Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየድርድር አብዮት ጥበቦች

የድርድር አብዮት ጥበቦች

ቀን:

በአገራችን ኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያለ አካልና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ሲደራደሩ ማየት የተለመደ አይደለም፡፡  የኢሕአዴግና የደርግ ባለሥልጣናት ለንደን ላይ ሲያደርጉት የነበረው ድርድርም ባለቀ ጉዳይ ላይ በመሆኑ ምንም አልተማርንበትም፡፡ ከዚያም በኋላ ቢሆን ሥርዓት ባለው መንገድ ድርድሮች ሲካሄዱ አላየንም፡፡ አሁን እየተካሄደ ያለው የኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች የፖለቲካ ድርድር የመጀመሪያው ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም፡፡ የድርድር ጥበብ አዋቂዎቹ ሮጀር ፊሸርና ዊልያም ኡሪ እንደሚሉት፣ ከአንድ ትውልድ በፊት በነበሩት ጊዜያት ውሳኔዎች የሚተላለፉት በትዕዛዝና በትዕዛዝ ብቻ ነበር፡፡  በቤተሰብም፣ በዕድርም፣ በሥራ ቦታም ሆነ በመንግሥት ደረጃ ውሳኔዎች የሚወሰኑት ፒራሚዱ ጫፍ ላይ ባለው ሰው ወይም በተወሰኑ ሰዎች ብቻ ነበር፡፡ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተምና ከኢንተርኔት አብዮት ጋር ተያይዞ በመጣው የድርድር አብዮት የጨዋታ ሕጉ ተቀይሯል፡፡ 

ትዕዛዝ በማስተላለፍ ብቻ የሚከናወኑ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች ውጤታቸው አስከፊ ሊሆን እንደሚችል የዓረቡ አብዮት ማሳያ ነው፡፡ በአገር ሰላምና ልማት ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸው ዜጎች በሚበረክቱበት አገር ውስጥ ሞትና ስደት እንደሚነግሡና የዋሻው ጫፍ ብርሃን በቀላሉ ሊገኝ እንደማይችል ዓለም ከሶሪያ እየተማረ ይገኛል፡፡ የዴሞክራሲ መሠረት ባልተጣለበትና አብዛኛውን ባገለለ የፖለቲካ አካሄድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጭምር ወደ አንድ አቅጣጫ ማየት ተስኗቸው ድርድርን ወደጎን በመተው፣ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድንና ፓርቲያቸውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የሶሪያ ሕዝቦች ስደትና ሞት ግን መቆሚያ አላገኘም፡፡ በመሆኑም ሁሉም ተሸናፊዎች እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ 
እንደዚህ ዓይነት ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜም የውጭ ጣልቃ ገብነት ሊኖር ይችላል፡፡ የአሜሪካ፣ የሩሲያና የአካባቢው አገሮች የተለያዩ ፍላጎቶቻቸውን መሠረት በማድረግ ያደረጓቸው ጣልቃ ገብነቶች ችግሩን ከማባባስ ባሻገር፣ የሶሪያውያንን ስቃይ መቼ ሊያበቃ እንደሚችል እንኳን ለመገመት አስቸጋሪ አድርገውታል፡፡ በመሆኑም አልፎ አልፎ የሚደረጉ ድርድሮች የሕዝብን ፍላጐት መሠረት ያደረጉ አለመሆናቸው አገሪቷን ከድጡ ወደ ማጡ አስገብቷታል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ከሶሪያ ጋር የሚወዳደር ባይሆንም፣ በየጊዜው የማይፈቱ ቅሬታዎች ወደ ቅራኔነት በመሸጋገር ለአገር ውድመት አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ማሳያ ነው፡፡ በመሆኑም የድርድር ፖለቲካ መጀመሪያችን አዋቂነት ነው፡፡ 

በአገራችን ኢትዮጵያ ድርድር ቦታ ያልነበረው ሲሆን፣ የሩብ ክፍለ ዘመን እንቅስቃሴያችን ወደ ድርድር ፖለቲካ ያስገባን መሆኑን ስንመለከት የሃያ አንደኛውን ክፍለ ዘመን የዴሞክራሲ አካሄድ በትክክል መያዛችንን ያመለክታል፡፡ ያሰብነው ወደ ታላቅነት የመመለስ ራዕይ ይህንኑ መንገድ እንድንይዝ አስገድዶናል፡፡ በቅርብ ጊዜ በተጀመረው የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ያየናቸው አመለካከቶችና አካሄዶች ለድርድር አዲስ መሆናችንን ያሳብቁብናል፡፡ በዚህ ለድርድር በተደረገ ድርድር፣ ‹‹እኔ በፖለቲካው ዓለም በርካታ ልምዶች ስላሉኝ እናንተን ወክዬ ከኢሕኢዴግ ጋር እደራደራለሁ፤››  ብሎ ተቀባይነት ያጣው ፓርቲ የአመለካከቱ አናሳነት ሲገርመን፣ ከድርድሩ በመውጣት የኋልዮሽ ተጉዟል፡፡ ከድርድር መውጣት አዲስ ነገር ባይሆንም፣ ከመንገዱ የወጣው ፓርቲ ግን ሕዝብን የመወከል ተግባሩን ፈፅሞ የረሳ ነው፡፡ 

ተደራዳሪዎቻችን የፖለቲካ ድርድር ጥበበኞች መሆን አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ተደራዳሪዎች የመጀመሪያ ጥበብ ሕዝብን ማክበር ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍልን የሚወክል ሲሆን፣ አባላትና ደጋፊዎችም ይኖሩታል፡፡ በመሆኑም የመራጮቹን መሠረታዊ ፍላጐት ለማሟላትና የፖለቲካ አስተሳሰባቸውን የሚያራምዱበት ማሽን መሆን መቻል አለበት፡፡ ወዴት እንደሚሄድ የማያውቅ የመርከብ ዘዋሪ መጨረሻው የአውሎ ንፋስና የማዕበል ሲሳይ መሆን ነው፡፡ በመሆኑም ድርድሩ ከፖለቲካ ራዕዩ ጋር እንደሚያያዝ በቅድሚያ ማወቅና መወሰን አለበት፡፡ የፖለቲካ ራዕዬንና ፕሮግራሜን ሕዝብ ከመረጠኝ በኋላ እሱን አማክሬ እቀርፃለሁ የሚል ፓርቲ ራሱ ሕዝብን ያላከበረ ፓርቲ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ተመርጠው ፓርላማ ያልገቡ ተመራጮችም ሆኑ አሁን ከድርድር የሚያፈገፍጉ ፓርቲዎች ሕዝብን ያከበረ የትግል ሥልት አልተከተሉም፡፡ አንድ ፓርቲ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ መንቀሳቀስ ሲጀምር ዋና ተግባሩ፣ በምርጫ ወንበሮችን መያዝና ድርድር በሚያስፈልግበት ጊዜ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ናቸው፡፡ 

ሕዝብን ከማክበር ባሻገር ተደራዳሪ ፓርቲዎች እርስ በርስ የመከባበራቸው አስፈላጊነት ሌላኛው ጥበብ ነው፡፡ ፓርቲው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ የቆየባቸው ጊዜዎች፣ የፖለቲካ አመለካከቱ፣ የሚወክላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችና የአባላቱ ማንነት ግምት ውስጥ ሳይገባ ሁሉም በእኩል ዓይን መተያየት አለባቸው፡፡ የትኛውንም ሐሳብ ቢያራምድ ሐሳቡን በሐሳብ መቃወምና መደገፍ እንጂ የግለሰብ ማንነት ላይ ማጠንጠን የለበትም፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች ለአገራችን አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ 
የአገራችንን፣ የአካባቢያችንና የዓለም አቀፍ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን መከታተልና መረዳት ሌላኛው ጥበብ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕገ መንገሥታዊ አወቃቀርና ፌዴራላዊ ሥርዓት፣ እንዲሁም የተጓዘባቸውን ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች፣ በውዝግብ የተወጠረውን የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችና የኢትዮጵያን አስተዋጽኦና ፈተናዎች፣ እንዲሁም በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች እየተከናወኑ ያሉትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አንድምታዎችና ተያያዥ ዕድሎችና ሥጋቶችን መከታተልና መተንተን ለድርድሩ ግብዓት ሊሆን ይችላል፡፡ በአጠቃላይም ተደራዳሪዎች የፖለቲካና ኢኮኖሚ ዕውቀታቸው የዳበረ ቢሆን ድርድሩን ለማቀላጠፍ ይረዳል፡፡ 

ሌላውና ቁልፉ ጥበብ ወደተሻለው አማራጭ ማዘንበልና መደገፍ ነው፡፡ እኔ ብቻ ያልኩልት ካልሆነ ብሎ ድርድሩን ረጅምና አሰልቺ ማድረግ ለአገርና ለሕዝብ አይጠቅምም፡፡ ተደራዳሪዎች ጥቅም እስካስገኘ ድረስ የራሳቸውን አማራጭ በመተውና የሌላውን በመደገፍ ድረድሩን በተቻለ መጠን ጠቃሚ ማድረግ አለባቸው፡፡ የድርድሩ ዋና ዓላማ ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የሚበጀውንና ሰላሟንና ብልፅግናዋን በማስቀጠል ዜጎቿ የሚኮሩባት አገር እንድትሆን ማድረግ፣ ወይም እንድትሆን መሠረት የሚጥሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ሊሆን ይችላል፡፡ 
ለምሳሌ ኢሕአዴግ የምርጫ ሥርዓታችን ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚችል አስቀድሞ ፍንጭ ሰጥቶናል፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች እንደሚፈልጉትም ይገመታል፡፡ አፈጻጸሙ ግን ሰፊ ድርድርና ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ጭምር የሚያስፈልገው ሊሆን ስለሚችል እጅግ ጥበብ በተሞላበት ማስተዋል ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ በዚህ ልዩ ነጥብ ላይ እኔ ያልኩት አካሄድ ብቻ ተቀባይነት ያግኝ የሚል ግትርነት ሳይሆን የሚያስፈልገው፣ ከዚህ የሕግ ማዕቀፍና አፈጻጸም ማሻሻያ በመነሳት ኢትዮጵያ ወቅታዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በማድረግ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቷ ዳብሮና በልፅጎ ዜጎች በሰላም፣ በመተሳሰብና በአንድነት የሚኖሩባት አገር እንድትሆን አስተዋጽኦ ማድረግ መሆኑን ማሰብ አለባቸው፡፡ 

በመሆኑም ድርድሩ ረጅም ጊዜ ሊወስድ የሚችልና በሒደቱም ለሌሎች ድርድሮች በር የሚከፍት፣ ድርድር ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ትውልድ የፖለቲካ ባህል እንዲሆን መሠረት የሚጥል መደላድል እንዲሆን ማድረግ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁላችንም ኃላፊነት በመሆኑ ልንኮተኩተው፣ ልናርመውና ውጤቱንም ለአገራዊ ሰላምና ብልፅግና ልንጠቀምበት ይገባል፡፡  የመገናኛ ብዙኃኖቻችን፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎችም ተቋማት የድርድር ፖለቲካን የሚያበረታቱ ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ድርድሩ ከድርድሩ ያፈገፈጉትንና ሌሎችንም ጨምሮ ቢካሄድ ተጠቃሚነታችን ይጨምራል፡፡ እንኳን ለድርድር አብዮት አበቃን!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...