Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ኢንተርኔቱን የበላው ጅብ ምነው አልጮህ አለ?

ሰላም! ሰላም! እንደምን ከረማችሁ? ‹‹አንዳንድ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች ወደ ኮስሞቲክስ መሸጫ መደብሮች እየተቀየሩ ነው፤›› በማለት ማንጠግቦሽ ለባለቤቷ ለደላላው አምበርብር ምንተስኖት አጫውታዋለች፡፡ ብዙ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች በሽግግር ሒደት ላይ ናቸው፡፡ ከማያዋጣ ወደ ተሻለ ትርፍ ፍለጋ የሚደረገው ሽግግር ይሳካ ወይም አይሳካ የታወቀ ነገር የለም፡፡ እኔ ደላላው ከባለቤቴ በተሰጠኝ ትዕዛዝ መሠረት ከአንድ የኢትፍሩት መደብር ተሠልፌአለሁ፡፡ የሠልፉ ዓላማ ደግሞ ስኳር ለመግዛት ነው፡፡ ደላላው እንኳን የስኳር ወረፋ ላይ ሊገኝ የሚወደውንም ሥጋ ተሠልፎ መግዛት አይወድም፡፡ የማንጠግቦሽ ትዕዛዝ ሆኖበት ነው እንጂ ሠልፍ ደስ አይለውም፡፡

ዛሬ ወረፋ ይዞ የሚገዛው ጥቂት ኪሎ ስኳር ምን ያህል ጊዜ እንደሚያቆየን ሳስበው ልቤ ተማረረ፡፡ ምክንያቱም ከጥቂት ቀናት በኋላ ተመልሼ መሠለፍ ስላለብኝ ነው፡፡ አልደላንም ብለው የሚያማርሩ ስኳር በኪሎ መግዛት እንደማይችሉ ይናገራሉ፡፡ በችርቻሮ የሃምሳ ሣንቲምና የአንድ ብር እያሉ ነበር የሚገዙት፡፡ ኢትፍሩት ደግሞ ገና በችርቻሮ ማከፋፈል አልጀመረም፡፡ ኪሎውን በሃያ ብር ለመግዛት ተራራ የሚሆንባቸው እነዚህኞቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች በችርቻሮ ግዥ መጎዳታቸው አልቀረም፡፡

አንዳንዶች የአዲስ አበባ ኑሮ የሰማይና ምድር ያህል ይለያያል የሚሉት ለዚህ ይመስላል፡፡ አንዳንዱ የደላው በነጋ በጠባው መኪና ሲቀያይር ሌላው መቀየሪያ ጫማ አጥቶ ጫማው ተቦትርፎ ይታያል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ባለው ዘመናዊ ቤት ላይ ሌላ የተሻለ የሚባለውን የዘመኑን ውድ ቤት ሠርቶ ወይም ገዝቶ ሲንቀባረር፣ ሌላው ቁርሱን በልቶ ምሳውን መድገም አቅቶት እግዜርን ይማፀናል፡፡ በቪኤይትና በደልቃቃዎቹ አውቶሞቢሎች ዓለማቸውን የሚቀጩ ባሉበት ምድር፣ ብዙኅኑ ሕዝብ ደግሞ ከፕላስቲክ በተሠራ ኤርገንዶ ጫማ ‹ልወዝወዘው በእግሬ› ይላል፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ የዚህ ዓይነቱ ጫማ በጣም ከመብዛቱ የተነሳ ‹‹ባጃጅ›› ተብሎ እንደሚጠራ ደላላው አምበርብር ከሰማ ሰንብቷል፡፡ ባጃጅም ተባለ ኤርገንዶ ተጠቃሚውን እያገለገለ ነው፡፡

በአንድ ወቅት ነው አሉ ሴትዬዋ አርግዛ ያማሯትን ነገሮች ዝርዝር ለባለቤቷ እየተናገረች ነበር፡፡ ባለቤትዋ የአምሮት ዓይነቶችን ይመዘግባል፡፡ ‹‹ሥጋ›› አለች በመጀመሪያ፣ ባል ደስ አለው፡፡ ‹‹ምንም ችግር የለም አገሩ ሁሉ ሥጋ ነው፣ ደግሞ ኪሎው 250 ብር ለገባ ሥጋ፣ እንኳን ዛሬ ያኔም ቢሆን ያለምንም ችግር ገዝቼ አመጣልሽ ነበር፡፡ ሥጋ እንደ ጉድ ይመጣል፤›› አላት፡፡ ሚስት ቀጠለች፣ ‹‹ብርቅዬ›› የሚባሉ የምግብና የቁሳቁስ ዝርዝሮችን ጠርታ ስታበቃ ባለቤቷን ያስደነገጠ አንድ ጥያቄ ጠየቀች፡፡ ምን ብላ? ‹‹ስኳር አማረኝ፤›› ብላ፡፡ ሰውዬው እንደ ቀላል ነገር ስኳር በመፈለግ አዲስ አበባን አካሎ ከጨረሰ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ገሰገሰ፡፡ ምናልባት ለወንጂ ቀረብ ይላል ብሎ በማሰብ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንድ መደብር ገብቶ፣ ‹‹ማነህ ስኳር አለ?›› ጠየቀ ሰውዬው፡፡ ባለሱቁ መለሰ፣ ‹‹አለ!›› ሰውዬው ማመን አልቻለም፡፡ ‹‹በእናትህ እውነትህን ነው?›› በደስታ እየተርገበገበ መልሶ ጠየቀው፡፡ ባለሱቁ የሰውዬው ሁኔታ ገርሞት ስኳሩ ያለበትን ጆንያ አሳየው፡፡ ዓይኑ ሥር ያለውን ስኳር እያየ በደስታ ጮቤ ረገጠ፡፡ የሚስቱ እርግዝና አምሮት መልስ አገኘ፡፡

ያቅሙን ያህል ከገዛ በኋላ ደስታውን ለባለቤቱ ሊያበስራት ስልኩን አንስቶ ቢሞክር አልሠራም አለው፡፡ ኔትወርክ የለም፣ በጣም አዘነ፡፡ ሰውዬው ራሱን እንደመሳት አድርጎታል፡፡ ባለሱቁን የጠየቀው ጥያቄ ግርምትን ያጭራል፡፡ ‹‹ባለሱቅ›› በማለት እንደገና ተጣራ፡፡ ባለሱቁም በነጋዴኛ ትህትና፣ ‹‹አቤት ጌታዬ ምን ልታዘዝ?›› በማለት የሰውዬውን ጥያቄ ለመስማት ጓጓ፡፡ ሰውዬው ጥያቄውን አቀረበ፣ ‹‹ኔትወርክ አለ?›› ሲለው፣ ባለሱቁ አማተበና ነካ ያደርገው ይሆን ወይ ብሎ፣ ‹‹ለጊዜው ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ነው!›› አለው፡፡ ሰውዬው ጥያቄውን አልጨረሰም፣ ‹‹የት አገኛለሁ በእናትህ?›› አለው፡፡ ባለሱቁም፣ ‹‹ምናልባት ዞር ዞር ስትል ቴሌን ታገኝ ይሆናል፤›› አለው አሁንም እየገረመው፡፡ ነገር ግን ባለሱቁ ሌላ ነገር ጠርጠር አደረገ፡፡ ምናልባት እሱ ሳይሰማ ቴሌ ኔትወርክ በካርድ መልክ ማከፋፈል ጀመረ እንዴ ብሎ ለማጠያየቅ ሰውየውን ተከትሎ ወደ ቴሌ አቅጣጫ አመራ፡፡

እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ከደብረ ዘይት አካባቢ የሚመጡ ተባራሪ ሥራዎችን መሥራት አልቻልኩም ብዬ አማርራለሁ፡፡ ‹‹አለን የምንለው የመገናኛ ዘዴ የሞባይል ስልክ ነው፡፡ የሞባይል ስልኩ ደግሞ ከአገልግሎት ይልቅ ለጌጥነት እየዋለ ነው፡፡ አንዳንዶች፣ ‹ቴሌ የት ደረሰ?› ብለው በጥያቄ ይቆዝማሉ፤›› ይላል፡፡ ደላላው በኔትወርክ ችግር ምክንያት ደብረ ዘይት ቢሄድም የሚፈልጋቸውን ሰዎች ግን ማግኘት አልቻለም፡፡ ስልኩን ደጋግሞ ሲደውል አንዳንዴ ፀጥ፣ ሌላ ጊዜ ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ናቸው፣ አንዳንዴ ደግሞ ስልኩ ተዘግቷል ሲለው ግራ ገባው፡፡ ‹‹ቴሌ ሠራተኛ መቀነሱን ሲነግረን ለምን ስለኔትወርኩ መቀነስ አብሮ አልነገረንም?›› በማለትም ጠየቀ፡፡ መልስ የሚሰጠው ባይኖርም፡፡ አንዱ፣ አንዳንድ የውጭ ዜጐች ሲናገሩ ሰማሁ በማለት ከየትኛውም አገር የቴሌኮሙዩኒኬሽን የአገልግሎት ክፍያ የኢትዮጵያ እንደሚወደድ ይናገራል፡፡ የተወደደውን ያህል ግን አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ ብዙዎችን አስመርሯል ይላል፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ከአዲስ አበባ አንድ ስንዝር ራቅ ብሎ ማየት በቂ ነው ሲልም ይደመጣል፡፡ ዛሬ ደግሞ የእኔ ቢዝነስ በኔትወርክ ምክንያት ሊመታ ነው፡፡ ኢንተርኔቱን የጀመርኩ ለታማ አለቀልኝ፡፡

ባለስኳሩ ሰውዬ ኔትወርክ ሲያስጨንቀው ውሎ ወደ ማታ ላይ ድክምክም ብሎት ወደ ቤቱ ይደርሳል፡፡ በአንድ ፌስታል ለባለቤቱ አምሮት መልስ የሚሆኑ የተለያዩ  ነገሮችን አጭቋል፡፡ በሌላኛው ትልቅ ፌስታል ስኳሩን ደብቆ ይዟል፡፡ እቤቱ እንደደረሰ በመጀመሪያ አንደኛውን ፌስታል አቀበላት፡፡ ወዲያው ውስጡ ያሉትን ሸቀጣ ሸቀጦች አገላብጣ አየቻቸው፡፡ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ሥጋ ወዘተ. ስታይ እንደማኩረፍ አለች፡፡ ‹‹ስኳሩስ?›› በማለት ጠየቀችው፡፡ ደብቆት የነበረውን ስኳር፣ ‹‹ሰርፕራይዝ!›› ብሎ አወጣው፡፡ ቤቱ በደስታ የተሞላ መሰለው፣ እንደዳሰበው አልሆነም፡፡ እየተነጫነጨች፣ እሷ የምትፈልገው በፌስታል ሳይሆን ቢያንስ አንድ ኩንታል እንደሆነ ስትናገር ኮሽታ ሳያሰማ ቤቱን ትቶላት ወጣ አሉ፡፡ አንድ ኩንታል ስኳር የመግዛት አቅሙ ቢኖረውም አከማችተሃል በሚል እንዳይታሰር ሠግቶ ነውም ብለዋል፡፡ ከደብረ ዘይት አዲስ አበባ አንድ ኩንታል ጭኖ ማምጣትም ራሱን የቻለ አበሳ ነው፡፡ ቆይ ስኳር ነው ያማራት? ወይስ ኩንታሉን ማየት? አንዳንዴ አምሮት ቅዥት ይሆን እንዴ?

እርጉዞች የሚያምራቸው ነገር አቅምን ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ሁኔታዎችን ጭምር ያገናዘበ ይሆን ዘንድ፣ የ‹‹ምን አማረሽ?›› ቀንን የሚያዘጋጁ ሰዎች ያስቡበት ዘንድ አቤቱታ መቅረቡን እኔ ደላላው እናገራለሁ፡፡ ባሻዬ በስኳር እጥረት ምክንያት፣ ‹‹እነ እንትና ቤት ሻይ እየተጠጣ ነው፤›› የሚባልበት ዘመን ሳይመጣ አይቀርም ይላሉ፡፡ ማንጠግቦሽ ደግሞ በከፍተኛ ድካም ያመጣሁትን ስኳር በቡና በሻይ እያለች አባክና ልትጨርሰው አልፈለገችም፡፡ እንዲያውም የምትወደውን ቡና ሳይቀር በጨው መጠጣት ጀምራለች፡፡ ሌላው ማንጠግቦሽ የዘየደችው መላ፣ ‹‹ቡና ሊጠጡ ሲመጡ ስኳር ይዘው ይምጡ፤›› ነው፡፡ ይህንን አዲሱን መፈክር የሰሙት ባሻዬ በማንጠግቦሽ ፈጠራ ተደንቀዋል፡፡ ባሻዬ ቡና በጨው ከሚጠጡ ባዶውን ቢጠጡ ይመርጣሉ፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ትንሽዬ የስኳር ዕቃ በካፖርት ኪሳቸው ውስጥ ይዘው መዞር ጀምረዋል፡፡ ማንጠግቦሽ ባዶውን ቡና ስትቀዳላቸው እሳቸው ደግሞ ስኳራቸውን አውጥተው ይጨምራሉ፡፡ በቃ ይህ አዲሱ የስኳር አጠቃቀም መመርያ መሆኑ ነው፡፡

ከስኳር መጥፋት ጋር በአንድ ወቅት በሬዲዮ የሰማሁትን አስታወስኩ፡፡ ‹‹የስኳር መጥፋት ምክንያቱ ገበሬው ስኳር መጠቀም በመጀመሩ ነው፤›› የሚል ዓይነት አስተያየት መስማቴን ካስታወስኩ በኋላ በሐሳቡ በጣም ተደሰትኩ፡፡ ወደ ገበሬ አባቴ ዘንድም ደወልኩ፡፡ ‹‹ሃሎ አባዬ?›› አባቱ በገመድ አልባ ስልክ ማውራት ጀመርን፣ ‹‹ሃሎ ልጄ ከየት ተገኘህ?›› አለ፡፡ ደላላው አንበርብር አባቴን ካየሁት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሰላምታችንን ከተለዋወጥን በኋላ ዋናውን ቁም ነገር ጠየቅኩ፣ ‹‹ለካስ እኛ በስኳር ዕጦት የምንገላታው እናንተ ስኳሩን ሁላ ሰብስባችሁ ገዝታችሁት ነው?›› ስለው፣ አባቴ ግራ ተጋባ፡፡ ያለው ስኳር እናንተ ዘንድ ነው የሚለው ንግግር የሚለው አሳጣው፡፡ ግራ ቢገባው፣ ‹‹ልክ ነህ! እውነት ብለሃል! በእርግጥ ለውጥ አለ! ድሮ በሁለት በሬ ነበር የማርሰው አሁን ግን በማኅበር ታቅፌ . . . ›› እሱ ግን እውነቱን ያውቀው ነበር፡፡ ሻይ የሚጠጣው ሌላው ልጅ ለበዓል ሲጠይቀው ስኳር ካመጣለት ብቻ ነው፡፡ ያኔ ገበሬው ተጠቃሚ በመሆኑ ነው ተባለ፡፡ እሺ አልን፡፡ በመቀጠል ነጋዴው አፍኖት ነው ተባልን እሺ ከማለት ውጪ አማራጭ አልነበረም፡፡ ነገ ደግሞ ሌላም ሊባል ይችላል፡፡ የሆነስ ሆነና የስኳር ጉዳይ የተነሳው የአንድ ሰሞን አሪፍ ማመካኛ ስለነበር ነው፡፡ አሁንስ አንዳንዴ ስኳር ሲያምረን እንዴት ያደርገናል? ኔትወርክ ሲጠፋስ እንዴት እንሆናለን? የሆነስ ሆነና አሁን ደግሞ ኢንተርኔቱን የበላው ጅብ ምነው አልጮህ አለ? መልካም ሰንበት!

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት