Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየአፍሪካው ፌስቲቫል

የአፍሪካው ፌስቲቫል

ቀን:

‹‹የትኛውም አገር ስንሄድ ከደቡብ አፍሪካ ነው የመጣነው ከማለታችን በፊት ከአፍሪካ ነው የመጣነው እንላለን፡፡ ደቡብ አፍሪካዊ፣ ናይጄሪያዊና ኢትዮጵያዊ ከሚለው ማንነት በፊት አፍሪካዊነታችንን ማስቀደም አለብን፤›› በማለት የተናገረው የደቡብ አፍሪካው ማፊኪዞሎ ባንድ ድምፃዊ ነው፡፡

የባንዱ ድምፃዊ ቲዎ ከሌላዋ የባንዱ ድምፃዊት ንህላንህላ ጋር ተጣምሮ ሙዚቃዎቻቸውን ያስደመጡት ግንቦት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ነበር፡፡ ድምፃውያኑ ለዘ አፍሪካን ሚዩዚክ ኤንድ ካልቸራል ኤክስቼንጅ ፌስቲቫል (አምሴፍ) ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ አቀንቃኞች መሀል ሲሆኑ፣ ግንቦት 19 እና ግንቦት 20 የተካሄደው ፌስቲቫል የመደምደሚያ ትርኢት አቅርበዋል፡፡

የአፍሪካ ቀን (ግንቦት 17) በተከበረበት ሳምንት መጨረሻ ቀናት የተካሄደው ፌስቲቫሉ፣ በአህጉሪቷ ጥበብና ባህልን ያማከለ ውህደት ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡ ለአፍሪካውያን አንድነት በፖለቲካው፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚው ዘርፍ ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን በሙዚቃ፣ በሥነ ጥበብ፣ በፋሽንና ባህላዊ እሴቶችን መሠረት ባደረገ መልኩም መከናወን እንደሚችል ማሳየትም የፌስቲቫሉ መነሻ ነው፡፡ የማፊኪዞሎ ባንድ አቀንቃኞች መድረክ ላይ ያወሱ የነበረውም ይህንን የአህጉሪቱን አንድነት ነው፡፡

ፌስቲቫሉ ላይ ከማፊኪዞሎ በተጨማሪ ቱኩ ከዚምባብዌ፣ ፓቶራንኪንግ ከናይጄሪያ፣ ጆሴ ካሜሊዮኔ ከኡጋንዳ፣ ዲጄ ክሎክ ከደበብ አፍሪካ፣ ዲጄ አድሪያን ከኬንያ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጆኒ ራጋ፣ ሔለን በርሔና ቤሪ የፌስቲቫሉ ተካፋይ ሙዚቀኞች ነበሩ፡፡ ፌስቲቫሉ በአህጉሪቱ በጥበብና ባህል ዘርፍ የተሰማሩ ሙያተኞችን እርስ በርስ የማስተሳሰር እንዲሁም ከኢትዮጵያና ከተቀሩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ታዳሚዎችን የትስስሩ አካል የማድረግ ግቡን ለመምታት ከጋበዛቸው መካከል የተለያዩ የአህጉሪቱ ኤምባሲዎች ተወካዮች ይገኙበታል፡፡

የጋናና የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲዎች የየአገራቸውን ባህል የሚገልጹ አልባሳት፣ ምግብ፣ ጌጣ ጌጥና ጽሑፎች ካቀረቡት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የየአገራቸውን ታዋቂ ሰዎችና ዕውቅ የቱሪስት መዳረሻዎች የሚገልጹ ጽሑፎች ለታዳሚው ከመስጠት በተጨማሪ ባህላዊ ምግባቸውን በማቅመስና ባህላዊ አልባሳት በመሸጥም አገራቸውን ያስተዋውቁ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ጠጅ፣ ዶሮ ወጥና ሌሎችም ባህላዊ ምግቦችን ያቀረቡም ነበሩ፡፡ የፋሽን ትርኢትና ሰርከስ ያሳዩትም ይጠቀሳሉ፡፡ በፌስቲቫሉ አንድ ጥግ ሙዚቃ ሲደመጥ በሌላው ጥግ ታዳጊዎችን የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ዳንሶችን የሚያለማምዱ አስተውለናል፡፡

ፌስቲቫሉ ከአፍሪካ ቀን ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ የተደረገው ጥረት የተካሄደበትን ዕለት ከቀኑ ጋር በመቀራረብ ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካን አንድነት የሚያቀነቅኑ ክንውኖች ለማካተት በመሞከር ጭምርም ነው፡፡ ሙዚቀኞችን ከተለያዩ የአህጉሪቱ አገሮች ጋብዞ መድረክ ላይ የሚያስተላልፉት መልዕክት የፌስቲቫሉን ዓላማ እንዲደግፍ ማድረጉ ይጠቀሳል፡፡ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች በርካታ ታዋቂ የጥበብና የባህል ፌስቲቫሎች ይካሄዳሉ፡፡ የማላዊውን ሌክ ኦፍ ስታርስ ፌስቲቫልና የማሊው ፌስቲቫል ሱር ለኒጀር መጥቀስ ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያን ያህል ዕውቅና ያላቸውና ለዓመታት ሳይቆራረጡ የዘለቁ ፌስቲቫሎች አሉ ለማለት አይቻልም፡፡ ትኩረታቸውን በአፍሪካ አንድነት ላይ ያደረጉ ፌስቲቫሎች ደግሞ ከናካቴው ሲካሄዱ አይስተዋልም፡፡ በኤስአይሲኤስ ሚዲያና ዲዋይኤምዲ ጥምረት የተዘጋጀው ፌስቲቫል በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ቢሆንም የታዳሚዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደሚደመጠው የፌስቲቫል ባህልን በመፍጠር በኩል አገሪቱ ብዙ ይቀራታል፡፡ ይህንን ባህል መፍጠር የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊነሳ ይችላል፡፡

በአገሪቱ ያሉ ባህላዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችም ከቤት ውጭ  በኅብረት የሚካሄዱ ክንውኖችን ያካትታሉ፡፡ በርካታ የጎዳና ክንውኖች ባሉበት አገር ከዚህ አካሄድ ጋር ተመሳሳይ የሆነውን ፌስቲቫል መልመድ ለምን አልተቻለም? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ፌስቲቫሎች ሲጀመሩ እንጂ ከዓመት ዓመት ሲዘልቁ አይታይም፡፡ የሙዚቃ፣ የቴአትርና ሌሎችም ፌስቲቫሎች ሲዘጋጁ የዘርፉ ባለሙያዎች ሳይቀሩ የመሳተፍ ፍላጎት አያሳዩም፡፡ አምሴፍ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ፌስቲቫሉን ተዘዋውሮ የተመለከተ ሰው የአገሪቱ ሙዚቀኞች መሰል መርሐ ግብሮችን ከመታደም የሚያግዳቸው ምንድነው? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡

በአብዛኛው ማኅበረሰብ ዘንድ በብዛት የሚጠቀሰው የፌስቲቫሎች መግቢያ ዋጋ መወደድ ነው፡፡ ይህ ከአዘጋጆቹ ጋር በመነጋገር ሊፈታ የሚችል ተግዳሮት ሲሆን፣ ምን ያህል የፌስቲቫል አዘጋጅ ፌስቲቫል ከማሰናዳት ባለፈ የተካፋዩን ማኅበረሰብ ቁጥር ማብዛት ላይ ያተኩራል የሚለው ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ፌስቲቫሉ በተካሄደበት ቀናት ዝናብ በመጣሉ የታሰበውን ያህል ሰዎች አለመታደማቸውን አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡ ፌስቲቫል ሲዘጋጅ በሚሠራው ማስታወቂያና ታዳሚዎች በፌስቲቫሉ ከተገኙ በኋላ ፌስቲቫልን እንዲያዘወትሩ የሚያበረታታ ሥራ የመሥራት ኃላፊነት የአዘጋጆቹ መሆኑ አይካድምና ፌስቲቫሎች የጥቂቶች ሳይሆን የብዙኃኑ የሚሆኑበት መንገድ ሊታሰብበት ግድ ይላል፡፡

ፌስቲቫሎች ሲዘጋጁ በአንዳች ጉዳይ እንዲያጠነጥኑ ከማድረግ አንፃር አምሴፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ የተለያዩ የአህጉሪቷ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ተቋሞች ለፌስቲቫሉ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በእርግጥ የአፍሪካ ዋና መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ፓን አፍሪካን ፌስቲቫል ለማዘጋጀት ዘግይታለች፡፡ የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ዓርማ ተደርጋ የምትታየው ኢትዮጵያ የአህጉሪቷን ኅብረት የሚሰብክ ጥበባዊና ባህላዊ ፌስቲቫል ማዘጋጀት የሚገባት ከዚህም ቀድሞ ነበር፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር አገሪቱ ወደ ኋላ ብትቀርም፣ ፌስቲቫል ተዘጋጅቶም የታደሙት ጥቂቶች ናቸው፡፡

ከተሳታፊዎቹ አንዷ ጆን ክራል የጋና አልባሳትን በፌስቲቫሉ እያስተዋወቀች ነበር ያገኘናት፡፡ ‹‹አፍሪካውያን ያላቸው ባህል ተመሳሳይ እንደመሆኑ በመሰል ፌስቲቫሎች ወደ አንድ መድረክ መምጣት አለባቸው፤›› ትላለች፡፡ በየአገሩ ያለው ባህል የሚታይበት መርሐ ግብር ሲዘጋጅ በአፍሪካውያን መካከል ያለውን ተመሳሳይነት መገንዘብ እንደሚቻል ታምናለች፡፡ ሆኖም ሐሳቡን ከማስፋፋት አንፃር ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የሚሳተፉ ሰዎች መበራከት እንዳለባቸው ትገልጻለች፡፡

የጋና፣ የኢትዮጵያ፣ የኮንጎና የደቡብ አፍሪካ ተሳታፊዎች ተከታትለው በተጣሉ ድንኳኖች ውስጥ ምርቶቻቸውን ያሳዩ ነበር፡፡ ከታዳሚዎች ጋር ከመወያየታቸው በተጨማሪ እርስ በርስም ስለየአገራቸው ሲያወሩም አስተውለናል፡፡ ቅዳሜ ከሰዓት በፌስቲቫሉ የተገኙ ታዳጊዎች ጥቂትም ቢሆኑ በየድንኳኑ እየተዘዋወሩ ይጎበኙ ነበር፡፡ የሥነ ጥበብ ሥራዎች በቀረቡበት ድንኳን ሥዕል ይመለከቱ የነበሩት ይጠቀሳሉ፡፡

በፌስቲቫሉ ዶሮ ወጥ ይዛ የቀረበችው ወይንሸት ደስታ እንደምትለው፣ አገሪቱ ራሷን ማስተዋወቅና ስለተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ማወቅ የምትችለውም ፌስቲቫሎች ሲበራከቱ ነው፡፡ በአገሪቱ የሚዘጋጁ ፌስቲቫሎች ኢትዮጵያ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ከመሆናቸው ባሻገር አፍሪካዊ መዳረሻ መፍጠር አለመቻሉ የፈጠረውን ክፍተትም ትናገራለች፡፡ ‹‹አገሪቱ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንደመሆኗ ለዚህ ዓይነት መርሐ ግብር ዘግይተናል፡፡ ጥሩ ጅማሮ ቢሆንም በስፋት መቀጠል አለበት፤›› ስትልም ታስረዳለች፡፡

ድምፃዊው ራስ ጃኒና ኢየሩሳሌም ሐፍቲ ከወዳደቁ የውኃ ፕላስቲኮች ቦርሳና ሌሎችም ቁሳቁሶች ይሠራሉ፡፡ በሥራው ለጎዳና ተዳዳሪዎች መተዳደሪያ ከመፍጠር ጎን ለጎን ንፁህ አካባቢ መፍጠርን ታሳቢ እንዳደረጉ የምትናገረው እየሩሳሌም፣ በፌስቲቫሉ ጤናማ የመኖሪያና የሥራ አካባቢ መፍጠርን ለማስተዋወቅ ተገኝታለች፡፡ እሷና ድምፃዊ እንደሚሠሩት ሁሉ ከአንድ አገር ባለፈ የዓለም ጉዳይ የሆኑ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት ፌስቲቫል አስፈላጊ እንደሆነም ትገልጻለች፡፡

ሐሳቧን የምትጋራው ሶፍያ አብዱ በባይላሞር የዳንስ ትምህርት ቤት ታስተምራለች፡፡ በፌስቲቫሉ ታዳጊዎችን የአፍሪካ ዳንስ ሲያለማምዱ ከነበሩ የዳንስ መምህራን አንዷ ስትሆን፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት ላይ ያተኮሩ የጥበብና የባህል መርሐ ግብሮች በማሰናዳት ረገድ ከሌሎች አገሮች ወደ ኋላ መቅረቷን ትስማማበታለች፡፡ በተለይም ወጣቶች ከኢትዮጵያዊ ማንነት ባሻገር ስለአፍሪካዊነት ሲያወሩ እንደማታይም ትናገራለች፡፡ አህጉራዊ ማንነት መፍጠር ከተፈለገ ሰፊ ድርሻ የሚወሰደው የጥበብና ባህል ፌስቲቫል መሆኑንም ታክላለች፡፡

ከአዘጋጆቹ አንዷ ደስታ መጎ (ዶ/ር)፣ ‹‹የአፍሪካ መቀመጫ በሆነች አገር ባህል ላይ ያተኮረ ፌስቲቫል ማዘጋጀት ፓን አፍሪካኒዝምን የሚገልጽ ዋነኛ መንገድ ነው፤›› ትላለች፡፡ ፌስቲቫሉን ዓመታዊ አድርጎ በሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ማካሄድ እርስ በርስ ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክረው ታምናለች፡፡ አፍሪካውያን የሚያመሳስላቸው ነገር ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርጉ መድረኮች አናሳ መሆናቸው፣ አንዱ አገር ራሱን ከሌላው በተለየ ዓይን እንዲመለከት አድርጓል፡፡

‹‹ቅኝ ያለመገዛት ታሪክ ኢትዮጵያን ከተቀረው አህጉር ለይቷታል፡፡ ዳግም መተሳሰር የሚቻልበት መንገድ መፈጠር አለበት፤›› ትላለች፡፡ በአፍሪካውያን መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠንከር በኩል ኢትዮጵያ ኃላፊነት እንዳለባትም ታክላለች፡፡ ኢትዮጵያን ከተቀረው አፍሪካ ነጥሎ የመመልከት ነገር፣ ኢትዮጵያውያን ሌሎች የአፍሪካ አገሮችን፣ ‹‹አፍሪካ ሄጄ አላውቅም›› ወይም የሌሎች የአፍሪካ አገሮችን ዜጎች ‹‹እነዛ አፍሪካውያን›› ሲሉ ለመደመጣቸው ምክንያት እንደሆነ ሳትጠቅስ አላለፈችም፡፡ በአፍሪካ መካከል ውህደት እንዲፈጠርና እንደ ጥቁር ሕዝቦች አንድነት እንዲንፀባረቅ ጥበብና ባህል የሚጫወተው ሚና ቀላል እንዳልሆነም ታስረዳለች፡፡

ሌላው አዘጋጅ የኤስአይሲኤስ ሚዲያ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌቱ ወይሳ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በነፃነት ትግል ወቅትና የአፍሪካ ኅብረትን በመመሥረት የተጫወተችው ሚና ይታወቃል፡፡ እነዚህ አፍሪካን የማዋሃድ ዓላማን ያነገቡ ናቸው፡፡ አምሴፍን የቀረፅነው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ ስለሆነ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ፌስቲቫሉ በአዲስ አበባ መከናወኑ የፓን አፍሪካኒዝም ሐሳብን የማስረፅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው፣ በየዓመቱ በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ሲካሄድ ሐሳቡ የበለጠ እንደሚስፋፋ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

በፌስቲቫሉ የተካፈሉ ሙዚቀኞችና በባህሉ ዘርፎች የሚሠሩ ባለሙያዎች የተመረጡት ለሐሳቡ ካላቸው ቅርበት አንፃር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ፌስቲቫሉ አፍሪካ ነክ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት እንዲሆን ታዳጊዎች ስለ አህጉሪቱ ያላቸው ዕውቀት የሚመዘንበት መርሐ ግብር የፌስቲቫሉ አካል መደረጉንም ይገልጻሉ፡፡ የሰዎች ነፃ ዝውውርን መወያያ ከማድረግ አንፃር በፌስቲቫሉ ከአይኦኤም ጋር የሠሩትን ሥራ ጠቅሰውም፣ የአፍሪካን ጥበብ ከማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር አያይዞ በማንሳቱ እንደሚገፉበት ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በኢኮኖሚና በፖለቲካ ከሚደረገው የውህደት እንቅስቃሴ በተጨማሪ የባህል ትስስር እንዲኖር የድርሻችንን መወጣት አለብን፤›› ብለው፣ አፍሪካ አቀፍ መሰናዶዎችን በማበራከት ረገድ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ኃላፊነት እንዳለበት ያክላሉ፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...