Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊግብፃዊው ባለሀብት በ25 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ

ግብፃዊው ባለሀብት በ25 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ

ቀን:

የፕላስቲክ ቱቦዎችንና መገጣጠሚያ ማሽነሪዎችን ለማስመጣትና በአገር ውስጥ ለመገጣጠም ከኢትዮጵያውያን ጋር ባለድርሻ በመሆን ያቋቋሙትን ኩባንያ መጠቀሚያ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤልሲ ከፍተው ካገኙት የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ከ62.2 ሚሊዮን ብር በላይ በውጭ ባንክ መደበቃቸው የተረጋገጠባቸውን ግብፃዊ መሆናቸው  የተጠቆመው ሚስተር አይመን አብደልሞታልብ ሙሳ ኢሳ፣ በ25 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ተሰጠ፡፡

የወንጅል ድርጊቱን በመመሳጠር ፈጽመዋል በማለት ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በተመሳሳይ መዝገብ ክስ ያቀረበባቸው የደቡብ አፍሪካ ተወላጅ መሆናቸው የተጠቆመው፣ አሜሪካዊው ሚስተር ማይክል ማትሰን ደግሞ እንዲከላከሉ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ ሚስተር አይመን የጽኑ እስራት ፍርድ የተሰጠባቸው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ከአንድ ዓመት በላይ መዝገቡን ሲመረምር ከከረመ በኋላ ነው፡፡

ሁለቱም  የውጭ አገር ዜጎች የተከሰሱት፣ በከባድ የማታለል ወንጀልና በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት፣ ኢትዮጵያውያንና ግብፃዊው ሚስተር አይመን በጋራ ባቋቋሙት ስታር ፓይፕና ፊቲንግስ ኩባንያ ውስጥ፣ ሚስተር ማትሰን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው መቃጠራቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚገልጽ ፍርድ ቤቱ በፍርዱ አስታውቋል፡፡ ሚስተር አይመን ለብቻቸው ካቋቋሙት ጎልደን ትሬዲንግ ኩባንያ በተጨማሪ፣ ከሚስተር ማትሰን ጋር በጋራ ያቋቋሙትና ዱባይ የሚገኝ ዋሶ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የሚባል ኩባንያ እንዳላቸውም አክሏል፡፡

ሁለቱ ተከሳሾች ከህንድና ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያስገቡ የገለጹዋቸውን የፕላስቲክ ቱቦና መገጣጠሚያ ማሽነሪዎችን በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ለማጓጓዝ የተለያየ መጠን ያለው ዶላር ለማስጫኛ በመክፈል፣ ዕቃዎቹን እንዳስገቡም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡ ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጊዜያት ተከሳሾቹ በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ እየጫኑ ዕቃውን ሲያስገቡ፣ ለማስጫኛ ያልከፈሉትን የገንዘብ መጠን የሚገልጽ ሐሰተኛ ማኅተም በመጠቀም ድርጊቱን መፈጸማቸውንም፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቶ ለፍርድ ቤቱ ማቅረቡን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በቻይና የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ  ወኪል የሆነው ‹‹ቻይና የውቅያኖስ አጓጓዥ ኤጀንሲ ሻንጋይ›› የሚል ሐሰተኛ የጭነት ደረሰኝ በማዘጋጀት፣ ‹‹የመጫኛ መነሻ ወደብ ሻንጋይ ቻይና፣ ጭነት ማራገፊያ ጂቡቲ የባህር ወደብ፣ መድረሻ ሞጆ ደረቅ ወደብና አጓጓዥ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ›› የሚል ሐሰተኛ ሰነድ አዘጋጅተው፣ የተለያየ መጠን ያለው ዶላር እንደተከፈለ በማስመሰል፣ በድምሩ 62,278,179 ብር ሚስተር ማትስንና ሚስተር አይመን በጋራ ዱባይ ማሽሩክ ባንክ በከፈቱት ‹‹ዋሶ ቴክኖሎጂ ግሩፕ›› ተብሎ በሚጠራው ድርጅት ሒሳብ (አካውንት) ውስጥ እንዲገባ ማድረጋቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

ተከሳሾቹ የተጠቀሰውን ገንዘብ ዱባይ በሚገኘው ድርጅታቸው ሒሳብ (አካውንት) ውስጥ ያስገቡትና ዕቃውን ያስጫኑት በ19,000 ዶላር ኤልሲ ከፍተው የውጭ ምንዛሪ ከሚሰጣቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ቢሆንም፣ እነሱ ግን በሚያቀርቡት ሐሰተኛ ሰነድ 40,000 ዶላር እየተቀበሉ ልዩነቱን ለግላቸው ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ ዝርዝር አድርጎ ያቀረበውን ክስ በሰነዶችና በሰዎች ለፍርድ ቤቱ ማስረዳት መቻሉን ፍርድ ቤቱ አስታውቀዋል፡፡

በሌሉበት ጉዳያቸው የታየው ሚስተር አይመን የወንጀል ድርጊቱን ቀርበው መከላከል ባለመቻላቸው፣ በ25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በፌዴራል ማረሚያ ቤት ሆነው የክስ ሒደቱን እየተከታተሉ የሚገኙት ሚስተር ማይክል ማትስን ደግሞ ዓቃቤ ሕግ ፈጽመዋል ብሎ ያቀረበባቸውን ክስ በሰነድና በሰው ማስመስከር በመቻሉ እንዲከላከሉ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የሚስተር ማይክልን መከላከያ ምስክሮች ለመስማት ለግንቦት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...