Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ስም አልባው ጥላ ቢሱ አገር ወዳድ

ትኩስ ፅሁፎች

ይህች የኔ አገር ነች፣ የተወለድኩባት፤

ይህን የማይል ሰው ነፍሱ የሞተበት በቁሙ ሙውት፤

ከቶ ይገኝ ይሆን የዚህ ሰው ዓይነት? እውን?

ልቡ በናፍቆት ነዶ ያልከሰለ፣ ከተሰደደበት ባይተዋርነት፤

ባዕድ ጠረፍ ለቆ ሲያስታውስ አገሩን ኮቴውም ሲያመራ ሲያስብ ወዳገሩ፣

አለ ብላችሁ ነው ያልተጨነቀላት የዚህ ዓይነት ኩሩ?

እንዲህ ያለ ካለም፣ ብሉ ደህና አርጋችሁ ታዘቡት አደራ፤

እሱን የሚያሞግስ አዝማሪም አይኖርም የሚይሽሞነሙነው ለሱ የሚራራ፤

ሹመቱም ቢበዛ፣ ዝናውም ቢያኮራው ፉከራው ቢንጣጣ፤

ያሰኘውን ያህል ሃብቱም ገደብ ቢያጣ፤

መጠሪያው ሹመቱ በዝቶ ቢትረፈረፍ፤

ገንዘቡም ቢበዛ በኃይሉም ቢመካ በትምክህት ቢንሳፈፍ፤

ይህ ስንኩል ወራዳ ራስ ወዳድ ፍጡር፤ በቁመናው ሳለ፤

ዝናውን ያጣታል እጥፍ ሞት ሲሞትም፣ ወዲያው ይወርዳታል

ወደ እርኩሲቷ አፈር ወደመነጨባት ወዳዋረዳት፤

ያኔ ይወርዳታል ግብአተ መሬቱን፡፡

  • በሰር ዋልተር ስኮት ስድ ትርጉም በዳዊት ዘኪሮስ

****

‹‹የነፍስ ምግብ››

አንድ ሊቅ ሰው ‹‹እኔ ጠንካራ ሠራተኛ ነው አእምሮዬ ሲደነዝዝ ቴኒስ በመጫወት እደሰታለሁ ኀዘኔን ልረሳው እንድችል ያደረገኝ ግን የተዋቡ ሙዚቆችን መስማት ነው፡፡›› አለ በእርግጥም በሰውና በዓለሙ መሃከል ፍጹም ሰላም ሰጭ ሁኖ የሚያስታርቀው የዕርቅ መሥዋዕት ጣዕም ያለው ዘፈንና ሙዚቃ ቃና ነው፡፡

ውብ ድምጽ ያላቸው ወፎች በረሃ ሃገራቸው ነው፡፡ ቃና ባለው ዜማ ከተዋበ ድምፃቸው ጋራ ሲዘምሩ ግን በረሃውን ገነት ያደርጉታል፡፡ እንዳዘነም ልብ የነበረውን ምድረ በዳ የገነት ያህል ሊለውጡት ችሎታ ሲኖራቸው አዳኞች አይተዋል፡፡ እንዲሁም የላባው ውበት ሊያኮራው የሚችል የቁራ አሞራ ደግሞ በዜማውና በድምጹ ክፋት እንደገነት ያማረችውን አገር በረሃ ያደርጋታል፡፡ ሰውም በሚኖርበት ርስቱ ላይ እንዲሁ ነው፡፡ የተዋጣ ቅያስ ባላቸው መንገዶች መጓዝ አይታው ሁሉ ደስ ያሰኘዋል፡፡

አበበቦችም በተተከሉበት ቦታ መጠለል አዲስ ስሜትና ዕረፍት ይሰጠዋል፡፡ ቅርፁ እጅግ አምሮ በታነፀ ቤት መኖርም ይመቸዋል፡፡ በሰገነት መቀመጥም እጅግ ክብር ያለው ሆኖ ያገኘዋል፡፡ ነገር ግን የነፍሰን አሥራው በማንቀሳቀስ ሰውን ደስ ሊያሰኘው የሚችል ጣዕም ያለው ሙዚቃና ባህል ያለው ዘፈን ባይኖር የማንኛውም የሚታይ ውበት ሁሉ ግምቱ አባይ ይሆናል፡፡

ተመስገን ገብሬ ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› (ኀዳር 1935)

*****

‹‹ሐሞት ሲሞት ፖለቲከኛ ይኮናል››

‘ደብርዬ’ ደብሪቱ (ታላቅ እህታቸው እንደሚጠሩአቸው) ‘ረቂቅ’ ሴት ናቸው (ዘንድሮ ሰው ‘ክፉ’ አይባልም)፡፡

አበበች የሥልጣን፣ የጉልበት ችሎታ መጠኑ ገደቡ የት እንደሚደርስ መገመት ይከብዳታል፡፡ በቀጣፊነቱ የሚኮራ ጉልበታም ብቻ እንደሆነ በወ/ሮ ደብሪቱ ይገባታል፡፡

‹‹በይ እረዳሻለሁ›› አሏት፡፡

ነገሩም ሕመሙም አበሳጭቷት ተነጫነጨች፡፡

‹‹እንዴ? ምን ልሁን ነው … ጥጋብ እኮ ነው እናንተዬ›› አሉ፡፡

ወደ ሐያ የሚሆኑ የሽንኩርት እራሶች መክተፍ ነበረባት፡፡ ከማቀዝቀዣ የወጣ የበሬ ሽንጥ ሥጋ መክተፊያው እንጨት ላይ ቀይ የሕፃን ልጅ ሹራብ መስሎ ወድቆአል፡፡ የተባ ቢላ መሐሉ ላይ ተጋድሞ፡፡ ቢላውና ሹራቡ ሽርክ ይመስላሉ፡፡ ፍቅርኛ ነገሮች ምናምን …

‹‹ስልክ ላድርግ መጣሁ›› ብለው ወጡ ደብሪቱ፡፡

ሥራ የሚያመልጡበት ጥበባቸው ረቂቅ ነው፡፡ እንደ ባህላችንም ነው፡፡ ዛሬ የመሥራት አቅም ሲጠፋ፣ ሐሞት ሲሞት ፖለቲከኛ ይኮናል፡፡ ይቀላል፡፡ ማላገጥ ሕግና ዓላማ ይሰጠዋል፡፡ ዓላማ ሳይደርስ ተመሃል ጎዳና እያቦኩ ቢቀርም … በሌላ እያሳበቡ መውደቅ ነው፡፡

‘ስልክ ልደውል’ ይሉና እንግዲህ ለሁለት ሰዓት ያህል ይጠፋሉ፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ ፈሳቸውን እየጠጣ ያ አልጋ አለማነጠሱ ደብሪቱ እራሳቸውንም ይገርማቸዋል፡፡ ጌትነትን ካልተኙበት ምኑ ጌትነት ሆነ፡፡ እመቤትነትም፡፡

ልጃቸው እንኳን አንድ ቀን አፏ ተስቶት ብትተቻቸው ‘አንቺም አልጋሽ የቢሮ ወንበር ነው’ ብለው ጆሮዋን ሲገርፏት እንደ ቀንድ አውጣ ተሰብስባ የሽሙጥና የኩርፊያ ልጋጓን ከመጐተት በስተቀር ቆማ አልመለሰችላቸውም፡፡ ማንንም ሰው ዝም የማሰኘት ችሎታ አላቸው፡፡

‹‹በል አንተ›› ብለው ሳይጠቁሙት ወሬ የሚጀምረውን ምሳሌ ጠቅሰው ‘መናገርን’ እስኪረግም ይወቁታል፡፡ መልካም ለመሆን ከፈለጉ ደግሞ የወደቀ ምራቅ ይመልሳሉ፣ ግመል ያሰክራሉ የአንድን የሰው ፀባይ የማያልቅ የሚቃረን የሚፋቀር ጐን ይሰጡታል፡፡ ‘ድንቅነት’ በእሳቸው ምላስ ሺሕ ፊት አላት … ‘ርግማን’ እልፍ ፊት አላት፡፡

እና ስልክ ለመደወል ቢጠፉ ለአካባቢው ሆነ ለማንም አይገርምም፡፡ የሚበቃ ምክንያት አላቸው፡፡ ባይኖርም ይሰጣሉ፡፡ ከሰጡ ደግሞ መቀበል ድንቅ ነው፡፡

አበባ ሥጋውን አመቻችታ ለመቁረጥ መስመር ስትፈልግ ልስላሴውና ቅዝቃዜው ማረካት፡፡ ቁርስዋንም ስላልበላች ቁርጥ ለመሞከር የድልህ ዕቃ አውጥታ ትንሽ ድልህ መክተፊያው ጣውላ ላይ ጠብ አድርጋ እየከተፈች አልፎ አልፎ ጥሬ ሥጋ እየዋጠች ሥራዋን ቀጠለች፡፡ ራስ ምታቱ ግን ኦ! ኦ! ያው ነው፡፡ ሻሽዋን አጠንክራ አናቷ ዙሪያ መጠምጠሙ ነው በትንሹም ቢሆን ያዋጣት፡፡

ስልክ መደወያ ቦታው በደብሪቱ የፈጠራ ችሎታ የሚወሰን ስለሆነ፣ ጭን የመሰለ ሰውነታቸውን ተሸክመው ማድ ቤት ሲገቡ መጀመሪያ ያዩት ግራ ጐኑ ላይ ቡግንጅ ያበቀለ የመሰለውን የአበባን ፊት ነው፡፡ ይሔ ቡግንጅ ደግሞ እንደ አናሳ ፍጡር ይነቃነቃል፡፡ ደማቸው ፈላ፡፡

‹‹ለራስሽ ደገስሽው?››

ቢላውን ቀምተው ቃጡባት ‹‹አንገቷን ማለት ነው›› አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ተደራሲያቸው ባይታይም፡፡ በነጠላ አይናገሩም ሲበሽቁ … የጐዳቸው አንድ ሰው ተከታይ አለው፤ እና ‹‹እናንተን ምን ማድረግ ይሻላል?›› ይላሉ … እሳቸውም ተከታይ አላቸው ግን አማራጭ ብዜቱን ገለልተኛ በግምት የሚመጠን ያደርጉታል፡፡

‹‹ምን ቢያደርጓቸው ይሻላል … ሴት ደረቅ እንጀራ አነሳት? … ቢበሉት ከቂጥ በላይ አይሆን … ‘ቂጣም ያሰኛል’›› አሉ፡፡

  • አዳም ረታ ‹‹ሕማማትና በገና›› (2004)

*******

ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን

ከጥንት ጀምሮ በቃል ሲነገር የሚኖረውን የአባቶቻችንን ተረት ብንመለከተው ብዙ የሚጠቅም ምክር እናገኝበታለን፡፡

በአርእስቱ እንደተነገረው ክፉ ሥራ መሥራት ጉዳቱ ለሠሪው ነው፡፡ ንብ ሌላውን አጠቃሁ ስትል በመርዟ ትነድፋለች፡፡ እሷም ይህን ክፋተ ከሠራች በኋላ አንድ ደቂቃ ሳትቆይ ትሞታለች፡፡ የእሳት ራትም እንዲሁ መብራቱን ለማጥፋት ስትሞክር ተቃጥላ ራሷ ትጠፋለች፡፡ ትንኝ ሰው ዓይን ለማወክ ትገባና ሕይወቷን አጥታ ተጎትታ ትወጣለች፡፡ እንክርዳድን የዘራ እንክርዳድን ያመርታል ክፉ የሠራም ሰው በክፋቱ ይጠፋል፡፡ በሰው የሚድነው በምነቱና በቅንነቱ ብቻ ነው፡፡

አያሌው ተሰማ ዘብሔረ ጎጃም የካቲት 20 ቀን 1935 ዓ.ም.

********                                                                   

ውይይት በሀብቴ አባ መላ

ከጦር ምርኮኛነት ተነስተው ለከፍተኛው ወታደራዊና ፖለቲካዊ መሪነት በበቁት ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ላይ፣ ቅዳሜ ግንቦት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው በትራኮን ሕንፃ ላይ ውይይት ይካሄዳል፡፡

“ሐሳብን በሐሳብ መፈተን” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው ወርኃዊው መድረክ  በታሪክ ምሁርና ተመራማሪ ባሕሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) ተዘጋጅቶ ለአንባቢያን የቀረበው “ሀብቴ አባ መላ ከጦር ምርኮኛነት እስከ አገር መሪነት” ለተሰኘው የታሪክ መጽሐፍ መነሻ ሐሳቡ የሚያቀርቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ብርሃኑ ደቦጭ ናቸው፡፡

ከውይይቱ በተጓዳኝ ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ቤተ መጻሕፍት ማደራጃና መገልገያ እንዲሆኑ በማሰብ ለሚቀጥሉት ተከታታይ ሦስት ወራት የመጻሕፍት ማሰባሰብና የመለገስ ፕሮግራም መጀመሩን አስተባባሪው አቶ በፍቅሩ ዳኛቸው ገልጸዋል፡፡

ሊትማን ቡክስ፣ ክብሩ መጽሐፍ እና እነሆ መጻሕፍት በጋራ በሚያዘጋጁትና ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ዝግጅት፣ የመጽሐፍ ዕቁብን ጨምሮ ከ25-50 በመቶ ቅናሽ የሚደረግበት የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ እንዲሁም ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ተሰናድተዋል፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች