ ያህል ጠርሙሶችን የማምረት አቅም እንደሚኖረው ሲጠቀስ ይህንን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጀምር ተጠቅሷል፡፡ በመጪው ዓመት ማስፋፊያ በማካሄድ በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ በሰዓት 18 ሺሕ ጠርሙስ ለማምረት የሚችልበትን ፕሮጀክት እንደሚተገብር አቶ ጣሰው አብራርተዋል፡፡ በማስፋፊያው ወቅት አሁን የሚመሩትን ጨምሮ 18 ሊትር ውኃ መያዝ የሚችል ጠርሙስም ለገበያ ታሽጎ እንደሚቀርብ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

ከዚህም ባሻገር ወደ ጂቡቲ ውኃ ለመላክ የሚያስችለውን ጥናት ለማካሔድ እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ተብራርቷል፡፡ የጂቡቲ ገበያን ተመራጭ ከሚያደርጉት መካከል ከደብረ ብርሃን በ90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሸዋ ሮቢት በኩል የሚያልፈው የባቡር መስመር ለውጭ ገበያ ዋናው ታሳቢ ነው፡፡

ታምሬና ቤተሰቡ ኩባንያ በአብዛኛው በመጠጥ አከፋፋይነት ሥራ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በአብዛኛው በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን፣ የኢትዮ ቴሌኮም የሲም ካርድና የቫውቸር ዋና አከፋፋይ በመሆን እየሠራ የሚገኝ ኩባንያ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከ60 በላይ የታሸገ ውኃ ለማምረት የተመዘገቡ ፋብሪካዎች እንዳሉ ሲታወቅ ከእነዚህ ውስጥ ከ50 በላይ የሚሆኑት ምርት እንደጀመሩና ገበያው ውስጥ እንደሚገኙ ይገመታል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች