‹‹ካልኖርኩት ምን እውነት እፅፋለሁ! የሚሉ አሉ፤ በቦታው ተጠቃለው አለዚያም ሥጋቸው ሲቀር ቀልባቸውን ልከው፡፡ ከንዱራም የነዚህ ግርፍ ነች፤›› የሚል መግቢያ የያዘው የወግ፣ የመጣጥፍ፣ የማስታወሻና የልቦለድ መድበል የሆነው ‹‹ከንዱራ›› ነው፡፡ መሰንበቻውን ለኅትመት የበቃው የአያሌው ወረታ መጽሐፍ በሰባት ርዕሰ ጉዳዮች የተከፈለ ነው፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ የተወደውም ከርዕሰ ጉዳዮቹ በአንዱ ነው፡፡ ወዮላችሁ!፣ ቤዛ፣ የኛ ቀበሌ ወጎች፣ የጉዱ ጣሴ ማስታወሻ፣ ናፅነት፣ አንጎልን ውጦ፤ ሌሎቹ ማስታወሻዎችና ወጎች ናቸው፡፡
በወዮላችሁ! እንዲህ የሚል ይገኝበታል፡፡ ዘመነ ኮንዶሚኒየም ሲቃረብ የሕዝብ ብዛት ይጨምራል፤ ቤት አልባዎች ይበዛሉ፤ የጨረቃ ቤቶች ይስፋፋሉ፤ መሬትም ዕንቁነቷን ታውጃለች፡፡ አልጠግብ ባዮች እንደ አሸን ይፈላሉ፤ መንግሥትንም መከታ ያደርጉታል፤ በጉያውም ይሰገሰጋሉ፡፡ እልፍ አእላፍ ቤት የለሾችንም ይንቁአቸዋል፤ ምሬታቸውንም ይዘባበቱበታል፡፡ ይህን ጊዜ ጭንቀትና አበሳ በመንግሥት ላይ ይወድቃል፡፡ እርሱም የባሰባቸውን ‹‹ኑ ወደ እኔ!›› ይላቸዋል፡፡ ሽቅብ ያሰፍራቸው ዘንድም ይሯሯጣል፡፡ የተቀሩትንም አይዟችሁ ይላቸዋል፡፡ ምድርን ግን ትመቻቸው ዘንድ ላላቸው ይመትርላቸዋል፡፡
በ194 ገጾች የቀረበው ከንዱራ ዋጋው 70 ብር ነው፡፡