Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ብቃት አልባ ተሽከርካሪዎች ከመንገድ ይወገዱልን!

በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በድንገት በተደረገ የተሽከርካሪዎች ምርመራ የተገኘው ውጤት፣ የከተማችንን ተሽከርካሪዎችን ገመና ያሳየ ሆኖ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እንደ ተቆጣጣሪው መሥሪያ ቤት ገለጻ፣ ከ3,200 በላይ ተሽከርካሪዎች በድንገት በተደረገባቸው ፍተሻ፣ አንድ ተሽከርካሪ ሊያሟላ የሚገባውን ሁሉ በመያዝ ብቁ የሆኑት 600 ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ግን ከብቃት መለኪያዎች በታች ሆነዋል፡፡

እንዲህ ያለውን አኃዛዊ መረጃ በመረጃነቱ ብቻ የምናልፈው አይደለም፡፡ መረጃው ሊያስደነግጠን ብቻም ሳይሆን በርካታ ጥያቄዎችን እንድናነሳ የሚገፋፋን ነው፡፡ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሥር ከሚሉት ተሽከርካሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ የቴክኒክ ችግር ያለባቸውና ብልሽት የማያጣቸው፣ በየሄዱበት የሚገተሩ፣ መንገድ የሚያጣብቡ አሮጌዎች እንደሚበዙባቸው የሰሞኑ መረጃ ይመሰክራል፡፡ ይህንን መረጃ እንደሰማሁ ያሰብኩት ኢትዮጵያ በተሽከርካሪዎች አደጋ ያጣቻቸው፣ አሁንም ልታጣቸው የምትችላቸው ዜጎች ብዛት ነው፡፡

የትራፊክ አደጋዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በ2008 ዓ.ም. ብቻ ከአራት ሺሕ በላይ ዜጎች በመኪና አደጋዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በአሥር ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንብረቶች ወድመዋል፡፡ ከኢኮኖሚው ጉዳት በላይ በአደጋዎች ጢስ የስንቱ ሰው ቤት የሐዘን ማቅ እንደለበሰ ስናስብ፣ ጉዳቱ ከሚባለውም በላይ ከባድ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከደረሱት አደጋዎች ምን ያህሉ ብቃት በሌላቸው ተሽከርካሪዎች እንደሚደርስ መገመትም ብዙም ከባድ እንዳልሆነ አሮጌዎቹን መኪኖችን ያየ የሚመሰክረው ነው፡፡

ለማንኛውም በድንገት የተደረገው የተሽከርካሪዎች ምርመራ አብዛኛዎቹ ተሽከርካሪዎች ጤና የጎደላቸውና ብቃት በጎደለው አቋም ላይ እንደሚገኙ እየታወቀ በከተማችን መንገዶች እንደልብ ሲንቀሳቀሱ መታየታቸው ነው፡፡ ስለዚህ አገሪቱ በቀዳሚነቷ የምትሠለፍበት የትራፊክ አደጋ መንስዔዎች መካከልም ከአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስ፣ ከተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ጉድለት ጋር ተዳምሮ በሚታይ ችግር ሳቢያ የሚከሰት እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡

የአሽከርካሪዎች ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ ከሰሞኑ ከሰማነው መረጃ አንፃር  ከ70 በመቶ በላይ ተሽከርካሪዎች ጉድለት ያለባቸው ከሆኑ፣ የአደጋው ምንጮችም በአብዛኛው የተሽከርካሪዎች ብቃት እንደሆነ ያስገነዝበናል፡፡ ስለዚህ የተሽከርካሪዎች ብቃት ጉድለት የአደጋ ክስተት ምንጭ ከሆነም ይህንን ጉድለት ለመቀነስ ብርቱ ሥራ መሥራት ግድ ይሆናል፡፡

ከሰሞኑ መረጃ ሌላም የሚከነክን ነገር አለ፡፡ ድንገተኛ ፍተሻ የተደረገባቸውና ብቃት ይጎድላቸዋል ከተባሉት ከ2,600 በላይ ተሽከርካሪዎች ምን ተደረጉ? የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መላሽ ያጓጓል፡፡ የተሽከርካሪዎቹን በሽተኛነት ብቻ ለይቶ ግን ደግሞ ምንም ዓይነት ዕርምጃ ሳይወሰድባቸው ከተሰናበቱ፣ አደጋው እየከፋ እንዲሄድ በይፋ መፍቀድ እንደ ማለት ነው፡፡ መንግሥት ይፋ ያደረገው መረጃ ስለተወሰደው ዕርምጃ ሳይሆን፣ ስለተሽከርካሪዎቹ ብቃት አልባነት መጥቀሱም ይህንን ሥጋት ያባብሰዋል፡፡ በእርግጥም ጉድለታቸው እየታወቀ ያለ ምንም ዕርምጃ ከተለቀቁ ድንገተኛ ፍተሻው ትርጉም አይኖረውም፡፡ እንዲህ የሚደረግ ከሆነስ በትራፊክ አደጋ ይህንን ያህል ሰው አለቀ ለሚለው መርዶ ተጠያቂው ማን ሊሆን ነው? ድንገት ፍተሻው ጤናማውን ጤና ካጣው ለመለየትና በቁጥር ለማስታወቅ ሲባል ብቻ የተደረገ ከሆነ፣ ቀድሞውንስ መፈተሹ ለምን አስፈለገ?

ከመረጃው ሌላ ህፀፅ ልንመዝ እንችላለን፡፡ ጉድለት አለባቸው የተባሉት ተሽከርካሪዎች ዓመታዊ የተሽከርካሪዎች ምርመራን አልፈዋል ተብለው ለዚሁ ማረጋገጫ የተሰጣቸው እንደሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ከዚያ በኋላ በድንገት ምርመራ ሲደረግባቸው ግን ብቁ አለመሆናቸው ተረጋገጠ፡፡ ስለዚህ ይህንን የብቃት ማረጋገጫ ያገኙት በተገቢው መንገድ እንዳልሆነ ያሳብቃል፡፡

ስለዚህ የተሽከርካሪ ምርመራ እንዲካሂዱ አደራ የተሰጣቸው ባለፈቃድ ተቋማት፣ ምርመራውን ሲያደርጉ ጉድለት ያለበትን ተሽከርካሪ ብቁ ነው ብለው የምስክር ወረቀት ይሰጣሉ ማለት ነው ወይ ያስብላል፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ የተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች ተሽከርካሪውን ለማስመርመር ሲቀርቡ ምዘናውን ለማሟላት በጊዜያዊነት ከሌሎች በመዋስ ተክለው የብቃት ማረጋገጫ ወስደዋል ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ በዓመታዊ የተሽከርካሪዎች ምርመራ ወቅት ጎዶሎ የተሽከርካሪ አካላትን በተውሶ በመሙላት ጤናማ ለማስመሰል የሚደረገው ዓይን ያወጣ ተግባር የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህን ተግባር ተቆጣጥሮ ዕርምጃ ባለመወሰዱም የችግሩ ምንጭ ዘርፈ ብዙ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ስለዚህ የአገሪቱን የትፊክ አደጋዎች ቁጥር እንዲጨምር ከሚያደርጉት ውስጥ አንዱ የአገልግሎት አሰጣጡ ያለበት ክፍተት እንደሆነ ያስገነዝበናል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጣችን አደጋ ከመድረሱ በፊት ቀድሞ በመገመት የመቆጣጠሩ ሥራ በትክክል በአግባቡ ሊተኮርበት እንደሚገባ ያሳየናል፡፡

የመንጃ ፈቃድ አሰጣጡ አሁንም ሊፈተሽ የሚገባው ነው፡፡ እርግጥ ነው ሥርዓቱን ለመቀየር ረቂቅ ሕግ እየተብላላ እንደሆነ እንሰማለን፡፡ የአሽከርካሪ ማሠልጠኛዎች፣ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ምርመራ ሰጪዎች ድርጅቶችና ሌሎችም ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ብቃት አልባ ተሽከርካሪዎችን ከመንገድ የሚያስወጣ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት