Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአገልግሎት አልባ የሕክምና መሣሪያዎች

አገልግሎት አልባ የሕክምና መሣሪያዎች

ቀን:

በምሕረት ሞገስና ታደሰ ገብረማርያም

በኢትዮጵያ የሚገኙ ሆስፒታሎች በተለይም በአዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለተለያዩ ሕመሞች መመርመሪያና ማከሚያ በሚያገለግሉ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች እየተደራጁ ነው፡፡ ዘመን ያመጣቸውን ሲቲስካንና ኤምአርአይ ጨምሮ የተለያዩ የመመርመሪያና የሕክምና መሣሪያዎችም በግልና በመንግሥት ሆስፒታሎች ይገኛሉ፡፡

በላቦራቶሪዎች ውስጥ በአንድ ጊዜ ከ80 በላይ የደም ምርመራ የሚያደርጉትን ጨምሮ በቀላሉ በሽታዎችን የሚለዩ ማሽኖች፣ የደም ግፊት መለኪያዎችና ሌሎችም ለቁጥር የሚታክቱ የሕክምና መሣሪያዎች ይገኛሉ፡፡

እነዚህ መሣሪያዎች  ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ ነው? በትክክል ይሠራሉስ? ብልሽት ሲያጋጥማቸው ማነው የሚጠግነው የሚለው ግን ለኢትዮጵያ የሕክምና ዘርፍ አሁንም ፈተና ነው፡፡

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሕክምና ተቋማትን የማስፋፋቱን፣ የሕክምና ተማሪዎችን ቁጥር የመጨመሩን ያህል ለሕክምና መሣሪያዎች ደኅንነት ከዚህ ቀደም ይሰጥ የነበረው ትኩረት እብዛም አልነበረም፡፡ በየሆስፒታሉና ጤና ተቋማቱ የሕክምና መሣሪያዎች ተበላሽተው መቀመጥ፣ ሕሙማንም በሽታቸውን የሚለይላቸውን መሣሪያ ፍለጋ ሲንከራተቱ የሚስተዋሉትም የሕክምና መሣሪያዎችን በአግባቡ የመጠቀም ክህሎትና ሲበላሹ የመጠገን አቅም ያለው በቂ ባለሙያ ባለመኖሩ ነው፡፡

የሁሉም ጤና ተቋማት እንቅፋት የሆነውን የሕክምና መሣሪያዎች ብልሽትና፣ ችግራቸውን አውቆ የመጠገን ክፍተት በተለይ በኢትዮጵያ ብርቅዬ የሆኑትንና በጥቁር አንበሰ ሆስፒታል ብቻ የሚገኙትን ሁለት የካንሰር ሕክምና ጨረር መሣሪያዎች ሲፈተን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ከካንሰር ሕሙማኑና  ሕክምና ፈላጊው ጋር የማይጣጣመው የካንሰር ሐኪሞችና ድጋፍ ሰጪ ሠረተኞች ቁጥር ላይ የጨረር ሕክምናው መሣሪያ እየተፈራረቀ መበላሸት ብዙ ታካሚዎችን ተስፋ ያስቆረጠ ነው፡፡ የሆስፒታሉ አካላትም በተደጋጋሚ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ቢጥሩም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማሽኑ የተበላሸበትን ምክንያት ማወቅ አልተቻለም ነበር፡፡

ለጨረር ሕክምና ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በሚመጡ የካንሰር ሕመማን በሚጨናነቀው የሆስፒታሉ የካንሰር ሕክምና ክፍልም፣ የተበሳጩ ታካሚዎችን ማየት፣ ብሶታቸውን ማዳመጥ፣ ከባለሙያ እግር ከእግር እየተከተሉ ሕመማቸው አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚፈልግ በመንገር የመታከም ጉጉታቸውን የሚገልጹም ጥቂት አይደሉም፡፡

ችግሩ ግን ከሐኪሞቹ አቅም በላይ ነው፡፡ ለወር ለሁለትና ሦስት ወራት ወረፋ ይዘው የጨረር ሕክምናውን ለማግኘት የሚጠባበቁ ሕሙማንም የጨረር ሕክምናውን ለማግኘት እንደጓጉ በዚያው ያሸልባሉ፡፡ ለዚህም ደግሞ የሕክምና ማሽኖቹ ሳይስተጓጎሉ ሁለቱም በአንድ ላይ መሥራት አለመቻላቸው እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡

የጨረሩ እንደ አብነት ተነሳ እንጂ ሌሎች የላቦራቶሪ ምርመራዎችን ለማድረግ የሚያግዙ መሣሪያዎች ተበላሽተው ተኝተው የሚታከሙትን ጨምሮ ብዙዎቹ ሕሙማን  ውጭ ወጥተው ተመርምረው ውጤት ይዘው የሚመጡበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ያለውም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ከሆስፒታሉ መሣሪያ ሳይታጣ በመበላሸቱ ብቻ ሕሙማን በሽታቸውን የሚያገኝላቸውን መሣሪያ ፍለጋ በከተማዋ ባሉ የግል ላቦራቶሪዎች ሲንከራተቱ ማየቱም የተለመደ ነው፡፡

ይህ ለምን ሆነ? ሲባል የሕክምና መሣሪያዎቹ መበላሸት፣ አዲስ እንደመጡ ፕሮግራም የሚያደርጋቸው ጠፍቶ መቀመጣቸውና በየጊዜው የሚያሻሽላቸው (Update) የሚያደርግ ባለሙያ አለመኖሩ ይጠቀሳል፡፡ የግል ሆስፒታሎች ቢሆኑም በሕክምና መሣሪያዎች ብልሽት የሚስተጓጎሉ ናቸው፡፡ የሕክምና መሣሪያዎች መበላሸታቸው ወይም ትክክለኛ ውጤት እየሰጡ ስለመሆናቸው ሳይታወቅላቸውም የሕክምና መረጃ የሚያዛቡበት ጊዜ ቀላል አይደለም፡፡

በሆስፒታሎችና በጤና ተቋማት ደግሞ ከሕክምና መሣሪያ አጠቃቀም ክፍተት፣ ወቅታዊ (Update) ካለማድረግ፣ ከዕውቀት ማነስ ጋር ተያይዘው ዘመናዊ የሚባሉ የሕከምና መሣሪያዎች ጭምር ያለአገልግሎት ተቀምጠው ይታያሉ፡፡ የተለያዩ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች ቢኖሩትም፣ በብልሽት አልያም በዕውቀት ክፍተት ምክንያት አገልግሎት የማይሰጡ የሕክምና መሣሪያዎች ከነበሩት የሕክምና ተቋማትም አንዱ አለርት ማዕከል ነው፡፡

የአለርት ማዕከል የሕክምና አገልግሎቱን እያሰፋና ዘመናዊ የሕክምና መሣሪዎችን እያስገባ ቢሆንም፣ በሆስፒታሉ ያለው ትልቁ ችግር የሕክምና መሣሪያዎቹን ጥቅም ላይ ማዋል መሆኑን የአለርት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መዘምር ከተማ ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡

እንደ አቶ መዘምር፣ በማዕከሉ በዕርዳታም ሆነ በግዢ የተለያዩ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች የሚገኙ ቢሆንም፣ ከአጠቃቀም፣ ጊዜያቸውን ከመጨረስ፣ ስለውጤታማነታቸው ማረጋገጥ ካለመቻልና ተጠግነው ሥራ ላይ ባለመዋላቸው አንዳንድ ጊዜ ቀዶ ሕክምና ይሰረዛል፡፡ ይኼ በታማሚዎች ላይ ከሚፈጥረው ቅሬታ በተጨማሪ የባለሙያዎች ተነሳሽነትን ይቀንሳል፡፡ በመሆኑም በሕክምና አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ብልሽት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ እንቅፋቶችን ለመቅረፍ በቅጥር ጊቢው የባዮ ሜዲካል ልቀት ማዕከል ከሁለት ወር በፊት አስመርቋል፡፡

ማዕከሉ ሲመረቅ ያነጋገርናቸው አቶ መዘምር እንዳሉት፣ የሕክምና መሣሪያዎችን የሚጠግን፣ ትክክለኛ የሕክምና ውጤት ስለመስጠታቸው የሚፈትሽና ለዘርፉ ባለሙያዎች የትግበራ ሥልጠና የሚሰጥ ሞዴል ማዕከል ነው፡፡

ማዕከሉ በየሆስፒታሉ የሚሠሩ ቴክኒሻኖችና ኢንጂነሮችም በየጊዜው በሚመጡ አዳዲስ መሣሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ ሥልጠና የሚያገኙበት ሲሆን፣ ማዕከሉ ከዚህ በፊት የሠለጠኑና በመሠልጠን ላይ ያሉትም መሣሪያዎችን እየነኩና እየሞከሩ ዳግም እንዲሠለጥኑ ዕድል የሚሰጥና በባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ዘርፍ ለልምምድ የሚሆኑ መማሪያ መሣሪያዎችን ክፍተትም በተወሰነ ደረጃ የሚያቃልል ይሆናል፡፡ ማዕከሉ ችግሩን በዚህ መልኩ ለማቃለል እየሠራ ቢሆንም ሌሎች ሆስፒታሎች ደግሞ በችግሩ ይፈተናሉ፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በልዩ ልዩ ምክንያት ለብልሽት የተዳረጉ የሕክምና መሣሪያዎችን ጠግኖ ለአገልገሎት ማዋሉ በእጅጉ አስቸጋሪና ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን የኮሌጁ የጤናው ዘርፍ ምክትል ፕሮቮስት ይናገራሉ፡፡

ምክትል ፕሮቮስቱ ዶ/ር ብርሃኔ ረዳኢ ከሪፖርተር ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ  እንደገለጹት፣ የሕክምና መሣሪያዎችን ጠግኖ ጥቅም ላይ ማዋሉ አስቸጋሪ እየሆነ ሊመጣ የቻለው በባዮሜዲካል ኢንጂነሮች እጥረት ምክንያት ነው፡፡

ይህ ጉዳይ አገር አቀፍ ችግር ቢሆንም በሕክምና ሥራ ላይ የሚያሳድረው ተግዳሮት በእጅጉ የከፋ መሆኑን ገልጸው፣ በየጊዜው ለብልሽት ከሚዳረጉትም መሣሪያዎች መካከል ኢንዶስኮፒና ራጅ የመሳሰሉት እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ገዜ ግን ሁለት ኩባውያን የባዮሜዲካል ኢንጅነሮች ተመድበው የጥገናውን ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙ፣ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ግን ዘለቀታዊ ሳይሆን ጊዜያዊ መፍትሔ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የሕክምና መሣሪያዎች በዕርዳታም ሆነ በሽያጭ የሚያቀርቡ ድርጅቶች የጥገና ማዕከልም አብረው እንዲያቋቁሙ በማድረግ ላይ መሆኑን አመልከተዋል፡፡ 

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የሕክምና ባለሙያ ደግሞ፣ በሁሉም የሕክምና ተቋማት የሕክምና መሣሪያዎች አስተዳደር ላይ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩንቨርሰቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኝ እንዳሉት፣ የሕክምና የላቦራቶሪ ዕቃዎች ብልሽትና የባዮሜዲካል ኢንጂነሮች እጥረት አገራዊና ሁሉም አተኩሮ ሊፈታው የሚገባ መሠረታዊ ችግር ነው፡፡

‹‹አንድ ትልቅ ማሽን ገዝተን ጥቅም ካልሰጠ ዋጋ የለውም፡፡ በሆስፒታላችን የካንሰር ሕክምና ሁለት ማሽኖች አሉ፡፡ ሆኖም ሁለቱም እኩል ሠርተው አያውቁም፡፡ በአንዴ የሚሠራው አንዱ ነው፤›› ያሉት ዶ/ር ዳዊት፣ ችግሩን ሲያጣሩም ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ሁለቱን ባንዴ ማንቀሳቀስ ስለማይችል መሆኑን መረዳታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ለብዙ ጊዜያት ችግሩ የማሽኑ ተደርጎ እንደነበር ቢታሰብም፣ ችግሩ የማሽኑ አልነበረም፡፡ ሆስፒታሉም ችግሩን የሚነገረው ሰው ከውጭ ከፍሎ ማምጣት ነበረበት፡፡ ላለፉት 18 ወራትም አንደኛው ማሽን ተበላሽቷል ተብሎ ነበር፡፡ ገንዘብ ተከፍሎ ባለሙያ ሲመጣ ግን ማሽኑ ችግር እንደሌለበት፣ ችግሩ የኤሌክትሪኩ አቅም ሁለቱን ማሽኖች ባንዴ ማስነሳት ስለማይቻል መሆኑ ታውቋል፡፡

እንደ ዶ/ር ዳዊት፣ ብቁ የባዮሜዲካል ኢንጂነር ቢኖር ችግሩን ለመፍታት  ሁለትና ሦስት ዓመት መጠበቅ አይጠበቅባቸውም ነበር፡፡

ይህን መሠረታዊ የጤናውን ዘርፍ ችግር ለመፍታት ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከኮሪያ መንግሥት ጋር በመተበበር የጥገና ማዕከላትን በተወሰኑ ሆስፒታሎች ለማቋቋም ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተመረጠ ሲሆን፣ በሚቀትሉ ስድስት ወራት ውስጥ የተሻለ የባዮ ሜዲካል አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ  ዳንኤል ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ በሚኒስቴሩ እንደ ዋና ችግር የተለየውም የሕክምና መሣሪያዎች አጠቃቀምና አያያዝ ጉድለት መኖሩ ነው፡፡

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር 13 የባዮሜዲካል ማዕከላት ማስገባቱንና ቁሳቁስ እየተከፋፈለ መሆኑን ጠቁመው፣ እነዚህ ሥራ ሲጀምሩ ለኅብረተሰቡ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችሉም ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ዳንኤል፣ በሕክምና መሣሪያዎች አጠቃቀም ላይ የሚታየው የባለሙያዎች የአቅም ክፍተት ሲሆን፣ ክፍተቱን ለመሙላትም የማዕከሎች መገንባት ወሳኝ ነው፡፡ በአገሪቱ የባዮሜዲከል ኢንጂነሮችና ቴክኒሻኖች ሥልጠና ቢሰጥም፣ ሠልጣኞቹ ከጨረሱ በኋላ የሚሠሩበት የተመቻቸ ሁኔታም አልነበረም፡፡ ሙያቸውንም ለማዳበር እንቅፋት ነበር፡፡

የሕክምና መሣሪያዎች ቴክኖሎጂ በየጊዜው እየተቀያየረ የሚሄድ በመሆኑ፣ አዳዲስ ማሽኖች በሚገቡበት ጊዜ የሚተገበር ሕክምና መሣሪያዎች አጠቃቀምና አያያዝ መመሪያ በፖሊሲ ደረጃ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ፖሊሲው ተግባራዊ ሲሆን፣ የሕክምና መሣሪያዎች ከመገዛታቸው በፊት ጀምሮ ጥገና እስከሚያገኙበትና እስከ አወጋገዱ ድረስ ያለውን በተደራጀ አግባብ የሚመራ ሲሆን፣ ይህም ቀጣይነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል፡፡

በኢትዮጵያ ሆስፒታል ትራንስፎርሜሽን ጋይድ ላይን ውስጥም አሠራሮች ቀጣይነት እንዲኖራቸው፣ ሆስፒታሎች በየተቋማቸው ያሉትን ባዮሜዲካል ባለሙያዎች የማደራጀት፣ በጀት የመያዝ፣ አስፈላጊውን ሥልጠናና ለባዮሜዲካል ማዕከሎች ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት እንዳላቸው ተቀምጧል፡፡

የሕክምና መሣሪያዎች ሲበላሹ ማወቅ ቢቻልም፣ የተበላሸውን ክፍል ለመቀየር ተለዋጭ ዕቃ  አለመኖር ሌላው የተለየ ችግር ሲሆን፣ እያንዳንዱ አስመጪ የሕክምና መሣሪያዎችን በሚያስገባበት ጊዜ በቂ የመለዋወጫ ዕቃና ወርክሾፕ እንዲኖርም ፖሊሲው የሚያስገድድ ይሆናል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...