Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ማራቶን ሞተርስ የሃዩንዳይ መኪኖችን ለመገጣጠም ስምምነት ተፈራረመ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በዓመት እስከ 2500 ተሽከርካሪዎች የሚገጣጥም ፋብሪካ ይተክላል

ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ በአገር ውስጥ ተሽከርካሪዎችን ለመገጣጠም ከደቡብ ኮሪያው ሃዩንዳ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራረመ፡፡ የሁለቱ ኩባንያዎች ስምምነት ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ እንደቆየ ነው፡፡

ማራቶን ሞተርስ ስድስት ዓመታት በፈጀ ሒደት ውስጥ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመትከል የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከማውጣት ባሻገር፣ የቦታ ጥያቄ አቅርቦ እስኪሰጠው ሲጠባበቅ መቆየቱ ተገልጾ፣ እነኚህን ሒደቶች በማጠናቀቅ ከሃዩንዳይ ኩባንያ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚችልበትን ድርድር ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል፡፡

ሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ሳሪስ አካባቢ በሚገኘው የመኪና ዕቃዎች መለዋወጫና የሽያጭ ማሳያ አዳራሽ ውስጥ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቱሉ ዲምቱ አካባቢ ለመገጣጠሚያ ፋብሪካው መገንቢያ የ30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ማግኘቱን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መልካሙ አሰፋ አብራርተዋል፡፡

የተሽከርካሪ መገጣጠሚያውን ለመገንባት ግማሽ ቢሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል በማስመዝገብ ፈቃድ ያገኘው ማራቶን ሞተርስ፣ መገጣጠሚያው ሲጠናቀቅ በዓመት ከ2,000 እስከ 2,500 ተሽከርካሪዎችን ለገበያ ለማቅረብ ማቀዱን ገልጿል፡፡

ስምንት ዓይነት ሃዩንዳይ ሠራሽ ሞዴሎችን በመያዝ ሥራ እንደሚጀምር የሚጠበቀው መገጣጠሚያ፣ የመጀመሪያው ምርት በመጪው ዓመት ጥር ወር ገደማ ለገበያ እንደሚያቀርብም አቶ መልካሙ ገልጸዋል፡፡

ከሚያስመጣቸው ሞዴሎች ውስጥ ኢዮን ባለ 800 ሲሲ የቤት አውቶሞቢልን ጨምሮ፣ ኤስዩቪ፣ የሰዎችና የአነስተኛ ጭነት ማጓጓዣ መኪናዎችን ለገበያ እንደሚያቀርብ ኩባንያው አስታውቋል፡፡

ዘመናዊ ፋብሪካ ለመገንባት የሚያስችሉና ለመገጣጠሚያ የሚውሉ ማሽኖችን ከደቡብ ኮሪያ በማስመጣት ወደ ሥራ እንደሚጀምር ያስታወቀው ኩባንያው፣ ሥራውን የሚከታተሉ የሃዩንዳይ ኩባንያ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንደሚመጡም ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡  

ማራቶን ሞተርስ እስካሁን ለገበያ ሲያቀርባቸው የቆዩት ከውጭ ሙሉ በሙሉ ተሠርተውና ተገጣጥመው የሚመጡ (Completely Built up) የነበሩ ሲሆኑ እነዚህ መኪኖች በአገር ውስጥ ሲገጣጠሙ ግን እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ግብዓት ከዚሁ በመጠቀም በአንድ ተሽከርካሪ ከ15 እስከ 18 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ለማምጣት እንደሚቻል አቶ መልካሙ ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት ለአብነት ኢዮን የሚባለው የቤት አውቶሞቢል ሞዴል የሚሸጥበት ዋጋ 425 ሺሕ ብር ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ተገጣጥሞ ሲቀርብ ግን የ16 በመቶ ቅናሽ እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡

‹‹አዳዲስ የቤት አውቶሞቢሎችን በአገር ውስጥ ገጣጥሞ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ከውጭ የሚገቡ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር በመቀነስ የመንገድ ላይ አደጋንና የበካይ ጋዞች ልቀትን ለመቀነስ አስተዋጽኦ ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡

እንደ አቶ መልካሙ ማብራሪያ፣ መገጣጠሚያ ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር ለመኪና ግብዓት የሆኑ ማለትም እንደ ባትሪ፣ ጎማ፣ የሰው ኃይልና ሌሎችም ተዛማጅ ግብዓቶች በአገር ውስጥ እንደሚሟሉ ይጠበቃል፡፡

ወደፊት በአገር ውስጥ የሚታየው የዘርፋ መስፋፋትና የኢንዱስትሪው ዕድገትን ተከትሎ የተሽከርካሪ ግብዓቶችን ከሃዩንዳይ ኩባንያ ጋር በመነጋገር ተመጣጣኝ መለዋወጫ ከአገር ውስጥ ምንጮች ለማቅረብ የሚቻልበት አቅም ከተፈጠረ፣ ከውጭ የሚገባውንም የሞተር አካል ለመቀነስ እንደሚቻል ተብራርቷል፡፡

በአንድ ሊትር ነዳጅ እስከ 26.7 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዝ የሚችሉ ተሽከርካሪዎችን ከስምንት ወራት በኋላ ገጣጥሞ ለገበያ ለማቅረብ የተነሳው ማራቶን ሞተርስ፣ ትልልቅ የጭነት ተሽከርካሪዎችንም ለማገጣጠም ዕቅድ እንዳለው አስታውቋል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ትኩረቱን በአስተኛና መለስተኛ አውቶሞሎች እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ማራቶን ሞተርስ የሚገነባው ፋብሪካ የሕንፃ ተቋራጭ ሠራተኞችን ጨምሮ ለ500 ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡ የሃዩንዳይ ተሽከርካሪዎችን ለመገጣጠም የተነሳው ማራቶን ሞተርስ ወደ ሥራው ለመግባትና ፈቃድ ለማግኘት ከሁለት ዓመት በላይ እንደወሰደበት አስታውሷል፡፡

መገናኛ አካባቢ ከሚገኘው የመለዋወጫና የሽያጭ ማሳያ በተጨማሪ ሳሪስ ሠፈር ውስጥ ባስገነባው ሕንፃ የሃዩንዳይ ምርት ማሳያና የመለዋወጫ ዕቃ ሸጫና መገጣጠሚያ ማዕከሉን ይፋ ካደረገ ሰነባብቷል፡፡

በአፍሪካ የሃዩንዳይ ተሽከርካሪዎችን ገጣጥመው ለገበያ በማቅረብ ከሚጠቀሱ አገሮች መካከል ደቡብ አፍሪካ ቀዳሚዋ ሆናለች፡፡ 60 ሺሕ የሃዩንዳይ መኪኖች ለገበያ ከሚቀርቡባት ደቡብ አፍሪካ ባሻገር፣ አልጄሪያ 50 ሺሕ መኪኖችን በየዓመቱ ለገበያ በማቅረብ ከቀዳሚዎቹ መካከል ተሠልፋለች፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች