የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ‹‹Leaders›› በሚለው መጽሐፋቸው እንደጠቀሱት፣ አገር በአንድ ግለሰብ ወይም ሥርዓት ምክንያት ልትወድቅና ልትነሳ ትችላለች፡፡ ኒክሰን ይህን የበለጠ በማስረጃ ሲገልጡት በዊንስተን ቸርችል የመሪነት ፀጋ ምክንያት አሜሪካና አጋሮቿ ዴሞክራሲ የሚያብብባቸው አገሮች ሲሆኑ፣ በማርሻል ስታሊን የአፈና ሥርዓት የተነሳ ደግሞ ምሥራቅ አውሮፓ ነፃነቱንና መብቶቹን ተቀምቶ ይኖር ነበር ብለዋል፡፡
ለአንድ አገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት መሠረቱ የአስተዳደር ሥርዓት እንደሆነ ሪቻርድ ኒክሰን ይገልጻሉ፡፡ ሥርዓቱ አምባገነን ከሆነ ሕዝብ ይጨቆናል፣ ሕዝብ ከተጨቆነ ደግሞ ልቡ ይሸፍታል፣ ከዚያ ነፃነት ፍለጋ ወደ ጫካ ይገባል ይላሉ፡፡ በተቃራኒው ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ከሆነና ሰብዓዊ መብቶችን አክብሮ ለልማት የሚታትር ከሆነ፣ ‹ንጉሡ ሺሕ ዓመት ይንገሡ› ዓይነት አባባል በሕዝቡ ዘንድ ይሰርፅና ሥርዓቱ እንዲቀጥል ይመኛል ይላሉ፡፡
ታዋቂው ጋናዊ የነፃነት ታጋይ ኩዋሜ ንኩሩማህ ‹‹Class Struggle in Africa›› በሚለው መጽሐፋቸው ደግሞ፣ ‹‹የመንግሥት ሥርዓት የአንድ አገር ክብደትና ቅለት መለኪያ መሣሪያ ነው፤›› ይላሉ፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ለሰው ልጆች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ ከሆነ የመንግሥት ሚዛን ይከብዳል፡፡ ማንም ሰው በቀላሉ አንስቶ ሊያንቀሳቅሰውና ሊወስደው እንደማይችል ያስረዳሉ፡፡ በውስጡ በሚሊዮን የሚቆጠር ደጋፊ ኃይሎች ስላሉና ክብደት ስላለው በቀላሉ ሊነሳ እንደማይችል ይጠቁማሉ፡፡ በተቃራኒው እነዚህን አክብሮና ጠብቆ ሊሠራ የማይችል ሥርዓት ከሆነ ደግሞ ክብደት እንደሌለውና በቀላሉ ሊነሳ ይችላል ይላሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት አፍሪካ በጎሳ ፖለቲካ (Tribe Politics) የተከፋፈለች ስለሆነ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ከባድ ቢሆንም የማታ ማታ ግን አምባገነን መንግሥታት መሸነፋቸው አይቀርም፡፡
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ጭቆናን እንቢ ብሎ ለለውጥ መነሳት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ በጥንት ጊዜ በታላቅነቱ የሚወደሰው የፈረንሣይ አብዮት፣ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ወዲህ ደግሞ በማርክሲስት ርዕዮት ዓለም በተመሩ ንቅናቄዎች አማካይነት ጉልህ ትርጓሜን አግኝቷል፡፡
ኢትዮጵያም በታሪኳ የተለያዩ የአስተዳደር ሥርዓቶችንና ንቅናቄዎችን አስተናግዳ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ ከጎሳው የፖለቲካ ሥርዓት እስከ ንጉሠ ነገሥቱ፣ ከደርግ ሥርዓት እስከ ኢሕአዴግ ድረስ የተለያዩ መሪዎችንና ሥርዓቶችን እንዲሁም ተቃውሞችንና ትግሎችን አስተናግዳለች፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ከ40 ዓመታት በላይ በሥልጣን በቆዩበት ዘመን ሁሉም መንገዳቸው አልጋ በአልጋ እንዳልነበር ታሪክ ይናገራል፡፡ ኢፍትሐዊ አሠራር፣ የዴሞክራሲ ዕጦት፣ የዜጎች መብት መጣስና የነፃነቶች አለመከበር፣ እንዲሁም ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ባለመኖሩ ጭቁኑ የኅብረተሰብ ክፍል የተለያዩ ትግሎችን አካሂዷል፡፡ በተለይ በታሪክ የታኅሳስ አብዮት እየተባለ የሚጠራው የ1953 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት አንዱ የዚህ አካል እንደነበር ይነገራል፡፡ ምንም እንኳ መፈንቅለ መንግሥቱ ቢከሽፍም፣ በአገሪቷ የነበረውን ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ሌሎች ምክንያቶች ለመፈንቅለ መንግሥቱ መነሳሳት አንዱ ማሳያ እንደነበር ታሪክ ከትቦታል፡፡ የንጉሡ ሥርዓት ሲወድቅ በወቅቱ የተደራጀ ኃይል ባለመኖሩ ወደ ሥልጣን እንደወጣ የሚነገርለት የደርግ መንግሥት፣ በትረ ሥልጣኑን ከያዘ በኋላም በርካታ ሕዝባዊ ተቃውሞችና ንቅናቄዎች ተስተናግደውበት እንደነበር ይጠቀሳል፡፡
የደርግን የአገዛዝ ሥርዓት በመቃወም የአስተዳደር ለውጥ እንዲመጣ ከታገሉት ኃይሎች መካከል ሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) አንዱ ነው፡፡ የደርግን የ17 ዓመታት የሥልጣን ጉዞ መግታት የቻለውም እሱ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሕወሓት የደርግን የአምባገነን የአስተዳደር ሥርዓት በመቃወም የትግራይን ሕዝብ ከዚህ ጭቆናና ግፍ ለማውጣት ያደረገው ትግል እንደነበር መዛግብቶች ይጠቁማሉ፡፡
የንጉሠ ነገሥቱን ሥርዓት ደርግ ጣለው፡፡ የደርግ ሥርዓትን ደግሞ በሕወሓትና የሌሎች ሦስት ድርጅቶች ግንባር የሆነው ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ነው፡፡ ለ26 ዓመታት ያህል በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ነው፡፡
ኢሕአዴግ በ26 ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ ያስመዘገባቸው ድሎችና ውጤቶች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ አገሪቱን ከማሽቆልቆል ጉዞ አውጥቶ በአሁኑ ወቅት ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ አድርጓል፡፡
ሕገ መንግሥት በመቅረፅ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ማስፈን፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ማረጋገጥ፣ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት ወዘተ እንደቻለ ኢሕአዴግ የሚኩራራባቸው ናቸው፡፡
በየዓመቱ ግንቦት 20 ሲመጣ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በተለያዩ ፕሮግራሞችና ዝግጅቶች በዓሉን ሲያከብር ይስተዋላል፡፡ በየዓመቱ የተለያዩ መሪ ቃሎች እየተመረጠና ብዙ ገንዘብ እየተበጀተ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ለሩብ ክፍለ ዘመን ያህል ሲከበር ቆይቷል፡፡
የዘንድሮው ግንቦት 20፣ 26ኛ ዓመት የድል ክብረ በዓል ደግሞ ‹‹የሕዝቦች እኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ፌዴራላዊ ሥርዓት እየገነባች ያለች አገር-ኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ ግንቦት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚሊየም አዳራሽ ከመከናወኑ በፊት ለሳምንታት ያህል በአገሪቱ በሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ ፓናሎችና ውይይቶች፣ እንዲሁም ሰማዕታትን በማሰብና በመዘከር እንደተከበረ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ገልጿል፡፡
የዘንድሮው የግንቦት 20 የድል በዓል እሑድ ግንቦት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ የማጠቃለያ ፕሮግራም ሲዘጋጅ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የተለያዩ አገር አምባሳደሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተው ነበር፡፡
26ኛው የግንቦት 20 የድል በዓል በሚሊኒየም አዳራሽ በተለያዩ ታዋቂና አማተር ድምፃውያን ሙዚቃ ታጅቦ ፕሮግራሙ ተጀምሯል፡፡ በአዳራሹ በመገኘት ለመታዘብ እንደተቻለው የተጠራው ሕዝብ ሙሉ በሙሉ አልመጣም፡፡ በአዳራሹ አራቱም አቅጣጫ ክፍተቶች ነበሩ፡፡
በዋናነት የዚህን በዓል ዓላማ ተረድተው ወደፊት ኢትዮጵያን ይረከባሉ የሚባሉት ወጣቶች በብዛት እንዳልመጡ አንዳንድ ተሳታፊዎች ስሜታቸውን አጋርተዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ በብዛት የተገኙት እናቶች በመሆናቸውና ወጣቶች በብዛት ባለመምጣታቸው ቅር እንደተሰኙ ተሳታፊዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ የተወሰኑ ወጣቶች ዘንድሮ በዓሉ እንዲያውም መከበር እንደሌለበት ሲናገሩ ቢደመጡም፣ ለምን እንደመጡ ለተጠየቁትም የተለያዩ ሙዚቃዎች ስላሉ ዘና ለማለት እንጂ በግል ለማክበር እንዳልሆነ በግልጽ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
የማጠቃለያ የግንቦት 20 የድል በዓል ዝግጅት በሰባት ሰዓት ይጀምራል ተብሎ ጥሪ ቢተላለፍም፣ ሳይጀመር እስከ አሥር ሰዓት መዝለቁ ቅር እንዳሰኛቸው ታዳሚዎች አክለው ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ ማሚቱ ብርሃነ ይባላሉ፡፡ የ60 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ በማጠቃለያ ዝግጅቱ ላይ ለመሳተፍ ሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝተው ነበር፡፡ የበዓሉ አከባበር ምን ይመስላል? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ዘንድሮ እንደከዚህ ቀደሙ ደማቅና ሳቢ አልነበረም ብለዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት በየዓመቱ በዚህ አዳራሽ እየተገኘን ታዋቂ አርቲስቶች፣ ታጋዮችና ሌሎች ሞቅና ደመቅ ባለሁኔታ ይከበር ነበር፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የዕለቱ ፕሮግራም በሙዚቃ ተጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ንግግር ማብቃቱ የዘንድሮው ክብረ በዓል የተቀዛቀዘ መሆኑ አንዱ ማሳይ እንደሆነ የክብረ በዓሉ ታዳሚዎች ተናግረዋል፡፡ ከክብረ በዓሉ ይልቅ ሰሞኑን ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የተመረጡት ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) በሥፍራው ተገኝተው ለታዳሚው ሰላምታ ሲያቀርቡ የተሰማው ጩኸትና ደስታ አዳራሹን በዓል፣ በዓል አስመስሎት ነበር፡፡
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ግንቦት 20 በኢትዮጵያ ውስጥ በእኩል የመልማት ጥያቄን የመለሰ፣ የሕግ የበላነትን በማስፈን የኢትዮጵያ ህዳሴ ፍኖተ ካርታ የተቀረፀበት ዕለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ግንቦት 20 በሕዝቦች መከባበርና መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገንባት፣ በረጅሙ የጭቆና ታሪክ የተደፈቀበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ይህን ይበሉ እንጂ አሁንም ድረስ በአገሪቱ ጭቆና መኖሩን የሚናገሩት የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ መሥራችና ፕሬዚዳንት የነበሩት ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ በዚህ ሥርዓት ሌሎች አገዛዞች ከዚህ በፊት ያደርጉት ከነበረው የተለየ ነገር እንዳላዩም ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩት የአካባቢ ንጉሦች፣ ንጉሥ ነገሥት ለመሆን በጦርነት እያሸነፉ የፈለጉትን ዓይነት ሥርዓት እየመሠረቱ ይኖሩ እንደነበር የሚናገሩት ኢንጂነር ይልቃል፣ አሁን ያለውን ሥርዓት ለየት የሚያደርገው በጎሳ አድርጎ ከዚያ በኋላ ጥቂቶች ሌላውን ጠፍንገው ይዘው የሚፈልጉትን የሚያደርጉበትና ብዙዎች ወደ እስር ቤት የተወረወሩበት ጊዜ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የጭቆና ታሪክ የተደፈቀበት ጊዜ ላይ እንደደረስን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢናገሩም አሁንም ድረስ ጭቆናው እንዳለ የሚናገሩት የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አባልና የፓርቲው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት ንጋት አስፋው (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ጭቆና ባይኖር ኖሮ እኮ ከዚህ በፊት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተከሰቱት ረብሻዎችና ተቃውሞዎች ባልተከሰቱ ነበር፤›› ባይ ናቸው፡፡ ስለሆነም የሰው ሕይወት አይጠፋም ነበር ይላሉ፡፡
ግንቦት 20 ይዟቸው የመጣ ብዙ ድሎች ቢኖሩም፣ ዘመኑ ከሚጠይቀው የአስተዳደር ሥርዓትና ዘመናዊነት አንፃር ሲታይ ግን አሁንም ብዙ የሚጎድሉ ነገሮች እንዳሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ሥልጣኔ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ እየተቀጣጠለ ባለበት በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ብዝኃነት፣ አብሮነትና መልካም ግንኙነት፣ ተደጋጋፊነትና አጋርነት፣ መከባበርና መቻቻል ሊጎለብቱና ወደ ከፍታ ወጥተው በተግባር ሊታዩ እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡
በሕገ መንግሥቱ ከሠፈሩት 106 አንቀጾች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ስለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተደነገጉ ቢሆኑም፣ ሕጉ ሳይሸራረፍ መሬት ላይ እንዲውል በማድረግ ረገድ ሰፊ ችግሮች እንዳሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የሰዎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፍ የተረጋገጠበት አገር መመሥረት እንዳልተቻለ ይገልጻሉ፡፡ ኢንጂነር ይልቃል የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ለአንድ አገር ዕድገት ወሳኝ ቢሆንም፣ ይህንን በኢትዮጵያ በተግባር ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ይናገራሉ፡፡
በ26ኛው የግንቦት 20 ክብረ በዓል ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ድሉ ባለፈው ሥርዓት የነበረውን የጎላ ችግር ሥር ነቀል በሆነ መንገድ በመፍታት ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እንዳስቻለ ግን ተናግረዋል፡፡ ኢንጂነር ይልቃል ደግሞ በአሁኑ ወቅት ኢሕአዴግ በአገር ውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ ባለመቻሉ፣ አገሪቷን በአስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጅ ውስጥ ከቷታል ይላሉ፡፡ ዶ/ር ንጋትም በዱላ የመጣ መንግሥት በመሆኑ በዱላ የአገሪቱን ሰላም እያስከበረ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ከዓመት በፊት በአገራችን በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ከ600 በላይ ንፁኃን ዜጎች ሞተው አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጅ ውስጥ ወድቃ ባለበት በዚህ ዘመን የዘንድሮው የግንቦት 20፣ የድል በዓል መከበር እንዳልነበረበት የሚናገሩ ወገኖችም አሉ፡፡ ምንም እንኳ አገሪቱ ግንቦት 20 የድል በዓልን በየዓመቱ ማክበር እንዳለባት በአዋጁ ላይ ቢደነገግም፣ የዘንድሮውን የድል በዓል ሁሉም በየቤቱ እንዲያስባቸው ቢደረግ ጥሩ ነበር የሚሉ ወገኖች ከየአቅጣጫው ይሰማሉ፡፡
ደርግ 17 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ረግጦ ሲገዛ በታሪኳ ወደማይቀለበስ የአንድነት ደረጃ የደረሰችበት እንደሆነ ሲናገር ኖሯል፡፡ ከሰማይ ትእዛዝ ካልሆነ በስተቀር ማንም አካል ቢመጣ ደርግን ከበትረ ሥልጣኑ የሚያነሳው እንደማይኖር ይገለጽ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ ኢሕአዴግ በበኩሉ ኢትዮጵያን ከመበታተን አድኖ ሁሉንም ሕዝቦች የሰላም ዘብ ያደረገ ሥርዓት መገንባት መቻሉን ይገልጻል፡፡ ኢንጂነር ይልቃል ደግሞ ኢሕአዴግ አገሪቱን አሳሳቢ ደረጃ ላይ የጣለ፣ አገሪቱን ብቻ ሳይሆን የሰዎችን አብሮ የመኖር ህልውና ችግር ውስጥ የከተተ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በመስዋዕትነት የተገኘውን የድል በዓል ወደ ተግባር የመነዘረው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ የሕዝቦችን ያልተገደበ ተሳትፎ በማስተባበር በመምራት፣ ፈጣን፣ ተከታታይና ፍትሐዊነት ላይ የተመሠረተ ልማት ማረጋገጥ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡ የተመዘገበው ዕድገት የዜጎችን ዕድገት ከማሻሻሉም በላይ ሁሉም ሕዝቦች አገሪቱ የምታመነጨውን ሀብት በግልጽና ፍትሐዊ ቀመር የሚከፋፈሉበት፣ የትኛውም ሕዝብ የበይ ተመልካች የማይሆንበትና የሚጠቀምበት ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ በተለይ አገሪቱ በዘረጋቸው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂና ባስመዘገበቸው ስኬት የአፍሪካ ድምፅ ለመሆን መብቃቷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት 26 ዓመታት አገሪቱ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ተጨባጭ ለውጥ ቢያመጡም፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራት ጉዞውን አስቸጋሪ እንዳደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
በተዘረጋው የፌዴራሊዚም ሥርዓት የዜጎች የፖለቲካ ኢኮኖሚ መብት የተጠበቀ መሆኑን ኢሕአዴግ ይገልጻል፡፡ የፌዴራሊዝም ሥርዓት መዘርጋት የአገሪቱን ሁለንተናዊ ችግር ከመፍታት አንፃር ጉልህ ሚና እንዳለው የመንግሥት አካላት ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 መሠረት ራስን በራስ የማስተዳደር ብሎም እስከ መገንጠል አንዱ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ውጤት እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ ግንቦት 20 ይዟቸው ከመጣ ጉዳዮች መካከል አንዱ ራስን በራስ የማስተዳደር ብሎም እስከ መንገጠል ሕገ መንግሥታዊ መብት መስጠት ተገቢ እንዳልሆነ ብዙዎቹ ሲቃወሙ ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም. በተደረገው አገራዊ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የዚህን አንቀጽ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መካተትና በተገቢነት ላይ ጥያቄዎችን አንስተው ሲሞግቱ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ኢንጅነር ይልቃል አሁንም ድረስ ይኼ ሥርዓት አገሪቱን ወደፊት አደጋ ላይ እንዳይጥላት ሥጋት አላቸው፡፡ ዶ/ር ንጋት በበኩላቸው፣ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከኢሕአዴግ የበረሃ ትግል ጋር ተያይዞ እንደመጣ ይናገራሉ፡፡ ቋንቋን መሠረት ያደረገው የፌዴራሊዝም ሥርዓት የኋላ የኋላ አደጋ ሊኖረው እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢሕአዴግ በ26 ዓመት ጉዞው 5.5 ሚሊዮን ወጣቶችን በጥቃቅንና አነስተኛ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች አደራጅቶ በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ቢችልም፣ አሁንም ድረስ በሥራ ፈጠራ በኩል የሚታዩ ክፍተቶች እንዳሉና የወጣቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ያልተሻገራቸው ድልድዮች መኖራቸውን ያምናል፡፡ በአገሪቱ ተከስቶ ለነበረው ሁከትና ብጥብጥ አንዱ ምክንያት ከወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር የተያያዘ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ይኼን ችግር ለመፍታትም መንግሥት አሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በመበጀት የአገሪቱን ወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት ሲንቀሳቀስ ተስተውሏል፡፡ ይኼም ሆኖ በቂ እንዳልሆነና አሠራሩ ላይም ሙሰኞች እጃቸውን በረዥሙ እንዳያስገቡበት ሥጋት አለ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለ26 ዓመታት በኢሕአዴግ የአመራር ሥርዓት ተሳፍሮ ወደ ልማት እያደረገ ያለው ጉዞ በጤናው፣ በትምህርቱ፣ በመንገድ ልማቱ ለውጦች እንዳስመዘገበ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ይገልጻል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ መልካም ጅምሮች ቢኖሩም እነዚህ ሥራዎች በጥራትና በብቃት የተሠሩ ባለመሆናቸው በታሰበው የልማት ጉዞ ተሳፍሮ በሚፈለገው ደረጃ ላይ መድረስ አስቸጋሪ እንደሆነ ኢንጂነር ይልቃል ይናገራሉ፡፡ ባንኮች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና የተለያዩ የግሉ ዘርፎች ጥሩ ጅማሬዎች ቢያሳዩም፣ እነዚህ እየፈጠሩት ያለው የሥራ ዕድል አበረታች ቢሆንም፣ የጥራትና የዘላቂነት ጉዳይ ግን አሁንም የአገሪቱ ትልቁ ችግር እንደሆነ ኢንጂነር ይልቃል ይጠቁማሉ፡፡
ከዛሬ 26 ዓመታት በፊት የአገራችን ወጣት ለጦርነት መስዋዕት ይሆን እንደነበር የገለጹት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ነገሪ ሌንጮ፣ በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን በልማት ላይ አድርጓል ብለዋል፡፡ የመንገድ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የቴሌ ኮሙዩኒኬሸን፣ ወዘተ ሥራዎች የሚበረታቱና በኅብረተሰቡ ዘንድ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑን የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ኢሕአዴግ በ26 ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ ወቅት መውጣት ያልቻላቸው ተራራዎች እንዳሉም ያስረዳሉ፡፡ ሥር የሰደደ ሙስና፣ የመልካም አስተዳዳር ችግር፣ ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች አለማክበር፣ የተጠያቂነት፣ የግልጽነት፣ ወዘተ ችግሮች አሁንም እንዳሉና እነዚህንም በአፋጣኝ መፍታት እንዳልተቻለ ይገልጻሉ፡፡ ዓለም ከደረሰበት የሥልጣኔ ደረጃና ዘመኑ ከሚጠይቀው ጥበብ የመነጨ አመራር በመፍጠር፣ አገሪቱን ከጫፍ ጫፍ ማንቀሳቀስ እንዳልተቻለና ወደፊትም የምትራመድበትን ዘዴ ከመቀየስ አንፃር ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡
የግንቦት 20 የድል በዓል ሲከበር የአገሪቱን ሁለንተናዊ ችግሮች በመፍታት ረገድ የላቀ ሥራ በማስመዝገብ መሆን እንዳለበት የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ የሕዝቦችን እኩልነት በማረጋገጥና ወደ ተሻለ ደረጃ በማሸጋገር በአገሪቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተገቢ እንደሆነም በመግለጽ፡፡ እንዲሁም ከሁሉም በላይ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ኢትዮጵያዊያን ተሳታፊ የሚሆኑበት አመቺ ሁኔታ መፍጠር መቅደም አለበትም ይላሉ፡፡
ከዚህ በፊት ተፈጥረው የነበሩት ችግሮች ማሳያ በመሆናቸው፣ መንግሥት ዛሬ ነገ ሳይል ቁርጠኛ በመሆን ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ መልካም ሥራ ማከናወን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ መንግሥት ሁሉንም ነገር ጨምድዶ ይዞ እኔ ብቻ መኖር አለብኝ፣ ሌሎቻችሁ እኔ የምላችሁን ብቻ አዳምጣችሁ መፈጸም ነው ከሚል አባዜ መውጣት እንዳለበት የሚናገሩት ኢንጂነር ይልቃል፣ የሐሳብ ብዝኃነት በአገሪቱ እንዲስተናገድ በሩን መክፈት አለበት ይላሉ፡፡ በ26 ዓመት የኢሕአዴግ ጉዞ በአገሪቱ ጠንካራ የፖለቲካ ምኅዳር በመፍጠር የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምፅ የሚሰማበትን ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበትም ያስረዳሉ፡፡
የሥልጣን ባለቤት ለመሆን ጉልበትና መሣሪያ ሳይሆን ሕዝብ ነው የሚለውን ጉዳይ ኢሕአዴግ በቅጡ መውሰድ እንዳለበት የሚናገሩ አሉ፡፡ ለወራት በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ረብሻ ከ600 በላይ ዜጎች ሕይወት ሲጠፋ፣ አንዳንዶቹ በመንግሥት ቸልተኝነት ዕርምጃ የተወሰደባቸው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የመንግሥት አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ያረጋገጠው ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በኢሕአዴግ የ26 ዓመታት የሥልጣን ዘመን አገሪቱ በሚፈለገው የዕድገት ደረጃ ላይ መድረስ እንዳልቻለች የሚናገሩት ዶ/ር ንጋት፣ የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ ነው የሚለውን መርህ በመያዝ መንግሥት ሪፎርም ማካሄድ አለበት ይላሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በ26ኛው የግንቦት 20 ክብረ በዓል ማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ በሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ በአንዳንድ ኪራይ ሰብባቢዎችና በልማት አደናቃፊ ኃይሎች የተነሳ መንግሥት በሁለት እግሩ ቀጥ ብሎ መሄድ እንዳልቻለ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢንጂነር ይልቃል የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ሆኖ የፈለገውን የሚሽርበት፣ መንግሥት በሠራው ሥራ ተጠያቂ የሚሆንበት፣ ዕርምጃ የሚወሰድበት፣ የሚከሰስበት፣ አለፍ ብሎም የሚቀጣበት ሥርዓት በአገሪቱ እስካልተበጀ ድረስ ወደፊት ከዚህም ቀደም በአገሪቱ ተፈጥሮ የነበረውን ዓይነት ክስተት ላለመከሰቱ ምንም ዋስትና የለም ባይ ናቸው፡፡ ዶ/ር ንጋት በበኩላቸው፣ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ሙሉ በሙሉ ካልተረጋገጠ ጉዳዩ አሁንም አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
የአገሪቱ የ26 ዓመታት የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ በእክሎች የታጀበና የሚፈለገውን ያህል ፍሬ ያላፈራ በመሆኑ፣ መንግሥት ራሱን ደጋግሞ መፈተሽ እንዳለበት ዶ/ር ንጋት ይናገራሉ፡፡ ክብረ በዓሉ ሲከበር የአገሪቱን ሁለንተናዊ ችግሮች ከሥር መሠረቱ በመለየትና ወደፊት ፈተና ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ ኢፍትሐዊ አሠራሮችን በማስወገድ፣ በሁሉም መስኮች ዕድገት ማስመዝገብ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡
በሕገ መንግሥቱ ላይ የሠፈሩ መብቶች ሳይሸራረፉ መሬት መውረድ እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ፣ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ ሁሉም ዜጎች በፍትሐዊነት የሚመሩባት አገር እንድትኖርም ያሳስባሉ፡፡