Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚንደረደሩ ስፖርታዊ ዝግጅቶች

ለቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚንደረደሩ ስፖርታዊ ዝግጅቶች

ቀን:

የኢትዮጵያ ስፖርት ከተለመደው አካሄድ ወጣ ማለት ይችል ዘንድ በቅርቡ ወደ ኃላፊነት የመጣው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አዲሱ አመራር የ2020 ኦሊምፒን መነሻ ያደረገ የአራት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በማውጣት የአገሪቱን ስፖርታዊ ተሳትፎ በውጤት የታጀበና እንደ ቀድሞው የአሸናፊነት ልዕልናን የተላበሰ ለማድረግ እንቅስቃሴ ከጀመረ ሳምንታትን አስቆጥሯል፡፡ እስከአሁን በትግራይ፣ በአማራና በደቡብ ብሔራዊ ክልሎች የመስክ ግምገማውን አድርጓል፡፡ ይኸው በሌሎችም ክልሎች ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በሐዋሳ በተደረገው  የመስክ ጉብኝት  የመጀመርያ ቀን ውሎ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ ጋር በክልሉ የካቢኔ አዳራሽ ተገናኝቶ የጉብኝቱን ዓላማ አስመልክቶ ውይይት አድርጎ ነበር፡፡  ርዕሰ መስተዳድሩ ለልኡካን ቡድኑ በወቅቱ እንደተናገሩት አዲሱ አመራር ኃላፊነቱን በተረከበ ማግሥት፣ ቀደም ሲል የነበረውን ‹‹ሠርገኛ መጣ›› ዓይነት አሠራር ወደ ጎን በማለት የጀመረው ይህ የሥራ ባህል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ምክንያቱም ቀደም ባሉት ዓመታት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ ሌሎችም የስፖርት ተቋማት በእንደዚህ ዓይነቱ መድረክ እንሰማ የነበረው ከገንዘብ ድጋፍ ጋር በተያያዘ ካልሆነ አብረን እንሥራ የሚል እንዳልነበረም ተናግረዋል፡፡ በማስከተልም አሁን በተጀመረው መልክ መቀጠል ከተቻለ የአገሪቱን የስፖርት  ትንሣኤ በአጭር ጊዜ ማብሰር እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ተቋሙ ለ2020 ኦሊምፒክ ቅድመ ዝግጅት ስፖርቱን ይመለከታሉ የተባሉ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ክንውኖችን አስመልክቶ ለአቶ ደሴ ዳልኬና ለሌሎችም የክልሉ ካቢኔ አባላት ይፋ አድርገዋል፡፡ የስፖርተኛ መፍለቂያ ክልሎች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ የተመለከቱ ቅድመ መሰናዶዎች ላይም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የመስክ ጉብኝቱን ዓላማ በተመለከተ በሩቁው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ላይ ያነጣጠረ፣ በቅርብ ሲታይም የአገሪቱን የስፖርት ዘርፍ መሠረተ ልማት ማጎልበትን  የሰነቀ ዕቅድና ዝግጅት እንዲደረግ ያለመ መሆኑን ጭምር ተናግረዋል፡፡ በዚሁ አግባብም ተቋሙ እስካሁን  የትግራይና የአማራ ክልሎችን ከፕሬዚዳንቶቹ ጀምሮ የክልል ካቢኔዎችን ጭምር በማካተት ተወያይቷል፡፡ ከሰሞኑም ወደ ሌሎች ክልሎች በማምራት ተመሳሳይ የመስክ ጉብኝቶችን እንደሚያደርግም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለመስክ ግምገማው ወደ ክልሎች ከማምራቱ አስቀድሞ አገር አቀፍ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ከአደረጃጀታቸው ጀምሮ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተመልክቶ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ብሔራዊ ሊያሰኝ የሚችል ቁመና እንዳልነበራቸው መታየቱም አይዘነጋም፡፡ ይሁንና የሰሞኑ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግምገማዊ የመስክ ጉብኝት መጠነ ሰፊ የሆነውን የስፖርቱን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ባይታሰብም ቢያንስ ኢትዮጵያ በዘርፉ የነበራትን የተፎካካሪነት አቅም አጠናክሮ ለመቀጠል ቅድመ ዝግጅቶችን ከወዲሁ ለመጀመር እንደሚያግዝ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው መሠረታዊ ዓላማ በኦሊምፒክም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ የመጣውን የአገሪቱን ስፖርት በቀጣይ ተፎካካሪ ማድረግ የሚቻልበትን አቅጣጫ ለማስቀመጥ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላትና ባለቤት ከሆኑት ክልሎች  ጋር ለመምክር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ተቋሙም ለዚህ የአራት ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ማዘጋጀቱንና በዕቅዱ መሠረትም ተተኪዎችን ማፍራት የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባ በጉብኝቱ ወቅት አያይዘው አስረድተዋል፡፡

ክልሎች ከመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ጀምሮ በአገር ውስጥ የሚያደርጓቸው ሁሉም ውድድሮች ታሳቢ አድርገው መንቀሳቀስ የሚኖርባቸው፣ ከሜዳሊያ ባሻገር ሊያመጣ የሚችለውን አገራዊ ፋይዳ ሊሆን እንደሚገባ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የድጋፍ መመሪያ ማዘጋጀቱን ጭምር ተናግረዋል፡፡ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በበኩላቸው፣ በአገር ውስጥ የሚደረጉ ውድድሮች ከመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ጀምሮ ሁሉም ትርጉም ያላቸው ሆነው እንዲቀጥሉ እነዚህን የመሰሉ መድረኮች ተጠናክረው ሲቀጥሉ ለውጡ በስፖርቱ ብቻ ሳይሆን ክልሎች እርስ በርስ የልምድ ልውውጥ እንዲያዳብሩ ያለው ፋይዳ ቀላል አለመሆኑን ጭምር ገልጸው፣ እስካሁን በሁለቱ ክልሎች በተደረጉት የመስክ ጉብኝቶች ለውጤት መነሻ የሚሆን ሥራ የተገኘበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ብዝኃነት በልብስ ብቻ ለምን?

በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ እንቅስቃሴን ለማጠናከር ተቋሙ እንደነዚህ የመሰሉ መድረኮችን በማመቻቸት ከክልሎች ጋር ለመሥራት ማቀዱ ትልቅ ነገር መሆኑን ያስረዱት አቶ ደሴ ዳልኬ፣ ክልሉ እንደ ብዝኃ ብሔረሰብነቱ በስፖርቱ ያለውን ሀብት በቅጡ አለመጠቀሙን አመልክተዋል፡፡ ‹‹አሁንም ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ይህንን የክልሉን እምቅ ሀብት መጠቀም የሚያስችል ተነሳሽነትን ወስዳችሁ አብረን ከሠራን ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም ስፖርት ትልቅ ጥቅም እንደሚኖረው ውጤታማም  ይኮናል፤›› ብለዋል፡፡

 “ብዝኃነት በልብስ ብቻ ለምን?” ሲሉ ያከሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የደቡብ ክልል በስፖርቱም ብዝኃነቱን ማረጋገጥ እንዳለበት፣ ለዚህ ደግሞ አሁን በተጀመረው ዓይነት ተቀናጅቶ የስፖርቱ ምንጭ ወደ ሆኑት  ክልሎች መውረድና መሥራት እንደሚጠይቅም ነው የተናገሩት፡፡

የደቡብ ክልል እንዲህ ዓይነቱ አገራዊ ፋይዳ ያለው ጅምርና እንቅስቃሴ ለጊዜው ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት እንዲኖረው ጽኑ ፍላጎት ያለው መሆኑን ያስረዱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ክልላቸው ከእንግዲህ በእያንዳንዱ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተሳታፊ መሆን እንዲችል የአብሮ መሥራት መርህን እንደሚያከብርና በሌሎችም ተመሳሳይ  እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ በበኩላቸው፣ ለዚህ የጉብኝት ፕሮግራም ተነሳሽነቱን የወሰዱትን አካላት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን አመስግነው ክልሉ አቅም በፈቀደ መጠን ለኦሊምፒክ መጠናከር አብሮ እንደሚሠራ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

ለተደረገላቸው አቀባበልና ዝግጁነት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ በበኩላቸው፣ ሚኒስቴሩና ኦሊምፒክ ኮሚቴ በጋራ የጀመሩት ይህ የመስክ ጉብኝትና ውይይት ዓላማው በዋናነት የአገሪቱን ስፖርት ወደ ተሻለ አቅጣጫ መውሰድ የሚቻልበትን ማዕቀፍ ለመፍጠር ነው ብለዋል፡፡ ለእስካሁኑ የስፖርቱ ውጤት ማሽቆልቆልና ውድቀት በመንስኤነት ከሚጠቀሱ አሠራሮች መውጣትና ከወቅቱና ከጊዜው ጋር መራመድ የሚችሉ አካሄዶችን መከተል የግድ እንደሚል ያከሉት ዶ/ር አሸብር፣ ለእያንዳንዱ ተሳትፎ ዕቅዶችን መሠረት ያደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች እንዲደረጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ድርሻ ድርሻን መውሰድና መንቀሳቀስ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ በመንግሥት በኩል ሊኖር የሚገባውን በተመለከተም ቀደም ሲል ኦሊምፒክን ጨምሮ በተለያዩ አለም ዓቀፍ ውድድሮች ተሳትፈው ውጤታማ ለሚሆኑ አትሌቶች ሲሰጡ የነበሩ ሽልማቶችና ክብሮች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡ ይኽም ለአገራዊ መግባባትና ውጤታማነት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ያከሉት፣ የእነዚህ ነገሮች መቀዛቀዝ አትሌቶች ከአገር ክብር ይልቅ የግል ጥቅም እንዲያስቀድሙ ምክንያት እየሆነ መምጣቱንም ባለመሸሸግ ነው፡፡

ኦሊምፒያኖችን በመወከል በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባሏ ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ፣ ቀደም ባሉት ዓመታት የደቡብ ክልል ያፈራቸውን ታላላቅ ቀደምቶችን በመጥቀስ አሁንም የቀደምቶቹን ታሪክ የሚያስቀጥሉ ወጣቶችን ክልሉ ሊያፈራ እንደሚገባ አሳስባለች፡፡ “ሁላችንም በአንድ ልብ ከሠራን ከሌሎች አገሮች የምናንስበት አንዳች ምክንያት አይኖርም“ በማለት አስተያየቷን በቁጭት ሰንዝራለች፡፡

ዘመናዊው የሐዋሳ ስታዲየም ችግሮችና የታቀዱ መፍትሔዎች

የደቡብ ክልላዊ መንግሥት እያከናወነ ከሚገኘው ግዙፍ የስፖርት መሠረተ ልማቶች መካከል በሐዋሳ ከተማ እያስገነባ ያለውና ግንባታውም በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ሁለገቡ የሐዋሳ ዘመናዊ ስታዲየም ይጠቀሳል፡፡ ስታዲየሙ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) መስፈርት ያሟላ ሆኖ መገንባቱም ተነግሮለታል፡፡ ከነዚህ መስፈርቶች መካከል የስታዲየሙ የእግር ኳስ ሜዳ ጨዋታ በሚከናወንበት ወቅት ዝናም ቢጥል ጨዋታ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል የማድረግ አቅም ያለው መሆኑ ነው፡፡ ይሁንና ከወራት በፊት የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከሲሸልሱ አቻው ጋር በሐዋሳ ስታዲየም ለነበረው የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ  ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ወቅት ዝናም በመዝነቡ ምክንያት ጨዋታው የተቋረጠበት አጋጣሚ መፈጠሩ አይዘነጋም፡፡  በዚህ የተነሳ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስለ ሐዋሳ ስታዲየም በርካታ አሉታዊ ጎኖች ሲነገሩ ቆይቷል፡፡ ምክንያቱም ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባ ከሆነ ችግሩ እንዴት ሊከሰት ቻለ? ለችግሩ ተጠያቂውስ ማን ነው? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ሲደመጡም ቆይቷል፡፡

በክልሉ የመስክ ጉብኝት ወቅት የሐዋሳ ስታዲየም ውኃ የመያዝና ጨዋታው እንዲቋረጥ የሆነበት አጋጣሚ ለምን የሚለው ጥያቄ ለክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ለወ/ሮ መሠረት መስቀሌና ለግንባታው ተቋራች ኃላፊዎች ቀርቦላቸው ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት የግንባታው ተቋራጭ ኃላፊዎች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የመሬትና የአፈር ጥናት ባለሙያዎች ጋር በመሆን ችግሩ እንዴትና ለምን ሊፈጠር እንደቻለ በማጥናት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የችግሩን አሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባት ክልሉም ጉዳዩን እየተከታተለው መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዋ በበኩላቸው፣ የችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነና እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ አሁን ላይ ምንም ማለት እንደማይችሉ፣ ይሁንና በግንባታው ተቋራጭና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እየተደረገ ያለው ጥናት ውጤቱ ከታወቀ በኋላ አስፈላጊው ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስምረውበታል፡፡ 95 በመቶ የተጠናቀቀው ስታዲየሙ የግንባታው አንድ አካል የሆነው የስታዲየሙ የፀሐይ መከላከያ ሽፋን በበጀት እጥረት ምክንያት ለጊዜው እንዲቋረጥ መደረጉም ተነግሯል፡፡ የሐዋሳ ዘመናዊ ስታዲየም  በወንበር 42 ሺሕ ተመልካቾችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን፣ ከስታዲየሙ ጎን ለጎን የውኃ ስፖርቶችን ጨምሮ መረብ ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስና ሌሎችንም ስፖርቶች አካቶ የያዘ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ስታዲየሙ ከአትሌቲክስ ጋር በተገናኘ የተለያዩ ጥናትና ምርምር የሚደረግባቸው ክፍሎችም አሉት፡፡

የሐዋሳ ሁለገብ ዘመናዊ ስታዲየም ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ርክክብ ከተደረገ በኋላ የአስተዳደሩን ጉዳይ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በጋራ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመመልከት ለክልሉ ድጋፍ የሚያደርጉበትና የሚያግዙበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚገባም ወ/ሮ መሠረት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዚህ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተስፋዬ ይገዙ  ሚኒስቴሩና ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በጋራ የአስተዳደሩንም ሆነ ሌሎች ተያያዥ ድጋፎችን የሚመለከቱ ማኑዋል በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ 

ሚኒስትር ዴኤታው ሌላው ያከሉት፣ የደቡብ ክልል መዲና የሆነችው ሐዋሳ በተለይም በአሁኑ ወቅት ትልቅ የኢንዱስትሪ መናገሻ እየሆነች ከመሆኗ አኳያ የጎልፍ ስፖርት ማዘውተሪያ ሊኖራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ምክንያቱን አስመልክቶ አቶ ተስፋዬ፣  የኢንዱስትሪውን መስፋፋት ተከትሎ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ ሐዋሳ የሚመጡበት ዕድል እንደሚኖር ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የስፖርት መሠረተ ልማት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ

ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በመስክ ጉብኝቱ ከተመለከታቸው የስፖርት መሠረተ ልማቶች መካከል የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባውና እስከ 15 ሺሕ ተመልካቾችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው የተነገረለት የእግር ኳስ ሜዳ ተጠቃሽ ነው፡፡ ስታዲየሙ በዋናው ግቢ የሚገኝ ሲሆን፣  ሙሉ በሙሉ ወንበር ተገጥሞለታል፡፡ በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ በየነ ስለሺ ስታዲየሙም ወንበር ከተገጠመላቸው ስታዲየሞች በወልዲያ ከተማ ከተገነባው የሼኽ መሐመድ አሊ አላሙዲን ስታዲየም ቀጥሎ ሁለተኛው እንደሚያደርገው ነው የተናገሩት፡፡ 

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በዝናም ምክንያት ጨዋታዎች እንዳይቋረጡ አስፈላጊው የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ የተሟላለት ነው፡፡  ከዚሁ ጎን ለጎን በስፋት በሚዘወተሩ ስፖርቶች ዙሪያ ጥናትና ምርምር እያደረገ መሆኑንና ከጥናቱ በተገኘው ውጤት መሠረትም ሥልጠናና ትምህርት እየሰጠ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር በጉብኝቱ ማጠቃለያ በሰጡት አስተያየየትም፣ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ክልሎች፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት በተወሰኑ ስፖርቶች ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ያለውን ስፖርት በአህጉራዊም ይሁን በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሳትፎን ለማሳደግ የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ለመግባት በሒደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ዕቅድ ዕውን መሆን በክልሎች መካከልም ሆነ በሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት የሚደረጉ ውድድሮች ግባቸው ከሜዳሊያና ከዋንጫ ባሻገር በኦሊምፒክም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ሊወክሉ የሚችሉ ስፖርተኞችን ማፍራት ቀዳሚው ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ከሁሉም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ጋር የተጠናከረ ግንኙነት መፍጠር የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...