Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አሁንስ አልበዛም?

ሰላም! ሰላም! “የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ቢኖራችሁ የኢትዮጵያን የሰሜን ተራሮች ተነስታችሁ ወደ ህንድ ውቅያኖስ ስጠሙ ብላችሁ ማዘዝ ትችላላችሁ፤” ብለው ማስተማር ቢጀምሩስ ቴክሳሶች? ሲያሻን ተራራ እያንቀጠቀጥን ሲያሻን ደግሞ ተራራው እየተንቀጠቀጠብን የእኛ መጨረሻ እንዲያው ምን እንደሚሆን ዝም ብሎ ማየት ነው። “ሴክሬት ዌፐን” ደብቀሻል እየተባባለች በሳዳም ሁሴን ሥልት አገር ስትበረብር፣ እኛ ተራራ የሞላው የማይበረበር አገር ይዘን በአውሎ ንፋስ አገር ፈጀን አሉ፡፡ እግዚኦ፡፡ አንዳንዱ ወሬኛ ነው እንጂ ግርም የሚለኝ። “አየህ አይደል አንበርብር አሜሪካ እኮ ወዳ አይደለም ሥር ሥራችን የምታቶሰቱሰው፤” ብሎ በቃ የሚያደርገውን አሳጣው። “እናንተ ልጆች ምን ነክቷችኋል?” ይኼ ከየትም ሊነሳ የሚችል የተፈጥሮ አደጋ ነው፤” ስል ማንጠግቦሽ፣ “እልልልል. . .” እያለች ከቤት ወጣች።

እኔ ደግሞ ይኼ የቢራ ቆርኪ ወይ መኪና ወይ ቤት ሸልሞልኝ ገላገለኝ ብዬ “ምነው?” ስል፣ “ለካ በቀደም አሜሪካ ቴክሳስ የተከሰተው የአውሎ ንፋስ አደጋ የእኛዎቹ የሰሜን ተራሮች አባረውት ኖሯል? እልልል. . . እኔ መቼ አውቄ?” እያለች ቀወጠችው። “ኧረ እባክሽ ቀልብ ግዥ። እዚያስ ቢሆን ኢትዮጵያ አይደለም እንዴ። ምን ቀረን ከዚህ በላይ። አገር በሁለት ምድብ ስትከፈል ያሳየን በሰው ልጆች ታሪክ የመጀመርያዎቹ እኛ ከሆንን ቆይተናል። እልል የምትይው ታዲያ እዚያ የሚያልቀውና የሚሰደደው ወገን አይደለም? ወገን ባይሆን ሰው አይደለም?” ስላት ረገብ አለች። ሰው በቃ በተጨበጠውም ባልተጨበጠውም ወሬ ‹እልልል. . .› ሲል እንጥሉን ‹ስካን› እስከ ማድረግ አቅም ያላቸው ጮሌዎች ሰማይዩን እንደተቆጣጠሩት ይረሳዋል ልበል? “ምሳር ላወቀበት ደን ይመነጥራል፣ አትቅደም ያለው በዓይን ይጠረጥራል፤” አለ ባህሩ ቃኜ ባህር በቃኘ ልቡ። ጉድ እኮ ነው። ግን እኔ ምለው? ለካ ኑክሌር ብቻ አይደለም አስፈሪ ከባድ መሣሪያ፡፡ አደራደሩን ላወቀበት ተራራም ተገን ነው። እንዳንቀጠቀጥኩህ ልኑር ካላሉት ማለቴ ነው። ምነው አጠፋሁ?

ይልቅ በቀደም ቤት ለማሻሻጥ ደንበኞቼን ቀጥሬ እየጠበቅኩ አቃሎ የመቅለል የዘመኑ ‹ፎርሙላ› ነገር ትዝ ብሎኝ ልቤን ‹ሳይለንት› አድርጌ አስባለሁ። ድንገት  ማንጠግቦሽ ደወለች። “ወዬ?” ስላት፣ “ሽሮ አልቆብኛል። ላስፈጭ ብሄድ መብራት የለም። ከባልትና ሁለት ምጥን ሽሮ ገዝተህ ና. . .” አለችን። ባለሙያዋ ሚስቴ መቼም ሁሌ አይሞላላትም። በተለይ ዘንድሮ አንዲህ ለይቶልን፣ “ምን ያመጣሉ?” ተብሎ መብራት መጫወቻ ከሆነ ወዲህ አቅቷታል። ነገሩ እኮ ግራ አጋቢ ሆኖ የምንበጣበጠው ሁሌ ሙሉ የሆነላቸው ሰዎች ደግሞ በጎን አሉ። እናም ወደ ጨዋታዬ ስመለስ ደንበኞቼ መዘግየታቸውን ተረድቼ እዚያው አካባቢ ባልትና ቤት ፍለጋ ጀመርኩ። ለሠፈሩ እንግዳ መሆኔን ስረዳ አንድ ልጅ እግር አውደልዳይ (በትምህርት ሰዓት የሚያውደለድሉትን ከዛሬ ጀምሮ በየሄዳችሁበት ቁጠሩማ። ምነው ስትሉዋቸው መልሳቸው መብራት የለም ነው)፡፡ ጠራሁና ‹‹እዚህ አካባቢ ሽሮ የሚሸጡ አሉ?›› ብዬ መጠየቅ። እኔም ያጠያየቄ ክፋት። እሱ ታዲያ ሰባት ቤቶች ቆጠረልኝ። እንዳልተግባባን ልብ በሉ።

“እንዴ ይኼ ሁሉ ባልትና ቤት በአንድ አካባቢ ያለው ሰው አተር ለቅሞ፣ አስፈጭቶ ቤቱ ማዘጋጀት ትቶ ነው?” ስል፣ “ሰባት ሺሕ ሰው ተሠልፎ ሲያስፈጭ መብራት ከሚባክን ሰባት ሰው ለሰባት ሺሕ ሰው አስፈጭቶ ቢያዘጋጅ የዋጣል በሚለው ያዘው፤” አለና እርሜን አወጣሁ። ወይ ሽሮ? እኮ ለሽሮም መብራት? ድሮ እኮ ሬስቶራንት በላሁ ተብሎ ጉራ የሚነዛው በእነ ላዣኛ፣ ቴላቴሊ፣ ፒዛ፣ ቺክን አሮስቶና መንዲ ምናምን ነበር። ኧረ ድሮ እኮ አሁን ነው ዝም አትበሉ ‘ፕሊስ’። እንዲህ ባዕድ አገር እንደ ገባ ሰው ለሽሮ ማብሰያ የሚሆን መብራትም ብልኃትም እያጣን፣ በሽሮ ቤት ጋጋታ ስመሰጥ ደንበኞቼ ከየት መጡ ሳልላቸው ከች ብለው፣ “ላረፈድንበት ና እዚህ ጋ ቆንጆ ሽሮ ቤት አለ። ምሳ እንጋብዝህ. . .” ብለው ይዘውኝ ላጥ። ከወንዱ የሴቱ ብዛት። ደግሞ ከሁሉ ከሁሉ የቢሉ ቢለዋነት። ታዲያ አስተናጋጁ ምን ቢለን ጥሩ ነው፣ “ዋጋው ምነው በዛ?” ስንለው፣ “በጄኔሬተር ስለምናብስል ነው፤” አይለን መሳላችሁ? እኔም ብቻ ዘንድሮ ተምታታብኝ!

በነጋታው አረፋፍጄ ቁርሴን በልቼ ቡናዬን ጠጥቼ ከቤቴ ወጣሁ። እንደ ትናንት በእንጥልጥል የተውኩት ቢዝነስ  ነበረኝና ወደዚያው መጓዝ ጀመርኩ። ነገሩ ሁለት ሺሕ  ካሬ ሜትር የሚሸጥ ቦታ ነው። ሁለት መቶ ካሬው ላይ ኤልሼፕ ቤት ተሠርቶበታል። ትናንትናውኑ የሚገዛ ሰው ፈልጌ አግኝቼ የሻጩ ቆይ ነገ ይሁን ስላለ ለአዳር ተወሰነ። በበኩሌ ከንክኖኛል። አሁኑኑ ሰው ካገኘህ አምጣና ወደዚያ ገላግለኝ ሲለኝ እንዳልነበር ምን ሰምቶ ነው ነገ ኑ ያለው እያልኩ ሳወጣ ሳወርድ ስልኬ ጠራ። ገዥው ደንበኛዬ ነው። ‹‹ወደ አንተ እየመጣሁ ነው። ያው ዋጋው 14 ሚሊዮን ብር ነው። አይተኸው ደግሞ መደራደር ነው፤›› አልኩትና ስልኩ ተዘጋ። ወዲያው ስልኬ መልሳ ጮኸች። ሻጩ ደንበኛዬ ነው። ‹‹አቤት አቤት. . .›› አልኩኝ ጭራዬን እየቆላሁ። ገና አፉን እንዳላሟሸ ያስታውቃል። ደህና አረፈድክ ሳይለኝ፣ ‹‹ቦታው በዛሬ ገበያ መሠረት ከ14 ወደ 16 ሚሊዮን ብር ገብቷል፤›› አይለኝ መሰላችሁ?

‹‹እንዴ ትላንትና እኮ 14 ነው ብዬ ተናግሬያለሁ። ደግሞ አሁን ቦታውን ለማየት ወደ እርስዎ እየመጣን ነው፤›› ስለው ‹‹የለም የለም። አንተ ዘመናዊ ደላላ አይደለህም እንዴ? ምንድነው በሚዲያ የዕለቱን የቢዝነስ ዘገባ መከታተል እኮ አለብህ።  ዶናልድ ትራምፕ ከተመረጡ ወዲህ ነገሮች ከመርገብ ይልቅ ይበልጥ እየከረሩ ነው። ሰሜን ኮሪያን ተመልከት። የሦስተኛው የዓለም ጦርነት ዳር ዳር ማለት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመሬትን ዋጋ ይመለከተዋል፤” ብሎኝ አረፈዋ። ግራ ገብቶኝ ባለሁበት ቆሜ ቀረሁ። ጊዜ ሳላጠፋ ለገዥው ደንበኛዬ ደውዬ የተባልኩትን ስነግረው፣ ‹‹እኛ እኮ ለአቶሚክ ቦምብ ሙከራ ልናከራየው አይደለም የምንገዛው? አሁን ይኼ ሁሉ ምን ያስፈልጋል?›› ብሎ አዘነ፡፡ ዘመንና ዘመነኛ ነቃሁ ነቃሁ እያለ ሲጫወት ግን አንዳንዴ ፍንጣሪው አያስፈራም? በገንዘብ ፍቅር አበድን እኮ እናንተ። ወይ ሰበብና ሰበቡ!

በዚያም በዚህ ብዬ ኮሚሽኔን ተቀበልኩ። ከባሻዬ ልጅ ጋር በመብራትና በኔትወርክ መቆራረጥ ምክንያት ተኳርፈን ነበር። የሰው ልጅ ምስኪኑ መሆን የፈለገውን ሳይሆን ያልፈለገውን በሚሆንባት በዚህች ዓለም፣ ስንት ዓመት ልኖር ይሆን ይኼ ሁሉ ብላችሁ ስታስቡት ዋጋ የሚያጣባችሁ ነገር ብዙ ነው። እና እኔም ኩርፊያዬን ረስቼ የባሻዬን ልጅ ደወልኩለት። እሱም ሥልጡን ነውና የወዳጅነቴን እንደገሰጽኩት ገብቶት ስልኬን አነሳ። “የት ነህ? የት ነህ?” ተባብለን እዚያች ግሮሰሪ ለመገናኘት ተቀጣጠርን። ስንገባ የሰሞኑን ብርድ የወትሮውን ታዳሚ በጊዜ አባሮት ከሦስት ከአራት ሰው በቀር ወንበሩ ባዶ ነው።

“እንኳን በርዶን፣ እንኳን መብራት ጠፍቶ ዘመኑ እንደሆነ እንዲሁም የባዶነት ዘመን ነው፤” አለኝ። እንዴት? ስለው፣ “አታይም በየአቅጣጫው በጋራ የሚመለከቱንን ነገሮች እንዴት እንዳገሸሽናቸው፡፡ መታሸት እኮ ለመድን አንበርብር፡፡ ለግል ጉዳይ፣ ለግል ጥቅም፣ ለግል ኑሮ ስንጣደፍ እኮ በማኅበር ዋጋ እያስከፈሉን ያሉትን ጉዳዮች ትተናቸዋል፤” አለኝ። ቆያይቶ ሲያስበው የባሻዬ ጩኸት ብሎም የሌሎች እግዚኦታ የተናጠል ብቻ መሆኑ እንደ ጎዳን ገብቶታል። እኔ ደላላው አንበርብር በበኩሌ ሰሞኑን ሲያብሰለስለኝ የሰነበተው ነገር ይኼ ሆኗል። አይታወቀንም እንጂ ቅርብ ለቅርብ ሆነን ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ የሆነው ከቁጥር አልፈናል። የምሬን ነው።

በሉ እስኪ እንሰነባበት። አሮጌው ዓመት ተቻኩሎ እንደወጣው አዲሱም ዓመት ይኼው ይከንፋል። ሳምንት ሆነን እኮ መስከረም ከጠባ። ዘመን እንኳ ነፍስ አውቆ ላያችን ላይ የፍጥነትን ዱላ ሲቀባበልብን እኛ እንዳለነው አልፈን እንዳለነው እንተካለን። አይነሽጠን፣ አይሞቀን፣ አይበርደን። ሰማይ እላያችን ላይ ተደፍቶ እያየን አርያም ዙፋን ፊት አንጥፋችሁ ተኙ ተብሎ የክብር ሥፍራ የተፈቀደልን እኮ ነው የምንመስለው። ባሻዬ አሁን፣ “ቆይ አንተ ምንህ ተነክቶ ነው? ምንድነው እንዲህ የሚያሳብድህ?” ሊሉኝ ወደ ቤቴ መጡ። አስቡት ይችን ለመጠየቅ ብቻ። ሲያዩኝ ብቻዬን ነኝ። ማንጠግቦሽ የታመመ ሰው ልትጠይቅ ወጥታለች። ከመውጣቷ በፊት ልታቁላላ የጣደችው ሽንኩርት እንደ ልማዱ መብራት ድርግም ሲል እዚያው ትታው ሄዳ መብራቱ ተመልሶ ሲመጣ አሮ ቀረ።

እና እኔ አዲስ ሽንኩርት ስከትፍ ነው ባሻዬ የደረሱት። እንደ ደረሱ ምንም ምንም አላሉም። ያችኑ፣ “ምንህ ተነካ?” የምትለዋን ጥያቄ ጠየቁ። “እንዴት ምንህ ተነካ ማለት? ለምሳሌ ይኼ ያረረው ግማሽ ኪሎ ሽንኩርት ነበር። እንደ ልጅ መጫወቻ ሽጉጥ መብራት እልም ቦግ ሲል ተረስቶ ከሰረ፡፡ አሁን ሌላ ግማሽ ኪሎ ሽንኩርት እየከተፍኩ ነው። በዚያ በኩል ቆጥቡ፣ ቅበጥርሶ፣ ገለመሌ፣ ምናምን ይሉናል። እዚህ ለሳምንት ያልነው፣ ለዕለት ያልነው፣ ለወር ያልነው ወረት ሳይበላ እየተበላሸ ይደፋል። ወረት ይዘን የምንበላው ሳናጣ ፆም እንውላለን። ከዚህ በላይ እኔ ነጋዴ መሆን አለብኝ ተነካሁ ለማለት። ቤተሰብ አስተዳዳሪ ግለሰብ መሆኔ ብቻ የብሶት መታወቂያ አያሰጠኝም ማለት ነው?” ስላቸው ባሻዬ፣ ‹‹አንተና 2010 ዓ.ም. አያያዛችሁ አያምርም። ደግሞስ መብራት ብርቅ ነው እንዴ? ከሰል ተጠቀም፤›› ብለውኝ ሹልክ ብለው ወጡ። ‹ይቺ ናት አገሬ ይቺ ናት አገርሽ› አለ ሰውዬው። ወደ ኋላ እየተንሸራተቱ ጊዜን ወደ ፊት መቁጠር “ብርቅ ነው እንዴ?” እንዳልል፣ ከመንሸራተት በላይ የሚያዳልጠው በዝቶ እያስቆዘመን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከመቆዘም በላይ ደረት የሚያስጥለው አልበዛም? አሁንስ አልበዛም? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት