Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምግልጽነት የተላበሰው የማክሮንና የፑቲን ውይይት

ግልጽነት የተላበሰው የማክሮንና የፑቲን ውይይት

ቀን:

በብራሰልስ በተደረገው የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እና በጣሊያን ሲሲሊ በተካሄደው የቡድን ሰባት አገሮች ስብሰባ ላይ የተሳተፉት የፈረንሣይ ፕሬዚዳንትና የጀርመን መራሒተ መንግሥት፣ ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ያደረጉት ቆይታ ብዙም አልተመቻቸውም ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፈረንሣይ የደረሱት፡፡

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፈረንሣዩ አቻቸው ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ከፓሪስ አቅራቢያ በሚገኘው ቬርሳይ ቤተ መንግሥት ሲገናኙ፣ የጋዜጠኞች ዓይን ያረፈው ሰላምታ አሰጣጣቸው ላይ ነበር፡፡

የ39 ዓመቱ ማክሮን በብራሰልስ በነበረው የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጉባዔ ላይ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በተጨባበጡበት  ወቅት፣ ‹‹የትራምፕ አጨባበጥ ጠንካራና ረዘም ያለ ጊዜ ይወስዳል፤›› ማለታቸው የመገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ፣ የማክሮንና የፑቲን እጅ አጨባበጥ እንዴት ይሆን? የሚለውም በጉጉት የተጠበቀ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የ‹‹ፍራንኮ ሩሲያ›› አጨባበጥ አንዱ በአንዱ ላይ ያለውን የበላይነት የሚያሳይ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት የነበረ ቢሆንም፣ ከግምትነት አላለፈም፡፡ ማክሮንና ፑቲን ለመጀመርያ ጊዜ ፊት ለፊት ሲገናኙ በመጨባበጥ ያሳለፏቸው ሰከንዶች ሰባት ሲሆኑ፣ የአጨባበጥ ዓይነቱም ትህትና የተሞላበት ነበር ተብሏል፡፡ ማክሮን ከፑቲን ጋር የነበራቸውን ውይይት ሲጨርሱም፣ ‹‹ነፃ የሐሳብ ልውውጥ›› እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡

ቅንጡ በሆነው ቬርሳይ ቤተ መንግሥት የተወያዩት ማክሮንና ፑቲን፣ በውይይታቸው ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ያልተግባቡባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ቢገልጹም፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ግን አብረው እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡

ቢቢሲ ፕሬዚዳንት ማክሮንን ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ ፈረንሣይ በሶሪያ ለዓመታት የዘለቀውን የእርስ በርስ ግጭት ለማስቆምና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከሩሲያ ጋር ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት ያሳወቀች ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን በበኩላቸው አገራቸው ከፈረንሣይ ጋር ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት እንዲኖራት እንደምትፈልግ ገልጸዋል፡፡ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ባላት ተቃርኖና ክራይሚያን ከሩሲያ ጋር በመቀላቀሏ ምክንያት፣ በአሜሪካ ፊታውራሪነት ማዕቀብ የተጣለባት ቢሆንም ፑቲን ይኼን ወደ ጎን እንዲተውና ከፈረንሣይ ጋር ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲኖራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ የውይይታቸው ዋና ጉዳይ ግን የሶሪያ ግጭትን ማስቆምና ሽብርተኝነትን መዋጋት ነበር፡፡

ማክሮንና ፑቲን ስለሶሪያ ምን አሉ?

በሶሪያ የእርስ በርስ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ኃያላኑ አገሮች በሶሪያ ላይ ያላቸው አመለካከት ለሁለት ተከፍሏል፡፡ አሜሪካና አውሮፓውያኑ የሶሪያው ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ከሥልጣን መውረድ አለባቸው ሲሉ፣ ሩሲያ ይኼንን አትደግፍም፡፡ ቻይና አብዛኛውን ጊዜ የመወሰን ዕድሉ ለሕዝቡ ይሰጥ የሚለውን አቋሟን ስታጠነጥን ኢራን የበሽር አል አሳድ ደጋፊ ነች፡፡ የአሜሪካ ሐሳብ አቀንቃኞች በአንድ በኩል፣ ሩሲያ ደግሞ በሌላ ጽንፍ መሠለፋቸው ለሶሪያ ከጦርነት ውጪ የፈየደው የለም፡፡

ሩሲያ በሽር አል አሳድን በመደገፍ መሣሪያ ከማስታጠቅ አንስቶ ጦር ሰብቃ እስከ መዋጋት ስትገባ፣ አሜሪካና አጋሮቿ ደግሞ አል አሳድንና ሽብርተኞችን ይዋጋሉ ለሚሏቸው ተቃዋሚዎች ጦር ያስታጥቃሉ፡፡ በምድረ ሶሪያም የአውሮፕላን ድብደባ ያደርጋሉ፡፡ ፈረንሣይ ደግሞ ከእነ አሜሪካ ጎራ በመሆን የበሸር አል አሳድ መንግሥትን በጦር መሣሪያ የሚደግፉትን ሩሲያንና ኢራንን ትቃወማለች፡፡

ፑቲንና ማክሮን ለሁለት ሰዓታት የዘለቀውን ውይይት ሲያሳርጉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ግን፣ አገሮቹ በሶሪያ ያለውን ብጥብጥ ለማረጋጋት ተቀራርበው ሊሠሩባቸው የሚችሉ ዕድሎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ፈረንሣይ በሶሪያ የሚገኘውን አይኤስ ለመዋጋት ከሩሲያ ጋር ጠንካራ ትብብር መፍጠር እንደምትፈልግ የገለጹት ማክሮን፣ አያይዘውም ሶሪያን ለማዳን ዴሞክራሲያዊ ሽግግርን እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም በኬሚካል ጦር መሣሪያ አጠቃቀም ላይ እንደማይደራደሩም ለማመልከት ‹‹የኬሚካል ጦር መሣሪያን አስመልክቶ ቀይ መስመር ከታለፈ ፈረንሣይ አፋጣኝ ምላሽ ትሰጣለች፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ 

የአንድን አገር መንግሥት በኃይል በማስወገድ አገርን ማነፅ ይቻላል የሚል እምነት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ ያንፀባረቁት ፑቲን፣ ሽብርን ለመዋጋት ተቀናጅቶ መሥራቱ  በየፊናው ከሚደረገው ጥረት በተሻለ አዎንታዊ ለውጥ ያመጣል ብለዋል፡፡

መሪዎቹ ሽብርን መዋጋት ላይ ትኩረት ቢሰጡም፣ ሚስተር ማክሮን ለፈረንሣይ ፕሬዚዳንትነት ሲታጩና የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ሩሲያ ልታደናቅፍ እንደነበር ሳይነሳ አልታለፈም፡፡ የማክሮን ተቀናቃኝ የነበሩት ማሪን ለፔን ምርጫው ከመከናወኑ ወር አስቀድሞ በሩሲያ ጋባዥነት ሞስኮ ተገኝተው ከፑቲን ጋር መምከራቸው፣ ሩሲያ የለፔን ደጋፊ መሆኗን ያመለከተ ነበር፡፡

ሩሲያ በፈረንሣይ የፕሬዚዳንት ምርጫ ሒደት ጣልቃ ገብታ ነበር?

ሚስተር ፑቲን የፈረንሣይ ዕጩ ፕሬዚዳንት የነበሩት ብሔረተኛዋና ወግ አጥባቂዋ ማሪን ለፔን እንዲያሸንፉ ይፈልጉ ነበር፡፡ ለፔንም በፕሬዚዳንት ፑቲን ጋባዥነት፣ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ከመከናወኑ ወር አስቀድሞ ሞስኮ ተገኝተው ከፑቲን ጋር ተወያይተዋል፡፡ ይህም ሩሲያ በምርጫው ጣልቃ ገብታለች አስብሏል፡፡ ይህንን አስመልክቶ በቬርሳይ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ምላሽ የሰጡት ፑቲን፣ ‹‹ምርጫው ላይ በተወሰነ ደረጃ ተፅዕኖ ለመፍጠር አልሞከርንም አንልም፡፡ ተፅዕኖ ለመፍጠር ፍፁም አይሞከርም ማለትም አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

የፈረንሣዩ ማክሮን በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት፣ ‹‹ሩሲያ የመረጃ ጦርነት እያካሄደች ነው፤›› ማለታቸውን በማስታወስ፣ ሩሲያ በአገሮች ምርጫ ላይ ጣልቃ ትገባለች ተብለው በጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ፑቲን፣ ‹‹የሚያወያይ ጉዳይ አይደለም፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡ ማክሮን ከፑቲን ጋር ከመወያየታቸው አስቀድመው ግን በሩሲያ መንግሥት የሚደገፉትን የሩሲያ መገናኛ ብዙኃንን የተፅዕኖና የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡

ሩሲያ ለፔን እንዲያሸንፉ የሳይበር ጠለፋ ለማድረግ ሞክራ ነበር የሚለውና ማክሮን በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት እንዳይሳተፉ ያገዷቸው ሁለት የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ለመሪዎቹ ውይይት እንደ ማዳመቂያ የተቆጠሩ ነበሩ፡፡

በዩክሬን ጉዳይ ምን መከሩ?

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያላትን ጣልቃ ገብነት ከማይደግፉ አገሮች ፈረንሣይ አንዷ ናት፡፡ ክራይሚያ እ.ኤ.አ. በ2014 ከሩሲያ ጋር መቀላቀሏን ተከትሎም በሩሲያ ላይ የተጣለውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ትደግፋለች፡፡ ሆኖም ፑቲን በሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ በመጠየቃቸው ምክንያት ሁለቱም መሪዎች ጉዳዩን መልሶ የሚያይ የጋራ ቡድን ለማቋቋምና ከጀርመን ጋር ለመወያየት መስማማታቸው ተነግሯል፡፡

መሪዎቹ በግብረ ሰዶማውያን መብቶች ላይ ተወያይተዋል ቢባልም፣ በሩሲያ የተወገዘ ነው፡፡ በፈረንሣይ መብት የሆነው ግብረ ሰዶማዊነት፣ በቺቺኒያ ሰዎችን ለምን ያስቀጣል በማለት ማክሮን ፑቲንን የጠየቁ ሲሆን፣ ፑቲንም፣ ‹‹ይህ የየአካባቢው አስተዳደሮች አሠራር ነው፤›› ከማለት ውጪ ስለግብረ ሰዶማዊነት ያነሱት ጉዳይ አልነበረም፡፡

የፈረንሣይና ሩሲያ ግንኙነት በተለይም በቀድሞው የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦላንዴ ጊዜ ውጥረት የነገሠበት ነበር፡፡ ሆኖም ለተመራጩ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ማክሮን ከፑቲን ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በሲሲሊ ከተካሄደው የቡድን ሰባት አገሮች ጉባዔና በብራሰልስ ከተካሄደው የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ስብሰባ ቀጥሎ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የፈተኑበት ነው ተብሏል፡፡ የማክሮን ፑቲንን መጋበዝም ሩሲያ ከምዕራባውያኑ ጋር የገባችበትን ውጥረት ለማርገብ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡  

ይህ በዚህ እንዳለ ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓ ጎብኝታቸው ወቅት ከአውሮፓ መሪዎች ጋር በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ቢወያዩም፣ አሜሪካ ከአሁን በኋላ ለአውሮፓ ደንታ እንደሌላት የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል ተናግረዋል፡፡ ‹‹አውሮፓ በአሜሪካ ላይ ከመተማመን ይልቅ በራሷ ላይ ብትተማመን ይሻላታል፤›› ብለዋል፡ ዶናልድ ትራምፕ ጀርመንን እንደ መጥፎ ነጋዴ አድርገው ምሳሌ ማቅረባቸውና ከአሜሪካ በተሻለ ተጠቃሚ ናት ማለታቸውም መርከልን አበሳጭቷል፡፡ ኢማኑኤል ማክሮንም የዶናልድ ትራምፕ ነገር የተዋጣላቸው አይመስሉም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...