በጽጌሕይወት መብራቱ
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለእልህ አስጨራሽ ፈተናዎች ሳይንበረከኩ ማንኛውንም መስዋዕትነት በመክፈል የተነሱለትን ዓላማ ከግቡ የማድረስ ችሎታ ያላቸውን ልጆች ማፍራት የሚችል ማኅበረሰብ በማንኛውም ዘርፍ ውጤታማ ነው፡፡ የማኅበራዊ ለውጡ ባቡር ከትክክለኛ ሐዲዱ ሳይወጣ እንዲጓዝ የሚያደርግ አቅም ያላቸው እነዚህ ፋና ወጊዎች ወይም ተምሳሌቶች፣ የተፈለገውን ስኬት ማስመዝገብ የሚችሉ በራሳቸው ብርታት ብቻ ግን አይሆንም፡፡ ለበጎ ተግባራቸውና ለጥንካሬያቸው ዕውቅና እየሰጠ በማበረታታትና ጥበቃ በማድረግ ኅብረተሰቡ ከጎናቸው ሲሠለፍ ነው፡፡ ይኼን የሚፈጽመውም በራሱ ይሁንታ በቆመና መንግሥት በሚባለው የጋራ ተቋም አማካይነት ነው፡፡ መንግሥት ራሱ በተምሳሌት ዜጎች መዋቀር ይኖርበታል፡፡ ይኼ ካልሆነ ግን እንኳን ተምሳሌቶችን ሊያፈራ ቀርቶ፣ ያሉትንም በሰበብ አስባቡ እየኮረኮመ አንገታቸውን እንዲደፉ፣ ያለበለዚያም ጨርሶ እንዲጠፉ ከማድረግ ላይመለስ ይችላል፡፡ ይኼኔ ነው እንግዲህ ጣጣው!
የአንድ አገር መንግሥት በወሬኞችና በአሉባልተኞች ከተተበተበ እንኳን ለፋና ወጊዎች ዜጎች ይቅርና ለአገርና ለሕዝቡ የሚተርፈው ጦስ የበዛ ነው፡፡ ምክንያቱም ወሬኞች ሁሉም ነገራቸው በወሬ ተቋጥሮ በወሬ የሚገመድ፣ በወሬ ተተርትሮ በመጨረሻም በወሬ የሚበተን ነውና፡፡ በዚህ መንደር ውስጥ የሚገኙ የኅብረተሰቡ ፋና ወጊዎች ተደፍቀው መልካም ስማቸው ሲጎድፍ፣ ደማቅ ምሥላቸው ሲደበዝዝ፣ ለጊዜውም ቢሆን ባይተዋሮች ይሆናሉ፡፡ ተምሳሌቶች ግን ራሳቸው እውነት ናቸውና ተስፋ ከማይቆረጥ ፅናታቸውና ጥንካሬያቸው የተነሳ፣ ታግለው ከማሸነፍ የሚበግራቸው አይኖርም፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ምን እየሠሩ እንደሆነ ሕዝቡና መንግሥት ገሀዱን እንዲያውቁት ለማድረግ ከታተሩ ከተቻለ ከመንግሥት፣ ይኼ ካልሆነ ግን እውነተኛውን ፍርድ ከሕዝባቸው ያገኛሉ፡፡ እግረ መንገዳቸውም ታሪካቸውን ለኋለኞች ያቆያሉ፡፡ እንግዲህ ከዚህ በመነሳት ነው በጋምቤላ ክልል በግብርና ልማት ተሰማርተው የሚገኙ ዜጎች ተምሳሌታዊነታቸውን እያሳዩ ያሉት፡፡ በምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑ፣ እየከፈሉት የመጡት መስዋዕትነት እስከ ምን ድረስ እንደሆነ፣ የወሬ ሳይሆን የተግባርና የልማት ወገኖች እውነቱን እንዲያውቁላቸው ያህል ነው ይህንን የትረካ ጽሑፍ የማቀርበው፡፡
ያልታሰበው ፈተና
ተደጋጋሚ የልማት ጥሪ ታቀርብ ወደነበረችው ጋምቤላ በግብርና ኢንቨስትመንት ለመሰማራት የመጡ ዜጎች የእርሻ ሥራ ፈታኝነት በሚገባ የሚያውቁ መሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በሑመራ፣ በመተማና በቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች ያገኙትን ተሞክሮ እንዳለ ጋምቤላ ላይ እንደሚተገብሩት ምንም ጥርጥር አልነበራቸውም፡፡ የበጀትና የሥነ ልቦና ዝግጅታቸው ትክክል እንዳልሆነ የተረዱት ከዚያ ወዲህ ነበር፡፡ እስከ ሁለት ሺሕ ብር በሚደርስ ወጪ አንድ ሔክታር መሬት የማይሞከር ሆኖ በሰው ኃይል በቀን አሥር ሔክታር ሲያፀዳ የለመደ ሁሉ አንድ ሔክታር መሬት በአንድ መቶ ሰው እንኳን ማፅዳት አዳገተው፡፡ ጭራሹንም በሰው ኃይል መሬት ማፅዳት የማይታሰብ መሆኑን ያረጋገጠ ሁሉ እንቅስቃሴዎቹን በጋምቤልኛ በመቃኘት አስተካክሎ ሥራውን ቀጠለ፡፡
ከጫካው ብዛትና ከዛፉ ግዝፈት የተነሳ እጅግ የሚከብደው የመሬት ፅዳት ተግባር የሚበላው የገንዘብ መጠን፣ እንዲሁም የሚፈጀው ጊዜ መርዘም ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነባቸው አንዳንዶቹ ሥራውን እያቋረጡ ወጡ፡፡ እጃቸውን መስጠት ያልፈቀዱት ግን ያለ የሌለ አቅማቸውን በመጠቀም ለማመን የሚከብዱ ማሳዎችን እያንጣለሉ ማሳየት ችለዋል፡፡ ይህም ከእነሱ በኋላ ለሚመጡት የሚያበረታና ወኔ የሚለግስ በመሆኑ ልማቱ በየአቅጣጫው እንዲጧጧፍ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ መንገድ፣ የስልክና የንፁህ ውኃ አቅርቦት በሌለበት በጥቅጥቅ ጫካዎች የተሰማሩ ዜጎች በተለያዩ ነፍሳት ይነደፋሉ፡፡ በተለያዩ በሽታዎች ይጠቃሉ፡፡ የሕክምና አገልግሎት የሚገኘውም እስከ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ ነው፡፡ ይኼንን ጫና መቋቋም ያልቻሉ በተለይ ከመሀል አገር የሄዱ ባለሙያዎች ሥራቸውን እየተው ይመለሳሉ፡፡ በቅርብ እነሱን መተካት የሚችል የሰው ኃይል ለማግኘት አይታሰብም፡፡ የእርሻው ልማት ደረጃ በደረጃ ሲቀጥል ችግሮችም ደረጃ በደረጃ እየሰፉ ይቀጥላሉ፡፡ የማሽነሪዎች መበላሸት፣ የቴክኒሽያንና የመለዋወጫ አቅርቦት ማግኘት የሚቻለው ወደ ጅማ ወይም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ነው፡፡ ነዳጅም እንዲሁ፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ወደ ጋምቤላ ሂዱ ሲሏቸው ወደ ሞት ሂዱ የተባሉ ይመስላቸዋል፡፡ ከስንት ድርድር በኋላ ለመሄድ ሲወስኑ የሚያስከፍሉት ዋጋ ‹አይጣል› ነው፡፡ የባንክ አገልግሎትን ብንወስድ የሚሻለው ካለመኖር ጋር ሲነፃፀር ብቻ ነው፡፡ በጋምቤላ ለእርሻ ልማት የሚወጣው ወጪ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ሲነፃፀር እስከ አሥር እጥፍ የሚደርስ ልዩነት እንደሚያሳይ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ ከዚህ ጫና ውጪ የእርሻ ሥራ መሠረታዊ ባህርይ የሚያመጣቸውን ፈተናዎች እንዴት መጋፈጥ እንዳለበት ማንም ይገነዘባል፡፡ ለዚህ ትግል ራሱን አዘጋጅቶ የመጣ አካል ለሌላ ትግል ሲዳረግ ግን ሁኔታዎች ውስብስብ ይሆኑበታል፡፡
ከጋምቤላ እስከ ጎጃምና ወላይታ በመሄድ ለአረምና ለአጨዳ የሚያስፈልጉ የጉልበት ሠራተኞችን ሰብስቦ ያላመጣ ሰው ለአንድ ዓመት ሙሉ የለፋበት ሥራው ገደል ገባ ማለት ነው፡፡ በሚሊዮን ብሮች ወጪ አድርጎ ያመጣውን በመቶዎች የሚቆጠር ሠራተኛ አንድ ሳምንት እንኳን ሳይሠራለት በሆነ ምክንያት እንደ ‹ንብ መንጋ› ተጠቅልሎ እየተመመ ጥሎ ሲሄድ፣ በዓይኑ በብረቱ ሲመለከት እንዴት እንደሚያሳዝን የደረሰበት ይመልሰዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ አበሳ በኋላ የተመረተ ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለመቅረብ በጋምቤላ ክልል በእያንዳንዱ ቀበሌ በተዘረጉ ኬላዎች የተጠየቀው ሁሉ እየተከፈለበት አዲስ አበባ ይደርሳል፡፡ በነገራችን ላይ ጋምቤላና ኬላ እጅግ በጣም የሚገርም ፍቅር ነው ያላቸው፡፡ በአዲስ አበባ የመገበያያ ቦታዎች በኢትዮጵያ ምርት ገበያም ሳይቀር ከጋምቤላ ለሚመጡ ምርቶች የሚፈጠረው ቃና የሚገርም ነው፡፡ ማንኛውም ዓይነት ምርት የመጣው ከጋምቤላ መሆኑ ከታወቀ፣ የሚቆረጥለት ዋጋ ከትክክለኛው የገበያ ዋጋ በእጥፍ ተቀንሶ ነው፡፡ ወደየትም ተይዞ ቢዞር ሁሉም ጋ የሚገኘው ምላሽ ተመሳሳይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ነጋዴዎች በአካልና በንግድ ፈቃድ ቢለያዩም በልባቸው አንድ መሆናቸውን የምንገነዘበው ያኔ ነው፡፡ ስንት አበሳ ዓይተህ ያመረትከው የሕይወትህን ልዋጭ እነሱ በጠየቁት ዋጋ ሸጠህ ሳይሆን፣ ጥለህ ከመሄድ ውጪ ምንም ዓይነት አማራጭ ታጣለህ፡፡ አንዱ ግን ሠርቶላቸዋል፡፡ ከጋምቤላ ጭኖ ያመጣውን ማሾ እንዲገዙት ሲጠይቃቸው በኩንታል ስድስት መቶ ብር እንደሚገዙት ይገልጹለታል፡፡ በየቦታው ይዞት ገዢ በማፈላለግ ቢዞርም ለውጥ አላገኘም፡፡ ለካ አንዱ ነጋዴ ያየውን ለሁሉም ማሠራጨት የተለመደ አሠራራቸው በመሆኑ ነበር ሚስጥሩ፡፡
በዚህ ይበሳጭና ከአዲስ አበባ ወደ ሸዋሮቢት ጭኖት ይሄዳል፡፡ እዚያ አንዱን ኩንታል በአንድ ሺሕ ስምንት መቶ ብር ይሸጠዋል፡፡ ማሾውን የገዛው ሰው ደግሞ ከሸዋሮቢት ወደ አዲስ አበባ አምጥቶ በሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ብር ሒሳብ ሲሸጠው፣ ይኼ ሁሉ ሲሆን ያ ሰው አተኩሮ እያየ ይታዘብ ነበር፡፡ እሱ ማለት ጋምቤላ ካሉ ባይተዋር ባለሀብቶች አንዱ ነው፡፡
‹‹ይኼ እኮ የእኛ ክልል ነው››
ጋምቤላ የሚለው ስም ሲነሳ አስደንጋጭና አስፈሪ ስሜት ከመቅፅበት በህሊናቸው ብልጭ የሚልባቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም በክልሉ በተለያየ ወቅት፣ በተለያየ ምክንያት፣ የብዙ ዜጎች ሕይወት እንደጠፋ በሰፊው ይወራል፡፡ በክልሉ ረዘም ካለ ጊዜ ጀምሮ በመኖር ላይ ያሉ ወገኖችን በፀጥታ ችግር ምክንያት ተሸክመውት ያለፉትን ሰቆቃ ለማስታወስ እንኳን ሲዘገንናቸው ይታያል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለውን ሁኔታ የእኔ ቢጤ ሲያማርረው ሲሰሙ ‹‹ኧረ እባካችሁ ግፍ አትናገሩ፤›› በማለት ነው የሚቃወሙት፡፡ የሚያወሩት ነገር ሲሰማ በራሱ በጣም ይዘገንናል፡፡ ያለፈው እንደ አስተላለፉ ቢያልፍም በአሁኑ ወቅት ያለው የፀጥታ ሁኔታ ያለው ፈታኝነት ምን ያህል እንደሆነ በውጫዊና በውስጣዊው መንስዔዎቹ ለማሳየት ልሞክር፡፡
በክልሉ ላለው የፀጥታ ችግር እንደ ምክንያት ከሚታዩት አንዱ በክልሉ ያሉ አንዳንድ የፀጥታ ኃይሎች የሚያሳዩት ከመስመር የወጣ ተግባር ነው፡፡ የክልሉ ነባር ተወላጆች ለልማቱ ያላቸው አመለካከት በጎ ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት በግብርናም ሆነ በሌላ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ከሌላ አካባቢ መጥተው ለተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያሳዩት አዎንታዊ አመለካከት አንዱ መገለጫ ነው፡፡ በተለይ ‹መሬትህንና ሀብትህን እየተዘረፍክ ነው› ብለው በተደጋጋሚ ቅስቀሳ ሲያላዝኑ ለነበሩ ፀረ ልማት ኃይሎች በዝምታ ሳይሆን፣ በተግባር የሰጣቸው የተቃውሞ ምላሽ ዓይነተኛ ማሳያም ነው፡፡ ተንኮልም፣ ቅንነትም፣ በተለይም ውሸት የሚባል ክፉ በሽታ እንደማይነካቸው የተመሠከረላቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይኼን የመሰለ ማንነት፣ ባህልና ሥነ ምግባር ካላቸው ሕዝቦች አብራክ የተገኙ አንዳንድ አወቅንና ተማርን የሚሉ የክልሉ ተወላጆችና የፀጥታ ኃይሎች ግን ሁኔታቸው መልካም አይደለም፡፡ በሕዝብና በመንግሥት የተሰጣቸውን ሕግንና ሰላምን የማስከበር ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው፣ ሕገወጥነትን የሚከተሉ የፀጥታ አስከባሪ ተብዬዎችን ማየት አሳዛኝ ነው፡፡ ወንጀልን አስቀድሞ መከላከል፣ ወንጀል ሲፈምም ወንጀለኞችን ተከታትሎ ወደ ሕግ የማቅረብ ዝንባሌያቸው ከሁኔታዎች ጋር የሚወሰን ነው፡፡ ገዳይ ሳይሆን ሟች፣ ዘራፊ ሳይሆን ተዘራፊ፣ በዳይ ሳይሆን ተበዳይ ወንጀለኛ ሊሆን ሁሉ ይችላል፡፡
በተለይም በኢንቨስትመንት በተሰማሩ ዜጎች ላይ የሚያሳዩት ጥላቻና የሚያሳድሩት ጫና ቀላል አይደለም፡፡ ዶሮ ይዞ ከማሰር ይልቅ አንድን ባለሀብት በሰደፍ ጀርባ ጀርባውን እየደሰቁ ወደ እስር ቤት መወርወር ለእነሱ ቀላል ነው፡፡ የሥነ ሥርዓትና የመብት ጥያቄ ማቅረብ እንደ ድፍረት ብቻ ሳይሆን ‹‹ኢንቨስተር ጠግቧል››፣ ‹ለመሆኑ ማንን ተማምኖ ነው? ይኼ እኮ የእኛ ክልል ነው፣ የትግራይ ወይም የአማራ፣ የኦሮሞ ወይም የደቡብ ክልል መሰለህ እንዴ?› . . . ወዘተ የሚሉ ብሔርንና ማንነትን መሠረት ባደረጉ ጥያቄዎች ወከባው ይቀጥላል፡፡ አስፈላጊ ከሆነ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ማባረር እንደሚችሉ ሲያስጠነቅቁ ኩራት እንጂ ይሉንታ ወይም ተጠያቂነት እንደሚኖርባቸው ማሰብ አይፈልጉም፡፡ አስጨንቀውና ረጋግጠው ደብድበው የመግዛት ፍላጎታቸው ከብረት የጠነከረ ነው፡፡ የሰው እጅና ኪስ ላይ ዓይናቸውን ከተከሉ መንቀያ የላቸውም፡፡ ከኪስ በረከት ሲቋደሱ ግን የፈላው ደማቸው የሚቀዘቅዝበት ፍጥነት ይገርማል፡፡ ከአውሬነታቸው ተመልሰው ለማዳ ይሆኑና እያፅናኑ ለእነሱ ደስ የሚል ፈገግታ ለአንተ ግን የሚያበሽቅ እየለገሱ፣ አጋርነታቸውንም እየገለጹ ከእስር ሲያሰናብቱህ እንደ ማሽላ ውስጥህ እየተቃጠለ የውሸት ሳቅህን እየገለፈጥክ ወደ ሥራህ መሄድ ነው፡፡
በተለይ ደግሞ ኢንቨስተር ላይ አቤቱታ አቅራቢ ከሄደላቸው የደስታቸውን ስሜት ለመቆጣጠር እንኳን ለመደበቅ አይሞክሩም፡፡ ያለበት ድረስ ሄደው እያዳፉ አምጥተው እነሱ የሚወስኑትን መቀበል እስኪችል ማጎር ነው፡፡ ማከራከርና ማሟገት ለእነሱ ከንቱ ድካም ነው፡፡ ኢንቨስተር ሁሌም ወንጀለኛ፣ ሁሌም አጭበርባሪ፣ ውሸታም ነውና፡፡ የእነሱን ሐሳብ መስማት አይቻልም የሚል አንቀጽ ሳኖራቸው አይቀርም፡፡ ማንኛውም አቤቱታና የዕርዳታ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ፈጥነው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የፈጣንነታቸው ምንጭ የደፈረሰ ፀጥታን ለማረጋጋት ወይም ወንጀለኛን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ቀዳሚ ሙያዊ ግዴታቸውን መሆኑ ቢሆን ኖሮ ዕፁብ ድንቅ ነበር፡፡ ይኼ ሙያዊ ግዴታ ሁለተኛ ደረጃ ነው፡፡ የፈጣንነታቸው ቀዳሚ ምንጭ ግን የሚከፈላቸው የውሎ አበል ነው፡፡ አቤቱታና የድረሱልኝ ጥያቄ ይዞ ሄዶ ፖሊሶች ተመድበውለት ይዞ የሄደ ሰው፣ እነሱ የጠየቁትን ገንዘብ መጠን ያለምንም ማንገራገር የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ግማሽ ሰዓትም ይሁን ሩብ ሰዓት ለእንቅስቃሴ ካዋሉ የውሎ አበል ማግኘት አለባቸው፡፡ ያለገንዘብ አገልግሎት የሚሰጡ በቢሯቸው ወይም በመሥሪያ ቤታቸው ቅጥር ግቢ ብቻ ነው፡፡ ይህ የውሎ አበል ጉዳይ ውስኖችን ብቻ ሳይሆን፣ የክልሉ ፖሊሶች በሁሉም ቦታ የሚፈጽሙት ተግባር ነው፡፡ መጥሪያ ወረቀት ለማድረስ ለሄዱበት እንኳን ክፍያ ይጠይቃሉ፡፡ በተለይ የሚያስከፍሉት የገንዘብ መጠን በጣም የበዛ ስለሚሆን፣ አማራጭ ያጣ ካልሆነ በቀር ወደ ፖሊስ ሄዶ የዕርዳታ አገልግሎት የሚጠይቅ የኅብረተሰብ ክፍል መጠኑ ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም በአካባቢው የወንጀል ድርጊት እንዳይንቀሳቀስ የራሱን ድርሻ ማበርከቱን መረዳት ቀላል ነው፡፡
የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሥሩ ያሉ የፀጥታ አስከባሪ አካላት የአገራችንንና የክልላችንን ሕገ መንግሥት ማስከበርና ኅብረተሰቡን ማገልገል የሚችሉት ሕዝቡና መንግሥት ከሚከፍሏቸው ደመወዝ ሌላ፣ ከአገልግሎት ፈላጊዎች ተጨማሪ ጥቅም እንዲያገኙ ወስኖላቸው ይሁን አይሁን ዕውቀቱ ባይኖረኝም፣ ድርጊቱ እንደሚፈጸም አያውቅም ብዬ ግን አንገቴ ቢቆረጥም ማመን አልችልም፡፡ እነዚህ መላውን የክልሉን ፀጥታ አስከባሪ አካላት የማይወክሉ ምግባረ ብልሹዎች በየጊዜው በሚካሄዱ ግምገማዎች እየተለዩ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው በተደጋጋሚ ዓይተናል፡፡ ጉዳዩ የሚያሳስበው ግን ብዙ ጥፋት ካደረሱ በኋላ መሆኑና በእነሱ እግር ተተክተው የእነሱን ተግባር ደግመው የሚፈጽሙ የአልጋ ወራሾቻቸው ቁጥር እየቀነሰ አለመታየቱ ነው፡፡ ከጋምቤላ ከውስጧ ስለሚመነጨው የፀጥታ ተግዳሮት ይህን ካልኩ ከውጭ ወደሚመጣባት ደግሞ ልሻገር፡፡
ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል
በጋምቤላ ክልል በርካቶች ንፁኃን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ዕልቂት እንዲከሰት ምክንያት በመሆን ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው ክስተት የሚመነጨው፣ ከጋምቤላ ክልል ዙሪያ ከሚገኙ ጎረቤቶች ነው፡፡ በዓለማችን ከሚገኙ አደገኛ ቦታዎች አንዱ በሆነው በምሥራቅ አፍሪካ፣ ይባስ ብሎም ከምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ ዓለምን እያስቸገረ የሚገኘው የደቡብ ሱዳን አዋሳኝ መሆኗ፣ በዙሪያዋ ያሉ ሕዝቦች በተደራጀ መንግሥታዊ ሥርዓት የማይተዳደሩ መሆናቸው፣ ወዘተ በእነዚህ ምክንያቶች በየወቅቱ የሚያጋጥማት የፀጥታ ችግር ነበልባሉ እየገረፏት ስትሰቃይ ኖራለች፡፡ አሁንም እየተለበለበች እንደሆነ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ ከዚህ አደገኛ ሁኔታ የምትወጣበት ዘመን መቼ ይሆን? ብለን ተስፋ ለማድረግ እንኳን ራሱ ተስፋው አይመጣልንም፡፡ ‹ከእሾህ የተጠጋ ቁልቋል ዘለዓለሙን እንዳለቀሰ ይኖራል› የሚለውን አባባል የፈጠረ ሰውዬ አትጠራጠሩ የጋምቤላን ሁኔታ በማጤኑ ነው፡፡ ይኼ ሐሳብ የመጣለት ወሩን በማላስታውሰው በ2008 ዓ.ም. የሙርሌ ታጣቂዎች ጋምቤላ ላይ የፈጸሙትን ድርጊት የታዘበ ሁሉ በደቡብ ሱዳን የተረጋጋ መንግሥት ባለመኖሩ የተፈጠሩ አዲስ ክስተት ሊመስለው ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በሙርሌ ላይ የወሰደው ዕርምጃ ችግሩን እስከ መቼውም አዳፍኖታል ብሎ ሊያምን ይችላል፡፡ አለማወቅ ነውና አይገርምም፡፡ በአካባቢው ያሉ ብሔረሰቦች ከተፈጠሩበት አሊያም በአካባቢው መኖር ከጀመሩበት ዘመን ጀምሮ የሚፈጸም የጀግንነት ማረጋገጫና የሀብት ማከማቻ የጀብዱ ተግባር ነው፡፡ እናም መቼም ሊቆም እንደሚችል ሁሉ አይታወቅም፡፡ በተለይም የሙርሌና የቡሜ ጎሳዎች የሕፃናትና የከብት ዘረፋ የሚያካሂዱት በተደራጀና በጣም ዘመናዊ በሚባሉ የጦር መሣሪያዎች እየተደገፉ በመሆኑ አስፈሪነቱና አውዳሚነቱ የገዘፈ ነው፡፡ በጋምቤላና በአካባቢው ሰላም የሚገኘው በክረምት ወራት ነው፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ ወንዞችም ይሞላሉ፣ ሜዳና ኮረብታዎች በረዣዥም ሳር ይሸፈናሉ፡፡ እስከዚያው ድረስ በእያንዳንዷ ዕለት በሰላም ውሎ ለማደር ምንም የሚያስተማምን ነገር የለም፡፡ በጋምቤላ ደቡባዊ ክፍል በዲማና አካባቢዋ ያለው የፀጥታ ችግር ምናልባትም በትክክል ተጠንቶ ውጤቱ ቢታይ፣ በዓለማችን በየቀኑ ብዙ ሰው ከሚሞትባቸው ቦታዎች የመጀመርያውን ደረጃ እንደሚይዝ ጥርጥር አይኖርም፡፡ የጋምቤላዋ ዲማ ወረዳ ቅድም ከጠቀስናቸው የሙርሌና የቡሜ ጎሳዎች ሌላ የበርካቶች የጥፋት ዱላ ክረምት ከበጋ እየቀጠቀጣት የምትኖር ናት፡፡ በወረዳዋ ከፍተኛ የወርቅ ሀብት አለ፡፡ ይኼ ያልሰበሰበው የአዳም ዘር የለም፡፡ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር ያለውና የሕዝብ እንቅስቃሴ መጠን የሌለው ዘረፋና ግድያ በየዕለቱ ያለማቋረጥ የሚከናወንበት አካባቢ ነው፡፡ እንዲያውም ከዲማ ከተማ በስተሰሜን ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ አንድ ቦታ አለ፡፡ በጫካ የተከበበ ሸጥና ዘዋራ መንገድ ያለበት ነው፡፡ ስሙ ቄራ ይባላል፡፡ በርካታ ሰዎች እየታረዱ የተጣሉበት ቦታ ስለሆነ ሕዝቡ ይህን ስም ሰጥቶታል፡፡ አሁን ይህ አካባቢ ወደ ዘመናዊ እርሻነት እየተቀየረ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በዚያ አካባቢ ማንኛውም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የሚደረገው በቅፍለትና በአጀብ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ መንቀሳቀስ ከቶ አይታሰብም፡፡ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመው በሕግ የሚፈለጉ በርካታ ወንጀለኞች ለመደበቂያነት የሚመርጡት የጋምቤላ ክልልን እንደሆነ በሰፊው ይነገራል፡፡ ከስማቸው ጀምሮ ማንነታቸውን በመቀየር ሰላማዊ መስለው እንደሚኖሩ የሚታሙት አካላት አድፍጠው መኖር ብቻ የሚበቃቸው አይመስሉም፡፡ ወንጀል የመሥራት ሱሳቸውን ለመወጣት አንዳንድ ለወንጀል ቅርብ ሆነው የሚያገኟቸውን የአካባቢ ተወላጆች በመመልመል፣ የግድያና የዘረፋ ልምዳቸውን በመጠቀም አብረውም በመሳተፍ የሰላማዊ ዜጎችን ሀብት ይዘርፋሉ፣ ሕይወት ያጠፋሉ፡፡ ይህም በተለያየ መድረኮች ሳይቀር በየጊዜው ሲገለጽ መስማት የተለመደ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ግን የመጣ ለውጥ አላየንም፡፡ ይኼን ጽሑፍ በማዘጋጀት ላይ እያለሁ ምን ሰማሁ መሰላችሁ? በግብፅ አሰማሪነት አሥራ ስድስት ሺሕ የሠለጠነ ጦር በደቡብ ሱዳን በኩል ወደ ጋምቤላ ገብቷል የሚል ወሬ ነው የሰማሁት፡፡ ወሬውን ለማመንም ላለማመንም ተቸገርኩ፡፡ በኋላ ግን ማመን ይሻለኛል አልኩ ለራሴ፡፡ ምክንያቱም ግብፅም ግብፅ፣ ጋምቤላም ጋምቤላ ናቸዋ፡፡ ቆይቶ ደግሞ በአንድ ወቅት በኡጋንዳ ይንቀሳቀስ የነበረው ሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ የተባለው የሽምቅ ተዋጊ ቡድን መሪ ለነበረው ጆሴፍ ኮኒ ከኡጋንዳ ብትባረር ወዴት ትሄዳለህ? የሚል ጥያቄ ሲቀርብበት፣ ‹‹ምን ችግር አለ ወደ ጋምቤላ እሄዳለሁ፤›› ብሎ የሰጠው መልስ ታወሰኝና በእምነቴ ፀናሁ፡፡
በነገራችን ላይ በጋምቤላ ክልል ከሚገኙ ብሔረሰቦች አንዱ የሆነው አኝዋ ብሔረሰብ እጅግ በሚገርም ሁኔታ ለእንስሳት ዕርባታ አመቺ የሆነ አካባቢ እያለው፣ እስካሁን ወደዚህ ጉዳይ አልገባም፡፡ የሚገባም አይመስልም፡፡ ምክንያቱም እንኳን እንስሳት ለማርባትና ለራሱ ሰላም ውሎ ሰላም ስለመግባቱ እርግጠኛ አይደለም፡፡ የወለዳቸው ልጆቹን አሳድጎ ለወግ ማዕረግ ሲደርሱ ስለማየቱ ምንም ዓይነት ዋስትና የለውም፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ከረዥሙ በአጭሩ ይህን የመሰለ እውነታ ባለበት ክልል ነው እንግዲህ ባለሀብቶች ወደ ጋምቤላ ዘምተው በግብርና ኢንቨስትመንት ሥራ የተዘፈቁት፡፡ እንኳን ከማንኛውም የመገናኛ አውታር በጣም ርቆ በየጫካው የተበተነን ቀርቶ፣ ራሱ የሚያስተዳድራቸውን በየከተማው የሚኖሩ ሕዝቦችን ሰላምና ደኅንነት በተገቢው መንገድ ማስከበር ያልቻለ መንግሥት ባለበት ሁኔታ ነው ልማት በጋምቤላ እየተፋፋመ ያለው፡፡
የደርግ አገዛዝ
ባለሀብቶች ከየትኛውም የዓለም ክፍል ቢነሱም፣ በየትኛውም የኢንቨስትመንት ዘርፍ ከመሰማራታቸው በፊት የሚያስቀምጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ልዩነት የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ኢንቨስትመንት በባህርይው ዓለም አቀፋዊ ነውና፡፡ የፖለቲካ መረጋጋት፣ ኢንቨስትመንት ፖሊሲና ማበረታቻዎች፣ የቢሮክራሲው የአፈጻጸም ብቃት እስከ ተከሳሽነትና ቁርጠኝነት፣ እንዲሁም የሕግ የበላይነት መከበር የመሳሰሉትን ሁኔታዎች ሳያጠኑና ሳይፈትሹ ዘው ብለው ውሳኔ ላይ አይደርሱም፡፡ ምክንያቱም በኢንቨስትመንት የሚሰማራ አካል ንዋይ ብቻ ሳይሆን በአካዳሚካዊ ዕውቀት፣ በፖለቲካዊ ግንዛቤ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፋዊ ተሞክሮ የተሻለ ብቃት እንደሚኖረው አጠያያቂ ስለማይሆን ነው፡፡ ይህን ኃይል ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚፈልግ አገርም ሆነ ክልል የተሻለ አቅምና ዝግጅት ሊኖረው የግድ ነው፡፡ የሁለቱ አካላት አቅም መመጣጠን ከሌለበት ግን የሚገኘው ውጤት ዕድገት ሳይሆን ውደቀት ይሆናል፡፡ በጋምቤላ የታየው ይኼው ነው፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ የሆነውን የመልማት አጀንዳ ወደ ክልሉ ለማስገባት የተደረገው ጥረት ‹‹በኩን ከመሃገርከ›› ዓይነት ስሜት እንጂ በተጠናና በተደራጀ መንገድ በቂ ዝግጅት ተደርጎበት አልተገባም፡፡ የተለያዩ የማስተግበሪያ ማዕቀፎች ሳይዘጋጁ የክልሉን ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ብቃት ባለው የሰው ኃይል ሳይደራጅ፣ መዋቅሩም እስከ ወረዳ ሳይዘረጋ ነው፡፡ በደመ ነፍስ እየተሠራ የመጣው አለ ከተባለም የአከራይና የተከራይን መብትና ግዴታን ከተወሰኑ ሐሳቦች ጋር ያያያዘ የመሬት መረካከቢያ የውል ሰነድ ነው፡፡ ይህ ሰነድ የክልሉ መንግሥትና ባለሀብቱ የገቡትን ውል ከመብትና ከግዴታ ጋር ተፈራርሙበት በፍትሕ ቢሮ ተመዝግቦ ፀድቋል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይም መንግሥትን ወክለው የተፈራረሙበት የወረዳ ባለሥልጣናት አያከብሩትም፣ አይገዙለትም፡፡ በአንድ መሬት ከተለያዩ ባለሀብቶች ጋር ውል ይፈራረማሉ፡፡ በሰነድ ላይ የተቀመጡትን ሕጎች እንኳን ለመተግበር ለማስታወስ ጊዜ የላቸውም፡፡ እንኳንስ ከበድ ያሉ የፖሊሲና የስትራቴጂ ማብራሪያ ይቅርና ራሳቸው የፈረሙበትንና በእጃቸው ላይ ከምትገኘው ትንሽ ሰነድ ላይ ያሉትን ሕጋዊ እሴቶች መሠረት ያደረገ ሐሳብና ጥያቄ ማቅረብ ከንቱ ድካም ነው፡፡ እንዲያውም ትክክለኛ የሆነውን ሕጋዊ ነገር ለማስረዳት መሞከር ማለት ባለሥልጣንን እንደ መናቅና እንደ መዳፈር ሁሉ ያስቆጥራል፡፡ ምክንያቱም ወዲህም የተከበሩ ገዢዎች፣ ወዲያም ዕውቀታቸው ሞልቶ የፈሰሰባቸው ናቸውና፡፡
በሕጋዊ አሠራርና በሕግ የበላይነት መመራትና መተዳደር የለመዱና የሕግ የበላይነትን ተማምነው የመጡ ዜጎች ጉዳያቸው በግለሰቦች መልካም ፈቃድ እግር ሥር መውደቁን ሲመለከቱ ብቻቸውን እያወሩ መሄድ ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ላይ ርህራሔ የፈጠረባት ከማትመስለው የጋምቤላ ፀሐይ የሚወረወረው ቃጠሎ ሲቀበላቸው ጭንቅላታቸው ምን እንደሚሆን ጭንቅላታቸው ራሱ ይወቀው፡፡ ኢንቨስተሩ በሕጋዊ መንገድ ከመንግሥት ተረክቦ፣ የሰው ዘር ሽታ እየናፈቀው ከአደገኛ የአራዊት መንጋ ጋር እየተጋፋ፣ ቀና ብሎ ሰማይን ለማየት እንኳን በማይፈቅድ ጫካ ውስጥ ገብቶ ለማመን የሚከብድ ገንዘብ እየከሰከሰ፣ ከቆራጥነት በዘለለ በጭካኔ በራሱ ላይ ወስኖ ልማት እያጣደፈ እያለ ከመብረቅም በላይ የሚያስደነግጥ ጩኸት የያዘ ደብዳቤ ይደርሰዋል፡፡ ‹‹እየሠራኸው ያለውን ሥራ አቋርጠህ በአስቸኳይ ሪፖርት እንድታደርግ!›› የሚል፡፡ የጨጓራ በሽታ ወይም የደም ግፊት ያልነበረው ጤነኛ ሰው፣ ለእነዚህ በሽታዎች እንደሚጋለጥ ካሰብን የነበረበት ምን ሊሆን እንደሚችል ምን እንበለው?
ከማንኛውም ይዞታ ነፃ መሆኑን አረጋግጦ የሰጠ የመንግሥት አካል እንደገና ከሌላ ጋር ያከራክራል፡፡ ቀምቶ ከኋላ ለሰጠው አካል ሊወሰን ሁሉ ይችላል፡፡ ሠራተኞች ማቴሪያሎች፣ ማሽነሪዎች ጫካ ውስጥ እንደተዘፈዘፉ ወደ ሌላ አተካሮ መግባት በረከት ይሆናል፡፡ ሰነዶችን ሁሉ ታቅፎ መንከራተት ነው፡፡ አንዱ የሰጠውን ውሳኔ ሌላው ሲያፈርሰው አዳዲሱ ያልሠራው የአርሰናል ቅሪላ ሆኖ መባዘን ብቻ፡፡ በወረዳው የሚጋጥመው ይኼ ሁሉ ችግር መነሻው የግብርና ኢንቨስትመንት ማስፈጸሚያ አሠራሮች በበቂ ሁኔታ አለመቀረፃቸው እንዳለ ሆኖ፣ ከባድ የሚባሉ ሕግና ደንቦችን ተግባራዊ ለማድረግ እንኳን የገነገነ የአቅም ማነስ በሰፊው መኖሩ ነው፡፡ ይህ ችግር በወረዳ ደረጃ ብቻ የሚከሰት ቢሆን ኖሮ እንደ መማፅናኛ ሊቆጠር ይችል ነበር፡፡ የሚያሳዝነው የአቅምና የአመለካከት ችግሩ እስከ ዞንና ክልል የሚዘልቅ መሆኑ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ራሱን በራሱ የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው ክልላዊ መንግሥት፣ ለደላሎችና ለሕገወጦች እጁን ሰጥቶ የአገር መነጋገሪያ የሆነበት ምክንያት ከዚህ ይመነጫል፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ አንድ ደስ የሚል ነገርም አለ፡፡ የኢንቨስትመንት ሥራው በሚካሄድበት አካባቢ ከሚኖሩ ማኅበረሰቦች ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላቸው ባለሀብቶች፣ በትልቁ የመንግሥት አካል በደል ሲደርስባቸው ዝም ብለው አለማየታቸው ነው፡፡ ተወካዮቻቸውን በመላክ በወረዳቸውና በአጋዣቸው ኢንቨስተር ላይ የሚፈጸመውን በደል ፊት ለፊት በመቃወም መፍትሔ እንዲሰጠው ሲያደርጉ በተደጋጋሚ ዓይተናል፡፡ ይኼን የሚገርም መልካም ተግባር ሳይመሰክሩ ማለፍ የበሉበትን ወጭት መስበር ይሆናል፡፡
በጋምቤላ የግብርና ልማት የተሰማሩ ዜጎች የልማቱ ተፈጥሯዊ ባህሪይ ከሚያመጣቸው ፈተናዎች ጋር መታገሉ ሳያንሳቸው፣ ሌሎች ወገብ የሚያጎብጡ አበሳዎች የመሸከም ጣጣ የገጠማቸው ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ብቻ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በዘረኝነትና በጥላቻ በተበረዘ የተበላሸ ፖለቲካዊ አመለካከት የተለከፉ በርካታ ግለሰቦች በክልሉ በብዛት አሉ፡፡ እነዚህ አውቀናል፣ ተምረናል የሚሉ ሰዎች በክልሉ የመንግሥት መዋቅር ተሰግስገው ከክልሉ ሕዝብና ከመንግሥት ዓላማና እምነት ውጪ ‹‹ሐበሻ›› የሚሉት መጤ ላይ በአጠቃላይ፣ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሠማሩ ዜጎች ላይ ደግሞ በተለየ መንገድ ጥላቻቸውን በግልጽ በማንፀባረቅ ከአስተዳደራዊ በደል እስከ ሰብዓዊ መብት ረገጣ ተግባር ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ የልማት ኃይሎች የሚፈጽሙትን መልካም ተግባር ያጣጥላሉ፡፡ ኢንቨስተሮችን በማስገደድ ሕጋዊ ያልሆኑና ከአቅም በላይ የሆኑ ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ ያደርጋሉ፡፡ ኢንቨስተሮች ያመረቱት ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ በወቅቱ እንዳይቀርብ የተለያዩ አክሳሪ ዘዴዎችን እየዘረጉ ማጉላላት ይፈጽማሉ፡፡
በሆነ ወቅት ባዶ እጅ አስቀርተው ሊባረሩ እንደሚችሉ ይዝታሉ፡፡ በውኃ ቀጠነ ዜጎችን ወደ እስር ቤት ይወረውራሉ፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢንቨስተሮቸን ማዋከብና ማስጨነቅ የተጠመዱ ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያዊነት ያላቸውን ጥላቻ እንኳን መደበቅ አይችሉም፡፡ አጋጣሚ ቢያገኙ ሌላ ቀውስ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም፡፡ ምስኪኑ ኅብረተሰብ ክፍተት ሊፈጥርላቸው እንደማይችሉ መሆኑ ነው ደግነቱ፡፡ በክልሉ ያለውን መንግሥታዊ አስተዳደር ሁኔታ የዘመናዊነት ጎዳና ጫፍ መርገጥ ይቅርና አቅጣጫው በየት እንደሆነ ፍለጋ የመግባት ዝንባሌ ያለውም አይመስልም፡፡ ረጋግጦና አስጨንቆ የመግዛት ጥማታቸውን እስከሚያረኩ ጊዜ የሚፈጅባቸው አምባገነን ግለሰቦች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ አመራር ለመስጠት ጥረት የሚያደርጉ የክልሉ ተወላጆች፣ በአምባገነኖቹ እየተዋጡ ድምፃቸው እንደማይሰማ እንዲያውም አድርባይ እየተባሉ እንደሚገመገሙ ይነገራል፡፡
ምርቃት
ጋምቤላ ክልል ላይ እኮ ሁሉም ነገር የሚፈጸመው በጉልበት ነው የልማት ሥራ ዘመቻው በማስገደድ ነው፣ ስብሰባ በማስገደድ ነው፣ መዋጮ በማስገደድ ነው፣ ሰላማዊ ሠልፍ፣ ባዛርና የንግድ ትርዒት፣ ወዘተ በማስፈራራትና በማስገደድ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ከማስፈራራት እስከ ማሰር ሄዶ ሄዶ ይጠናቀቃል፡፡ በውይይት መድረክ ከተገልጋይ ጋር ተመካክሮና ተነጋግሮ፣ ባለድርሻ አካላትን አሳትፎና አሳምኖ መምራት ሲተገበር አይታይም፡፡ ሌላው ይቅርና የክልሉ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እየሆነ ባለው በግብርና ኢንቨስትመንት ከተሰማሩ ዜጎች ጋር እንኳን ከወረዳ እስከ ክልል ባሉት እርከኖች፣ በአምስትና በስድስት ዓመታት ውስጥ አንድም ጊዜ የመወያየት መድረክ ተዘጋጅቶ አያውቅም፡፡ ‹‹የባንኮች ገንዘብ ተዘርፎ . . .›› የሚለው አሉባልታ ከፈጠረው መደናበር ማግሥት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ከክልሉ ኢንቨስተሮች ማኅበር አመራር አባላት ጋር ታኅሳስ 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ሐሳብ የመለዋወጥ ሙከራ ከማድረጋቸው በቀር ሌላ ሙከራ ተድርጎ አላየንም፡፡ የክልሉን የግብርና ልማት ችግሮች ለመፍታትና ልማቱን ለማቀላጠፍ የሚያስችሉ ድጋፎች እንኳን በክልሉ በፌዴራል መንግሥቱ እንኳን ሲሞከር አላየንም፡፡ የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑትን አካላት ወደ ጎን እየተው የተለያዩ ውሳኔዎችን በትዕዛዝ መልክ ያወርዳሉ፡፡ ይህም ባለሀብቶችን ለእንግልትና ለምሬት እየዳረገ ነው፡፡
ከባለሀብቶቹ ጋር በተገቢው ሁኔታ ውይይትና መግባባት ሳይደረግበት በባለሀብቶች ላይ የተጫነው የመሬት ኪራይ ዋጋ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ለመወያየት ቢሞከርም በደፈናው አካሄድ ወደ ተግባር በመግባቱና በሕግና በሥርዓት ሊመራ ባለመቻሉ ከፍተኛ ቅሬታን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ የሕጋዊ አሠራር ጥያቄ ሲቀርብም የሚሰማ አካል ባለመገኘቱ፣ ይህንን ጽሑፍ እያዘጋጀሁ ባለሁበት ጊዜ ከዲማ እስከ ላሪ በየጫካው ለልማት የተሰማሩ ዜጎች እየተለቀሙ ወደ እስር ቤት እየተወረወሩ ነበር፡፡ በተለይም ጉዳዩ የማይመለከታቸው ተቀጣሪ ሠራተኞችን በመያዝ ለእስራት፣ ለድብደባና ለእንግልት መዳረጋቸው በጣም ያበሳጫል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የራሱን ህልውና ያረጋገጠ ክልል በሕግ የመመራት፣ የሕግ የበላይነትን የማስፈን ግዴታ ይኖርበታል፡፡ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በሚገባ ማክበር ይጠበቅበታል፡፡ ይህንን ያልዳሰሰ የክልሉ የጥልቅ ተሃድሶው ግምገማ ተካሂዶ ከሆነ ውጤቱ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› ከመሆን አያልፍም፡፡
መሸኛ
የጋምቤላ የግብርና ኢንቨስትመንት በአሁኑ ጊዜ የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ የበቃው ከላይ በመጠኑም ቢሆን ለመግለጽ በሞካከርኳቸው እውነታዎች ተጋፍጦና እያሸነፈም ነው፡፡ ማንም ሊገዛው ይቅርና ሊሰማው የሚዘገንን ፈተናና ውጣ ውረድን ለመሻገር በበቁ ጠንካራ የልማታችን ተምሳሌት ዜጎች አሁንም በጥንካሬያቸው አሉ፡፡ በርካታ ጀግኖች ደግሞ ከልማት ሥራቸው ጋር እንደተጣበቁ በአረመኔ ወንጀለኞች ገጀራና ጥይት እየተመቱ ደማቸው በጋምቤላ ጫካዎች ፈሶ ቀርቷል፡፡ አስከሬኖቻቸውም በአቡጀዲ እየተጠቀለሉ ወደየመጡበት አካባቢ ተሸኝቷል፡፡ ከዚህ ይሻላሉ የሚባሉትን የተለያየ የአካል ጉዳተኝነት አጋጥሟቸዋል፡፡ በተሟላ ሁኔታ ይዘውት የገቡት የሰውነታቸው አካል በየጫካው ተቆራርጦ ወድቆባቸው የተረፋቸውን ይዘው እየቀጠሉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የልማት ተምሳሌት ዜጎች ላይ ግፍ ከፈጸሙ ወንጀለኞች አንድም እንኳን ወደ ሕግ ቀርበው አለመታየቱ ዳግም ሌላው አስገራሚ ሁኔታ ነው፡፡
ዕድሜ ዘመናቸውን ጥረው ግረው ያፈሩትን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘባቸውን በወንበዴዎች ተዘርፈዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ሳይበቃ የዘር ልዩነት እየተደረገባቸው ሰብዓዊ መብታቸው እየተረገጠና ክብራቸው እየተገፋ የሕግ የበላይነት እንደናፈቃቸው አሁንም እየታገሉ ነው፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግሥት አካላት ድረስ ምን ሆናችሁ? ምን ገጠማችሁ? ምን እንርዳችሁ? የሚላቸው የመንግሥት አካል ሳያገኙ እዚህ ደርሰዋል፡፡ አንዱና ትልቁ ረዳታቸው የነበረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ነበር፡፡ እሱም የፖለቲከኞች ቁማር ቤት የሆነ ይመስላል፡፡ ይህንን የመሰለ ተጋድሎ እየፈጸሙ ያሉ ፋና ወጊ ዜጎች ተግባራቸውም፣ ራሳቸውም የሚሠሩበት አካባቢም ባይተዋር ሆነው የሚቀጥሉበት ዘመን እስከ መቼ እንደሆነ ባይታወቅም እነሱ ግን በብሔር፣ በቋንቋ፣ በዘርና በሃይማኖት ሳይለያዩ በአንድ የልማት ቋንቋ ብቻ እየተነጋገሩ እዚህ እያደረሱት እንደመጡ፣ ክፉውንም ደጉንም በአንድነት እየተጋፈጡ ተምሳሌትነታቸውን በወሬ ሳይሆን በተግባር ማሳየታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ማዕበሉ ፀጥ ሲልና ሁሉም ነገር ወደ ልቦናው ሲመለስ እንዳሁኑ ሳይሆን ተሸላሚዎች መሆናቸው አይቀርም፡፡ ለማንኛውም ማሰማመሪያ ቀለም ሳይቀባባ፣ ከማጥላላት ስሜት ሳይመነጭ፣ በተጨባጭ እየሄደ ያለውን ኑሮ፣ እየተቻለ የመጣውን ሸክም፣ እየተገፋ ያለውን ተራራ፣ ሳላባዛና ሳላንዛዛ ያቀረብኩትን ይኼን ጽሑፍ በዚህ አጠናቅቃለሁ፡፡ ደህና ሁኑ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡