Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየአዲስ አበባን ፅዳትና ውበት የሚያጠፋ እንከኖች

የአዲስ አበባን ፅዳትና ውበት የሚያጠፋ እንከኖች

ቀን:

በሮቤ ባልቻ

130 ዓመታት አካባቢ ዕድሜ ያላት አዲስ አበባ፣ በስፋት እንጂ በፅዳትና ውበት ብዙም እንዳላደገች የሚያነሱ ጸሐፍት እያለፉ አስተያየቶች ሲሰነዝሩ እናያለን፡፡ አስተያየቶቹም ከተማዋ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን በስፋት እንደምታስተናግድና የአፍሪካ መዲና መሆኗንም የሚያወሱ ናቸው፡፡ ጸሐፍቱም መናፈሻዎችና አረንጓዴ ሥፍራዎች በበቂ አልተመቻቹም፣ የፅዳት አጠባበቁም ዝቅተኝነት ስሟን፣ ዝናዋንና የዕድሜ ርዝማኔ አይመጥንም የሚል አንድምታ ያለው ሐሳብና የመሳሰሉትን ሲያነሱ ይስተዋላል፡፡

የከተማዋ አመሠራረት ታሪክ ተደጋግሞ የተነገረ ስለሆነ፣ ይህ ጸሐፊ እዚያ ውስጥ በዝርዝር መግባት አይፈልግም፡፡ ግን ከተማዋ ከነባሩ የአሰፋፈር ሁኔታ ተላቃ ዘመናዊ እንድትሆን አሮጌውና የቆየው መንደር በመልሶ ማልማት መርህ በአብዛኛው መፍረስ ከጀመረ መሰነባበቱን እናውቃለን፡፡ በሚፈርሰው አሮጌ መንደር አካባቢ መልሶ የሚለማው ከተማ ተፈላጊውን ውበት እንዲላበስ ምን ያህል እየታሰበበት ነው ለሚለው ጥያቄ፣ ወደፊት መልስ የምናገኝለት ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን በፅዳቱና ውበቱ ዙሪያ በከተማዋ የሚታዩትን በጎ ሥራዎችና ጉልህ ችግሮች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ጎን ለጎን አስቀምጦ ማየት ያስፈልጋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነባርና ያረጁ ሠፈሮችን አፍርሶ፣ ነዋሪዎቹን ወደ ሌሎች ሥፍራዎች የማዛወሩ ሥራ በስፋት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በፈረሱ ሠፈሮች ላይ መልሶ ልማት የተጀመረባቸው አካባቢዎች በጥሩ ጎን የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የጋራ መኖሪያ መንደሮች (ኮንዶሚኒየም) ተገንብቶባቸው ነዋሪዎች ገብተውባቸዋል፡፡ ከፊል ቦታዎቹ ደግሞ ለግል አልሚዎች ተላልፈው ማለፊያ ግንባታዎች ተካሂደውባቸዋል፡፡ ግንባታዎቹ  በተካሄዱባቸው የተወሰኑ ሠፈሮች በፅዳትና ውበት ጉድለት ላይ ብዙም የሚስተዋሉ ችግሮች የሉም፡፡ ግን አዲስ ሠፈር ሲመሠረት ወይም ግንባታ ሲካሄድ የፍሳሽ መውረጃ ቦዮችን ከዋናው መሥመሮች ጋር መገናኘቱንና አለመገናኘቱን፣ ደረጃ የጠበቀ መሆኑን ቁጥጥር የሚያደርግ ዘርፍ መኖሩ ወይም ሥራውን በትክክል መወጣቱ ያጠራጥራል፡፡

ምክንያቱም ግንባታው ተካሂዶ፣ ነዋሪዎች ገብተውበት፣ ወይም የንግድ እንቅስቃሴው ተጀምሮ በጥቂት ወራት ውስጥ ፍሳሹ ኮብል ድንጋይ ወይም አስፋልቱ ላይ ሲፈስ ይስተዋላል፡፡ ይህ ለከተማዋ ውበትም ሆነ ለጤና ጎጂ ስለሆነ ሊታረም የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

ለመልሶ ማልማቱ ከፈረሱ ሠፈሮች ገሚሶቹ ገና ግንባታ አልተጀመረባቸውም፡፡ ይህም በመሆኑ ነዋሪዎቹ የቆሻሻ መጣያና መፀዳጃ ሆነው ይታያሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለመጥፎ ጠረንና ለተዋህስያን መራቢያ ምክንያት ሆኖ እየታየ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ከፊል የቆርቆሮ አጥር ቢታጠርላቸውም የችግሩን እውነታ ማስቀረት አይሆንም፡፡ ለምሳሌም አንዱን ከተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ ወደ ዲአፍሪክ ሆቴል አቅጣጫ የታሰበውን የመልሶ ማልማት ዕቅድ ማንሳት ይቻላል፡፡ ሠፈሩ መፍረስ ከጀመረና ነዋሪው በአብዛኛው ከለቀቀ ከሦስት ዓመት ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ ጥቂት ግለሰቦች እያለፈ ግንባታ ማካሄድ ጀምረው ይታያሉ፡፡ በስፋት ግን ሠፈሩ በከፊል ፈርሶ ከመታየት ውጪ የተፈጠረ ነገር የለም፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለመልሶ ማልማቱ ተግባር በርካታ ሠፈሮችን በአንድ ጊዜ ማፍረሱ ሥራውን ሳያሰፋበት አልቀረም፡፡ አስተዳደሩ በራሱ አቅም ሁሉንም አካባቢ መልሶ መገንባት እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ እንደ ቦታዎቹ ስፋትና ተበታትኖ መገኘት ጨረታ አውጥቶ ለግለሰቦች ለማስተላለፍም ሰፊ ጊዜና የሰው ኃይል ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም፣ የአስተዳደሩ ምክር ቤት በዚህ ዓመት ተጨማሪ ሠፈሮች ማፍረሱን ላልተወሰነ ጊዜ መግታቱን ያስታወቀው፡፡ ለማንኛውም እስካሁን ፈርሰው የሚገኙትን ሠፈሮች አስተዳደሩ በራሱ አቅም መገንባቱንና ለአልሚዎች የማስተላለፉን ሥራ ጊዜ ሳይሰጥ ቢያከናውነው መልካም ነው፡፡ ለከተማው ውበትም ሆነ ለአካባቢው ጤና ሲባል ቦታዎቹ ለታለመላቸው ዓላማ ቶሎ ሊውሉ ችግሮቹ ሊቃለሉ ይችላሉ፡፡ አሮጌና ነባር ሠፈሮችን መልሶ የማልማቱ ተግባር አቅም ባገናዘበ መንገድ ደረጃ በደረጃ ቢከናወን የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአንድ ጊዜ በርካታ ነባር ሠፈሮችን አፍርሶ ልማቱን ለማስተዳደርና ለማስተላለፍ መሞከር፣ ከአቅም በላይ የሆነ ውጥረት ውስጥ የሚያስገባ ይሆናል፡፡ ይህ በሥራው ጥራትና በዕቅድ ክንዋኔውም ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር አካሄድ ነው፡፡

የመልሶ ግንባታ ልማት በተካሄደባቸው ሠፈሮች አልፎ አልፎ ከሚታዩ የፍሳሽ መውረጃ መስመሮች ብልሽት ውጪ በአብዛኛው ለዕይታ መልካም ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ አረንጓዴ ቦታዎች ለሁሉም ሠፈሮች ተዘጋጅተዋል፡፡ ይህ መልካም አካሄድ ነው፡፡ ነዋሪው አረንጓዴ ሥፍራዎቹንና ሌሎች የተዘጋጁለትን ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫዎች በአግባቡ ጠብቆ እንዲገለገልባቸው የማገዝና ምክር መስጠት፣ የአስተዳደሩ ባለሙያዎች ቀጣይ ሥራ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በከተማዋ ዋና በተባሉ ባለሁለት አቅጣጫ መንገዶች አካፋይ መሀል ላይ በተዘጋጀው የአትክልት ሥፍራ ዛፎችና ውብ አበባዎች ተተክለዋል፡፡ አብዛኞቹ ፀድቀው እንክብካቤም እየተደረገላቸው ነው፡፡ ለጥንቃቄ ሲባልም ለአብዛኞቹ የብረት አጥር ተሠርቶላቸዋል፡፡ የሚገርመው ግን አጥሮቹ በየጊዜው በተሽከርካሪዎች ተገጭተው መውደቃቸው ነው፡፡ አስተዳደሩም ሳይሰለች መልሶ ይሠራቸዋል፡፡ ይህ በተለይ በቦሌ መንገድ ላይ በተደጋጋሚ ስለሚታይ የተለየ ቁጥጥርና ክትትል ይፈልጋል፡፡

በሌሎችም አውራ መንገዶች ዳርቻዎች ላይ በየዓመቱ ክረምት መግቢያ ላይ  አስተዳደሩ የተለያዩ ችግኞች ተከላ ያደርጋል፡፡ ከፊሉ በእግረኛ ተረጋግጦ ቢመክንም፣ ፀድቀው ለዓይን ዕይታ ውብ የሆኑም አሉ፡፡ ከሚተከሉ ችግኞች አብዛኞቹ ፀድቀው እንዲገኙ የተሻሉ ዘዴዎች ይፈለጉ ከማለት ውጪ፣ ጥረቱ መልካም መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡

በአንዳንድ ዋና መንገዶች ዳርቻዎች ላይ በሰዎች እንዳይወሰዱ ሆነው የተዘጋጁ፣ መደገፊያ ያላቸው አግዳሚ መቀመጫዎችም ጥሩ ማረፊያ ሆነዋል፡፡ በከተማዋ በሚገኙ መለስተኛ መናፈሻዎችና ማረፊያዎችም ጭምር ተዘዋውሮ የተመለከተ ሁሉ፣ ማረፊያዎቹ ለሕዝቡ ምን ያህል ጠቃሚና አስፈላጊ እንደሆኑ መገንዘብ ይችላል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና መናፈሻ አገልግሎት ዘርፍ ለብዙኃን መገናኛ በተለያየ ጊዜ ስለከተማዋ ውበት ማብራሪያ ሲሰጥ ሰምቻለሁ፡፡ ጥረቱ የሚታይ ነውና መልካም ተግባር ሊባል ይችላል፡፡ ነባር የመናፈሻ ሥፍራዎች የሚባሉትን እንደ ብሔረ ጽጌ፣ ሸገር፣ አምባሳደር የመሳሰሉትን ብዙም አልሄድባቸውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህና ሌሎችም ያልተጠቀሱት ተመሳሳዮች በአብዛኛው ለሠርግ፣ ለቀለበትና ለተመሳሳይ ዝግጅቶች አገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡

ዘላቂ ማረፊያዎች አካባቢም ብዙ ጥሩ ነገሮች መሠራታቸው የታወቀ ቢሆንም፣ ሕዝቡ ወደነዚህ ሥፍራዎች የሚሄደው ለማረፍ፣ ለመወያትና ለመጨዋወት አይደለም፡፡ በሞት የተለየን የቤተሰብ አባል፣ ጓደኛ ወይም ዕድርተኛ ለመሸኘት ነው፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም ቢሆን ዓይናችን ጥሩ ነገር ማየት የለበትም ማለቴ አይደለም፡፡ በዘላቂ ማረፊያዎቹ አካባቢ ለተከናወኑ መልካምና ድንቅ የውበት ሥራዎች አድናቆት አለኝ፡፡ ግን መናፈሻዎች በየዋና መንገዱ አቅራቢያዎች፣ በየወረዳዎችና በየአካባቢው የተሻለና በቂ ትኩረት ሊያገኙ ይገባል ለማለት ፈልጌ ነው፡፡

የበለጠ ግልጽ ለማድረግ በርካታ የመንግሥትና የግል ድርጅት ሠራተኞች በሚገኙባቸው የከተማው ክፍሎች ማረፊያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ሠራተኛ በምሳ ሰዓት አረፍ ብሎ መንፈሱን አድሶ ወደ ሥራው ይመለሳል፡፡ ሌላውም የከተማው ነዋሪ፣ አረፍ ብሎ ያነባል፣ ይጨዋወታል፣ ጊዜ ያሳልፋል፡፡ ይህ አገልግሎት በአብዛኛው የከተማው ክፍል ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ለምሳሌ ትልቅ የሚባለውን የቦሌ መንገድ እንመልከት፡፡

በአውሮፕላን ማረፊያው ቀለበት መንገድ አደባባዩ ላይ በአበባ ያጌጠ መልካም ማረፊያ አለ፡፡ ይህ በቀለበት መንገዱ ድልድይ ሥር የተዘጋጀው ማረፊያ መቀመጫዎችም ተዘጋጅተውለታል፡፡ ሰዎች አረፍ ብለው ሲጨዋወቱ፣ ጊዜ ሲያሳልፉ መመልከት በጣም ደስ ያሰኛል፡፡ ከአውሮፕላን ማረፊያው ቀለበት መንገድ ጀምሮ ቦሌ ሩዋንዳ ድልድይ በመባል በተለምዶ እስከሚጠራው አካባቢ ድረስ ያለው የሕንፃ ግንባታ ብቻ ነው፡፡ እዚህ ‹‹የሩዋንዳው›› ቀለበት መንገድ ድልድዩ ሥር ‹አሰር› በተባለ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ማረፊያ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ቦታው ቀደም ሲል ጥሩ አያያዝ ያልነበረውና የፅዳት ጉድለት የሚታይበት ነበር፡፡ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ‹‹አሰር ፓርክ›› በሚል ስያሜ መልኩንና ዕይታውን አሻሽሎና ቀይሮ እየሠራ ነው፡፡ ይህ ሲጠናቀቅና አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ሌላ ተጨማሪ ማረፊያ በዚህ መንገድ ላይ ይኖራል ማለት ነው፡፡ አስተዳደሩ ቦታው በዚህ መልክ እንዲዘጋጅ መፍቀዱና ኩባንያውም ዕቅዱን ሥራ ላይ ማዋሉ የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ክፍት ቦታዎች ላይ ሰፋ ያሉ መዝናኛዎች፣ ማረፊያዎችና የሕፃናት መጫወቻ በተወሰኑ ርቀቶች ላይ በከተማዋ እንደሚያስፈልጉ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

የአስተያየቴ ትኩረት ከተማዋ የሕንፃ ክምር ብቻ እንዳትሆን፣ መተንፈሻ ቦታዎች በሕንፃዎች መሀል እያለፉ እንዲኖሩ ለማመልከት ነው፡፡ የከተማ ውበት ሕንፃ ብቻ አይደለም፡፡ ከተማዋን ለማሻሻል አዳዲስ ግንባታዎች ሲታቀዱ፣ በተወሰኑ ርቀቶች ላይ መናፈሻዎችና መዝናኛ ሥፍራዎች አብረው ከግምት ሊገቡ ይገባል፡፡ ይህ ለከተማዋ ውበት፣ ፅዳትና ዘመናዊነትም ትልቅ ድርሻ ስለሚኖረው ከግምት ሊገባ ይገባል፡፡

የሕዝብ ማረፊያ፣ መዝናኛና መናፈሻዎች ሲነሳ አስተዳደሩ መንከባከቡ ላይ ተጨማሪ ወጪና የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ ይገምት ይሆናል፡፡ ቦታዎቹ ለግል ባለሀብቶች መተላለፋቸው የሚያስገኙትንም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማሰብ ይኖራል፡፡ ነገር ግን እኩል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የሠራተኛውና የሕዝቡ ውስጣዊ ስሜት ወይም አዕምሯዊ ዕረፍት ማግኘት መሆኑም መዘንጋት የለበትም፡፡ በአግባቡ ከተጠና ደግሞ ማረፊያዎቹ የገቢ ምንጭ ሊሆኑም ይችላሉ፡፡

የቦሌን መንገድ እንደ ምሳሌ አነሳሁት እንጂ በሜክሲኮ፣ በቄራ፣ በሳሪስና በሌሎቹም የከተማዋ አካባቢዎች ክፍት ቦታዎች ሲገኙ በቅድሚያ የሚታሰቡት የሕንፃዎች ግንባታ ብቻ እንዳይሆኑ የተመጣጠነ ሥራ ቢከናወን መልካም ነው፡፡ የአስተዳደሩ የውበትና መናፈሻ አገልግሎት ዘርፍም መሀል ከተማ በሚገኙ ክፍት ቦታዎች ላይ ለመሥራት መጠየቅ፣ መከራከርና ማስፈቀድ የመቻል አቅም ሊፈጥር ይገባል፡፡ የምህንድስና ባለሙያዎችም በዛሬው ዘመን የአንድ ከተማ ውበት መሥፈርት (መለኪያ) ምን እንደሆነ እያወቁ አለማማከራቸውና ተግባራዊ አለማስደረጋቸው ለወደፊት ያስወቅሳቸዋል፡፡

አስተዳደሩ ካሳያቸው መልካም ጅምሮች ሌላው ከመፀዳጃ አገልግሎት ጋር አያይዞ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ያከናወናቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ በከተማዋ አብዛኛው ሥፍራዎች ተንቀሳቅሼ ለማየት ዕድል ባይኖረኝም የተወሰኑትን ተመልክቻቸዋለሁ፡፡ ውኃ ሰማያዊ ቀለም የተቀቡና ከሩቁ የሚለዩ መፀዳጃ ቤቶችና ሌሎችም አገልግሎት መስጫ ኪዩስኮች የተካተቱበት ነው፡፡ ቡና፣ ሻይና መለስተኛ የስናክ አገልግሎትም ይሰጣሉ፡፡ ቦታዎቹ ተከልለው ሳርና ተክሎች እንዲለመልሙባቸው ሆነው ስለተሠሩ ለዓይን ዕይታም ጥሩ የሚባሉ ናቸው፡፡ መቀመጫዎች ስለተዘጋጁላቸው ሰዎች አረፍ ብለው የሚፈልጉትን አገልግሎት ሲጠቀሙ መመልከት ይቻላል፡፡

መፀዳጃ ቤቶቹን ለመጠቀም የሚከፈል እስከ አንድ ብር የሚደርስ ክፍያ አለ፡፡ ክፍያ በቦታው አገልግሎት የሚሰጡ ዜጎች የሚተዳደሩበት ስለሆነ፣ ተገቢና ተጠቃሚውንም የማይጎዳ ነው፡፡ ግን ይህንን ክፍያ ለመክፈል አቅሙ የሌላቸው ጎዳና ተዳዳሪዎችና አቅመ ደካሞች ከፍለው ይጠቀማሉ ማለቱ አያስተማምንም፡፡ አገልግሎቶቹ ባሉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ጎዳና ተዳዳሪዎችና አቅመ ደካሞች ‹‹ዳቦ ግዛልን›› ከማለቱ ጎን ‹‹የመፀዳጃ ቤት ክፈልልኝ›› ማለት ቢለምዱ፣ ፅዱ ከተማ ማየት የሚፈልግ ሁሉ በደስታ እንደሚሰጣቸው ይሰማኛል፡፡ ለዚህ አገልግሎት ክፈልልኝ ማለቱ የተለመደ አይደለምና እስኪለመድ ችግሩ በከፊል የሚቀጥል ይመስለኛል፡፡

የመፀዳጃ ቤት አገልግሎቱ ጅማሮ ነው እንጂ የተስፋፋ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ጅማሮው ግን ተጠናክሮ ቢቀጥልና አገልግሎቱ እያለ ሜዳ ላይ መፀዳዳቱን በማይተው ግለሰቦች ላይ ቁጥጥርና ተግሳጽ ቢጀመር መልካም ነው፡፡ ይህን ለማለት ያስቻለኝ አገልግሎቱ ባለባቸው አካባቢዎች ግንብ ተደግፈው ‹‹የሚቆሙ›› (የሚፀዳዱ) አቅሙ ያላቸው ግለሰቦችን እየተመለከትን ስለሆነ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማን ፅዳት ለመጠበቅ አስተዳደሩ መልካም ዕርምጃ ከወሰደባቸው ጉዳዮች አንዱ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ባለው መልክ በሰፊው የሰው ኃይል ያደራጀበት የአገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ በየሠፈሩ ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ሠራተኞቹ የሚያካሄዱት የደረቅ ቆሻሻ ማንሳትና ማፅዳት ሥራ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና የሚያስመሰግንም ነው፡፡ ሠራተኞቹ በአብዛኛው ወጣት ሴቶችና እናቶች ሲሆኑ፣ ይህን አድካሚ ሥራ በጥንካሬና ከልብ ሲያከናውኑት መመልከት ክብር የሚያሰጣቸው ነው፡፡ የፅዳት ሥራው ሳይጀመር ወይም ሳይከናወን ከቤቱ ማዶ የወጣ ሰው፣ ከተማዋ በየዕለቱ ባትፀዳ ኖሮ ምን መልክ ሊኖራት እንደሚችል መገመት ይችላል፡፡ ከየሱቁ፣ ከየሆቴል ቤቱ፣ ከየጫት መቃሚያውና ከሌሎችም ሥፍራዎች ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ የሚጣሉ ነገሮች የሚያስገርሙ ናቸው፡፡ ደረቅ ቆሻሻ በማዳበሪያ ወጥቶ የሚደረደረው ከመኖሪያ ቤቶችና ከጥቂት አገልግሎት መስጫዎች ብቻ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ በስፋት ግን እንዳለ ያለ መያዣ የሚበተኑ ደረቅ ቆሻሻዎች ይበዛሉ፡፡ በዚህ ረገድ የየአካባቢው  አስተዳደር ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ አጥፊዎችን የሚያርምና የሚያስተምር ቡድን ቢኖረው መልካም ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የደረቅ ቆሻሻ ፅዳት ሠራተኞች በሥርዓት የተዘጋጀውንም ሆነ የተዝረከረከውን ቆሻሻ ማንሳታቸውን ቀጥለውበታል፡፡ አድናቆትና ክብር ይገባቸዋል የምለውም ለዚህ ነው፡፡

እንግዲህ የአዲስ አበባ ከተማን ውበትና ፅዳት የሚቀንሱና የሚያሰተቹ በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ የጠቃቀስኳቸው ጥቂቶቹን ብቻ ነው፡፡ የመንገድ ዳር ንግድ፣ መፍትሔ ያጣውና በተለያየ መልኩ እየታየ ያለው ልመናና ሌሎችም ችግሮች ከከተማዋ ውበትና ፅዳት ጋር ተያይዘው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ በአብዛኛው የእነዚህ ችግሮች መሠረታዊ መነሻ ድህነት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ድህነት ሲወገድ አብረው ይወገዳሉ እያልን በቀጠሮ የምናቆያቸው ሊሆኑ አይገባም፡፡ የእነዚህ ዜጎች ሰብዓዊ መብትና ክብር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ምን መደረግ እንዳለበት የሚያመለክቱ የመፍትሔ ሐሳቦች በተለያ ጊዜያት በዚሁ ጋዜጣ ቀርበዋል፡፡ ለችግሮቹ መፍትሔዎች እስከሚገኙ ድረስ ደጋግሞ ሐሳቦች ማቅረብ አይከፋምና በሌላ ጊዜ ምልከታዬን በእነዚህ ላይ አደርጋለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...