Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትመረጃ አጥላይነትና መራጭነት የእኛ ድርሻ ነው

መረጃ አጥላይነትና መራጭነት የእኛ ድርሻ ነው

ቀን:

መረጃ የኑሮ እንቅስቃሴያችንና ዕርምጃችን እስትንፋስ ነው፡፡ መረጃ ኃይል ነው፡፡ በተለይ በዛሬው ጊዜ የመረጃ ኃይልነት በእጅጉ ጎልቶ ታይቷል፡፡ በየትኛውም መስክ በሚካሄድ ሩጫና ውድድር ያለመረጃ ተቀናቃኝን በልጦ ማለፍ አይቻልም፡፡ አንዲት ተሰውራ የቆየች መረጃ አፈትልካ ለመንግሥት አስተዳዳሪ መሪ መወገጃ ልትሆን ትችላለች፡፡

መረጃን የመሸሸግና የትኛውንም መሸሸጊያ ሰብሮ መረጃ ላይ የመድረስ/የማዳረስ ትግል ውስጥ የመረጃ ቴክኖሎጂ እየገሰገሰ ነው፡፡ መረጃን ሚስጥር የሚያደርገው ዘዴ ማፍረሻው እንዲፈለሰፍ መነሻ ይሆናል፡፡ በአፀፋው እንደገና ማፍረሻውን የሚያሸንፍ የሚስጥር ዘዴ ይፈልጋል፡፡ ሆኖም የአጥቂነቱን ሥፍራ የያዘው መሰናክሎችንና ርቀቶችን (መራራቆችን) እያሸነፉ መረጃን የማዳረሱ ቴክኖሎጂ እንደመሆኑ ጊዜው የመረጃ ምንጮች፣ ማስተላለፊያዎችና ማከማቻዎች የተራቀቁበት (አንድ መደርደርያ ሙሉ የመጻሕፍትና የሰነድ መረጃን የእስኪርቢቶ እፊያ በምታክል የመረጃ ቋት ይዞ መዞር የሚቻልበት) የመረጃ ዘመን ነው፡፡

ለአብዛኛዎቻችን የቅርብ የዘወትር መረጃ ምንጮቻችን ሬዲዮ፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንዲሁም ቴሌቪዥን ናቸው፡፡ ከዚያ በላይ ሰፊ ተጠቃሚ ያለው ከማይም እስከ ምሁር፣ ከተራ ሰውና ሥራ አጥ እስከ ማዕከላዊ መንግሥት አባላት ድረስ የሚገለገሉበት የመረጃ ማሠራጫ ሹክሹክታ መሆኑን ሳንዘነጋ ነው፡፡ ሕዝብን ለማሳወቅና አመለካከቱን ለመግራት የሚሞከረውም በእነዚሁ ሰፊ መገናኛዎች አማካይነት ነው፡፡ በቀለብ ሸመታ ውስጥ በቀጣፊ ሚዛንና ሐሰተኛ ነገር በተጨማመረበት ሸቀጥ መጭበርበር እንደሚያጋጥም ሁሉ፣ በመገናኛም ላይ አይጠፋምና የመገናኛ ብዙኃን ቀለብተኞች የማንጓለልና የመምረጥ ችሎታቸውን ማዳበር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ዛሬ ይህንን ጥረትና ትጋት እነ ዩኔስኮ የሚዲያ የመሠረተ ትምህርት ብለው ሰይመውታል፡፡ እኔም በዚህ ጉዳይ የማውቃቸውን ፍሬ ነገሮች ለመወርወር ሞክሬአለሁ፡፡

አንዳንዶቻችን ታትሞ ለሕዝብ የቀረበን ነገር ያለጥያቄ ወይም ያለጥርጣሬ መቀበል እንዳለብን አድርገን እናስባለን፡፡ ከጽሑፍ ያገኘነውን መረጃ ለሰው ነግረን ‹‹የሚሆን አይመስለኝም፤›› የሚል ምላሽ ስናገኝ፣ ‹‹በመጽሐፍ ላይ ያለ እኮ ነው፤›› የሚል መከራከሪያ ለማቅረብም እንሞክራለን፡፡ ከመንገድ ወሬ ይልቅ በኅትመት ሥራዎች ውስጥ ለተጣራና ለትክክለኛ መረጃ የበለጠ ዕድል ይኖራል፣ አገኛለሁም ተብሎ ተስፋ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ላይ መሥፈር ለአንድ መረጃ ትክክለኛነት ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም፡፡ በመጽሐፍ ውስጥ የሚያከራክሩ፣ እውነትነታቸው ያልለየላቸውና ጊዜ የሻራቸው ነገሮች ሠፍረው ሊገኙ ይችላሉ፡፡ አንድ መጽሐፍ አንዱን ሲል ሌላው መጽሐፍ ደግሞ ተቃራኒውን የሚያወራበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ወደ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ መጽሔትና ጋዜጦች ስንመጣ ደግሞ ችግሩ ከዚህም ይሰፋል፡፡

አንድ መገናኛ (ሚዲያ) የሚያቀርበው መረጃ ጥራትና አስተማማኝነት በብዙ ነገሮች ይወሰናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዓላማ ወይም ተልዕኮ አንዱ ነው፡፡ በኅትመትም ሆነ በአየር ሞገድ የሕዝብ መገናኛ ዝግጅት ውስጥ የሚያሳውቁ፣ የሚቀሰቅሱ፣ በምክንያት የሚከራከሩ፣ የልዩ ልዩ ድርጊቶችን ወሬ የሚዘግቡ፣ ታሪክ የሚያስታውሱ፣ ሙያዊ/ሳይንሳዊ ትንታኔ የሚሰጡ ሥራዎች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ እነዚህን የመሳሰሉት ሥራዎች የተለያየ ትልልቅ የተልዕኮ ከረጢት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የፕሮፓጋንዳ ተልዕኮ፣ ነግዶ የማትረፍ ወይም ሙያዊ/ሳይንሳዊ ተልዕኮ፡፡

ፕሮፓጋንዳ ሰፊ ተከታይ ማበጀት፣ ለተወሰነ ተግባር ሕዝብን የማነሳሳትና ከተወሰነ ጎጂ/ጠንቅ ከተባለ ባህርይ ወይም ወግ በማራቅ ተግባር ላይ ያተኮረና የሚሽከረከር መጽሔት፣ ጋዜጣ ወይም ፕሮግራም ፕሮፓጋንዳዊ ሊባል ይችላል፡፡

ፕሮፓጋንዳ ሲባል ብዙዎቻችን ከመንግሥትና ከውሸት ቱልቱላ ጋር አዛምደን እንወስደዋለን፡፡ እንደ ፀረ ኤድስ፣ ፀረ አደንዛዥ ዕፅና ፀረ ጎጂ ባህል የመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች አሳምኖ አስተሳሰብና አኗኗርን የማቃናት ሥራ የሚሠራባቸው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ቀዳሚና ወሳኝ በሆኑ ችግሮች ላይ በማተኮር ምክንያት እንደ አስፈላጊነቱ የሚደበዝዙና የሚጋነኑ እውነቶች ሊኖሩ (ጭራም የሚጠቀሙ ውሸቶች ሊታከሉ) ቢችሉም፣ ሁሉም ተጨባጭ ማኅበራዊና ሰብዓዊ ችግሮችን ለማቃለል የሚውሉ ናቸው፡፡ ሥራውን የሚያካሂደው አካል መንግሥታዊ አካል መሆኑና አለመሆኑም በይዘቱ ላይ ብዙም ልዩነት አያመጣም፡፡

ፖለቲካና አስተዳደር ነክ በሆነ መስክ የሚውል የመንግሥትም ሆነ የፓርቲ ፕሮፓጋንዳ እንዳለ በውሸት የተሞላ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ የፖለቲካ መረጋጋትና ብሔራዊ መግባባት መኖር አለመኖር፣ በቀውስና በጦርነት ግብግብ መጠመድ አለመጠመድ በፕሮፓጋንዳ ይዘት ላይ ልዩነት ያመጣል፡፡

በእኛ አገር መንግሥታዊ የሕዝብ መገናኛን የምናውቀው የገዢ አካል ሥልጣንን በማስጠበቅ (የሕዝብ ህሊናን በመቆጣጠር) ተግባር ተውጦ ሆኖ ነው እንጂ፣ ዴሞክራሲ መሠረት በያዘባቸው አገሮች መንግሥታዊ መገናኛዎች የመንግሥት ፖሊሲን ማክበራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በሰፊ ነፃነት ሕዝብን ያገለግላሉ፡፡

ንግዳዊነት፡- ለሽያጭ መዋል ብቻውን ንግዳዊነትን አይገልጽም፡፡ ፕሮፓጋንዳዊ የፓርቲ ልሳናትም ለገበያ ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ የፖለቲካ ሰዎች ወይም ፓርቲዎች አማራጭ ሐሳባቸውን ለሕዝብ ‹‹ለሽያጭ ያቀርባሉ››፣ ሕዝብ የሚሻለውን መርጦ ‹‹ይገዛል›› እየተባለ አንዳንድ ጊዜ የሚነገረውም ሕዝብን ለመማረክ የሚደረግ የቅስቀሳ ፉክክርን በንግድ ቋንቋ ለመግለጽ ነው እንጂ፣ የፕሮፓጋንዳ ዋና ትርፍ ተከታይ ማብዛት ሲሆን ህልውናው በንግድ ላይ የቆመ ሚዲያ ግቡ ገበያ (ገቢ) ማግኘት ነው፡፡ ይህም በሚያቀርባቸው ሥራዎች ላይ የራሱን ተፅዕኖ ይብዛም ይነስ ያሳድራል፡፡

ጉዳዮችና ዜናዎች ገበያ በማሞቅና በማባረር ዋጋቸው ሊመረጡ፣ ሊጣሉና ሊናፈሱ ዕድል አላቸው፡፡ ገበያን የማብዛት ግፊትና ውድድር ያልተጣሩ ነገሮችን እስከ ማውጣትና በጥቅም እስከ መመሳጠር ሊያደርስ ይችላል፡፡ በመጽሔትና በጋዜጣ የፊት ገጽ ላይ ማራኪ ሽወዳ በመጠቀም፣ ሽያጭ እንዲደራ የሚደረግበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ለምሳሌ ስለዝነኛ ሰው ቅንጣት ያህል ወሬ ይዞ በፊት ገጽ ላይ የዝነኛውን ሰው ፎቶ በትልቁ ማውጣት፣ እነ እንቶኔ መግለጫ አውጡ የሚል በትልቁ ርዕስ ይቀመጥና ከሥር አንዲት ዓረፍተ ነገር ጥቅስ ይቀመጣል፡፡ በቂ መረጃ ያልተነገረበት ውዝግብ/ግጭት ባለበት ሰሞን ‹‹እየተሸፋፈነ እንጂ ብዙ ነገር አለ . . . ይህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም . . ሊያበጣብጡን የሚፈልጉ አሉ . . . ›› እንደማለት የመሰለ ጥቅስ በትልቁ ተጽፎ እነ እገሌን አነጋግረናል (በውስጥ አዋቂ ከሚመስል ሰው) ሲባል ከፍተኛ ጉጉት በአንባቢ ላይ ይፈጠራል፡፡ ውስጥ ተገብቶ ሲነበብ ግን ቃለ መጠይቁ በጣም ግለሰባዊ ሕይወት ላይ ያተኮረና ያች በትልቁ የተጻፈችው ጥቅስ እንደ እግረ መንገድ የተነገረች ጨረፍታ ሆና ልትገኝ ትችላለች፡፡ ‹‹መግለጫ አወጡ!›› የተባለው ነገር የሚያጠግብ ዘገባ ወይም ትንታኔ የሌለበት የአንድ አንቀጽ የአሉ ወሬ ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ የዚህ ዓይነት አታላይ አቀራረብ ለአገራችን እንግዳ አልነበረም፡፡ አይደለም ከማለት ይልቅ አልነበረም ያልኩት ችግሩ ከእነ ጋዜጦቹ አብሮ ስለጠፋ ነው፡፡  

የሕዝብና የአገርን ትልልቅ ጉዳዮችን ከእነ ፖለቲካዊ መዘዛቸው ወደዚያ አሽቀንጥሮ የውጭና የውስጥ ዝነኛ የፊልም፣ የሙዚቃና የስፖርት ሰዎችን የሚመለከቱ ሐሜቶችንና የጓዳ ሚስጥሮችን በማቅረብ ላይ (ሽሽጉን በማወቅ ጉጉት ላይ) ንግድን መመሥረትም ሌላ ፈርጅ ነው፡፡ በእዚህ ፈርጅ የተሰማሩ ነጋዴዎች ከትልልቅ ጉዳይ ርቀው የሹክሹክታ ቀለብተኛ/ሱሰኛ የሆኑ ደንበኞችን በማራባት ሚና በፕሮፓጋንዳ አጠባ ከሚያጃጅሉ ሚዲያዎች ጋር በውጤት ላይ ይዛመዳሉ፡፡ ይህ ሁሉ መወራቱ የንግድ ሩጫ የት ድረስ ሊያደርስ እንደሚችል ለማሳየት እንጂ፣ ከትርፍ ጥቅም ጋር ንግዳዊ ያልሆኑ ኃላፊነቶችን አቻችሎ መሥራት አይቻልም ለማለት አይደለም፡፡ ከማቻቻልም አልፈው ትልልቅ የኅብረተሰብ ቁም ነገሮች ላይ የሚያተኩሩ፣ ቶሎ ቡፍ የሚል ትርፍ ባለበት ከመሯሯጥ ይልቅ በሕዝብ ዘንድ ክብርና ታማኝነት በማግኘት ዘላቂ ገበያ መፍጠር የሚሠሩ አርቆ ተመልካቾች ባይበዙም አልታጡም፡፡

ሙያዊ፡- ከተለያዩ የሙያ መስኮች/ተቋማት የሚወጡ ሙያን ብለው በተገቢው ሥነ ምግባር የተከናወኑ ትንተናዎችን፣ ግኝቶችንና ማብራሪያዎችን የሚያቀርቡ መደበኛና ልዩ ሥራዎች በዚህ ውስጥ ይካተታሉ፡፡ በእነዚህ ኅትመቶች ውስጥ ባለሙያ ያልሆነ ሰው የጻፈው ሙያ ነክ ሥራ አይቀርብም፡፡ ባለሙያ ቢሆንም የመረጃ ይዞታውና አተረጓጎሙ ተገምግሞ ነው የሚወጣው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ‹‹በምርምር ተገኘ››/‹‹ተረጋገጠ›› ተብሎ በንግድ ሚዲያ ሊወጣ የሚችለው ሁሉ በሙያ መጽሔት (ጆርናል) ላይም መንገዱ ጨርቅ አይሆንለትም፡፡ ሙያተኛ ግለሰቦች የሚያካሂዷቸው የንግድ መጽሔቶች/ጋዜጦች ለትርፍ የሚሠሩ በመሆናቸው ከላይኞቹ ይለያሉ፡፡  በእኛ አገር ገና ቢሆንም በዓለም ውስጥ ልዩ ልዩ ኢንዱስትሪዎችና ኩባንያዎች በበኩላቸው ገበያን የሚያደራ ምርምርና ግኝት እያሠሩ በሕዝብ መገናኛዎች ውስጥ እንደሚበትኑም መታወቅ አለበት፡፡

እስካሁን ከተነጋገርነው ሙያዊ ተልዕኮ ያለው የመረጃ ምንጭ ከሁሉም የተሻለ አስተማማኝነት እንደሚኖረው እንገነዘባለን፡፡ ችግሩ ግን የዚህ ዓይነት የመረጃ ምንጭ እንደ ልብ የሚገኝ አይደለም፡፡ እንደ ልብ ያለው ከሬዲዮና ቴሌቪዥን ሌላ የአጠቃላይ ፍጆታ ጋዜጣና መጽሔት ነው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ የሚገኘውን እንዳለ መውሰድም ሆነ እያሳደዱ ማጣራት አጉል ችግር ይሆናል፡፡ ይህንን ችግር ካሉት ውስጥ፣ የተሻለ ታማኝነት ያለው የቱ ነው ብሎ ማማረጥ ይቀንሰዋል፡፡

የመታመን ክብር የሚገነባው ለመረጃዎች አድሏዊ ካለመሆን፣ ከተወዛጋቢ ወገኖች የሚፈልቁ አቋሞችን፣ መረጃዎችንና ክርክሮችን በነፃ አዕምሮ ለመፍረድ እንዲቻል ዕድል ከመስጠት፣ በተቻለ ውራጅ ያልሆነ መረጃዎችን ከመጠቀም ጥንካሬና እውነትነታቸው የሚያጠራጥርና የራስን የመታመን ክብር የሚያጎድፉ ወሬዎችን ካለማውጣትና ከመሳሰሉት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ሥነ ምግባር ተላብሶ የመታመን ሞገስን ለማግኘት ጊዜ ይወስዳል፡፡ በኢትዮጵያ የምናወራለትን ክብር የተቀዳጀ የብዙኃን መገናኛ ለማየት ያስቻለ ከባቢ አየርና ምኅዳር ገና የለም፡፡ መሻሻልና መንጓለሉ እንኳን እክል አጋጥሞታል፡፡  

በታማኝነቱ ስም ያተረፈ መጽሔት፣ ጋዜጣ፣ ወዘተ ቢኖርም ባይኖርም ስም ለማትረፍ የሚጣጣርን ደንበኛ ማድረግ አንድ ነገር ነው፡፡ ግን ይታመናል ወይም ዝና አበጅቷል ተብሎ በዚያ ላይ የተወራን ሁሉ ሳያቅማሙ መቀበል ይጎዳል፡፡ የሚዲያ ስም ለእያንዳንዱ ዘገባና ትንታኔ ትክክለኛነት ሙሉ ለሙሉ ዋስትና አይሆንምና ከዚያ መገናኛ የምናገኘውን ነገር በተገቢ መመዘኛዎች ከመመዘንና ከሌሎች ምንጮች ጋር ከማገናዘብ መዘናጋት አይኖርብንም፡፡ መቼም ቢሆን ጭፍን ተቀባይ አለመሆን መመርያችን ሊሆን ይገባል፡፡

አንዳንድ መመዘኛ የሚሆኑ ነጥቦችን እናንሳ

  • ከሁሉም በፊት ለንባብ ያነሳነው መጽሔት/ጋዜጣ ከታተመው የቆየ መሆን አለመሆኑን ማስተዋል አለብን፡፡
  • ላቀረባቸው ጽሑፎች ወይም ዘገባዎች የመረጃ ምንጩን ያሳውቃል? ካላሳወቀ ለምን?
    • የመረጃ ምንጩ ግለሰብ ከሆነና ግለሰቡ ባለመፍቀዱ ወይም ለግለሰቡ ደኅንነት ሲባል ስም የደበቀ ከሆነ፣ ይህንኑ መግለጽና ስለመረጃው የአስተማማኝነት ጥንካሬ ያለውን ግምት መግለጽ ይገባዋል፡፡
    • ምንጭ ካላሳወቀ ያለምክንያት ምንጩን አይደብቅምና ምንጩ የማይታመን ሆኖበት ነው? ከተባራሪ ወሬ የተወሰደ ይሆን? ጊዜው ካለፈበት ምንጭ ወስዶት ይሆን? ብሎ መጠርጠር ተገቢ ጥንቃቄ ነው፡፡
  • የመረጃ ምንጩን ካሳወቀ ሌሎች ጥያቄዎች ይከተላሉ፡፡
    • የመረጃው ምንጭ የሆነው ሰው/ተቋም አስተማማኝ መረጃ ለመስጠት የሚያበቃ ሥልጣን/ዕውቀት/ነፃነት አለው? ለመረጃው ወገናዊነት አለው? በተለይ የሁለት ወገን ቅራኔን በተመለከተ ከአንደኛው ወገን ብቻ የሚገኝ መረጃ ከአድሏዊነት አያመልጥም፡፡ እናም የዚህ ዓይነቱን መረጃ ተቃራኒው ወገን ከሚለው ጋር ወይም ሌላ ከሁለቱም ውጪ የሆነ ወገን ከዘገበው ጋር አመሳክሮ ማበጠር ይገባል፡፡ ዘገባ አቅራቢውም ይህንን ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡ ከሁለት ወገን የሚባለውን አገናዝቦ ለማቅረብ ጥሮ አንዱ ወገን መረጃ ቢነፍገው ይህንኑ ማሳወቅ አግባብ ነው፡፡
    •  ጋዜጠኛው ቀጥተኛ የዓይን ምስክር የሆነበትና በሰነድ፣ በፎቶ፣ በቃለ መጠይቅ፣ ወዘተ የተቀረፁ መረጃዎች ላይ የተመሠረተ ጥንቅር ይበልጥ ክብደት ይሰጠዋል፡፡ ይህ እውነት የሚሆነው ግን ጥንቅሩን የሚሠራው ክፍል የሐሰት ምስክርነት ከማቀናበር ተግባር ጋር ያለው ርቀትና የዘገባው ጉዳይ ጣጠኛ መሆንና አለመሆን ሳይዘነጋ ነው፡፡
  • ዘጋቢ ጋዜጠኛው ቀጥተኛ የዓይን ምስክር ሳይሆን፣ ከሁለተኛ እጅ ከዓይን ምስክሮችና ድርጊቱ ከተፈጸመባቸው ሰዎች የሚያሰባስበው መረጃ የሚሰጠው ዋጋ ከላይኛው መለስ ይላል፡፡
  • የዓይን ምስክር የሌለበትና ሰማን ከሚሉ ሰዎች ቃል የተጠናቀረ ዘገባ ደግሞ የሚሰጠው ዋጋ ከሁሉም አነስተኛ ነው፡፡
  • ምንጭ ሆኖ ያገለገለው የጽሑፍ ውጤት (መጽሐፍ፣ ጆርናል መጽሔት፣ ወዘተ) ከሆነ፣
    • በምንጭት የተጠቀመበት ጽሑፍ ጊዜው ያለፈበት መሆን አለመሆኑን ማስተዋል ያሻል፡፡ በጊዜ ውስጥ ብዙ አዳዲስ ለውጥ ይመጣልና፡፡
    • ጊዜው ያለፈበት ባይሆንም መረጃው ውራጅ መሆን አለመሆኑ ልዩነት ያመጣል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሊቅ አንድ የምርምር ጽሑፍ አሳተሙ እንበል፡፡ ቀጥታ የሊቁን የአንድ ምርምር ጽሑፍ በመረጃ ምንጭነት መጠቀምና ምርምሩን በተመለከተ ግምገማ ካደረገ ጽሑፍ ላይ ወስዶ አንድ የውጭ የንግድ መጽሔት ቢዘግብና ከዚያ ላይ ደግሞ አንድ የአገራችን መጽሔት ቢቀዳ መረጃው ከአራተኛ እጅ የተገኘ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ነገሩን እናስፋው፡፡ የውጭው መጽሔት/ጋዜጣ የወሰደው ከአስተማማኝ ምንጭ ነው? ወይስ አይደለም የሚለው ጥያቄ ራሱን የቻለ ነው፡፡ እሱን እንተወው፡፡ የውጭው ጋዜጣ ወይም መጽሔት ከየትም ወሰደው ከየት መቼም እንዳለ ሳይቀንስ ሳይጨምር አያስቀምጥም፡፡ ይመርጣል፣ በራሱ ቋንቋ ይገልጻል፣ የሚጠቅሰውን ይጠቅሳል፣ አስተያየቱን ያሳርፋል፣ ወዘተ እዚህ ላይ ይብዛም ይነስ ለብረዛ ዕድል አለ፡፡ የእኛ አገር መጽሔት/ጋዜጣ ሲወሰድ ደግሞ የራሱን መረጣ የማብራራትና የመጠቅለል ሥራ ያካሂዳል፡፡ በዚም ውስጥ ለለውጥ ዕድሉ ይኖራል፡፡ ወደ አገርኛ ቋንቋ ሲተረጎም ደግሞ የቋንቋ ችሎታና የሙያ ዕውቀት ጉዳይ ሥራውን ይሠራል፡፡ አንድ ሰው የፈለገውን ያህል የቋንቋ ችሎታ ቢኖረው ለሙያው በቂ አቅርቦት ሳይኖረው የሕጉንም፣ የጤናውንም፣ የጠፈር ሳይንሱንም ጉዳይ ሳያሳስትና ሳያዛባ ይተረጉማል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ የሚወጡ ሕክምናና ጤና ነክ የምርምር ወሬዎች ለሙያው ቅርበት ባላቸው ሰዎች ይተረጎማሉ? ይኼ ቢቀር በተገቢ ባለሙያ ይዘታቸው ይፈተሻል? እንጃ! ለማንኛውም የመጠንቀቅ አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ተጠራጥሮ የማይጠግብ ጠይቆ የማያባራ አዕምሮ ያስፈልጋል፡፡  
  • የቀረበው ሥራ አገነባቡ እንዴት ነው? ሌላው መጠየቅ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
    • አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ላይ ላዩን ሚዛናዊ ምሥል ድብቅ ወገናዊነት ይታይበታል? ለምሳሌ የሁለቱንም ወገኖች መከራከሪያዎችና ማስረጃዎች በሚመለከት የሚያዳላ መረጣ ተደርጓል?
    • ሎጂክ ነክ ሽወዳዎች አሉበት? ለምሳሌ በቃለ መጠይቅ ተፈጽሟል የተባለን ጥፋት በማስረጃ ውድቅ በማድረግ ፈንታ፣ ‹‹ሥውር የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ከጀርባ አሉ . . . › እንደ ማለት ያለ ነገር ይበዛበታል?
    • ምርምራዊ ሥራዎችን በተመለከተ የምርምር አካሄዱም ምን ያህል የሚታመን ሙከራዊ ነው? ከሆነስ የተጠናቀቀ ነው? ወይስ ገና መንገድ ላይ ያለ? (ለምሳሌ ገና በዓይጦች ላይ እየተሞከረ ያለ) ከአዲስ ምርምር/ግኝት ወሬ ጋር ዕውቅ ባለሙያዎች ወይም ተቋማት ዘንድ አስተያየት አብሮ ቀርቧል፡፡

የሚዲያ ደንበኞች የሚቀርቡላቸውን ውጤቶች ከላይ እንደተገለጸው በገምጋሚ ዓይን የሚመዝኑና በዚህም መሠረት ለተለያዩ ውጤቶች ያላቸውን ደንበኝነት የሚያንሸራሽሩ ወይም የሚያጠቡና የሚያሰፉ ከሆነ፣ ጋዜጠኞችም ለማሻሻል ይተጋሉ፡፡ መትጋታቸውም የተሻሻሉና የመረጃ ውጤቶችና የተከበሩ ሚዲያዎች ላይ ያደርሳል፡፡

የመምረጥ፣ የማጥለልና የማንጓለል ችሎታችን ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ለማሳየት ሁልጊዜ ከምንረታበት የትግል መስክ ውስጥ አንዳንዶቹን ምሳሌዎች እናመልክት፡፡

ለምሳሌ የገቢና የኑሮ ደረጃ መራራቅን ሳያገናዝቡና እሱን ሆን ብሎ ሸምጥጦ ዋጋን በዶላር ተመኑ በማነፃፀር ብቻ የኢትዮጵያ የነዳጅ፣ የኢንተርኔት፣ ወዘተ ዋጋ ከእነ አሜሪካና ከእነ ሲንጋፖር ሁሉ ርካሽ ነው ይባላል፡፡ እንዲህ ያለ እውነት ያዘለ ውሸት ለሕዝብ ለማቃም መድፈር የተቻለው ሽወዳው የቱ ዘንድ እንዳለ የሚያጋልጥ አንባቢ፣ አድማጭ፣ ሚዲያ ስለሌለ ነው፡፡

የዋጋ ንረት አጠቃላይ ጉዞ ውስጥ መሆናችን ይታወቃል፡፡ ከወር ወር የምንሰማው ዜናና መረጃ ግን ንረት መቀነሱን ለማሳመን የሚተጋ ዘመቻ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ አንድ ትንሽ እውነት አለ እንኳን ቢባል፣ የዘንድሮው የግንቦት ወር የዋጋ ንረት ወይም ጭማሪ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ንረት ሲወዳደር አነስተኛ መሆኑን፣ ወይም የግንቦት ወር የዋጋ ንረት ከሚያዝያ ወር ያነሰ መሆኑን እንጂ ዋጋ መቀነሱን አይደለም፡፡

መረጃን የማጥለልና የማንጓለል ጉዳይ አስፈላጊነት ይህን ያህል ወሳኝ የትግል መስክ ነው፡፡     

    ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

    

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...