ከደብረ ብርሃን ከተማ እስከ አንኮበር ድረስ የሚገነባውን የመንገድ ፕሮጀክት ጨረታ ካሸነፈው የኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ተነጥቆ ሁለተኛ ለወጣው የቱርክ ኩባንያ ቢሰጥም፣ የቱርክ ኩባንያ የአቅም ማሳያ ዋስትና ማቅረብ ባለመቻሉ ፕሮጀክቱ ተጓቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የቱርክ ሜንታክ ሴይቱን ኩባንያ የአቅም ማሳያውን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ካላቀረበ፣ ፕሮጀክቱን በድጋሚ እንደሚነጥቅ አስታውቋል፡፡
የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የወጣውን የደብረ ብርሃን አንኮበር 42 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ጨረታ፣ የኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን አሸንፎ ነበር፡፡ ነገር ግን ፕሮጀክቱን ፋይናንስ የሚያደርገው የዓለም ባንክ ለዚህ መንግሥታዊ ኮርፖሬሽን ብድር ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ሁለተኛ ለወጣው የቱርክ ሜንታክ ሴይቱን ጆይንት ቬንቸር ኩባንያ ሰጥቷል፡፡
የቱርክ ኩባንያ ይህንን መንገድ ለመገንባት 784 ሚሊዮን ብር በማቅረብ ሁለተኛ የወጣ ሲሆን፣ ያቀረበውን መጫረቻ አሥር በመቶ የአቅም ማሳያ ዋስትና (ፕሮፎርማንስ ቦንድ) ማቅረብ ይጠበቅበት ነበር፡፡
ኩባንያው ከዚህ ገንዘብ ውስጥ የተወሰነውን አቅርቦ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እንዲታገሰው ቢጠይቅም፣ ላለፉት ወራት ማቅረብ አለመቻሉ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የቱርክ ኩባንያ የሚጠበቅበትን ዋስትና በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ካላቀረበ ፕሮጀክቱን እንደሚነጠቅና ባለሥልጣኑም ሌሎች አማራጮችን ያያል፡፡
ይህ ፕሮጀክት የደብረ ብርሃን፣ አዋሽ አርባ ፕሮጀክት አካል ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በሦስት ምዕራፍ የተከፈለ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ከደብረ ብርሃን አንኮበር፣ ሁለተኛው ከአንኮበር ዱለቻ፣ ሦስተኛው ከዱለቻ አዋሽ አርባ ድረስ ነው፡፡
ሁለተኛውን ምዕራፍ ከአንኮበር ዱለቻ ያለውን መንገድ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን፣ ሦስተኛውን ምዕራፍ የኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ተረክበው በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡
ነገር ግን የመጀመሪያው ምዕራፍ ፕሮጀክት ጨረታ ከወጣ ሁለት ዓመት ቢቆጠርም፣ እስካሁን ወደ ግንባታ ባለመገባቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም በደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ፋብሪካዎችን እየገነቡ ያሉ ኩባንያዎች ቅሬታቸውን እያቀረቡ ነው፡፡
ይህ መንገድ በአስፋልት ደረጃ ይገነባል ተብሎ የታቀደ በመሆኑ፣ ግንባታው ለአካባቢው ማኅበረሰብ የተሻለ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረው፣ ከዚህ በተጨማሪም አንኮበር የቱሪስት መስህብ በመሆኑም ለአካባቢው ማኅበረሰብ የተሻለ ጥቅም እንዳለው የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ፡፡
ደብረ ብርሃን ከተማም የኢንዱስትሪ ማዕከል እየሆነ በመምጣቱ፣ ኩባንያዎችም በተለይ ጂቡቲ ለመጓዝ አዲስ አበባ መግባትን የሚያስቀር አቋራጭ በመሆኑ የፕሮጀክቱን ዕውን መሆን እየጠበቁ ቢሆንም፣ ፕሮጀክቱ በመጓተቱ ቅሬታቸውን እያቀረቡ መሆኑ ታውቋል፡፡
‹‹ለፋብሪካ ግንባታ ከጂቡቲ የሚመጡ ዕቃዎችን በአዲስ አበባ ማሳለፍ የግድ ይላል፡፡ ነገር ግን መንገዱ ቢጠናቀቅ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን መቀነስ የሚቻል በመሆኑ ከጊዜና ከወጪ ያድን ነበር፤›› ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ በኢንዱስትሪ ዞን ፋብሪካ እየገነቡ ካሉ ኩባንያዎች መካከል የአንዱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡፡
ይህ ፕሮጀክት ሊጓተት የቻለበትን ምክንያት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንደሚሉት፣ የዓለም ባንክ ፋይናንስ በሚያደርጋቸው ኩባንያዎች የግሉ ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆን ይፈለጋል፡፡ ኮንትራክተሩ የመንግሥት ቢሆን እንኳ ራሱን ችሎ በነፃነት የሚንቀሳቀስ ተቋም መሆን አለበት፡፡
ከዚህ አንፃር ሁለተኛ ለወጣው የቱርክ ኩባንያ ሥራው ቢሰጥም፣ ኩባንያው በወቅቱ የሚጠበቅበትን ማቅረብ ባለመቻሉ ፕሮጀክቱ እየተጓተተ መሆኑን እነዚሁ ወገኖች ያስረዳሉ፡፡