Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልቻይና የምትታወስበት የዕንቁ ገበያ

ቻይና የምትታወስበት የዕንቁ ገበያ

ቀን:

ለጥንታዊ ሥልጣኔያቸው ከፍተኛ እውቅና ከሚሰጡ ሕዝቦች መካከል ቻይናውያን ይጠቀሳሉ፡፡ አለባበስ፣ አመጋገብና ሌሎችም የዕለት ከዕለት ክንውኖቻቸው ባህልን ያማክላሉ፡፡ የባህል መገለጫዎቹ ባህል ነክ እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው እንደ ሙዚየም፣ ጋለሪና ጥንታዊ ቤተ መንግሥት ባሉ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ከባህል ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት በሌላቸው ቦታዎችም ይስተዋላሉ፡፡ እንደ ምሳሌ የአገሪቱን ኪነ ሕንፃ መውሰድ ይቻላል፡፡ እጅግ ዘመናዊ በሚባሉ ሕንፃዎች የአገሪቱን ጥንታዊ፣ አገር በቀል ዕውቀት የተመረኰዙ ዲዛይኖች ይታከላሉ፡፡

የተመልካችን እይታ የሚስበው ማራኪ ኪነ ሕንፃ በጉልህ የሚስተዋለው በጣሪያ ክፈፍ  አሠራራቸው ነው፡፡ በብዛት በቀይና ሰማያዊ ቀለማት የሚሠራው የጣሪያው የላይኛው ክፍል ልዩ ልዩ ቅርፆች አሉት፡፡ በቻይና ታሪክ የላቀ ቦታ ያላቸው ፎርቢድን ሲቲ፣ ሰመር ፓላስና ቴምፕል ኦፍ ሔቨንን የመሰሉ ጥንታዊ ቤተ መንግሥቶችና ቤተ አምልኮዎች የተሠሩበትን ዲዛይን የተከተለም ነው፡፡

በሚንግ ሥርወ መንግሥት ወቅት የቻይና ነገሥታት መቀመጫ የነበረው ፎርቢድን ሲቲ፣ ከሚገኝበት ስፍራ በቅርብ ርቀት የሚገኘው ሆንግካዎ ፐርል ማርኬት የተሠራው ጥንታዊውን ኪነ ሕንፃ ተመርኩዞ ነው፡፡ ባጭሩ ፐርል ማርኬት (ፐርል ገበያ) በመባል የሚታወቀውና በቻይና መዲና ቤጂንግ የሚገኘውን የገበያ ማዕከል ከውጭ ለተመለከተ ሰው ከጥንታዊ የአገሪቱ ቅርሶች አንዱ ሊመስለው ይችላል፡፡ ፐርል ማርኬት ግን የዘመናዊቷ ቻይና አሻራ ከሆኑ ስፍራዎች አንዱ ነው፡፡

- Advertisement -

ለማዕከሉ መጠሪያነት የተመረጠው ፐርል (ዕንቁ) የሚሸጠው በገበያው በአንደኛው ክፍል ሲሆን፣ በተቀረው አራት ሕንፃ ሌሎች ቁሳቁሶች መሸመት ይቻላል፡፡ በገበያ ማዕከሉ ኤሌክትሮኒክስ፣ አልባሳት፣ የቤት ውስጥ መገልገያዎችና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡ በተለይ ለአገሪቱ እንግዳ የሆኑ ሰዎች በብዛት የሚገኙት የቻይና ባህላዊ ቁሳቁሶች በሚሸጡበት ክፍል ነው፡፡

ባህላዊ ቁሳቁሶቹ በሚሸጡበት ክፍል  የአገሪቱን ታሪክና ኪነ ጥበብ ከሚያሳዩ ዕቃዎች በተጨማሪ፣ የጥንታዊ ሥልጣኔ አሻራቸውን የሚያንፀባርቁ መገልገያዎችም ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ ብዙዎች ወደዚህ አካባቢ ከመምጣታቸው አስቀድመው ከእንቁና ሌሎችም የከበሩ ድንጋዮች የተዘጋጁ ጌጣ ጌጦች የሚሸጡበትን ይጎበኛሉ፡፡ ከከበሩ ድንጋዮች የተሠራ የጣት ቀለበት፣ የጆሮ ጌጥና የእግር አምባር አቅማቸው ፈቅዶ የሚገዙ፣ ዲዛይናቸውን ለመመልከት ብቻ ወደ ማዕከሉ የሚያቀኑም አሉ፡፡

ቤጂንግ ሆሊዲይ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ በዓመት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ዕንቁ ለማግዛት ሲሉ ብቻ ወደ ማዕከሉ ይጓዛሉ፡፡ የቀድሞዋ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸር በአንድ ወቅት ወደ ማዕከሉ ማምራታቸውም ተገልጿል፡፡ በወቅቱ ከተከበሩ ድንጋዮች በተሠሩት ጌጣ ጌጦች ዲዛይን ተማርከው እንደነበርና በተለይ የእንቁ ጌጣ ጌጦቹ የበለጠ ቀልባቸውን እንደሳቡት ተመልክቷል፡፡

በፐርል ማርኬት ሌላ ጥግ የዘወትር ልብሶችና ጫማዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎችና የጉዞ ሻንጣዎች ይገኛሉ፡፡ ወደ ገበያው ለሸመታ ለሚሄደው ሰው ባጠቃላይ በማዕከሉ ካሉ ነጋዴዎች ጋር በዋጋ መደራደር እንደሚያስፈልግ ስለሚነገረው ሻጮቹ በመጀመሪያ በጠሩት ዋጋ የሚሸምት የለም፡፡ ‹‹አይቀንስም?›› ‹‹ኧረ መሸጫ ዋጋውን ንገሩኝ?›› ‹‹የመጨረሻው ስንት ነው?›› የመሰሉ የኢትዮጵያውያን የዘወትር የዋጋ መደራደሪያዎች እዛም ሥራ ላይ ይውላሉ፡፡ ቋንቋው ቢለወጥም የዋጋ ክርክሩ ተመሳሳይ ነው፡፡

የማዕከሉ አንድ ክፍል ሲ ፉድ (እንደ አሳ ያሉ የባህር ውስጥ እንስሳት ምግቦች) የሚገኙበት ነው፡፡ በመላው ዓለም እውቅናን እያገኘ የመጣው የቻይና ምግብ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለገበያ የቀረበበት ክፍል ዘወትር በተስተናጋጆች ይሞላል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም አገሮች የቻይና ሬስቶራንቶች እየተበራከቱ ከመሄዳቸው አንፃር፣ ስለ ባሕላዊ ምግቦቹ ዓይነት ብዙዎች ያውቃሉ፡፡ የማያውቁም በቻይና የአመጋገብ ባሕል የሚዘወተሩ ምግቦችን ለማወቅ ከግብይት በኋላ እግረ መንገዳቸውን ጎራ ይላሉ፡፡

የቻይናን ባህል በሚያንፀባርቀው ክፍል አንድ ጥግ ከሲልክ የተሠሩ አልባሳት ይገኛሉ፡፡ ከጥንታዊ ቻይና አንስቶ ከአንዱ ዘመን በሌላው የአለባበስ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ጥቅም ላይ የሚውሉ ልብሶች አሉ፡፡ ከነዚህ መካከል በሲልክ የተሠሩት አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ በአገሪቱ አንድ ሰው በማኅበረሰቡ እንዳለው ቦታ የተለያየ ዲዛይን ያላቸው ልብሶች ይለብሳል፡፡ በዓለም እውቅናን ካተረፉ የቻይና ልብሶች መካከል የሴቶች ባህላዊ ልብስ ይጠቀሳል፡፡ በብዛት ደማቅ ቀለም ያላቸውን ረዣዥም ባህላዊ ቀሚሶችም በርካቶች በገበያው ይሸምታሉ፡፡

ታዋቂ የፋሽን ዲዛይነሮች የቻይናን ባህላዊ አልባሳት አሠራር ከዘመናዊው ጋር እያዋሀዱ ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ፐርል ማርኬት ደግሞ ቱባውን የቻይና አለባበስ ባሕል ያማከለ ነው፡፡ ለሕፃናትና ለአዋቂዎችም የሚሆኑ ባህላዊ ልብሶችና ጌጣ ጌጦች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጡ ሲሆን፣ የብዙዎችን ኪስ አለመጉዳታቸው ማዕከሉን የሸማቾች ምርጫ አድርጎታል፡፡

ቻይናውያን ባሕላቸውን አክባሪ መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል፡፡ ከባሕላቸው መገለጫ አንዱ ለሆነው ቋንቋቸው ማንደሪን የሚሰጡትን ቦታ እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ በገበያ ማዕከሉ የሚሸጡት ሲልክ የአንገት ልብሶች የማንደሪን ጽሑፍ የሰፈረባቸው ናቸው፡፡ አላፊ አግዳሚውን ወደ ሱቃቸው ከመጋበዝ የማይቦዝኑት ሻጮች ዕቃቸውን ለማስተዋወቅ ምርቱ ቱባ የቻይና ባህልን የሚያንፀባርቅ፣ ሸማች ለራሱ ወይም ለሌሎች ሰዎች ስጦታ ቢገዛውም የሚኩራራበት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ላቀረቡት ዕቃ በመጀመሪያ ከሚጠሩት ዋጋ ተደራድሮ የማስቀነስ ሒደት ጥቂት ደቂቃዎች ሲመስድም፣ በስተመጨረሻ የወደዱትን ዕቃ መሸመት አይቀርም፡፡

የረዥም ዓመታት ታሪካቸውን ከሚያንፀባርቁ  ቁሳቁሶች መካከል የግሬት ዋል፣ የቲናመን ስኩዌር፣ የሰመር ፓላስ፣ የፎርቢድን ሲቲና የቴምፕል ኦፍ ሔቨን ምስል የተንፀባረቀባቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ቦርሳ፣ ዋሌት፣ የስልክ መሸፈኛ፣ የቁልፍ መያዣ የጠረጴዛ ጌጥ፣ ሰሀን፣ ብርጭቆና ሌሎችም በርካታ መገልገያዎች ይጠቀሳሉ፡፡

አብዛኞቹ የስጦታ ዕቃዎች ታሪካዊ ቦታዎችን በምሥል የሚያሳዩ ሲሆን፣  ቦታዎቹን አስመስለው የተሠሩ ቅርፆችም ለገበያ ቀርበዋል፡፡ በቻይና ታዋቂ ከሆኑ ተፈጥሮና ታሪክን አጣምረው የያዙ ቦታዎች ሰመር ፓላስ ባህር፣ ፓርክና ጥንታዊ ቤተ መንግሥቶች ያካተተ ሲሆን፣ በኪነ ሕንፃ ጥበባቸው ከሚደነቁ ስፍራዎች አንዱ ነው፡፡ በሰመር ፓላስ ከሚገኙ ሕንፃዎች መካከል አንድ ወይም ሁለቱን የሚወክሉ መጠነኛ ቅርፆችም በማዕከሉ በብዛት ይሸጣሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ1989 ከነበረው የቻይና ፖለቲካዊ አብዮት ጋር ተያይዞ የሚታወሰው ቲናመን ስኩዌርን የሚወክሉ ቅርፆችም ይገኛሉ፡፡ ማግኔት ያላቸውና በማንኛውም ብረት ለበስ ቁሳቁስ ላይ መጣበቅ የሚችሉ ቅርፆች ያሉ ሲሆን፣ በብረትና በፕላስቲክ የተሠሩ ቅርፃ ቅርፆችም ይሸጣሉ፡፡ በጨርቅና በስፖንጅ ከተዘጋጁት ቅርፆች በስፋት የሚገኙት ደግሞ የፓንዳ ምስሎች ናቸው፡፡

ቻይና ውስጥ ከሚወደዱ እንስሳት መካከል ፓንዳ አንዱ ነው፡፡ ቤጂንግ ውስጥና በሌሎችም የቻይና ግዛቶች በሚገኙ የእንስሳት ማቆያዎች ውስጥ ፓንዳዎች በብዛት ይገኛሉ፡፡ አይፓንዳ በተሰኘ የቻይና ኦንላየን ጣቢያ የፓንዳዎች እንቅስቃሴ ለ24 ሰዓታት በቀጥታ ይተላለፋል፡፡ ሥርጭቱን የሚከታተሉ በርካታ ቻይናውያን፣ የግዙፍ ፓንዳዎችን እንቅስቃሴ ለሰዓታት መመልከት ያዝናናቸዋል፡፡ ይኼ በአገሪቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንስሳ በባሕላዊ ቁሳቁሶች መሸጫ መደብርም ምስላቸውና ቅርፃቸው ከሚቸበትቡ ውስጥ ይጠቀሳል፡፡

በቻይናውያን ዘንድ በቾፕስቲክ መመገብ የተለመደ ነው፡፡ ለብዙዎች በሁለት ቀጫጭን የእንጨት መያዣያዎች ተጠቅሞ መመገብ በቀላሉ የሚለመድ ባይሆንም፣ ቾፕስቲክ ካለው እውቅና አንፃር በፐርል ማርኬት በስፋት ይሸጣል፡፡ ከቾፕስቲኩ ጋር አብረው የሚሄዱ አነስተኛ የሻይ ስኒዎችም ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ የቡና ባህል እንደሚወደደው ሁላ ቻይናውያን ለሻይ ሥርዓታቸው ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ፡፡ በማዕከሉ በተለያየ ዲዛይን የተሠሩ የሻይ ስኒዎች የሚገኙትም ለዚሁ ነው፡፡

ቻይና ውስጥ በሕንፃዎች፣ በጎዳና ላይና በሌሎችም ሕዝብ የሚበዛባቸው አካባቢዎች የድራገን ምሥልና ቅርፅ ይስተዋላል፡፡ በቻይና አፈ ታሪክና ተረቶች ውስጥ የድራገኖች ሚና ሰፊ ነው፡፡ ድራገኖች የብርታትና ድል አድራጊነት ተምሳሌት ሲሆኑ፣ ለሰዎች መልካም እድል እንደሚያመጡም ይታመናል፡፡ በፐርል ማርኬት በመጠን አነስተኛ ከሆኑ የድራገን ቅርፆች እስከ ግዙፎች ይሸጣሉ፡፡ ከድራገን ቅርፅች ጎን ለጎን የጎራዴ ቅርፆችም ለበያ ቀርበዋል፡፡

በቻይናውያን ታሪክ ከተለያዩ ጦርነቶች ጋር የተያያዙት ወቅቶች ሲነሱ የቻይና ጎራዴ አሠራርም ተያይዞ  ይጠቀሳል፡፡ በይበልጥ ከጥንታዊት ቻይና ታሪክ ጋር የተያያዙ ፊልሞች ሲሠሩ የጎራዴ ውጊያ ትዕይንቶች ይታከሉባቸዋል፡፡ ትልልቆቹን ጎራዴዎች  ሸምቶ ከቻይና ወደ የትኛውም አገር ለመጓዝ የአየር መንገዶች ሕግ አይፈቅድምና ከመጻፍ የማይበልጥ ርዝመት ያላቸው ጎራዴዎችን መግዛትን ብዙዎች ይመርጣሉ፡፡ በቻይናና በዓለም ላይ ተወዳጅ የሆነው የኩንግ ፉ ጥበብን የሚያሳዩ የግርግዳ ጌጦችም የገበያው አንድ አካል ናቸው፡፡

በፐርል ማርኬት ሦስተኛው ፎቅ መሀል ላይ ግዙፍ የቡድሀ ቅርፅ ይገኛል፡፡ አጠገቡ ዕጣንና ሰንደል ይጨሳል፡፡ ቡዲዝም በቻይና ማኅበረሰብ ካሉ ሃይማኖቶች አንዱ ሲሆን፣ ቻይና ውስጥ የቡድሀን ምስል ወይም ቅርፅ ለማግኘት ብዙ ርቀት መጓዝ አያስፈልግም፡፡ በገበያው ውስጥም በተለያየ መጠን የቡድሀን ቅርጽ ማግኘት ይቻላል፡፡ ለቤት ውስጥ ጌጥ ከሚሆኑ ቁሳቁሶች አንስቶ መገልገያዎችም በቡድሀ ቅርፅ ተሠርተው ይቸበቸባሉ፡፡

ቀይ በቻይናውያን ባህል መሠረት መልካም ዕድልን የሚወክል ቀለም ነው፡፡ ቀይ የደስታ ቀለም በመሆኑ ሰዎች ሐዘን ላይ በሚሆኑበት ወቅት አይጠቀሙበትም፡፡ ብዙ ቻይናውያን ቤታቸውን ሲያስጌጡ ቀይ ቀለም ያላቸው ግብዓቶች የሚጠቀሙትም ለዚሁ ነው፡፡ በበር፣ መስኰትና በአራቱም የቤት ማዕዘን ግርግዳዎች የሚንጠለጠሉ ቀይ የቤት ጌጦች የማዕከሉ ሌላኛው ገጽታም ናቸው፡፡

ፐርል ማርኬት የቻይና ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ እንዲሁም ታሪክ፣ ባህልና ጥበብ በአንድ ተጣምሮ የሚገኝበት ነው፡፡ ሻጮቹ ለቱሪስቶች ውድ ዋጋ ቢጠሩም፣ አሠራራቸውን ያወቀ ሰው ተከራክሮና ተደራድሮ በፍትሐዊ ዎጋ መሸመት ይችላል፡፡ የቻይና ቆይታቸውን የሚያስታውሳቸው ቁሳቁስ አልያም ለወዳጅ ዘመድ ስጦታ መግዛት ለሚፈልጉ ገበያው የተመቸ ነው፡፡

በፐርል ማርኬት ውስጥ የበርካታ አገር ዜጎች ሲሸምቱ ይስተዋላል፡፡ ሸማቾች ከአገራቸው የመጣ ሰው ሲያገኙ ከዚህ ቀደም የማያውቁት ሰው መሆኑ ሳይታያቸው በደስታ በቋንቋቸው ይነጋገራሉ፡፡ አብረው የሚሸምቱና የሚገባበዙም አይጠፉም፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ለልብስና ኤሌክትሮኒክስ እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶች ሸመታ ቻይናን ምርጫቸው ካደረጉ ሰነባብተዋል፡፡

ቤጂንግ ውስጥ ታዋቂ ከሆኑ የገበያ ማዕከሎች መካከል ፐርል ማርኬትና ሲልክ ማርኬት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይም በፐርል ማርኬት በርካታ ኢትዮጵያውያን ይገበያያሉ፡፡ በማዕከሉ በተዘዋወርንበት ወቅትም በተለያየ ምክንያት ወደ ቻይና ያመሩ ኢትዮጵያውያን ገጥመውናል፡፡ ለአጭር ሥልጠና፣ ዘለግ ላለ ትምህርትና ለግብይት የሄዱት ይጠቀሳሉ፡፡

ቻይናውያን በቋንቋቸው ለሚያናግራቸው ወይም ለማነጋገር ከሚሞክር ሰው ጋር ደስ እያላቸው ስለሚግባቡ ብዙዎቹ ጥቂትም ቢሆን ማንዳሪን ይችላሉ፡፡ በግብይታችን ወቅት በቻይና ስለነበረን ቆይታና ስለ አገራችንም ተነጋግረናል፡፡ ስልክ ቁጥር ተለዋውጠን፣ ባመቸን ጊዜ ለመገናኝት ተስማምተን፣ በአገሪቱ የነበረንን ጊዜ ለማስታወስ ይሆናሉ ያልናቸውን ቁሳቁሶች ከፐርል ማርኬት ሸምተን ተለያይተናል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...