- አንተ ከአሜሪካ መቼ መጣህ? እዚህስ እንዴት መጣህ?
- ሳምንት ሆነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በፊት ሳውቅህ የእኛ ተቃዋሚ ነበርክ፡፡
- አሁንም እቃወማለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምትቃወመን ከሆነ በዓላችን ላይ ምን ትሠራለህ?
- እኔ እኮ ጽንፈኛ አይደለሁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማን ነው ታዲያ ጽንፈኛ እባክህ?
- እናንተን አምርረው የሚቃወሙና ዓይናቸውን ጨፍነው የሚደግፏችሁ፡፡
- የእኛ ደጋፊዎች ጽንፈኛ ናቸው እንዴ?
- ሁሉንም አላልኩም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የትኞቹ ናቸው ታዲያ ጽንፈኞች?
- ድንጋዩን ዳቦ ነው ብለው የሚያፈጡት ናቸዋ፡፡
- እንደዚህ ይላሉ እንዴ?
- እነሱ እኮ ምንም ዓይነት ተቃራኒ ነገር ማየትም መስማትም አይፈልጉም፡፡
- ለምን ይመስልሃል እባክህ?
- ነገሮችን የሚያዩት ከጥቅማቸው አንፃር ብቻ ስለሆነ ነዋ፡፡
- እንዴት እንዲህ ልትል ቻልክ?
- ብዙዎቹን አውቃቸዋለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በምሳሌ አስረዳኝ፡፡
- መንግሥት ሲሳሳት ለማረም አይፈልጉም፡፡
- እሺ?
- ሰዎች ገንቢ ሐሳብ ሲያቀርቡ ያበሻቅጣሉ፡፡
- እሺ?
- ትንሿን ነገር እያጋነኑ የሌለ ምሥል ይፈጥራሉ፡፡
- እሺ?
- የአገር የጋራ ጉዳይን ብሔር ውስጥ ይወሽቃሉ፡፡
- ሌላስ?
- የሚደግፉት መንግሥት ችግር ውስጥ ሲገባ ይጠፋሉ፡፡
- ምን?
- ያኔ አመፁ ሲቀጣጠል እኮ ጠፍተው ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በኋላስ?
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲታወጅ ቀና አሉ፡፡
- ከዚያስ?
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የዴሞክራሲ ውጤት ነው ማለት ጀመሩ፡፡
- አንተ ትዋሻለህ እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር ማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ ገብተው ማየት ይችላሉ፡፡
- የእኛን ደጋፊዎች እንዲህ ስታብጠለጥል ስለተቃዋሚዎቹስ ምን ትላለህ?
- እነዚያም ከእጅ አይሻል ዶማ ናቸው፡፡
- እንዴት?
- ዓይናቸውን በጥሬ ጨው አጥበው ይዋሻሉ፡፡
- ምን ይላሉ?
- አገሪቱ እንደ ሶማሊያ ተፈረካክሳለች ሲሉ ነበር፡፡
- ሌላስ?
- እርስ በርሳቸው ሲናጩ ይከርሙና በትንሽ ጉዳይ ጊዜያዊ ወዳጅነት ይፈጥራሉ፡፡
- እሺ?
- ጥቂት ሳይቆዩ ደግሞ እርስ በርስ ይባላሉ፡፡
- እሺ እባክህ?
- በሐሰተኛ ወሬዎች አንድ ወር ይዝናናሉ፡፡
- ከዚያስ?
- ሌላ አዲስ ወሬ እስኪፈጠር ያደፍጣሉ፡፡
- በዚ ላይ ደግሞ…
- ምን?
- እዚህ አገር አዲስ ነገር ተሠራ ሲባል ዓይናቸው ደም ይለብሳል፡፡
- ለምን እንዲህ ይሆናሉ?
- አንደኛው በባዕድ አገር መኖር በራሱ ትልቅ ጫና አለው፡፡
- ሁለተኛውስ?
- ፕሮፓጋንዳ ሲጋቱ ስለሚከርሙ ግራ ይጋባሉ፡፡
- ልማታችንን ማድነቅ አይፈልጉም አይደል?
- እናንተን በጣም ስለሚጠሉ ሥራችሁ አይጥማቸውም፡፡
- የሚሠራ መንግሥት ይጠላሉ ማለት ነው?
- አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ምንድነው?
- ይኼ የአገሪቱን ችግር ነው የሚያሳየው፡፡
- የምን ችግር?
- የጋራ የሚባል መግባቢያ በመጥፋቱ ነዋ፡፡
- እኛ ምን እናድርግ ታዲያ?
- ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር መሥራት አለበት፡፡
- እነሱ አንፈልግም ካሉስ?
- በጽንፈኛነት መቀጠል አያዋጣም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማለት?
- ጽንፈኝነት ሲመክን የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት ይደመጣሉ፡፡
- ስለዚህ?
- የተሟላ ዴሞክራሲ የሚሰፍነው በዚህ መንገድ ብቻ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ዳያስፖራውን አሰናብተው ከአንድ ደጋፊ ጋር እየተነጋገሩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር በዓሉ እንዴት ነው?
- ዘንድሮ በረድ አድርገን እያከበርነው ነው፡፡
- በነገራችን ላይ ክቡር ሚኒስትር ደህና ነዎት?
- ለምን ጠየቅኸኝ?
- ስሜትዎ ቀዝቅዞብኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኸውልህ ወዳጄ?
- አቤት ክቡር ሚኒስትር?
- የ26 ዓመታት ድላችንን ስናከብር መለስ ብለን ማየት አለብን፡፡
- ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
- ከ26 ዓመታት በፊት እኮ ለ17 ዓመታት ታግለናል፡፡
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ያኔ የታገልነው ሕዝብን ከደርግ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት ነበር፡፡
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ደርግ የሚወክለው ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጭቆናን ነበር፡፡
- ትክክል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼ ጭቆና በምን ይገለጻል?
- ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ባለመቻል፡፡
- ልክ ብለሃል፡፡
- ፍትሕ በማጣት፡፡
- ትክክል ብለሃል፡፡
- እስር ቤት በመወርወር፡፡
- ትክክል ነህ፡፡
- ጥያቄ ያነሱትን በመግደል፡፡
- በደንብ ገብቶሃል፡፡
- በገዛ አገር ባይተዋር መሆንም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ትክክል ወዳጄ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር?
- አቤት?
- ይህንን ጉዳይ ለምን አነሱት?
- እኛ ላይም ጥያቄ እየተነሳ እንዳለ መዘንጋት የለብህም፡፡
- ይኼ እኮ የፀረ ሰላም ኃይሎች ወሬ ነው፡፡
- እንደሱ አትበል፡፡
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- ችግራችን ሲነገረን ብናዳምጥ አንጎዳም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በጠራ መስመር እየተመራን ነው እኮ?
- አንተ አይገባህም እንዴ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ያ ሁሉ አመፅ የተነሳው ለምን ይመስልሃል?
- በፀረ ሰላም ኃይሎች ሴራ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለመሆኑ ጥልቅ ተሃድሶ አላደረግክም፡፡
- ያኔ ለሥራ ጉዳይ ውጭ ነበርኩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ተሃድሶ አልገባህማ?
- ለጥቂት ነው ያለፈኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በቃ ሌላ ዘር ተሃድሶ እስኪመጣ…
- ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
- የፅሞና ጊዜ ያስፈልግሃል፡፡
- የት ነው እሱ?
- በርህን ዘግተህ…
- በሬን ዘግቼ ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
- ጥልቅ ግምገማችንን በጥልቀት ታነበዋለህ ገባህ?
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮአቸው ገብተው ከጸሐፊያቸው ጋር እየተነጋገሩ ነው]
- ዛሬ ቀጠሮ አለኝ?
- የለዎትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዲያ ከሆነማ ቤት ልሂዳ፡፡
- አንድ ሰው ግን በስልክ ሊያናግርዎት ይፈልጋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማን ነኝ አለ?
- ኢንቨስተር ነኝ ነው የሚለው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን ፈለገኝ?
- አስቸኳይ ነው ብሎ ስልኩን ትቷል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እዚሁ ደውይና አገናኚኝ፡፡
- ይኸው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማን ልበል?
- ክቡር ሚኒስትር ልማታዊ ኢንቨስተር ነኝ፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ለልማቱ ዘብ የቆምኩ ሀቀኛ ኢንቨስተር ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሱን ተወውና ምን ፈልገህ ነው?
- እንደሚያውቁት አባል ለመሆን ጥቂት የቀረኝ የልብ ደጋፊ ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጉዳይህ ምንድነው?
- ክቡር ሚኒስትር አንድ ችግር ገጥሞኝ ነው፡፡
- ምንድነው እሱ?
- መሬት በድርድር ጠይቄ እንቢ ተባልኩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በጨረታ ተወዳደር፡፡
- የውጭ ምንዛሪም በአስቸኳይ እፈልጋለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ወረፋ ጠብቅ፡፡
- የባንክ ብድር በፍጥነት ፈልጌ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንተ ከማን በልጠህ ነው እባክህ?
- የእኔ ኢንቨስትመንት ልዩ ስለሆነ…
- እንዲህ የሚባል ነገር አላውቅም፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር አንድ ይበሉኝ?
- አንተ ሰውዬ ነገርኩህ እኮ?
- ክቡር ሚኒስትር የሚያስፈልገውን ሁሉ በእኔ ይተውት፡፡
- አንተ አጭበርባሪ ዝም ትላለህ አትልም?
- እኔ እኮ የቤተሰብዎ የቅርብ ወዳጅ ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን አልክ?
- የቤተሰብዎ የቅርብ ወዳጅ ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማነው ደግሞ ከቤተሰቤ ጋር ያስተዋወቀህ?
- ክቡር ሚኒስትር እንዳይቆጡ?
- ለምን?
- ያስተዋወቀኝ እኮ…
- ማን ነው?
- የቅርብ አማካሪዎ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ወስላታ ሁሉ!
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠርተው እየጮሁበት ነው]
- አንተ ብለህ…ብለህ…
- ምን አደረግኩ ክቡር ሚኒስትር?
- ያን ሞላጫ ኢንቨስተር ተብዬ ከማን ጋር ነው ያስተዋወቅከው?
- እሱን ነው እንዴ ሞላጫ የሚሉት?
- ምን ልበለው ታዲያ?
- ኧረ የተከበረ ኢንቨስተር ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት ነው የተከበረ የሚባለው ይኼ ሌባ?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ይረጋጉ፡፡
- ለመሆኑ ከማን ጋር ነው ያስተዋወቅከው?
- ከባለቤትዎና ከሴት ልጅዎ ጋር ነው ያስተዋወቅኩት፡፡
- ለምን ብለህ?
- ጠቃሚ ሰው ስለሆነ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼ ወስላታ ምኑ ነው የሚጠቅመው?
- ትልቅ ውለታ ሊሠራልዎት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ የሌባ ውለታ አላውቅም ገባህ?
- ክቡር ሚኒስትር ተረጋግተን እናውራ፡፡
- ከእንዳንተ ዓይነቱ የሌባ ጉዳይ አስፈጻሚ ጋር እንዴት ነው የማወራው?
- ክቡር ሚኒስትር ትዝ ይልዎታል?
- ምኑ እባክህ?
- ባለቤትዎና ልጅዎ አሜሪካ መዝናናት እንደሚፈልጉ የነገሩኝ?
- እና?
- አሁን ችግሩ ተቀረፈ እኮ?
- እንዴት ሆኖ?
- ይኼ እርስዎ የሚያወግዙት የዋህ ኢንቨስተር ነዋ?
- ምን አደረገ?
- ወጪውን በሙሉ እችላለሁ ብሏል፡፡
- አንተ አብደሃል እንዴ?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር አያክርሩ?
- ምን አልክ አንተ?
- አንድ ጽንፍ ይዘው መላወሻ አሳጡኝ እኮ?
- እኔ ነኝ ጽንፈኛ?
- ይኼው ከቅድም ጀምሮ አንድ ነገር ይዘው አለቅ ብለዋል፡፡
- ከሌባ ጋር አልሞዳሞድም ማለት እንዲህ ያስብላል?
- አሁን እኮ ሁሉም ነገር አልቋል ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑ ነው የሚያልቀው?
- አለ አይደል ክቡር ሚኒስትር?
- ምን?
- በቃ አሁን የባለቤትዎና የልጅዎ ቲኬት በኦንላይን ተቆርጦ ተልኳል፡፡
- የምን ቲኬት?
- የሚበሩበት ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የት ነው የሚበሩት?
- ላስ ቬጋስ!