Wednesday, September 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ምክንያታዊነት ሲጠፋ ብልሹ አሠራር አገር ያጠፋል!

  ምክንያታዊነት ከአስተሳሰብ ይጀምራል፡፡ ምክንያታዊነት በመርህ የሚገዛ ሲሆን፣ በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ የሚያጋጥሙ ማናቸውንም ነገሮች በተጠየቅ (Logic) ለመመርመር ይረዳል፡፡ ብልሹ አሠራር ግን በጭፍን መነዳትና ያለማገናዘብ የሚነጉዱበት ስለሆነ ውጤቱ ጎጂ ነው፡፡ ከግለሰብ አንስቶ እስከ አገር አጠቃላይ ጉዳዮች ድረስ በዕውቀትና በልምድ ላይ የተመሠረቱ ነገሮችን መጨበጥ ካልተቻለ፣ ስሜታዊነትና ደንታ ቢስነት እየተጋገዙ ብልሹ አሠራር ያሰፍናሉ፡፡ በአገር ደረጃ ሲሆን ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ካልተደረገ በደንታ ቢስነት ብቻ የሚወሰኑ ውሳኔዎች አገር ያጠፋሉ፡፡ ምክንያታዊነት ግን ሁሌም እንዴት? ለምን?  መቼ?  የት?  ምን?  የመሳሰሉትን ወርቃማ ጥያቄዎች እያቀረበ እውነትን ከሐሰት ያጠራል፡፡ አገር ጠያቂና ሞጋች ትውልድ ማፍራት አለባት የሚባለው ከአሉባልታ ይልቅ ጥሬ ሀቅ ስለሚበልጥ ነው፡፡ በአሉባልታ ላይ የተመሠረተ ማኅበረሰብ በስሜታዊነት ስለሚነዳ ዘወትር ለብልሹ አሠራር ይጋለጣል፡፡ በዚህ መነሻ አሁን ያለንበትን አጠቃላይ ሁኔታ ስንቃኝ፣ ከምክንያታዊነት ይልቅ ደንታ ቢስነት ገንግኖ ይታያል፡፡ ከመርህ ይልቅ ገጠመኝ ይበዛል፡፡

  ከመንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ስንነሳ አቀራረፃቸው ምን ያህል ሳይንሳዊ ነው ብሎ መጠየቅ  ተገቢ ይሆናል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች  የሚወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከአገር ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር አዋጭ ናቸው? ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተግባራዊ የሚደረጉባቸው ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች ክፍተቶች የሉባቸውም? በአፈጻጸም ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማስተካከል ወይም ለመፍታት የሚረዱ ውጤታማ አሠራሮች አሉ? ውጤቶች የሚገመገሙት በምን ዓይነት መለኪያና ስታንዳርድ ነው? የምዘናና የቁጥጥር ሥርዓቱ ምን ይመስላል? ወዘተ. ተብሎ ጥያቄ ሲቀርብ አጥጋቢ ምላሽ የለም፡፡ የታቀዱ ሥራዎች ከሚጠበቀው ደረጃ በታች ለምን ውጤት አስመዘገቡ ሲባል ‹የአፈጻጸም ችግር ስለነበረ ነው› ተብሎ ድፍን ምላሽ ይሰጣል፡፡ በሕጉ መሠረት ለምን ተግባራዊ አልተደረገም ተብሎ ሲጠየቅ ‹የግንዛቤ ችግር ስለነበረ ነው› ይባላል፡፡ ተቋማት በጥሩ መሠረት ላይ ባለመገንባታቸው ምክንያት ብቻ በየጊዜው አዳዲስ መዋቅር ይሠራባቸዋል፡፡ በአግባቡ የሠለጠነ የሰው ኃይል ጥያቄ ሲነሳ መልሱ እጥረት አለ ነው፡፡ ለተፈጠሩ ችግሮች በተደራጀ መንገድ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ መዝረክረክ ባህል ሆኗል፡፡ ምክንያታዊነት ጠፍቶ በስሜታዊነት መንጎድ በርትቷል፡፡ ደንታ ቢስነት ከፍቷል፡፡ ብልሹ አሠራር በዝቷል፡፡

  ለምክንያታዊነት መጥፋትና ለደንታ ቢስነት ማበብ አንድ ሌላ ማሳያ አለ፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለፓርላማው ያቀረበው ሪፖርት ይህንን አባባል ያጠናክራል፡፡ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚታዩ ግድፈቶችን ለዓመታት ነቅሶ በማውጣት ይታወቃል፡፡ እነዚህ ግድፈቶች በየዓመቱ እንዲታረሙ በተደጋጋሚ ምክረ ሐሳቦችን ቢያቀርብም፣ ዘንድሮም ብልሹ አሠራሮች ተከምረው መጥተዋል፡፡ በሪፖርቱ መሠረት በቢሊዮን ብሮች የሚገመት የአገር ሀብት ተዝረክርኳል፡፡ ዋና ዋና የሚባሉት የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ ያልተወራረዱ ሒሳቦች፣ ያልተሰበሰቡ የታክስ ገቢዎች፣ ያልተወራረዱ የታክስ ሒሳቦች፣ በሒሳብ ሪፖርት ውስጥ ያልተካተቱ ገቢዎች፣ ማስረጃ ያልተሟላላቸውና ያልተረጋገጡ ሒሳቦች፣ ደንብና መመርያ የጣሱ ክፍያዎች፣ የግዥ አዋጅ ደንብና መመርያ ያልተከተሉ ግዥዎች፣ ማስረጃ ሳይኖር በወጪ የተመዘገቡና ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጠ ሒሳቦች፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማማከር ፈቃድ ሳይኖር ለግንባታዎች ክፍያ መፈጸም፣ ወዘተ. ናቸው፡፡ ይህ ምክንያታዊነት የጎደለው ብልሹ አሠራር ሕግ በመጣስ ጭምር የተፈጸመ ነው፡፡ የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት የታሪክ ተጠያቂነትን እንደሚያመጣ ደግሞ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

  ትውልድ ይቀረፅባቸዋል ተብሎ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው የትምህርት ተቋማት ሕግ ማክበርና ማስከበር ተስኗቸው በየጊዜው በዋና ኦዲተር ሪፖርት ይቀርብባቸዋል፡፡ ከሒሳብ አለመወራረድ እስከ ጉድለት፣ ብሎም አሳዛኝ ብክነት ድረስ ስማቸው የሚነሳው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የብልሹ አሠራር መናኸሪያ ሲሆኑ ያሳፍራል፡፡ ወጣቶች ዕውቀት የሚገበዩባቸውና የሚመራመሩባቸው የትምህርት ተቋማት፣ አዘቅት ውስጥ የሚከታቸው አጉል ድርጊት ውስጥ ሲዘፈቁ ማየት በራሱ ያሳምማል፡፡ የትምህርት ተቋማቱ ከሚያስተምሯቸው ወጣቶች በተጨማሪ ለሚገኙባቸው ማኅበረሰቦች ችግር ፈቺ ዕውቀቶችን ማመንጨት ሲገባቸው፣ ለማሰብ አዳጋች የሆነ ተግባር ውስጥ ሲገኙ ምን ይባላል? በአርዓያነት የሚጠቀሱላቸው ተግባራትን እንዲያከናውኑ ሲጠበቁ፣ ከሙስናና ከብልሹ አሠራር ጋር ስማቸው ለምን ይያያዛል? በየዓመቱ በሚቀርብ ሪፖርት ላይ ስማቸው በጥቁር ቀለም ደምቆ ከሚያዩ ይልቅ ለምን አይታረሙም? በተለይ በዚህ ችግር በተደጋጋሚ ተጠቃሽ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እስከ መቼ በዚህ ሁኔታ ይቀጥላሉ? ይህ ጥያቄ እነሱ ላይ የሚነጣጠረው ለወጣቶች ከሚኖራቸው ኃላፊነትና ከተጣለባቸው ትልቅ አደራ አንፃር ነው፡፡ በምክንያታዊነት የማይመራ የትምህርት ተቋም አያስፈልግምና፡፡

  ሌላው ትልቅ ችግር የሚስተዋለው ማኅበረሰቡ ውስጥ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ሲባል ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ ወዘተ. አደረጃጀቶች ማለት ነው፡፡ እነዚህ የተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች በመንግሥት አሠራርም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች ተሳታፊ የመሆን መብትም ግዴታም አለባቸው፡፡ የሚወክሉት ማኅበረሰብ በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተና ራሱን ችሎ እንዲቆም የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዚህ ዘመን በመረጃ ላይ ያልተመሠረቱ በርካታ ውዥንብሮች ይሰማሉ፡፡ እነዚህን ውዥንብሮች ሳያጣሩ በደመነፍስ ውሳኔ ላይ የሚደርሱ ወገኖች ለችግሮች ይጋለጣሉ፡፡ በተለይ በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ መግባባት እንዲፈጠርና የተበላሸው የፖለቲካ ባህል እንዲያከትም ማድረግ ሲገባ፣ በምክንያታዊነት ላይ ያልተመሠረቱ ጭፍን ጥላቻዎች እንዲነግሡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡ ምክንያታዊነት እየጠፋ ስሜታዊነት ልቋል፡፡ ምንቸገረኝ ባዮች በዝተዋል፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ ሰዎች ዳር እየያዙ፣ አገር የሚያጠፉ ደግሞ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ውዥንብር ይፈጥራሉ፡፡ ጠይቆ ከመረዳት ይልቅ በአሉባልታ መዋጥ የዘመኑ መገለጫ ሆኗል፡፡ ከዚህ ማጥ ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኃላፊነት ያለባቸው ወገኖች ለምን ብለው መነሳት አለባቸው፡፡

  አገር ታፍራና ተከብራ የምትኖረው ልጆቿ በአንድነት ለጋራ ዓላማ ሲቆሙ ነው፡፡ የቀድሞዎቹ ጀግኖች አባቶችና እናቶች አገራቸውን ከወራሪዎች ጠብቀው የቆዩት፣ ልዩነቶቻቸውን ችላ በማለት አንድነታቸው ላይ በማተኮራቸው ብቻ ነው፡፡ ብዙዎቹ አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች በቅኝ ገዥዎች ሲማቅቁ ኢትዮጵያ የነፃነት ችቦ እያበራች የኖረችው በዚህ ተምሳሌታዊ እሴት ነው፡፡ አሁን ግን ጎራ ለይቶ የጠላት መሳለቂያ መሆን ግድ አልሰጥ ብሏል፡፡ ልዩነትን አቻችሎ አንድነት ላይ ማተኮር የሞኝ ዜማ ሆኗል፡፡ ከጊዜያዊ የሥልጣን አምሮት በላይ የአገር ጉዳይ እየተረሳ ነው፡፡ ምክንያታዊ ሆኖ በልዩነት ላይ መነጋገር ሲገባ በነገር እየተጠዛጠዙ ለነገ ዕልቂት መቀጣጠር ልማድ ሆኗል፡፡ ይህ ደንታ ቢስነት የተፀናወተው አደገኛ አካሄድ በፍጥነት መታረም አለበት፡፡ ከአገር በላይ ምንም የለምና፡፡ ይህንን በአፅንኦት ማሰብ ይገባል፡፡ ብልሹ አሠራሮች ዝም በተባሉ ቁጥር አገር ለአደጋ ትዳረጋለች፡፡ ነገሮችን ረጋ ብሎ በማየት መልክ ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ባመሆኑ ግን  ምክንያታዊነት እየጠፋ ብልሹ አሠራር አገር እያጠፋ ነው!   

   

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ሕገወጥ ገንዘብ አስተላላፊዎችን አስጠነቀቀ

  የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በሕገወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ድርጊት ተሰማርተዋል ያላቸው...

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በቤንዚንና ነጭ ናፍጣ ላይ ጭማሪ ተደረገ

  ከዛሬ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓም እኩለ ሌሊት ጀምሮ...

  ‹‹ለሰላምና ለዕርቅ መሸነፍ የለብንም›› ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ

  የሰው ልጅ ጠብን በዕርቅ፣ በደልን በይቅርታ፣ ድህነትን በልማት፣ ክህደትን...

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡...

  ጦርነቱና ውስጣዊ ችግሮች

  መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡ ከዚህ ኢፍትሐዊ ዓለም መፍትሔ ይገኛል ብሎ መጠበቅ የማይቻልበት ጊዜ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ የዓለምን ሚዛን ያስጠብቃሉ...

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...