በሺፈራው ተስፋዬ
ከዕፍታው የቀረበ ማስታወሻ ይህ ጽሑፍ በአገር አቀፍ ደረጃ በአክሲዮን ማኅበራት ላይ ሊሠራ ለታሰበው ጥናት የመነሻ መሠረት እንዲሆን እየተሠራ ካለው የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት (Preliminary Study) ግኝቶች ውስጥ፣ ጊዜ የማይሰጡና አስቸኳይ መፍትሔዎች የሚያስፈልጋቸውን ወሳኝ የአክሲዮን ማኅበራት ችግሮችንና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ነቅሶ በማውጣትና በማሳየት፣ የሚመለከታቸው ባለቤቶችና ባለድርሻ አካላት በሙሉ እስካሁን ከታየው ወይም ከደረሰው በላይ ከባድ ጉዳት ከመድረሱ፣ ከፍተኛ የዜጎችና የአገር ሀብትም ከመባከኑ ወይም ከመውደሙ በፊት ተገቢውን ወቅታዊ ዕርምጃ እንዲወስዱ ለማስታወስ ወይም ለማሳሰብ የቀረበ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት ዕፍታ ነው፡፡
ደረጃውን የሰቀለው የ1952 ንግድ ሕግና አዲሶቹ ሙከራዎች
የአክሲዮን ማኅበራትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በ1952 ዓ.ም. በታወጀው የንግድ ሕግ ውስጥ በአንቀጽ 6 ሥር የተካተቱ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ሕጉ ሳይሻሻል፣ የአፈጻጸም ደንብና መመርያ ሳይወጣለት በመጪው መስከረም 58ኛ ዓመቱን ያከብራል፡፡ በእርግጥ ቀደም ሲልም ሆነ በቅርብ የንግድ ሕጉን በተለይም የአክሲዮን ማኅበራትን ድንጋጌዎች ለማሻሻል ጥረቶች እንደነበሩ ይነገራል፣ እንዳሉም ይታወቃል፡፡ ቀደም ሲል የተደረጉትን የማሻሻያ ረቂቆች ለጊዜው ማግኘት ያልተቻለ ሲሆን፣ በቅርቡ የቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ ረቂቆች ለማየት ተችሏል፡፡ ሁለቱም ጥረቶች በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮችን ያነሱና የያዙ ቢሆንም፣ ከዚህች አጭር ጽሑፍና ከትኩረቱ ውሱንነት አንፃር ጥቂት ጉዳዮችን ብቻ በማሳየት ማለፍ ተመርጧል፡፡
በቀድሞው ፍትሕ ሚኒስቴር አመራር ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በተውጣጡ የሕግ ባለሙያዎች ተረቆ የቀረበው ረቂቅ፣ ቀደም ሲል ከተሠሩት ጥናቶች ላይ ትምህርት አልወሰደም፡፡ የራሱም የሆነ መሠረታዊ ጥናት የለውም፡፡ እስከ ዛሬ ያጋጠሙትና ወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ከግንዛቤ ሳያስገቡ፣ በአጠቃላይ ሁኔታዎች ግምገማ (General Situational Analysis) ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ አንዳንድ ረቂቅ ሐሳቦች ያሉትን ችግሮች የሚያባብሱና ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ሊያመዝን እንደሚችል በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ የመነሻ ሐሳቦቹ ግምታዊ፣ ንድፈ ሐሳባዊና በግል ገጠመኝም ከችግሮቹ ጋር የመተዋወቅ ዕድል ያልነበረ ስለሚመስል፣ በችግሩ ለቆሰለ ሰው፣ በሰው ቁስል እንጨት እንደ መስደድ ዓይነት ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የገቡት አክሲዮን ማኅበራት በተግባር (Defacto) በአንድ ሰው ተመሠርተው፣ ምንም ዓይነት ትርጉም ያለው ተሳትፎና ሥርዓት በሌለበት ሁኔታ ሆኖ እያለ፣ አክሲዮን ማኅበራት በአንድ ግለሰብ ይደራጁ የሚል ሕግ ተረቆ ቢፀድቅ ምን ውጤት እንደሚኖረው በጉዳዩ ላይ ትንሽ ቅርበት ያለው ሰው ወይም ትንሽ ማሰላሰል የሚችል ውጤቱን በጥልቀት መረዳት ይችላል፡፡
የአክሲዮን ማኅበራት አባላት ያልሆኑ ሰዎች የቦርድ አባል እንዲሆኑ የሚለውም ሐሳብ ዓላማ፣ ግብና ውጤት ምን እንደሆነ ለመረዳት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ባለሙያ ካስፈለገ በቅጥር ወይም በአማካሪነት ወይም በአክሲዮኑ ማስገባት እየተቻለ ማለት ነው፡፡ የመተዳደሪያ ደንብ እንዳይቀርብ ማለት በፍጹም ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም እንኳን ደንብ ሳይቀርብ ቀርቶ፣ ደንቡ ቀርቦም በሥውር የሚሠራው ተገቢ ያልሆነና ሕገወጥ ሥራ ዓይነቱና ይዘቱ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ስለሆነም ግለሰብ የራሱን የግል ተቋም እንጂ የሕዝብ ኩባንያ ማቋቋም የለበትም፡፡ በአንድ በኩል ከላይ የተገለጡት ዓይነት ከባድ ችግሮችን የሚፈጥሩ ረቂቅ ድንጋጌዎች ሲኖሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ማሻሻያ ተብሎ የቀረበው የአርትኦት (Editing) ሥራ ይመስላል፡፡ የንግድ ሕግ ማሻሻል በሕግ ባለሙያዎች ብቻ የሚሠራበት ስፋትና ጥልቀት ባለው አገራዊ ጥናት ላይ ለምን እንዳልተመሠረተም ግልጽ አይደለም፡፡ ጥራት ያለው ሥራ ለመሥራት አቋራጭ መንገድ ያለ አይመስልም፡፡ መሥራት ያለበትን ወሳኝ ሥራ መሥራት ግድ ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በተለይ አክሲዮን ማኅበራትን በተመለከተ የንግድ ሕጉን በሚገባ መረዳትና ካለው ተጨባጭ ችግሮች አንፃር ያለውን ትርጉምና አንድምታ በመመርመር፣ በውስብስብ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቀው መራመድ ያቃታቸውንና ሀብታቸው፣ ዕድላቸው፣ ድርጅታቸው እየወደመ ያሉትን ለመታደግ የሚያስችል መመርያ በማዘጋጀት፣ በዘመቻ መልክም ቢሆን ጥረት ማድረግ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ በአስቸኳይ መሥራት ሁለገብ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
በንግድ ሚኒስቴር የተረቀቀው ረቂቅ የተሻለ ለችግሮቹ ቅርበት ያለውና መፍትሔም ለመስጠት የሞከረ ነው፡፡ ይህም መሥሪያ ቤቱ ለችግሩ ካለው ቅርበት የተነሳ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ቢሆንም ረቂቁ ብዙ መዳበር አለበት፡፡ ችግሮቹን ለይቶ ከዚያ አንፃር የሕግ መፍትሔ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን የችግሮቹን መነሻ መሠረትና አማራጭ መፍትሔዎችን፣ በአክሲዮን የውስጥ ሥርዓትና በሕግ አስከባሪ አካላት መካከል፣ በሚዛናዊነት ማከፋፈልና አፈጻጸሙን ማሳለጥ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ረቂቅ ትልቁ ፈተና፣ የንግድ ሕጉ የአፈጻጸም ደንብ ይሁን ወይስ ይህን እንደ አዋጅ ወስዶ ሌላ የአፈጻጸም ደንብና መመሪያ ይዘጋጅ የሚለው ነው፡፡ ውሳኔው የመሥሪያ ቤቱ ሲሆን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የግል አስተያየት ቀደም ሲል የቀረበው ነው፡፡
በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ዘመን የተረቀቁት የንግድ ሕጉን የመሳሰሉት፣ በተለይ አክሲዮን ማኅበራትን የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ከ57 ዓመታት በኋላ እንኳ ሕጉን በአግባቡ ማዳበርና ማሻሻል ቀርቶ፣ በአግባቡ ለመረዳትና ለመተግበር አለመቻላችን የሕጉ ጥራትና ደረጃ የላቀ እንደነበረ ያሳያል፡፡ በእርግጥም በዚያን ዘመንም ሕጉ አገሪቱ ከነበረችበት በመቶ ዓመት የቀደመ ነው ሲባል እንደነበረ ይነገራል፡፡ ቢሆንም በዘመናዊ ሕግ አገሪቱን የማዘመኑ ህልም የተሳካ አይመስልም፡፡
የአክሲዮን ማኅበራት የላቀ ሚና በልማት ውስጥ በመርህ ደረጃ የልማት አከናዋኝ አካላት በሆኑት በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ በግል፣ በኅብረተሰብ ምሥረታ ድርጅት፣ በልማት ድርጅቶች፣ በጥቃቅንና አነስተኛ፣ ወዘተ በሁሉም የሚቻለው ሁሉ መሠራት አለበት፡፡ ነገር ግን በትክክል ከተሠራ በዘላቂነት፣ በተደራሽነት፣ መሠረታዊ ለውጥ በመምጣት፣ ከፍተኛ ካፒታል በመፍጠር፣ ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ግብር በአግባቡ በመክፈል፣ በግልጽ አሠራር፣ የሌሎችን የልማት አከናዋኞች ሥራ በማገዝና በማመቻቸት፣ ለዴሞክራሲያዊ ቢዝነስና ተቋም አመራር በማለማመድና በማሠልጠን፣ ትርጉም ያለው ሁለንተናዊ ለውጥ በማምጣት፣ ወዘተ በመሳሰሉት መመዘኛዎች ማወዳደር ከተቻለ የአክሲዮን ማኅበራት ሚና የላቀ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በተለይ በምዕራባውያን አገሮች እስከ አሥር ሚሊዮን ባለአክሲዮን ዜጎችን በአንድ አክሲዮን ውስጥ ብቻ በማሳተፍ ተፅዕኖና ልዩነት ፈጣሪ የቢዝነስ ተቋም መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ህንድን የመሳሰሉ እየተመነደጉ ያሉ አገሮች የአክሲዮን ማኅበራትን ዕምቅ ሀብት አሟጦ ለመጠቀም “Corporate Ministry” የሚባል የመንግሥት ተቋም መሥርተው እየሠሩ ነው፡፡ ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያና ኬንያ የመሳሰሉት ይህን ተቋም በሚገባ እየተጠቀሙ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በእኛ አገር በዚህ ረገድ ሕጉ ከተደነገገ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ቢሆንም፣ በተግባር የሚታየው ገና ጅምር ሲሆን፣ የችግሩ ውጥንቅጥነት እጅግ ያስደነግጣል፣ ያስፈራራልም፡፡ የደርግ ሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ለአክሲዮን የማያመች እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ ያለፉት 26 ዓመታትም አክሲዮን ማኅበራት ተገቢ ቦታቸውን አግኝተዋል፣ ምቹ ሁኔታዎችም ተፈጥሮላቸዋል፣ መሥራት የሚችሉትን ያህልም ሠርተዋል ማለት አይቻልም፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ለጥቃቅንና አነስተኛ የዕድገት ግብ ሲቀመጥላቸው፣ አክሲዮን ማኅበራት ግን ስማቸውም እንኳን ሊጠቀስ አልበቃም፡፡ በሌላ በኩል ዜጎች አክሲዮን ማኅበራት አመቺ ሆነው ስላገኙዋቸው፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ያለውን ሕግ በመጠቀም በሺሕ የሚቆጠሩ አክሲዮን ማኅበራትን አቋቁመዋል፡፡ ቢሆንም አመቺ የመንግሥት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ወቅታዊ ሕግና አፈጻጸም ባለመኖሩና ከሁሉም በላይ ከተወሰኑ አክሲዮን ማኅበራት መሥራቾች፣ ቦርድና ማኔጅመንት በሚመነጩ ችግሮች የተነሳ በዜጎችና በአገር ሀብት፣ የዕድገት ዕድልና ተስፋ ላይ ወደር የሌለው ወንጀል ተፈጽሟል፡፡
ከአክሲዮን ማኅበራት ልማትና ጥፋት ጋር ተያይዞ የሚወደሱና የሚከሰሱ አካላት ቀደም ሲል እንደተመለከተው አክሲዮን ማኅበራት ለአጠቃላይ አገራዊ ልማትና ብልጽግና ትልቅ ሚና ስለሚጫወቱ፣ መሥራቾች ትልቅ ክብርና ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ ክብርና ምሥጋናም ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊ ተጠቃሚም መሆን አለባቸው፡፡ በተለይ ምሥረታው የሚጠይቀው ትግልና መስዕዋትነት በአግባቡ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ ለሕዝብ ቃል ገብተው፣ በሕግ መሠረት ተቋቁመው፣ የሕዝብ ሀብት ከሰበሰቡ በኋላ፣ በትክክል ሥራውን ሠርተው ሁሉንም ተጠቃሚ እንደማድረግ ፈንታ የራሳቸውን አሻንጉሊት፣ ተላላኪና አቀባባይ ቦርድና ማኔጅመንት በሥውር ወይም በግልጽ ሰይመው፣ ሁሉን ነገር ለራስ በማድረግ ስግብግብነትና እንዳረጀች ድመት የፈጠሩትን ሁሉ እንብላ ካሉ፣ ወደር የሌለው ጥፋት መሆኑ አይቀርም፡፡ አንዳንድ ጊዜ መሥራቾች የቦርድ ሰብሳቢና የማኔጅመንት አመራርም በመሆን ሥርዓቱንና ሥራውንም ያበላሹታል፣ ሀብቱንም ይዘርፉታል፡፡ ይህ በጊዜያዊና በትንሽ ጥቅም ታውሮ ራስን እንደ ማጥፋት ይቆጠራል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ራሳቸው ሁሉንም ቦታ ባይዙም ደካማ ተወካዮቻቸውን ሥልጣን ላይ ያስቀምጡና በሕግና በሥርዓት መሥራት ቀርቶ ተቋሙን ማፍረስ፣ ሥራውን ማበላሸት፣ ሀብቱን መዝረፍ ዋና ሥራ ይሆናል፡፡ ይህ ችግር እንዳይጋለጥ በአክሲዮን ድምፅ ሽፋን መስጠትና የከፍተኛ ባለአክሲዮኖችንም ድምፅ በምሣ ግብዣና በተሳሳተ መረጃ እየጠፋ ባለው ሀብታቸው ላይ የጥፋት ውሳኔ ተባባሪ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ ትክክለኛውን የአክሲዮን ልማት ሥራ ማከናወን የማይችሉ ቦርድና ማኔጅመንት፣ በእንደዚህ ዓይነት የጥፋት ሥራ ላይ በመሠማራት የዜጎችና የአገር ሀብት፣ የልማት ዕድል እንዲባክን ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ዓይነት እየወደመ ያለው የአክሲዮን ማኅበራት ሀብት ምን ያህል እንደሆነ በትክክል መገመት ያስቸግራል፡፡ ሕግና መንግሥት ባለበት አገር እንደዚህ ዓይነት ወደር የሌለው ጥፋት ለዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በዜጎችና በኅብረተሰቡም ላይ በቀላሉ የማይጠገን ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ስለሆነም ዜጎች ሀብታቸውን፣ ዕውቀታቸውን ጉልበታቸውን አስተባብረው ልማት እንዲያከናውኑና እምነትም እንዲያዳብሩ፣ በሕግና በመንግሥት ላይም እምነት እንዲኖራቸው፣ ኩባንያዎችን ተቆጣጥረው (Company Capture) አድርገው ጥፋት የሠሩት መሥራቾች፣ ቦርድና ማኔጅመንት ለጥፋታቸው በሕግ ሊጠየቁና ፍትሕም ሊበየን የግድ ይሆናል፡፡
የቦርድ አባላትና የማኔጅመንት ምርጫ መመዘኛዎች አንዳንድ የዋህ የሚመስሉ ብልጣ ብልጦች፣ ከፋይናንስ ዘርፍ ውጪ ባሉ አክሲዮን ማኅበራት የቦርድና የማኔጅመንት ምርጫ የቢዝነስ ባለሙያ እንዲሆን ሕጉ አያስገድድምና የሙያ መመዘኛ ማስቀመጥ ሕገወጥ ነው፣ የባለአክሲዮኑንም የመመረጥ መብት ይረግጣሉ ይላሉ፡፡ ይህ የአክሲዮን ማኅበራትን ሥራና የሕጉን ድንጋጌ ይዘትና ፍላጎት በሚገባ ካለመረዳትና የቦርድና የማኔጅመንት ወንበር ላይ ተዘፍዝፎ የሚጠበቅባቸውን ሥራ ሳይሠሩ ወፍራም ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት ከሚቋምጡ ወገኖች፣ ወይም ሁኔታውን በጥልቀት ከማይረዱ ወገኖች የሚሰጥ የዋህ አስተያየት ነው፡፡ አክሲዮን ማኅበራት በብዙ ካፒታል፣ በከፍተኛ ድርጅት የላቀ የሙያ ሥራ የሚያከናውኑ ቦርድና ማኔጅመንት የቢዝነስ ተቋማትን፣ በከፍተኛ የቢዝነስ ሳይንስና ጥበብ የሚመሩበት ነው፡፡ ከፍተኛው አመራር (Top Business Management) ቦርድ ሲሆን፣ መካከለኛው አመራር (Middle Management) ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ ሁለቱም ቢዝነስ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ዕቅድና ቁጥጥር እንዲሁም የምዘናና የግምገማ (Business Analyis and Evaluation) ለመሥራት የላቀ የቢዝነስ ዕውቀት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ሕግ መደንገግ አይጠበቅበትም፡፡ ምክንያቱም ይህ ጉዳይ በእንግሊዝኛው “It Goes Without Saying” እንደሚባለውና በአማርኛው ደግሞ “ሳይታለም የተፈታ ነው” እንደሚባለው በመሆኑ ነው፡፡
ሕግ እንደ ድርሰት ወይም እንደ ታሪክ ዝርዝሩን ሁሉ እንዲጽፍ መጠበቅ የለበትም፡፡ የቢዝነስ ኩባንያን የሚያክል ትልቅ ተቋም መሥርቶ በቢዝነስ ማይማን (Business Ignorant) እንዲመራ በማድረግ ሀብቱንና የሥራ ዕድሉን እንዲጠፋ የሚያደርግ፣ ጤናማ አዕምሮ ያለው ባለሀብት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሁሉም መብትና ግዴታ እንዳለበትና ቢዝነስ የመምራቱን ግዴታ በብቃት መወጣት የማይችል ሁሉ፣ መብት አለኝ ብሎ ሊከራከር አይችልም፡፡ መብት አለን ብለው ቦርድና ማኔጅመንት ወንበር ላይ ተዘፍዝፈው ተቋሙ እጃቸው ላይ እየጠፋ ለምን የቢዝነስ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ዕቅድ፣ ወዘተ አውጥታችሁ አትተገብሩም ሲባሉ፣ በጉባዔ አዳራሽ ብቻ ሳይሆን በጋዜጣም ላይ ወጥተው ይህን መሥራት አይጠበቅብንም በማለታቸው መሳቂያና መሳለቂያ ሆነዋል፡፡ መቶ በመቶ ያተርፍ የነበረውን ኩባንያ በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ኪሣራ ውስጥ ያስገቡበት ተጨባጭ መረጃ አለ፡፡ ስለሆነም ቦርድና ማኔጅመንት ሥልጣን ላይ ለመውጣት መብቱን ለመተግበር (Exercise) ለማድረግ ኃላፊነትን በብቃት ለመውጣት መቻልና ግዴታን በሚገባ መውጣት ቅድመ ሁኔታ መሆኑ ግድ ነው፡፡
ነገር ግን የቢዝነስ ባለሙያና ሙያ አስፈላጊና ጠቃሚ እንጂ በራሱ ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ ባለሙያው ቅን፣ የሚታመን፣ ሀቀኛ፣ ኃላፊነት የሚሰማውና ግዴታውን በሚገባ የሚወጣ መሆን አለበት፡፡ እነዚህ የማኅበራዊ ካፒታል እሴቶች ሲሆኑ ችግር ያለባቸው አክሲዮን ማኅበራት ውስጥ ዶክተር ሳይንቲስቱ፣ የተከበሩ አዛውንቱ፣ ጎልማሳው ባለሙያ ካለምንም ይሉኝታ ነጭ ውሸት ይዋሻሉ፣ የተሰጣቸውን እምነትና አደራ ይበላሉ፣ በኃላፊነት ስሜትና በታማኝነት ከመሥራት ይልቅ እጅግ የወረደ ተግባር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ለቦርድና ለሥራ አስኪያጅነት የሚመረጡ ሰዎች በጥንቃቄ መመረጥና ውጤት ካላስገኙና ችግር ከፈጠሩ ካለምንም መዘግየት በተሻለ መተካት አለባቸው፡፡ ጥፋት ከሠሩም ሳይዘገይ በሕግ ፊት ማቅረብ እንደሚገባ የንግድ ሕጉ ደንግጓል፡፡
አፍራሽ ማነው? አድራጊው ወይስ አጋላጩ? ይህ ጥያቄ ችግሮች በከፋባቸው አክሲዮን ማኅበራት ውስጥ መነሳቱ የተለመደና የሚያጋጥም ነው፡፡ ጥያቄው የውጭውን አዳማጭ ብቻ ሳይሆን የውስጥ ባለቤቶችንና ባለድርሻ አካላትንም ግራ ሲያጋባ ይታያል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የመረጃዎቹ በግልጽ አለመቅረብና በግልጽ ውይይት በመመዘኛና በመረጃ ላይ ተመሥርቶ ቀርቦ ተመርምሮ ውሳኔ ካለመስጠትና በይፋ ካለመግለጽ የሚመነጭ ነው፡፡ አፍራሽ የሚለው ፍረጃ በተለይ ከቦርድና ከማኔጅመንት በተቃዋሚዎቻቸው ላይ የሚቀርብ ሲሆን፣ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ በአክሲዮን ማኅበራት ውስጥ ችግሮችና ጥፋቶች እንዳሉ የተገነዘቡና እንዲስተካከልም የሚገፉ ባለአክሲዮኖች በበኩላቸው ቦርድና ማኔጅመንትን በድክመትና በጥፋት ማጋለጥ፣ ሲበዛም በአፍራሽነት መፈረጅ የተለመደ ነው፡፡
በእርግጥ ለማፍረስ ቅርበትና ሥልጣን ያለው ቦርድና ማኔጅመንቱ ሲሆን፣ ድክመቱንና ጥፋቱን የሚቃወሙት ሲቻል በጉባዔ ላይ፣ ካልተቻለም በብዙኃን መገናኛ ማቅረብና ማጋለጥ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ጉዳይ የጅቡንና የአህያዋን ተረት ይመስላል፡፡ ጅቡ ከላይ እየጠጣ ከታች የምትጠጣዋን አህያ ውኃውን አደፈረሽብኝ ብሎ ነገር እንደፈለጋት ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ ለማንኛውም የአፍራሽነትን ክስ ብያኔ ለመስጠት ጭብጥ ይዞ ከግራ ቀኙ የሚቀርበውን መረጃና ማስረጃ በሚገባ መረዳት፣ መመርመርና እውነቱን አንጥሮ ማውጣት ግድ ይሆናል፡፡ ቢሆንም ቦርድና ማኔጅመንት እውነቱን ከመጋፈጥ ይልቅ የድብብቆሽ ጨዋታ መጫወትና እውነትን በመደበቅና የእነሱን ጥፋትና መገለጫ፣ ለሌላው ሲሰጡ የሚያሳይ የአንድ አክሲዮን ሁኔታ እነሆ የቦርዱ ሰብሳቢ ለብቻው፣ አምስት የቦርድ አባላት ሳያውቁና ሳይፈቅዱ እንዲያውም እየተቃወሙ 105 ሠራተኞች አባረዋል፡፡ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተዘግተው ሠራተኞች ተባረዋል፡፡ የትምህርት ክፍሎች ተዘግተውና መምህራን ተባረው፣ ተማሪዎችም ተበትነዋል፡፡ ካለምንም ጥናት ከገቢ ጋር የማይገናኝ የደመወዝ ጭማሪ በማድረግ ተቋሙን ለአደጋ አጋልጠዋል፡፡ ከሕጉና ከአሠራር ውጪ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ይህን የሠሩት የቦርዱና የማኔጅመንት መሪዎች ሥራቸውን የሚቃወሙትን በአፍራሽነት ሲፈርጁ፣ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው አመራሩን በአፍራሽነት ከሰዋል፡፡ ታዲያ አፍራሹ ማነው? አድራጊው ወይስ አጋላጩስ?
የአክሲዮን ማኅበራት (Public Companies) ተወካዮች (ቦርድና ማኔጅመንት) የሥልጣን ገደብና ተጠያቂነት በአክሲዮን ማኅበራት አሠራር ቦርድ በጠቅላላ ባለሀብቱ በቀጥታ ተወክሎ የቢዝነስ ማኔጅመንቱን በበላይነት የሚመራ ሲሆን፣ ማኔጅመንቱ ደግሞ በቀጥታ በጠቅላላ ባለሀብቱ ባይወከልም፣ ጠቅላላ ባለሀብቱንና ኩባንያውን በመወከል ይዋዋል፣ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ በዚህ ዓይነት አሠራርና ሒደት ማኔጅመንቱ ሥልጣኑን ያገኘው በቀጥታ ከወካዩ ማለት ከጠቅላላው ባለሀብት እንዳገኘው ይቆጠራል፡፡ ይህ ማለት ማኔጅመንት የቦርዱ ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ ሁኔታ የኩባንያው ወይም የጠቅላላው ባለሀብት ተወካይ ማለትም ተተኪና ተወካይ ስለሚሆን ቀጥታ ሕጋዊ ግንኙነትና ውጤት ይኖራል ማለት ነው፡፡ ማኔጅመንት በውክልና ሥልጣኑ በመሥራት የመዋዋል፣ የመሥራትና የማሠራት፣ ሥራዎችን በሚሠራበት ጊዜ በሕግ፣ በውልና የሥራው ፀባይ ከሚጠይቀው ውጭ በመውጣት የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ጥፋቶችን በሚሠራበት ወቅት፣ ተጠያቂነቱ በራሱ በማኔጅመንቱ እንጂ ኩባንያውን ጠቅላላ ባለሀብቱን የሚመለከት አይሆንም ወይም መሆን የለበትም፡፡
በተለይ በጥፋቱ ኩባንያው ወይም ተቋሙ ተጎጂ በሚሆንበት ወቅት (በፍትሐ ብሔርም ሆነ በወንጀል) ተጠያቂነቱን ማኔጅመንቱ በግል መውሰድ አለበት እንጂ ጉዳት ደርሶበት እያለ፣ በተጨማሪ በተደራራቢ የማኔጅመንቱ ጥፋትና ጉዳት የሚሸከምበት ወይም የሚሸፍንበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ለምሳሌ ማኔጅመንት ከሕግና ከቅን ልቦና ውጪ ግልጽ የሆነ ጥፋት በሠራተኛው ላይ ፈጽሞ እያለና በዚህም ኩባንያውም ተጎጂ በሚሆንበት ጊዜ፣ በፍርድ ቤት የሚወሰነውን ቅጣት ወይም ካሣ በቀጥታ ራሱ ማኔጅመንቱ መሸፈን አለበት፡፡ አሁን እንደ ሚታየው እኔ ምን ቸገረኝ፣ ወጪውን የሚሸፈነው በኩባንያው ነው እየተባለ የሚሠራውን ኃላፊነት የጎደለው ሥራ ዋጋ መክፈል ያለበት ማኔጅመንቱ ነው፡፡ በወንጀል (በሙስናና በደረቅ ወንጀል) በኩባንያው ሀብት፣ መብትና ጥቅም ላይ ለተከናወነውም ድርጊት በቀጥታና በግል መጠየቅ ያለበት ራሱ ማኔጅመንቱ መሆን አለበት እንጂ፣ ኩባንያው/ባለሀብቱ መሆን የለበትም፡፡
አሁን እየታየ ያለው ኃላፊነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ፍጹም ሕጋዊና ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ማኔጅመንት በማናለብኝነትና በሕገወጥነት በሠራተኞች ላይ ለሚፈጽመው ሕገወጥ ሥራ በተለይም ቦርዱ ሕገወጥ ነው እያለ፣ ማኔጅመንት የሚያደርሰው ጉዳት ሲኖርና ጉዳዩ ፍርድ ቤት ሲሄድ የፍርድ ቤት ወጪዎች፣ የጠበቃ ወጪ፣ የጥፋትና የቅጣት ወጪዎች በኩባንያው ላይ ለሚደርሰው የገጽታ ብልሽት ዋጋውን መክፈል ያለበት ማኔጅመንቱ በግል መሆን አለበት፡፡ ኩባንያው/ጠቅላላው ባለሀብት ተደራራቢ የማኔጅመንት በደሎችን የሚቀበልበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ ምክንያት ሊኖር አይችልም፣ አይገባምም፡፡ ይህ ጉዳይ በግልጽና በዝርዝር አዲስ በሚሻሻሉት ሕጎችና የአፈጻጸም ደንቦችም ውስጥ መካተት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ሕጋዊና ፍትሐዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ሁሉም የየድርሻቸውን ሲወስድና የሚከፍለው ዋጋ ሲሰማው ጥፋት ከመሥራቱ በፊት ሁለት ጊዜ ማሰብ ይጀምራልና ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡