Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የቱሪዝም ዘርፉ በሌላ ሙያ በሠለጠነ ሰው መሞላቱ አንዱ ክፍተት ነው››

አቶ ልዑል ዮሐንስ፣የአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የስሜን ተራራ፣ ፋሲለደስና ሌሎችም በርካታ ቅርሶች የሚገኙበት የአማራ ክልል ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የተለያዩ የባህልና ቱሪዝም ውይይቶች አስተናግዷል፡፡ በጎንደር የባህልና ቱሪዝም ዐውደ ጥናት ሲካሄድ በላሊበላ ለሙዚየም አስተዳዳሪዎች፣ አስጎብኚዎችና ሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ስለ መርሐ ግብሮቹና በክልሉ ስላሉ ቅርሶች ጥበቃና አጠቃላይ የቱሪዝም ዘርፉ እንቅስቃሴ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ልዑል ዮሐንስን ምሕረተሥላሴ መኰንን  አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ላሊበላ የተካሄደው የአራት ቀናት ሥልጠና የትኩረት አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው?

አቶ ልዑል፡- ሥልጠናውን የሰጠነው በቱሪዝም ልማት፣ በቅርስ እንክብካቤና በባህል ፖሊሲው ላይ ነው፡፡ በክልሉ ትላልቅ ገዳማትና ቅርሶች ስላሉ የሃይማኖት አባቶች ቅርሶቹን ስለሚይዙበት መንገድና ስለ ግምጃ ቤት አስተዳደር አሠልጥነናል፡፡ ለምሳሌ እንደ ዋልድባ፣ ማኅበረ ሥላሴና ጣና ያሉ ገዳማት ላይ ትላልቅ ሙዚየም የሚያስተዳድሩ አባቶች አሉ፡፡ ሥልጠናው በአመራሮች፣ ባለድርሻ አካላትና የሃይማኖት ሰዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የሰጡት የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ሥልጠናውን የምንሰጠው በየዓመቱ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት የተካሄደው ደብረ ማርቆስ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ከቅርስ ጥበቃ ጋር በተያያዘ በክልሉ ያሉ ተግዳሮቶችን ሥልጠናው በምን መንገድ ይቀርፋል ተብሎ ይታሰባል?

አቶ ልዑል፡- የቱሪዝም ልማቱን በተመለከተ ትልቁን ምስል ያለመመልከት ችግር አለ፡፡ ባለሙያው ቱሪዝም ምን ማለት ነው? ከሚለው ጀምሮ እንዴት ይለማል የሚለውን አያውቅም፡፡ አብዛኛው በቱሪዝም ያልሠለጠነ ስለሆነ ሥልጠና ያስፈልጋል፡፡ የቱሪዝም ዘርፉ በሌላ ሙያ በሠለጠነ ሰው መሞላቱ አንዱ ክፍተት ነው፡፡ በመዳረሻ ልማት በተለይም ከሙዚየም አስተዳደር ጋር በተያያዘም ክፍተት አለ፡፡ ትልቆቹ ሀብቶችና የቅርሶች ምሽጎች ገዳማት ስለሆኑ እነዚህን የሚያስተዳድሩ አባቶች በእውቀት መታገዝ አለባቸው፡፡ ቅርሶቹን ወደ አንድ ማዕከል መሰብሰብ ስለማንችል የሙዚየም ግንባታ ዲዛይን ሰጥተናል፡፡ በጀት እንመድብና እንዲገነባ እናደርጋለን፡፡ የሙዚየም አስተዳደር ከቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ ጋር ይያያዛል፡፡ በገዳማቱ ግምጃ ቤቶች ዕቃ በዕቃ ተደራርቦ ይገኛል፡፡ የትኛው ዕቃ ከየትኛው ቀጥሎ እንደሚመጣ፣ እንዴት ማናፈስ እንደሚችሉና በአጠቃላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ እንዴት እንደሚከላከሉ ስለ ዘመናዊ ሙዚየም ሳይንስ አሠልጥነናል፡፡ አባቶቹ ላሊበላ እንዲመጡ የፈለግነው ተከዜ ገዳምን ለማሳየት ነው፡፡ በገዳሙ ጥላ ዘርግተው አይለምኑም፡፡ አባቶቹ በዕደ ጥበብና እርሻ ላይም ኢንቨስት የሚያደርጉበት ተሞክሮ ወደ ሌሎች ገዳሞችም እንዲስፋፉ እንፈልጋለን፡፡  ባረጁ ቅርሶች ጥገና በኩል በክልሉ ብዙ ክፍተት አለ፡፡ በባህል ፖሊሲው መጤ ባህሎችን ስለማቋቋም ማስገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡ ባለድርሻ አካሎቹ መረጃ ስለሌላቸው ፈተናዎቹን አያውቋቸውም፡፡ አመራሮች ነገ ቦታውን ለቀው ሲሄዱ፣ አብዛኞቹ ባለሙያዎች ግን ጡረታ እስከሚወጡ በቦታው ስለሚቆዩ በየዓመቱ ሥልጠናውን እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኞቹ የዘርፉ ሠራተኞች በሙያው አለመሠልጠናቸው ምን ተፅዕኖ አሳድሯል?

አቶ ልዑል፡- በቅርስ ጥገና ያለብን ፈተና ከቴክኖሎጂ፣ ከገንዘብና የሰው ኃይል ጋር ይያያዛል፡፡ አላዋቂ ሰዎች ይጠግናሉ፡፡ ላሊበላን አላዋቂ ሰዎች ጠግነውት እንዴት እንደተበላሸ ማየት ይቻላል፡፡ በየቦታው እየገጠመን ያለው ፈተና አላዋቂዎች ወደ ቅርስ ጥገና መግባታቸው ነው፡፡ በሙያው ያልሠለጠነ ሰው ዘርፉን ሲመራው፣ ቅርሱን ሲጠብቅ፣ ባህሉን ለማልማት እንቅስቃሴ ሲያደርግ፣ ሙዚየም አስተዳድራለሁ ሲልም ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ ለምሳሌ በክልሉ የሙዚየምን ችግር ለመፍታት በየገዳማቱ ሙዚየም መሠራት ተጀመረ፡፡ በፊት እያገለገሉ ዕጣን ይታጠኑ የነበሩት ዕቃዎች በሙዚየሙ ሳይታጠኑ አይጥ እና ብል በልቷቸው ተበላሹ፡፡ የሙዚየሙ አስተዳዳሪዎች ሙዚየሞች መታጠን እንዳለባቸው ማወቅ አለባቸው፡፡ በዚህ ወቅት እሳት እንዳይነሳ ጥንቃቄም ያስፈልጋል፡፡ የአጭር ጊዜ ሥልጠና የንቅናቄው አንድ አካል ሲሆን፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ረዥም ሥልጠና እየሰጠን ነው፡፡ በየቦታው የሕዝብ ውይይትም እያደረግን ነው፡፡ ዘርፉን የሚመሩት ሰዎች ለረዥም ጊዜ ስለሠሩ ችግሮቹን ያውቋቸዋል፡፡ መፍትሔውን ከነገርናቸው አብዛኛው ሰው ስህተቱን አርሞ ለውጥ ይመጣል፡፡ ከሥልጠና በኋላ በየቦታው የመጣውን ለውጥ እንከታተላለን፡፡ ያሠለጠናቸው ሰዎች በየዞኑ ሄደውም ያሠለጥናሉ፡፡ ውጤቱ በረዥም ጊዜ ስለሚታይ ጊዜ ይወስዳል፡፡ የአስጎብኚዎች ማኅበር ተወካዮችም በየአካባቢያቸው ስላለው ክፍተት ሠልጥነዋል፡፡ ለምሳሌ ስሜን ተራራ አካባቢ ያለው ዋናው ችግር እንግዶች ሲታመሙ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ዕርዳታው ጥሩ አለመሆኑ ነው፡፡ ላሊበላ ቤተ ክርስቲያናት ከተሠሩለት ሃይማኖታዊ ዓላማ አንፃር ክብር ያለመስጠት ክፍተት አለ፡፡ የጎንደር ችግር ከመስተንግዶ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የባህር ዳር ክፍተት ከውኃ  ቱሪዝም ጋር ይያያዛል፡፡ ገዳማቱ ሲጎበኙ በጀልባ ጉዞና በከተማዋ መካከል ያለው አገልግሎት ከፍጥነትና ከጥራት አንፃር መሻሻል አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በጎንደር ከተማ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በተዘጋጀ ጉባኤ በክልሉ ካሉ ችግሮች መካከል ከአስጎብኚዎች ሙያዊ ብቃትና ከመስተንግዶ ጋር የተያያዙ ክፍተቶች ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህን ለመፍታት ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ልዑል፡- የጥናትና ምርምር ጉባኤውን ስናዘጋጅ ከምርምሮቹ የሚገኙ ሐሳቦችን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ አብዛኞቹ የጥናት ውጤቶች በክልሉ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ከሌሎች ክልሎች የተነሱትም ከኛ ጋር ይመሳሰላሉ፡፡ ችግሮቹ ምን እንደሆኑና ስለሚፈቱበት መንገድ አስተምረውናል፡፡ የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረምና የባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከሚኒስቴሩ ጋር ያዘጋጀው የመጀመሪያው የጥናት ጉባኤ በጋራ መሥራት እንደምንችልና የተሻለ ነገር እንደምናገኝ ያየንበት ነው፡፡ ቱሪዝም ለኢትዮጵያ አዲስ ቢዝነስ ነው፡፡ ከሌሎች ዘርፎች አኳያ አዲስ በመሆኑ አሠራሩ ግድፈት ቢኖረውም እየሄድንበት ያለው ፍጥነት ይደነቃል፡፡ ከ10 እና 15 ዓመታት በፊት የነበረውና አሁን ያለው ሲነፃፀር በጎንደር ብቻ ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በመስተንግዶ ቱሪስቶች የሚጠብቁት ዓለም አቀፍ ደረጃ አልደረስንም፡፡ ቱሪስቱ ምሳውን አንድ አገር እራቱን ሌላ አገር የሚበላበት ዘመን ነው፡፡ ይህ ማለት በአንድ ቀን የሁለት አገሮችን አገልግሎት ያነጻጽራል፡፡ በዚህ በኩል ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአጭርና የረዥም ጊዜ ትምህርት ይሰጣል፡፡ የማስጎብኘት ቢዝነስን ሳይንስ በማድረግ ክፍተት ቢኖርም አብዛኞቹ በልምድ ረዥም ጊዜ ስላስጎበኙ የጎላ አይደለም፡፡ ሌላው ለቢዝነሱ ያላቸው አመለካከት ነው፡፡ አስጎብኚ ከቱሪስቶቹ ጋር ፊት ለፊት የሚገናኝ አምባሳደር ነው፡፡ በአስጎብኚዎቹ ዘንድ የባህል አምባሳደር ነኝ ብሎ ያለመመልከትና ቢዝነሱን ብቻ የማየት ነገር አለ፡፡ በዘርፉ የገፅታ ግንባታ የኢኮኖሚ ጠቀሜታን መቅደም አለበት፡፡ በሥነ ምግባር በኩል ከታማኝነት ጀምሮ በአለባበስ ኢትዮጵያዊ ማንነት መግለጽንም ይጨምራል፡፡ በአለባበስ ክፍተት አለ፡፡ የባህል አምባሳደር የባህል ልብስ ለብሶ መቅረብ አለበት፡፡ በዚህም ከአስጎብኚዎች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ የቱሪስቶችን ደኅንነት አደጋ ላይ መጣልና ማጭበርበር ባይኖርም ከፍተኛ ሒሳብ መጠየቅ አለ፡፡ ወጥ የሆነ ክፍያ አውጥተን ለማስተካከል ሞክረናል፡፡

ሪፖርተር፡- ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎችን በማፍራት ይጠቀሳል፡፡ የተማረውን የሰው ኃይል በዘርፉ በመቅጠር እየተጠቀማችሁበት ነው?

አቶ ልዑል፡- አሁን ዘርፉን እየተቀላቀሉ ያሉት አስጎብኚዎች የቱሪዝም ተመራቂዎች ናቸው፡፡ ሌሎቹ ትምህርት ክፍሉ ከመከፈቱ በፊት በሌላ ዘርፍ የሠለጠኑ ናቸው፡፡ አብዛኞቹን ባለሙያዎች ስፖንሰር አድርገን ሁለተኛ ዲግሪ አስተምረናቸዋል፡፡ ተከታታይ የአጭር ጊዜ ሥልጠናም ይሰጣል፡፡ ከቋንቋ ዕውቀት ጋር የተያያዘ ክፍተት አለ፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምረው መሠረታዊ የቱሪዝም ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ለአስጎብኚዎች የሚያስፈልጉ ከእንግሊዝኛ ወጪ ያሉ ቋንቋዎች ላይ ተጨማሪ ዕውቀት ለመስጠት ሥርዓተ ትምህርቱን ማስተካከል አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በመዳረሻ ልማት በኩል የመሠረተ ልማት በስፋት አለመዘርጋትና የመስተንግዶ ጥራት አለመኖር በቱሪዝሙ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ አይደለም?

አቶ ልዑል፡- አዲስ ቢዝነስ በመሆኑ ገንዘብ ያለውና ዕውቀት ያለው ተቀናጅተው እየሠሩ አይደለም፡፡ ከአገልግሎት ጋር የተያያዘ ችግር በኛ ክልል ብቻ ሳይሆን የአጠቃላይ ኢትዮጵያ ችግር ነው፡፡ ሽንት ቤትና ማዕድ ቤት በግርግዳ መለየቱ ለንፅሕና ግድ እንደሌለን ያሳያል፡፡ መስተንግዶና ንፅሕና ላይ መሠራት አለበት፡፡ የመዳረሻ ልማት ኢንቨስትመንት ያስፈልገዋል፡፡ በባህልና ቱሪዝም ቢሮ አቅም የሚሠራ አይደለም፡፡ መንገድ፣ ውኃና መብራት መዘርጋት ምን ያህል እንደሚያስቸግር ይታወቃል፡፡ አንድ መዳረሻ፣ መዳረሻ እንዲሆን ከተፈለገ ግን የግድ መሠረተ ልማቶች መሟላት አለባቸው፡፡ ሥራችንን እንድንሠራ በቅድሚያ መሠረተ ልማቶቹ መሟላት አለባቸው፡፡ በዚህ ክልል በመዳረሻ ልማት ያለው ችግር አብዛኞቹ የቱሪስት መስህቦች ተራራ አካባቢ መገኘታቸው ነው፡፡ አስቸጋሪ መልክአ ምድር ላይ በመሆናቸው አስቸጋሪ ግንባታ ይጠይቃሉ፡፡ ጊዜና ገንዘብ ይወስዳልም፡፡

ሪፖርተር፡- የቱሪስቶች ፍሰት እንዲጨምር ከመዳረሻ ልማት ባሻገር ለቅርሶች እንክብካቤ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቅርሶችን ከመንከባከብ ጋር ከተያያዘዙ ችግሮች ባሻገር ጉዳት ሲደርስባቸው የሚደረግላቸው ጥገናም ተግዳሮቶች ይገጥሙታል፡፡

አቶ ልዑል፡- ስለ ቅርስ ስናወራ አንደኛው ያለውን ቅርስ ለማወቅና እንዳይዘረፍም የሚደረገው የቅርስ ምዝገባ ነው፡፡ ሁለተኛው የቅርስ እንክብካቤ ቅርስ ተበላሽቶም ተሰንጥቆም ከሆነ ጉዳቱ እንዳይቀጥል የሚሠራ ነው፡፡ በፀሐይና ዝናብ ከተበላሸ ላሊበላ እንደተደረገው በመከላከያ ጉዳቱ ባለበት እንዲቆም ማድረግ ነው፡፡ ሦስተኛው ጉዳቱን ጠግኖ ወደነበረበት መመለስ ነው፡፡ ከምዝገባ አኳያ እንደ አገርም የተሻለ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ከእንክብካቤ አኳያም ጥሩ ብንሠራም በጥገና መሠረታዊ ክፍተት አለ፡፡ አብዛኞቹ ቅርሶች የተሠሩት በአገር በቀል ዕውቀት ሲሆን፣ ይኼ ስለጠፋ መመለስ ይጠበቅብናል፡፡ በተቻለው አቅም እየሠራን ቢሆንም የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ርብርብ እንፈልጋለን፡፡ ቴክኖሎጂውን ተረድቶ የሚሠራ የሰው ኃይል ያስፈልገናል፡፡ በክልሉ ያሉ ቅርሶች የተሠሩት በኖራ ነው፡፡ የኖራ ቴክኖሎጂ አገር በቀል ዕውቀት ሲሆን፣ አሁን እየጠፋ ነው፡፡ በክልሉ ያሉ በርካታ ሥዕሎች የተሠሩበት ቀለምም አገር በቀል ነው፡፡ ዘመናዊ ቀለም አሲድ ስላለው መጠገን አልተቻለም፡፡ ይህንን ተረድቶ የሚሠራ ሰው ስለሌለ ገበያው ክፍት ነው፡፡ የቅርስ ጥገና ጨረታ ስናወጣ ትንሽ ዕውቀት ያለው ሰው ያሸንፋል፡፡ የጎንደር ሥልጣኔ ለ250 ዓመት በኢትዮጵያ መናገሻነት የተገነባ ግዙፍ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ይህን ግዙፍ ሀብት ሙሉ በሙሉ እንጠግን ከተባለ ብዙ ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል፡፡ ይኼ በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ርብርብም የሚፈታ ነው፡፡ ገንዘቡ እንዴት እንደሚሰበሰብና እንደሚተዳደር ሥርዓት አዘጋጅተን ጽሕፈት ቤት እያቋቋምን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ቱሪዝም ሲነሳ የሚዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች (ታንጀብል ካልቸራል ሔሪቴጅስ) የሚሰጣቸው ትኩረት ያህል ለማይዳሰሱ (ኢንታንጀብል) ሲሰጥ አይስተዋልም፡፡ ባህላዊ ቅርሶችን ለቱሪዝም በማዋል ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ልዑል፡- ይኼ አገራዊ ችግር ነው፡፡ ቱሪዝሙ የተመሠረተው በውጪ ቱሪስቶች ነው፡፡ በአገር ውስጥ ቱሪዝም ላይ ተመሥርቶ የውጪው እንደ ማሟያ መታየት አለበት፡፡ ለውጪው ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚቻለው አገሩን ተንቀሳቅሶ የተረዳ ዜጋ ስንፈጥር ነው፡፡ የማስታወቂያ ሥራው በአብዛኛው የሚታወቁና ግዙፍነት ያላቸው ቅርሶችን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ይህን የምንሠራው ቀላሉ ሥራ ስለሆነ ነው፡፡ በማስታወቂያ ሥራ የመጀመሪያው አዲስ ነገር ወደ ሰው ማስተዋወቅ ነው፡፡ ሁለተኛው የሚያውቁትን የማስታወስ ሥራ ነው፡፡ የሚያውቁትን ማስታወስ ብዙ ገንዘብና የሰው ኃይል ስለማይጠይቅ እየተሠራበት ነው፡፡ በእርግጥ ማስታወቂያ ከመሥራት በፊት መሠረተ ልማት መዘርጋት አለበት፡፡ ካስተዋወቅን ቱሪስቱ ይመጣል፡፡ ስለዚህ ማስታወቂያ ከመሥራታችን በፊት የመሠረተ ልማትና የመስተንግዶ ሥራዎቹ መጠናቀቅ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የአካባቢው ኅብረተሰብ አኗኗር ማራኪ ነው፡፡ ይህ ወደ ካፒታልነት ሳይቀይር እንግዳ መጥራት ግን አንችልም፡፡ እንግዳ መጥቶ ተከፍቶ ከሚሄድ አለመጥራት ይሻላል፡፡ ከዚያ በኋላ የሚያምነን አይኖርም፡፡ በክልሉ ‹‹አክቲቪቲ ቤዝድ ቱሪዝም›› [አሳታፊ ቱሪዝም] ብለን የጀመርነው ፕሮጀክት አለ፡፡ ቱሪስቱ መጥቶ ከማየት በዘለለ ፈጭቶና አቡክቶ የሚጋግርበትና ሌላም የኛ ሕዝብ የሚሠራውን የሚሠራበት አንድ መንደር ለመሥራት እያሰብን ነው፡፡ ይህንን ባለሀብትም ሊሠራውም ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ ትውፊታዊ ተውኔቶችን፣ ፊልሞችንና ሌሎችም የኪነ ጥበብ ሥራዎችን መጠቀም ይቻላል፡፡ እናንተ ኪነ ጥበቡን ምን ያህል ተጠቅማችሁበታል?

አቶ ልዑል፡- የባህል ኢንዱስትሪው ፊልምን ጨምሮ ምንም ያልተሠራበት ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ በኩል ከቢሮ ጀምሮ እስከ ወረዳ ያለውን በአዲስ መልኩ እያዋቀርን ነው፡፡ የቴአትር፣ የፊልምና የሥነ ጽሑፍ ሥራው ባህላችንን እንዲያስተዋውቅ በማድረግ በኩል ክፍተት አለ፡፡ በመጀመሪያ አደረጃጀታችንን አስተካክለን በቀጣይ የምንለውጠው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሉ ይገነባል ካሉን የባህል ማዕከል ባሻገር አሁን ያሉት የባህል ማዕከሎች በቂ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው?

አቶ ልዑል፡- በትልልቅ ከተሞች ላይ የባህል ማዕከላት ለመገንባት መሠረተ ድንጋይ ተጥሏል፡፡ አንዳንዶቹ ተጀምረዋል፡፡ በክልሉ ወደ አንድ ሚሊዮን ብር አካባቢ የሚያወጣ ሙዚየም ለመሥራት ድንጋይ ጥለናል፡፡ ባህል እንዲያድግ ከተፈለገ የባህል ማዕከል ያስፈልጋል፡፡ ኢንቨስትመንቱ ግን ከባድ ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከደርግ ጀምሮ የነበሩ የስብሰባ አዳራሾችን ወደ ባህል ማዕከል በማዞር የባህል ቡድኖች እንዲጠቀሙባቸው እያደረግን ነው፡፡ በክልሉ ያሉት ከ80 በላይ የባህል ቡድኖች የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሉ ያሉትን ፓርኮች ጨምሮ በአገሪቱ ያሉ ፓርኮች ከሕገወጥ የሰዎች ሠፈራ፣ ከእንስሳትና ደኖች ጥበቃ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች ተጋርጠውባቸዋል፡፡ ከነዚህ ፓርኮች የስሜን ተራራ ይጠቀሳል፡፡ ችግሮቹን ለመቅረፍ ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ልዑል፡- በክልሉ የፓርኮችና የአካባቢ ጥበቃ መሥሪያ ቤት አለ፡፡ ፓርኮች ከኛ ጋር የሚገናኙት ከፓርኮች የሚገኘውን ጥቅም ወደ ቱሪዝም በመቀየር በኩል ነው፡፡ የእንስሳቱን ህልውናና የፓርኩን ድንበር መጠበቅ የአካባቢ ጥበቃን ይመለከተዋል፡፡ ይህ አሠራር አንዳንዴ አለመናበብ ይፈጥራል፡፡ ሌላው ችግር በፓርኮችና በአካባቢው ኅብረተሰብ መካከል ያለው ግንኙነት ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በፊት ከፓርኩ ሲያገኝ የነበረውን ጥቅም በመምራት በኩል ክፍተት አለ፡፡ ስለ ፓርኮች አስፈላጊነት በሚገባ ካለመሠራቱ ጋርም የተያያዘ ነው፡፡ ሆኖም የተሻለ ህልውና ያላቸው ፓርኮች የሚገኙት በክልሉ ነው፡፡ ስሜን  ተራራ ከነበረበት የምዝገባ የመሰረዝ አደጋ (ኢንዴንጀርድ ሊስት) እየወጣ ነው፡፡ አብዛኞቹን መስፈርቶች አሟልቷል፡፡ በቅርቡ የሚመዝን ኮሚቴ ይመጣል፡፡ የሠፈራ፣ የመልሶ ማልማትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በአገው ምድር፣ ወሎና ሰሜን ሸዋ ላይ አዳዲስ ፓርኮች ወጥተዋል፡፡ ችግሩ የፓርኮቹ መኖር ሳይሆን ለቱሪስት መስህብ ማድረግ አለመቻሉ ነው፡፡ ቱሪስቶቹ በፓርኮቹ በሚያደርጉ እንቅስቃሴ ከመሠረተ ልማት አለመዘርጋት ጋር የተያያዘ ችግር አለ፡፡ ፓርኮቹ ከተከለሉ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበት ጥያቄም ይነሳል፡፡ ተጠቃሚነቱ በዘገየ ቁጥር በፓርኩና በሰዎቹ መካከል አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ ችግሩን ለመፍታት መዋቅሩን ማስተካከል እንዳለብን እየተነጋገርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ የነበረው አለመረጋጋት በቱሪዝም ዘርፍ ያሳደረውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የምታደርጉት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ልዑል፡- የከተሞች ፎረም በጎንደር ከተማ መካሄዱ በጊዜያዊነትም ቢሆን ገበያው ላይ መሟሟቅ ይፈጥራል፡፡ ትልቁና ዘላቂው ግን የፈጠረው የገጽታ ግንባታ ነው፡፡ የአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከተሞች ነዋሪዎች ወደ ጎንደር ሲመጡ ስለ ጎንደር ተመሳሳይ ዕይታ ይኖራቸዋል፡፡ ጎንደር በአገር ደረጃም አለ የሚባለው የቱሪስት መዳረሻ ነው፡፡ እንደ አገር የምንኮራባቸው ቅርሶችና የተሻለ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ያለበት አካባቢ ነው፡፡ የገጽታ ግንባታው የውጪ ቱሪስቶች እምነት እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡ እዚህ አካባቢ ያሉ ቅርሶች የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ቅርሶችም ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ የዓለም ሕዝብ ቅርሶች ናቸው፡፡ ሰዎች ወደዚህ ሲመጡ የሚያዩት የራሳቸውን ቅርስ ነው ማለት ነው፡፡ በቅርቡ የዓለም ቱሪዝም ዋና ፀሐፊ መጥተው ጎብኝተውን ነበር፡፡ የሳቸው መምጣት የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከዛ በፊት ሥልጠናዎችና ኮንፈረንሶችም ተካሄደዋል፡፡ ይህ ለኛ የተለየ ትርጉም አለው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን

ቢሻን ጋሪ ፒውሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ ወደ ውኃ የማከም ቴክኖሎጂ ሥራ የገባው በየጊዜው በኢትዮጵያ የተከሰቱ ውኃ ወለድ በሽታዎች መደጋገምን ዓይቶና ጥናት አድርጎ ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. ቢሻን...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...

ሕይወትን ለመቀየር ያለሙ የቁጠባና ብድር ማኅበራት

ወ/ሮ ቅድስት ሽመልስ በግሎባል ስተዲስ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እንዲሁም በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ሠርተዋል፡፡ በኮርፖሬት ፋይናንስ ካናዳ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ...