Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፓርላማ አባላት በዋና ኦዲተር ሪፖርት ሳቢያ ራሳቸውን ወቀሱ

የፓርላማ አባላት በዋና ኦዲተር ሪፖርት ሳቢያ ራሳቸውን ወቀሱ

ቀን:

  • የኦዲት ሪፖርቱ ከአምናው የገዘፉ ችግሮችን አሳይቷል
  • 5.2 ቢሊዮን ብር ያልተወራረደ ሒሳብ
  • 379 ሚሊዮን ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት
  • 4.1 ቢሊዮን ብር ውዝፍ ታክስ

የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር ማክሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ባቀረበው ሪፖርት፣ የጥፋተኝነት ስሜት የተሰማቸው የፓርላማ አባላት ራሳቸውንና ምክር ቤቱን ጭምር ወቀሱ፡፡

ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ በ2008 በጀት ዓመት በመሥሪያ ቤታቸው የተካሄዱትን የፋይናንስ ሕጋዊነት የክዋኔ ኦዲቶች አስመልክቶ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ከቀረበው ሪፖርት ጋር ሲነፃፀር የባሱ የሕግ ጥሰቶች በመስተዋላቸው፣ እንዲሁም ከዓመት ዓመት የአስፈጻሚው የሕግ ጥሰትን ፓርላማው ማስቆም ባለመቻሉ ያዘኑና የጥፋተኝነት ስሜት የተሰማቸው የምክር ቤት አባላት ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የሕወሓት ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉ ገበረ እግዚአብሔር ዋና ኦዲተር ገመቹና ተቋማቸው ያቀረቡትን ሪፖርት አድንቀው፣ የተሰጠውን ተልዕኮ የሚፈጽም የፓርላማው ቀኝ እጅ እንደሆነ መስክረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይሁን እንጂ ኦዲተሩ የሚያቀርቡትን ሪፖርት እንደ መረጃ ወስዶ በአስፈጻሚው አካል ላይ ዕርምጃ በመውሰድ፣ የሕዝብ ሀብትና ንብረትን ከብክነት ማዳን አለመቻሉን በቁጭት ተናግረዋል፡፡

‹‹ክቡር አፈ ጉባዔ ይህ ጨዋታ ማብቃት አለበት፤›› ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዋና ኦዲተር ሥራውን በድፍረትና በልዩ ሁኔታ ሲሠራ እኛ ሥራችንን እየሠራን አይደለንም፡፡ የሚመለከተውን አካል ተጠያቂ ማድረግ አለብን፡፡ የተከበሩ አፈ ጉባዔ ሕዝብ ይጠይቀናል፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በየዓመቱ በኦዲተሩ የሚቀርበው የኦዲት ሪፖርት ትልቅ ጥናታዊ ጽሑፍ ይወጣዋል ያሉት ወ/ሮ ሙሉ፣ ‹‹ለዚህ እኛ ተጠያቂ ነን፤›› ብለዋል፡፡ የብአዴን ተወካይ አቶ ታደሰ መሰሉ በበኩላቸው፣ ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ነፃነቱን ጠብቆ እንዲሠራ ማረጋገጥ የሚችለው ሪፖርቱ በድፍረት ባስቀመጣቸው ግኝቶች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በየዓመቱ ደንብና መመርያ የማያከብር፣ የግዥ ሥርዓት የማይከተል የሥራ አስፈጻሚው ባለሥልጣን ‹‹ማነው የሚቀጣኝ እያለ ነው?›› ብለዋል፡፡

‹‹በየዓመቱ ተመሳሳይ ነገር እየደገምን መሄድ የለብንም፡፡ ዕርምጃ መውሰድ መጀመር አለብን፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ የኦሕዴድ ተወካይ አቶ ተስፋዬ ዳባ በተመሳሳይ ባነሱት ሐሳብ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕርምጃ ለመውሰድ ቃል የገቡ በመሆኑ በ2010 ዓ.ም. ዕርምጃ ተወስዶ ፓርላማው ሪፖርት ሊቀርብለት ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹ዋና ዓቃቤ ሕጉ የፓርላማ አባል በመሆናቸውና አሁንም በመሀላችን የሚገኙ ስለሆነ፣ ለጉዳዩ አፅንኦት እንደሚሰጡት እምነቴ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ ባቀረቡት ሪፖርት የፋይናንስ ሕጋዊነትንና የክዋኔ ኦዲትን የተመለከቱ ግኝቶችን አቅርበዋል፡፡ የጥሬ ገንዘብ አያያዝና አጠባበቅ ትክክለኝነት ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ብቻ 144,716 ብር ጥሬ ገንዘብ ጎድሎ ተገኝቷል ብለዋል፡፡ በሒሳብ መግለጫ ሪፖርት በተደረገውና በቆጠራ የተገኘው ጥሬ ገንዘብ መካከል በአምስት መሥሪያ ቤቶች ቆጠራ ከመዝገብ ጋር ሲነፃፀር 379.4 ሚሊዮን ብር ጉድለት መገኘቱን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ሪፖርት የስድስት መሥሪያ ቤቶች ሒሳብ መግለጫ ሪፖርት የተደረገውና በቆጠራ የተገኘው 284,971 ብር ብቻ ነበረ፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ 190/2002 በተደነገገው መሠረት የሰነድ ሒሳብ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ፣ በ113 መሥሪያ ቤቶች በድምሩ 5.2 ቢሊዮን ብር በደንቡ መሠረት ያልተወራረደ ሒሳብ መገኘቱን በሪፖርታቸው አስረድተዋል፡፡

ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና አገልግሎት ሰጪዎች በገቢ ግብር፣ በቀረጥና ታክስ፣ እንዲሁም በሌሎች ገቢ መሰብሰብን በሚፈቅዱ ሕጎች ገቢ የሰበሰቡ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ብቻ 1.13 ቢሊዮን ብር ገቢ ሳይሰበሰብ መቅረቱን ሪፖርት አድርገዋል፡፡

ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢን በተመለከተ በቀረቡት ሪፖርት ደግሞ 4.1 ቢሊዮን ብር ውዝፍ ገቢ መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡ ደንብና መመርያ ያልተከተሉ 91 መሥሪያ ቤቶች 98.7 ሚሊዮን ብር ከፍለው መገኘታቸውን፣ የግዥ አዋጅ ደንብና መመርያ ሳይከተሉ የተፈጸሙ ግዥዎችን በተመለከተ ደግሞ፣ በ79 መሥሪያ ቤቶች 324.9 ሚሊዮን ብር የመንግሥት ግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመርያ ሳይከተሉ ግዥ መፈጸማቸውን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

ማስረጃ ሳይኖር በወጪ የተመዘገበ 36 ሚሊዮን ብር፣ የማማከር ፈቃድ ሳይኖር ያላግባብ ተረጋግጦ የተፈጸመ 260.9 ሚሊዮን ብር የግንባታ ክፍያ መኖሩን ገልጸዋል፡፡

ሪፖርቱን ያዳመጠው ፓርላማው ለመጨረሻ ጊዜ ወደ እንቅስቃሴ እንደሚገባ፣ የወንጀል ይዘት የታየባቸው የኦዲት ግኝቶችም ላይ ዋና ዓቃቤ ሕግ እንዲላክ ወስኗል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...