እነሆ መንገድ ከመሪ ወደ መገናኛ ልንጓዝ ነው። ‹‹ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቆጣጠር የውይይት መድረክ ተዘጋጀ፤›› ይላል የሬዲዮ ጋዜጠኛው። ‹‹ዝንት ዓለም ውይይት ዝንት ዓለም ስብሰባ! በስብሰባ ለእግረኛ ቅድሚያ ይሰጣል እንዴ? ወይስ ፍጥነት ተቆጣጥሮ ይሾፈራል? ሁሉም ችግር የሚፈታው በክትባትና በወሬ ይመስላቸዋል፤›› ይላሉ አንድ አዛውንት። ‹‹እና እርስዎ ምን መደረግ አለበት ነው የሚሉት?›› አላቸው ገና ተሳፍሮ አጠገባቸው የተቀመጠ ወጣት። ‹‹ዘመኑ የፍጥነትና የውድድር ነው እያልን ፍጥነትና ውድድርን ሁሉ ነገር ውስጥ ማስገባት መተው፡፡ ዴሞክራሲውም ቀስ ብሎ መምጣት ካለበት ቀስ ብሎ ይምጣ። ለራሱ ሁሉም አለቃ መሆን ሳይለምድ እንዳሻህ ቢባል ያው ወደኋላ አይሆንም?›› ብለው ብን ብን የሚለው ሳላቸው ያጣድፋቸው ጀመር።
ወያላው ወዲያ ወዲህ እየተሯሯጠ ይጮሃል። ሾፌሩ ሞተር እያሞቀ በሞባይል ስልኩ ያወራል። ‹‹እኔ ለትምህርት ቤት ክፈይ ብያት እኮ ነው እሷ የዓመቱ ነው ብላ ድግስ የደገሰችው? እንዴ እኔ ከማያስብልኝ ሰው ጋር እንዴት እኖራለሁ?›› ይላል። ‹‹እህ እና የሚካኤልን ድግስ ላትደግስ ኖሯል? እሱ ሰይፍ ታጣቂው ሲጠሩት የማይዘገይ ባይኖርልን ኑሮን ብቻችንን እንችለዋለን? ምን ይላል ይኼ?›› አዛውንቱ ከሳላቸው ጋር እየታገሉ። ሾፌሩ፣ ‹‹ብቻ ምከሩዋት እኔ በዚህ ኑሮ ቀኑን ሙሉ አንድ መቀመጫ ላይ ተቀምጬ በፀሐይ ስቀቀል እየዋልኩ፣ እሷ ከልጆችዋ በፊት የምታስቀድመው ነገር ካላት ልንግባባ አንችልም። ሲኖር ምንም አይደል፣ ከሌለ እኮ ሁሉን የሚያውቅ አምላክ እንደ ሰው አይደለም ለምን ይቀየማል?›› ብሎ ስልኩን ይዘጋል። ወያላው፣ ‹‹ሞልቷል!›› ብሎ በሩን ይከረችማል። ከሾፌሩ ጋር ሁለት ሴቶች፣ ከጀርባው አዛውንቱና ወጣቱ ተሰይመዋል። ከእነሱ ጀርባ እኔና አንዲት ወይዘሮ አለን። ከኋላችን አንድ ጎልማሳ ከተማሪ ኮረዳ ልጁ ጋር ተሰይሟል። መጨረሻ ወንበር አንዲት እናት አፍ የፈታች ሕፃን ልጇች ታቅፋ ከሦስት ወጣቶች ጋር ተጣበው ተሰይመዋል። ጉዟችን ተጀምሯል።
አዛውንቱና ወጣቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባብተው ጨዋታቸው ደርቷል። ‹‹እሱ ያልባረከው ኑሮ ምን ቢቆጠብለት፣ ቢታቀድለት ያዋጣ መስሎህ ነው? አይምሰልህ! የዘንድሮ ልጆች ለገንዘብ ብቻ እንጂ ለሃይማኖት፣ ለባህልና ለትውፊት ጉጉት የላችሁም። መስሏችሁ ነው. . .›› ይሉታል። ወጣቱ፣ ‹‹ኧረ እንደ እሱ አይደለም አባት! ፈጣሪ እኮ የብርና የወርቅ ችግር የለበትም። የእሱ ችግር የልብ ነው። ሰው ልቡን ከሰጠው ሌላ አይፈልግም እሱ። ደግሞ የቄሳሩንና የእግዜሩን መለየት ጥበበኝነት እንጂ ደንታ ቢስነት አይመስለኝም፤›› ብሎ ይሞግታቸዋል። ‹‹ተወኝ እስኪ! እናንተና ይኼ መንግሥት መቼም መልስ አታጡም። ምንም እንኳ መልስ ባይሆንም መልሳችሁ. . .›› ሲሉት ሳላቸው ጠናባቸው። ይኼን ጊዜ ወደ መጨረሻ ወንበር ወሬ ሰማንና ጆሯችንን ወደዚያ ተጣደ።
‹‹ሚሚዬ ስምሽ ማን ነው?›› አንደኛው ወጣት የታቀፈችዋን ሕፃን ያናግራታል። ‹‹አንጀሊና›› መለሰች ሚሚዬ እየተኮላተፈች። ‹‹እ?›› ልጁ ደገመና ጠየቃት። ‹‹ስምን ሆሊውድ ያወጣዋል’ ማለት መጀመራችን እኮ ነው፤›› ይላል አንደኛው ጓደኛው። ‹‹እስኪ ወደፊት ምን መሆን ነው የምትፈልጊው ንገሪኝ?›› እያባበለ በስሟ ቅስሙ የተሰበረው ወጣት በራዕይዋ ሊፅናና ሲጠይቃት ‹‹ሞዴል›› ብላ መለሰችለት። ወጣቱ ጥያቄውን ቢያቆም እንደሚሻል አምኖ ግንባሯን ሳመና ወደ ጓደኞቹ ዞረ። ‹‹አልሰማኋትም ምን አለች?›› አለው ጓደኛው። ‹‹አንተ ደግሞ ደህና ደህና ነገር አትሰማም! ሞዴል አለችህ፤›› አለው ሦስተኛው። ‹‹እሱንማ ሰምቻለሁ ግን ሞዴል ምን? አርሶ አደር? ተዋናይ? ነጋዴ? ሞዴል ምን?›› ሲል ዘንዶ ሊጎትት አጥብቆ ሲጠይቅ ጓደኛው ‘እረፍ’ አለው። ዘንድሮስ ተስፋም የሚደረግበት ነገር የተነጠቅን ነው የምንመስለው?
ሲኤምሲ አካባቢ ስንደርስ ጋቢና የተቀመጡት ሁለት ሴቶች ‹‹ወራጅ›› ብለው ወረዱ። ሁለቱም የለበሱት ቀሚስ እጅግ በጣም አጭር ስለነበር ሲወርዱም ሆነ ሲሳፈሩ የሚያያቸውን አስበርግገዋል። ወያላው፣ ‹‹ፓ! ኑሮዬ እንዲህ ሲኒማ ባይሆንልኝ ኖሮ በፓስቲና በሽሮ ብቻ እንዴት እገፋው ነበር?›› ሲል ሾፌሩን አናገረው። ሾፌሩ ግን የባለቤቱ ጉዳይ አዕምሮውን የተቆጣጠረው ይመስላል። አላናገረውም። ‹‹እናንተን እያየ በስንት ትግል ያገኘነውን እኩልነትና መብት ሲያቃልል የሚውለው ስንቱ ይሆን?›› አሉ አጠገቤ የተቀመጡት ወይዘሮ። ከጀርባችን ደግሞ ጎልማሳው ወደ ደረሰች ኮረዳ ልጁ አፍጥጦ፣ ‹‹ታያለሽ አንቺ እንደዚህ የለበስሽ ቀን አባት የለሽም እኔም ልጅ የለኝም፤›› ይላታል። ወዲያ ተጋላጭ አለባበስ በለበሱት ሴቶች ተተክታ የተሳፈረች እህት ጋቢና እየተመቻቸች፣ ‹‹እኛስ እንዲህ የፈለጋችሁትን አስቡ የሚል አለባበስ እየለበስን ወንዱ አይደለም መድፈር ዘልዝሎ ቢጠብሰን ይፈረድበታል? ፍትወት እኮ ደመነፍሳዊ ሆኖ ከእይታ እኮ ነው የሚጀምረው፤›› ብትለው ሾፌሩን፣ ከእንቅልፉ እንደቀሰቀሱት ሁሉ እየተደናበረ፣ ‹‹ምን አልሽኝ አልሰማሁሽም?›› ብሏት አረፈው።
‹‹በል ተወው! እናንተማ ምን አለባችሁ እንደ ልባችሁ የፈቀዳችሁትን ታስባላችሁ ታደርጋላችሁ። እኛ ሴቶች ነን እንጂ መግባባት አቅቶን መብትና ልቅነትን አግባብቶ ማለያየት ያቃተን፤›› ብላ በረጅሙ ተነፈሰች። ስለመደፈር ሲነሳ ወዲህ ደግሞ ጨዋታው ደርቷል። ‹‹ሰው ግን እንዴት ጨካኝ ሆኗል?›› አለች ልጅ የታቀፈችው እናት። ‹‹እኔስ ይኼን ስሰማ ሴት ልጅ መውለዴ ያሳስበኛል፤›› ብትል ጎልማሳው ዘወር ብሎ ‹‹አይምሰለሽ ልጅ በልጅነቱ ያስያስዙትና ያስተማሩትን አይረሳም። የራስን ኃላፊነት መወጣትና መከታተል እንጂ ከዚህ አልፎ ለሚሆነው በወለዱት ልጅ ፆታ ማሰብ አያስኬድም፤›› ብሏት ‘ወራጅ’ አለ። ታክሲያችን ስትቆም አዛውንቱ፣ ‹‹ጊዜው የሰይጣን ሆኖ እንጂ፣ እውነት ከአስተዳደግና ከሕግ አስከባሪዎች አቅም በላይ ሆኖ ነው ይኼን ሁሉ ጉድ የምንሰማው?›› ይላሉ። ሌላውም እንደ ራሱ አመለካከትና እምነት የሚጠይቀውን ይጠይቃል። ጎዳናው ጊዜን ያስተቻል፣ ጊዜ ደግሞ መልሶ ወደ እኛ ይጠቁማል!
ጉዟችን እንደ ቀጠለ ነው። በጎልማሳውና በልጁ ምትክ ሁለት ወጣቶች ገብተው ተሰይመዋል። ‹‹ኧረ እንኳን እግዚያብሔር አተረፈህ!›› ይላል አንደኛው። ‹‹በጣም እንጂ! እኔ አሁን እንኳን እንደ አህያ የምረገጥ፣ እንደ ትልቅ ሰው በጥፊ የምጠፈጠፍ ልጅ ነኝ? እ. . .›› ሲል ከፍተኛ ድብደባ እንደ ደረሰበት ወዲያው ይገልጽልናል። ‹‹ቆይ ግን ፀቡ በምን ተጀመረ? መቼም እዚህ አገር ሲጀመር ስብሰባና ውይይት የሚፈልግ ነገር ፀብና ጭፈራ ብቻ ነው›› አለ ወዳጁ። አጠገቤ የተቀመጡት ወይዘሮ፣ ‹‹እንዲያ! የዘንድሮ ምርጫ ደግሞ ከቅስቀሳው ስድቡ ብሶበታል፤›› ይሉኛል ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብለው። ምኑን ከምን አገናነኝተው ምርጫ እንዳደረሱት ግን አልገባኝም። ‹‹ይኼውልህ እኔ ሱቄን እየዘጋሁ ነው፤›› ተደብዳቢው ልጅ ታሪኩን በአጭሩ ይናዘዛል።
‹‹አላየኋቸውም! ዘወር ስል እከሌን ያሯሩጡታል። ‘ኧረ በፈጠራችሁ ምንም አቅም የሌለው ልጅ ነው ተውት!’ ብዬ ልገላግል ስገባ እኔን ይዘው እንካ ቅመስ። የእኔ ስም ተጠርቶ ሲጮህ የሰማው ታላቅ ወንድሜ ዘሎ ሲወጣ እሱንም ይዘው ቀጠቀጡት። የሚገርምህ እኮ ‘ፌንት’ ሠርቼ ወድቄ በእግሩ አንገቴን ረግጦ ድንጋይ ሊጭንብኝ ሲል እኮ ነው ሰው ያተረፈኝ፣›› ብሎ ሳይጨርስ፣ ‹‹ወይ ጉድ? ከሰው ጋር ነው የተጣላኸው ወይስ ከእንስሳ ጋር?›› ብለው አዛውንቱ ጠየቁት። ‹‹ምኑን አውቄ አባት? ሁሉም የተቀላቀለበት ዘመን አይደል!›› አላቸው። ወዲያው ትረካው ለመላው የታክሲዋ ታዳሚዎች ሆነና አረፈው። ‹‹ከዚያ ይኼንን ጆሮዬ አያችሁት? ስለተሰነጠቀ ሊሰፋ አንድ አንጋፋ ሆስፒታል ብሄድ ማደንዘዣ የሚባል ነገር የለም። ዶክተሩ ‘የማደንዘዣ ያለህ’ ቢል ማን ይስማው? ሆስፒታል የወሰዱኝ ሰዎች ሮጠው ሄደው ሁለት ማደንዘዣ ገዝተው አንዱን ሌላ ጊዜ እንዳትቸገር ብለው ሰጡት። ይኼውላችሁ እንዲህ የምታዩኝ በቸርነቱ ተርፌ እንጂ በሕግና በአፋጣኝ ሕክምና አይደለም፤›› ብሎ ፈገግ አሰኝቶን አበቃ። እሱ ቢያበቃም የእሱ ዕጣ በምን ሰዓት ለማናችን እንደምትወጣ የማናውቅ ተሳፋሪዎች በሐሳብ መወዝዘወዛችን አላበቃም። ጎበዝ? መገላገልም ብሎ ብሎ አላገላግል አለ እንዴ?
ወደ መዳረሻችን ነን። ‹‹አያድርስ እንዲያው ሰውን ግን ምን ነካው? መተዛዘን እንደዚህ ብርቅ ሊሆን ጫፍ ደረሰ?›› ስትል መጨረሻ ወንበር ላይ ልጇን የታቀፈች ሴት፣ ከተቀመጡ ወጣቶች አንዱ ድግሞ፣ ‹‹ልብ ብለን ካየነው እኮ በየአቅጣጫው የችግራችን መባባስ ተጠያቂው ተቋም ሳይሆን ሰው ነው፤›› አለ፡፡ ‹‹እንዴት?›› አለው ተደብዳቢው አገጋሚ። ‹‹የመልካም አስተዳደር ችግር የእኛው ባህሪ ችግር ነው። ተቋም የሰዎች ስብስብ ነው። ቀበሌና ክፍለ ከተማ ስትሄድ የሚያስተናግድህ ሰው ነው። ያውም ማሰብ ማመዛዘን የሚችል የሰው ልጅ። ሰው ለህሊናው ሲል እንኳን በክፉ ጊዜ ይተባበራል። ሰው ራሱን ችግር ውስጥ ከቶ የሚረዳዳ ፍጡርም ነው። በናዚ ጊዜ ብዙ ጀርመኖች አይሁዶችን ደብቀዋል። እኛ ለአንድ ጉዳይ አንዲት የወረቀት ሥራ ለማስፈጸም ፍዳ ስናፍስ ምን ይባላል? ሙስናውም እንዲያ ነው። ሰው ጠፋ ለሀቅ የሚታገል፡፡ ዴሞክራሲም ያለገደብ የሚሰፍነውና ትርጉም የሚኖረው እኮ መጀመሪያ ራሱን አክብሮ ሌሎችን የሚያከብር ሰው ሲታነፅ ነው፤›› ብሎ ዝም አለ። ወዲያው ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ከፈተው። እኛም ‘የሰው ያለህ!’ እያልን መገናኛ ላይ በሐሳብ ተገናኝተን በተግባር እየተለያየን በየፊናችን ነጎድን። ግን ሰው ሳይጠፋ ‹የሰው ያለህ› ማለትን ምን አመጣው? መልካም ጉዞ!