Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየቴክኖሎጂ አብዮት በሙዚቃ

የቴክኖሎጂ አብዮት በሙዚቃ

ቀን:

ብስራት እጅጉ መደበኛ ቀኑን የሚጀምረው ጠዋት ለስለስ ያሉ ሙዚቃዎችን በሙዚቃ ማጫወቻው በማዳመጥ ነው፡፡ ከቤት ወጥቶ ወደ መሥሪያ ቤት ሲጓዝ መኪና ውስጥ ከፍላሹ ሙዚቃ ይሰማል፡፡ በሥራ መካከል አዕምሮውን ለማፍታታት ላፕቶፑ ላይ የጫናቸውን ሙዚቃዎች የማዳመጥ ልማድም አለው፡፡ የአገር ውስጥ ድምፃውያን አልበም ሲለቀቁ ሲዲ ቢገዛም፣ ሙዚቃዎቹን ወደ ፍላሹና ስልኩ ኮፒ አድርጎ ያዳምጣል፡፡ ‹‹መኪና ውስጥም ሆነ ቤት ሆኜ ከሲዲ የቀዳሁትን ሙዚቃ እሰማለሁ፡፡ ሲዲ የምገዛው ለድምፃውያኑ ያለኝን ክብር ለማሳየትና ሲዲውን ለታሪክ ለማስቀመጥ ብቻ ነው፤›› ይላል፡፡

በሲዲ ሙዚቃ ለማዳመጥ ቢፈልግ እንኳን ዘመን አመጣሽ የሙዚቃ ማጫዎቻዎቹ እምብዛም ለሲዲ ቦታ የላቸውም፡፡ ማጫዎቻዎቹ ከሲዲ ይልቅ ለፍላሽ ምቹ ከመሆናቸው በተጨማሪ በርከት ያሉ ሙዚቃዎች በፍላሽና ሚሞሪ ካርድ ይዞ ረዘም ላለ ጊዜ ማዳመጥን ይመርጣል፡፡ የየዘመኑ ገፀ በረከት የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሙዚቃ የሚደመጥበትን መንገድ እየለወጡ መጥተዋል፡፡ ከሸክላ ወደ ካሴት ከዛም ወደ ሲዲ የተሸጋገረው የሙዚቃ አቅርቦት፣ ዛሬ ደግሞ ዲጂታል ዓለም ወዳመጣቸው ቴክኖሎጂዎች ከፍ ብሏል፡፡ እንደ ብስራት ያሉ የሙዚቃ አድማጮች ሙዚቃ በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ እንዲቀርብላቸው ይፈልጋሉ፡፡

በየዘመኑ የመጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጊዜ ሲያልፍባቸው ከገበያ ወጥተዋል፡፡ ከካሴት አንፃር ሲዲ የተሻለ በሆነበት ወቅት የሲዲ ማጫዎቻዎች በየዓይነቱ ገበያውን አጥለቅልቀውታል፡፡ ዛሬ ከሲዲ በተሻለ አገልግሎት የሚሰጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተገኝተዋልና የከተማም ይሁን የገጠር ነዋሪዎች ፍላሽ የሚያስግባ የሙዚቃ ማጫዎቻ (ዲቪዲ ፕለየር ወይም ቴፕ) ይገዛሉ፡፡ በብዙ የኤሌክትሮኒክስ መሸጫ ሱቆች ደግሞ ሬዲዮና ፍላሽ የሚቀበሉ ማጫዎቻዎች ብቻ ይሸጣሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ማጫዎቻዎች በምግብና በመጠጥ ቤቶች በመዝናኛ ስፍራዎች ብሎም ቤት ውስጥ ተመራጭ እየሆኑ ነው፡፡   በጉዞ ወቅት መኪና ውስጥ ያለው አማራጭም ሙዚቃዎችን በፍላሽ ይዞ መጠቀም ነው፡፡ ቴሌቪዝኖችን እንደቀድሞ ቪኤችኤስ (ቪዲዮ ካሴት) የሲዲ ወይም የዲቪዲ ማጫዎቻዎች በኬብል መቀጠል እየቀረ መጥቷል፡፡ ቲቪዎቹ የፍላሽ ማስገቢያ ፖርት ስላላቸው ፊልሙንም ሆነ ሙዚቃውን በፍላሽ ይዞ ማየት ይቻላል፡፡ በእርግጥ በአገሪቱ ከሲዲ ውጪ እንደ ፍላሽ ያሉ አማራጮች ጥቅም ላይ ሲውሉ ሕጋዊነታቸው በጥርጣሬ የታጀበ ነው፡፡

ኅብረተሰቡ ፍላሽና ሚሞሪ ካርድ መጠቀምን ቀላል ሆኖ ቢያገኘውም ሙዚቀኞች ለብዝበዛ የተጋለጡበት አካሄድ በመሆኑ ለዓመታት እሮሮአቸውን አሰምተዋል፡፡ ሙዚቀኞች መብታቸው እንዲከበር ለዓመታት ቢታገሉም ሕገወጥ የሙዚቃ ሥርጭቱን ለመቆጣጠር ከባድ ሆኗል፡፡ ሕገወጥ የሙዚቃ ሥርጭት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የበርካታ አገሮች ራስ ምታት ሲሆን፣ ያደጉ አገሮች ሙዚቃ በዘመን አመጣሽ መንገድ ለገበያ በማቅረብ ችግሩን ለመፍታት ይሞክራሉ፡፡ ይህንን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ የሚጠቅሰው ብስራት፣ ‹‹ሙዚቀኞች ለሙዚቃ አድማጩ በሚቀል መንገድ ሙዚቃዎቻቸውን ሲያቀርቡ ሕገወጥ አካሄዱ ቀስ በቀስ ይቀረፋል፤›› ይላል፡፡

በርካታ አገሮች የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፍሬ በሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሙዚቃ መሸጣቸው የሙዚቃውን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የጥበብ ኢንዱስትሪውን ሲያበለፅገው ታይቷል፡፡ ሙዚቀኞች ከሥራቸው የሚገባቸውን ጥቅም አግኝተው የተደላደለ ኑሮ ሲመሩም ይስተዋላል፡፡ የመረጃ ወይም የቴክኖሎጂ ዘመን ውጤቶችን በመተግበር ረገድ ኢትዮጵያ ከበርካታ አገሮች ኋላ ብትሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተስፋ ሊጣልባቸው የሚችል የሙዚቃ ማሰራጫ መንገዶች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ በያዝነው ዓመት ሙዚቃ በአነስተኛ ገንዘብ በስልክ ወይም ኮምፒውተር የሚገዛባቸው አፕልኬሽኖች ለኅብረተሰቡ እየተዋወቁ ነው፡፡

በሙዚቃ ባለሙያዎች ጥምረት የተመሠረተው አውታር መልቲሚዲያ ነጠላ ዘፈን በ4.50 ሳንቲምና አልበም በ15 ብር በሞባይል የሚገዛበት አፕልኬሽን ይፋ ካደረገ ወራት የተቆጠሩ ሲሆን፣ አፕልኬሽኑ አገልግሎት መስጠት ሊጀምር እንደሆነ በቅርቡ ተገልጿል፡፡ ኤልያስ መልካ፣ ኃይሌ ሩትስና ጆኒ ራጋ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን ከወራት በፊት እንደተናገሩት፣ ሙዚቃን በቀላሉና በአጭር ጊዜ ለማሰራጨት እንዲሁም በሙዚቃው በድምፅ፣ በግጥም፣ በዜማ፣ በቅንብርና በፕሮዳክሽን የሚሳተፉ ባለሙያዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር ነው፡፡ በሞባይል የአየር ሰዓት ክፍያ ሙዚቃ የሚያሸምተው አፕልኬሽን፣ ለዓመታት መብታቸው የተጣሰ ሙዚቀኞችን የሚጠቅም መሆኑን ሙዚቀኞች ሲናገሩም ነበር፡፡

በቴሌ በኩል የኢትዮ ቴሌኮም ኢንዳይሬክት ፓርትነርስ ማኔጀር አቶ ሙሴ ደስታ፣ ተቋሙ ከቴሌ ጋር ተጣምሮ ሙዚቃ መሸጥ ከሚፈልግ ማንኛውም አካል ጋር አብሮ እንደሚሠራ ተናግረው ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም ኦላየን ሙዚቃ በማቅረብ የሚታወቀው አሪፍ ዘፈን ከቴሌ ጋር አብሮ እንደሚሠራ ያሳወቀው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነበር፡፡ የአሪፍ ዘፈን ሥራ አስኪያጅ ኤፍሬም ተክሌና የሽያጭ ኃላፊዋ ምዕራፍ ክፍሌ እንደተናገሩት፣ ነጠላ ዘፈን በሦስት ብር እየሸጡ ከሚገኘው ገቢ ቴሌ 40 በመቶውን ይወስዳል፡፡ ስለሁለቱ ተቋሞች አብሮ መሥራት የተነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ ከኢትዮ ቴሌኮም የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም፣ አሪፍ ዘፈን በስምምነታቸው መሠረት እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡

እነዚህ መንገዶች ለሙዚቀኞች፣ አድማጮችና የሙዚቃ ዘርፍ ባጠቃላይ ምን ይዘው ይመጣሉ? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ ዘመነኛ የሙዚቃ አቅርቦቱ አሁን ካለው አሠራር አንፃር ለዘርፉ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ መኖሩ ባይካድም፣ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ከግምት መግባት ያለባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የኢትዮጵያን ጅማሮ ከተቀረው ዓለም ጋር የሚያነፃፅረው ሙዚቀኛ ዘለቀ ገሠሠ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘመንን ዘላ ወደ ቴክኖሎጂው ዓለም ብትሸጋገርም ጅማሮው ለኢትዮጵያ ጥበብ ጥሩ ጊዜን ያመጣል፤›› ይላል፡፡

ዘለቀ በሙዚቃው ለውጥ ያመጣል የሚለውን ቴክኖሎጂ ያማከለ አካሄድ የሚያነፃፅረው ለዓመታት ከነበረበው ሕገወጥ አሠራር ጋር ሲሆን፣ እንደ ምሳሌ  በአንድ ወቅት ወልድያ ከተማ የገጠመውን ይጠቀሳል፡፡ ይጓዝበት የነበረው መኪና ሲዲ ስለማያጫውት የከተማዋን ነዋሪዎችን ሙዚቃ ቤት ስለመኖሩ ጠየቀ፡፡ ሙዚቃ ቤት ሲል ግራ የተጋቡት ነዋሪዎች ‹‹ፍላሽ ቤት ማለትህ ነው?›› ሲሉ ጠየቁት፡፡ ‹‹ፍላሽ ቤት›› የተባለው ሙዚቃ በፍላሽ የሚቸበቸብበት ሕገወጥ ሙዚቃ ማከፋፈያ ነበር፡፡ ይህን መሰል አሠራር የአገሪቱ ሙዚቀኞች በድህነት እንዲኖሩ፣ ሲታመሙ እንኳን መታከሚያ አጥተው እንዲለምኑ አድርጓል፡፡

ለሕገወጥ የሙዚቃ ዝውውር ቢውልም ፍላሽም የቴክኖሎጂ ውጤት ነው፡፡ ሙዚቃን በድረ ገጽ በሕጋዊ መንገድ ሸጦ ባለሙያዎችን ተጠቃሚ ማድረግም እንዲሁ፡፡ ድምፃዊውም ‹‹ቴክኖሎጂ ያደረሰውን ጉዳት ቴክኖሎጂ ያክመዋል፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ አሪፍ ዘፈን  ማሳቹሰትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (የኤምአይቲ) ምሩቃን የሆኑ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ አውታር ደግሞ ሙዚቀኞች ያቀረቡት አማራጭ መሆኑን የሚገልጸው ዘለቀ፣ የግብይት አማራጩ የሌሎች አገሮችን ጥበብ እንዳሳደገው ለኢትዮጵያም ጠቀሜታ እንደሚኖረው ያስረዳል፡፡

በዓለም ዕውቅ ባለሙያዎችን ያፈሩና ሙዚቃ በማሰራጨት ስኬታማ የሆኑ ተቋሞች በሙዚቀኞች የሚተዳደሩ መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ሙዚቀኞች የዘርፉን ችግር ስለሚረዱ መፍትሔ በማበጀት ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ ከደንበኞች ከሚገኘው ገቢ ባሻገር ሙዚቀኞች ግብይቱን መቆጣጠር የሚችሉበት መንገድ ነው፡፡ አድማጮች ሙሉ አልበም መግዛት ካልፈለጉ ከአንድ አልበም የወደዷቸውን ዘፈኖች ብቻ መግዛት ይችላሉ፡፡ ሙዚቃም ከአገር ውስጥ ባሻገር ለዓለም አቀፍ ገበያ ይቀርባል፡፡ ‹‹ወጣት ድምፃውያን አልበም አውጥተው ለማደግ የሚፍጨረጨሩት ለሥራው የሚያወጡት ገንዘብና ገቢያቸው ስለማይመጣጠን ነው፤›› የሚለው ባለሙያው፣ በዓለም ደረጃ በጥበብ ኢንዱስትሪው ተጠቃሽ እየሆነ በመጣው የናይጄሪያው ኖሊውድ የሙዚቃ ሽያጭ ኦን ላይን መሆኑን እንደ ማሳያ ያነሳል፡፡

ሙዚቀኞች በሥራቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች መብት አስከባሪ በሚል እየተቋቋመ የሚገኘው ማኅበር የለውጥ ምዕራፉ አንድ ገጽ መሆኑን ይናገራል፡፡ በአሜሪካ እንዲሁም ከአፍሪካ በደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያና ሌሎችም አገሮች ተተግብሮ ውጤታማ የሆነው አሠራር፣ በአገሪቱም ሥራ ሲጀምር የሙያተኞችን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን ያክላል፡፡ በእርግጥ ማኅበር ከማቋቋምና የግብይት ሥርዓቱን ከማዘመን በተጨማሪ የኮፒ ራይት ሕጉን በማስከበር ረገድ ብዙ ሥራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ኅብረተሰቡ ወደ ዘመነኛው መንገድ ተሻግሮ ዋና ቅጂ (ኦሪጂናል) ሙዚቃ መግዛትን ባህል እንዲያደርግ ማሳመን የግድ ይላል፡፡ በዚህ ረገድ የመንግሥት ተቋሙ ቴሌ ከሙዚቃ ሽያጩ የሚወስደው ድርሻ የሙዚቀኞችን ጥቅም እንዳይገዳደር መሠራት ያለባቸው የቤት ሥራዎችም አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ ቀደም ባለው ዘመን አሳታሚዎች የሙዚቀኞችን ሥራ ለገበያ የሚያቀርቡበት አሠራር፣ ሙዚቃ በየጓዳው በሕገወጥ መንገድ እየታተመ በመምጣቱ መሸፈኑን ይገልጻሉ፡፡ በሙዚቀኞች እሮሮ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ ቢፀድቅም ሕጉ ባለመከበሩ ሕጋዊ አሳታሚዎችን ጨምሮ በሙዚቃው ያሉ ባለሙያዎች ከችግር አልተላቀቁም፡፡ በርካታ አሳታሚዎች ዘርፉን ጥለው ሲወጡ ድምፃውያን ሥራቸውን የማሳተም ግዴታም ወደቀባቸው፡፡ የአልበማቸውን ሽያጭ ተቆጣጥረው በገቢው እንዳይጠቀሙ ሕገወጥ ሥርጭት እንቅፋት ሆነ፡፡ ከቴሌ ጋር በመሆን ሙዚቃ ኦን ላይን የሚሸጥበት አሠራር ለዚህ መፍትሔ ቢሆንም፣ ከድምፃውያን በተጨማሪ የግጥምና ዜማ ደራሲዎችና አቀናባሪዎች የጥቅሙ ተካፋይነታቸው መረጋገጥ አለበት ይላሉ፡፡

በዳዊት ገለጻ፣ አሠራሩ ታዋቂ ድምፃውያንን ብቻ ሳይሆን ጀማሪዎችንም ያማለከ መሆን አለበት፡፡ ዘመነኛ ቴክኖሎጂን መተግበር ብቻውን የሙዚቃ ሽያጩን ሕጋዊ አያደርገውም፡፡ ‹‹ከኢትዮጵያ ውጪ ኦን ላይን ሙዚቃ እየሸጡ ያላግባብ የሚጠቀሙ አሉ፡፡ አገር ውስጥ ቢሆን መደራደር ይቻል ነበር፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ሙዚቃን ከኢንተርኔት አውርዶ (ዳውንሎድ) መግዛት ለተጠቃሚዎች ቀላል ከመሆኑም በላይ ሙዚቀኛ ሊቆጣጠረው የሚችለው መንገድ ቢሆንም፣ በቴክኖሎጂው ሕገወጦች እንዳይጠቀሙ ጥንቃቄ እንደሚያሻም ያክላሉ፡፡

‹‹ቀድሞ አልበም እንጂ ነጠላ ዜማ የመሸጥ አማራጭ አልነበረም፡፡ ቴክኖሎጂውን ለመውረስ ብንዘገይም ከቀድሞው የተሻለ አሠራር ነው፤›› ይላሉ፡፡ ሆኖም ሙዚቀኞች የሚበዘበዙበት መንገድ ሳይሆን የቀድሞ ጉዳታቸውን የሚካሱበት እንዲሆንም ይጠይቃሉ፡፡

ድምፃዊቷ ቤቲ ጂ፣ አልበሟን ራሷ ለማሳተም ከመገደዷ በባሰ የሲዲ ሽያጭ ትርፋማ እንደማያደርግ ትናገራለች፡፡ የሲዲ ገበያ በዓለም አቀፍ ገበያም እንደመውደቁ አድማጮች ቀላሉን በሶፍት ኮፒ የመጠቀም አማራጭ ወስደዋል፡፡ ‹‹አድማጮች ቀድመውን ሄደዋል፡፡ ላፕቶፕና መኪና ፍላሽ ስለሚቀበሉ ተደብቀው ሙዚቃ በፍላሽ የሚሸጡት ከባለሙያው በላይ እየተጠቀሙ ነው፤›› ትላለች፡፡ የሲዲ ሽያጭ የስቱዲዮን ወጪ እንኳን ስለማይሸፍን ድምፃውያን ከኮንሰርት የሚገኝ ገቢን ተስፋ ከማድረግ ያለፈ አማራጭ የላቸውም፡፡ ይህ በሙዚቃው ያደረሰውን ተፅዕኖ ስትገልጽ፣ ‹‹ሁለተኛ አልበም የመሥራት ሐሳብ ያስፈራል፡፡ ድጋሚ ስፖንሰር ፈልጎ የማሳተም ጫናው ቀላል አይደለም፤›› በማለት ነው፡፡

ዘፋኞች ካለባቸው ጫና አንፃር ሥራቸውን የሚያቀል የኦን ላይን ግብይትን እንደምትደግፍ ቤቲ ጂ ትናገራለች፡፡ አሁን የሕገወጥ አካሄዱ ማስተግበሪያ የሆኑትን ስልክና ላፕቶፕ የሕጋዊ ግብይት መሣሪያ በመሆናቸው ደስተኛ ናት፡፡ አሠራሩ ሙዚቀኞች ከአድማጮቻቸው ጋር በቀጥታ እየተገናኙ በጥበባዊ ሥራቸው የሚጠቀሙበት ነውም ትላለች፡፡ ሙዚቃ ለሽያጭ የሚቀርብባቸው አፕልኬሽኖች በይፈ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት የሙዚቀኞችና የሻጮችንም ጥቅም የሚያስጠብቅ ውል ስለሚኖር ባለሙያው ከሥጋት ነፃ እንደሚሆን ታምናለች፡፡ ‹‹አንድ ሲዲ በ11 ብር ታትሞ፣ ለአከፋፋይ 13 ብር ተሽጦ፣ አዝዋሪ ከ25 እስከ 30 ብር ቢሸጠውም እኔ የማተርፈው አንድ ብር ከምናምን ነው፡፡ ኦን ላይን ሽያጭ ከዚህ የተሻለ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሲዲ ለማስታወሻነት በጥቂቱ እንጂ እንደ ቀድሞ በብዛት አለመታተሙ ወጪ ይቀንሳል፤›› ስትልም ትገልጻለች፡፡

ሙዚቀኛው ሔኖክ መሐሪ ስለ አሪፍ ዘፈንና አውታር የተለያየ አስተያየት አለው፡፡ ‹‹አውታር በሙዚቀኞች የተፈጠረ መገበያያ ነው፡፡ አሪፍ ዘፈን ባለፉት ዓመታት ሳይፈቀድለት የብዙ ሙዚቀኞችን ሥራ ኦን ላይን ሲሸጥ ነበር፤›› ይላል፡፡ የሙዚቀኞችን ሥራ ለገበያ ለማቅረብ የቴክኖሎጂ ውጤትን መጠቀም የሚደገፍ ሐሳብ ቢሆንም፣ ለጥቅም ብቻ ወደ ዘርፉ በሚገቡ ነጋዴዎች እንዳይበዘበዝ ይሠጋል፡፡ ‹‹አማራጭ ይዘው የመጡ ቢመስልም አልሸሹም ዞር አሉ እንዳይሆን፤›› ሲል የሙዚቀኛው ተጠቃሚነት ካልተረጋገጠ እርባና ቢስ እንደሚሆን ይገልጻል፡፡

በሙዚቃ ሽያጩ ባለሙያው ገሸሽ ተደርጎ ባለሀብቶች የሚያዙበት ከሆነ ከቀደሙት ዓመታት ለውጥ እንደማይመጣ ሔኖክ ይናገራል፡፡ የሙዚቀኞችን የሞራልና የኢኮኖሚ መብት የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትና ሙዚቀኞች ሀብታቸውን ራሳቸው የሚያስተዳድሩበት ሥልጣን ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይገልጻል፡፡ ከዚህ ቀደም ከሙዚቀኞች ጋር የተገባ ውል ለ30 እና 40 ዓመታት ሳይታደስ ሙዚቃ በሕገወጥ መንገድ በሚሸጥበት መንገድ ሙዚቀኞች ሲበደሉ እንደመኖራቸው፣ ዘመን አመጣሹ አሠራር ነፃ አውጭ መሆን እንዳለበትም ያስረግጣል፡፡ ለኅብረተሰቡ ትክክለኛውን መረጃ የመስጠት ነገር ተያይዞ ሊታሰብበት እንደሚገባም ያክላል፡፡

‹‹ቴክኖሎጂው ሰው ሙዚቃ ለማግኘት የሚሄድበት ሳይሆን በእጁ የሚያገኝበት ነው፤›› የሚለው የኢትዮጵያ ዲጄዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዲጄ አሮን ነው፡፡ ዲጄዎች ሙዚቃ በሲዲ ማጫወትን ከዓመታት በፊት አልፈው ዘመነኛ ቴክኖሎጂ እየተጠቀሙ ቢሆንም፣ ድምፃውያን ሥራቸውን በቀድሞው መንገድ ከማቅረብ አልፈው አልዘመኑም ይላል፡፡ የዘመኑን መንገድ የሚከተሉት ዲጄዎች ብቻ ሳይሆኑ አድማጮችም ናቸው፡፡

‹‹በሌላው አገር ሲዲ ወይም ሸክላ ለማስታወሻነት ብቻ የሚተው ነው ፡፡ ጊዜው የደረሰበት ቴክኖሎጂ ለሙዚቃ ዘርፍ ችግር መፍትሔ ስለሚሰጥ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፤›› ይላል ዲጄው፡፡ አንዱ ባለሙያ ሌላውን የሚወነጅልበት አሠራር ሳይሆን ለጋራ ለውጥ የሚተጋበት እንዲሆንም ያሳስባል፡፡

በሱ ገለጻ፣ ከቴክኖሎጂው ጎን ለጎን በሮያሊቲ ክፍያና ሌሎችም የኮፒ ራይት ጉዳዮች ረገድ ያሉ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው፡፡ የሙዚቃ ንግድ ቢዝነስ እንደመሆኑ ቴሌ ከየትኛውም ተቋም ጋር መሥራቱ አይቀርም፡፡ ተጠቃሚው ለአንድ ሙዚቃ የሚከፍለውን ገንዘብ በማሳነስ ዘርፉን የሚቀላቀሉ ተፎካካሪዎች መምጣታቸውም አይቀርም፡፡ በዚህ ረገድ በሙዚቃ ሥራው የሚሳተፉ ባለሙያዎች ባጠቃላይ የሚጠቀሙበትና ኅብረተሰቡም በቀላሉ ሙዚቃ የሚያገኝበት መንገድ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ከሌሎቹ ባለሙያዎች ጋር ይስማማበታል፡፡

ብስራት እንደ ብዙኃኑ አድማጮች ሙዚቃ ለገበያ የሚቀርብበት መንገድ ቢቀልለት ይመርጣል፡፡ ‹‹ሙዚቃ በስልኬና በላፕቶፔ ማዳመጤ ስለማይቀር ግዥውም በዚያው መንገድ ቢሆን ይቀላል፡፡ ሙዚቃው የሚደመጥበት ጥራትና የቆይታ ጊዜውም ይረዝማል፤›› ይላል፡፡ ከሰሞኑ የሰማቸው ዘመነኛ የሙዚቃ መገበያያ ድረ ገጾችንም ተስፋ ጥሎባቸዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...