Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለተማሪዎች ምገባ ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል ተገባ

ለተማሪዎች ምገባ ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል ተገባ

ቀን:

  • መንግሥት በጀት እንዲይዝ እየተሠራ ነው

በአዲስ አበባ በመንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከሚማሩ ተማሪዎች፣ በወላጆች ወይም በአሳዳጊዎች አቅም ማነስ ምክንያት ምግብ ማግኘትና ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ ተማሪዎችን፣ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ የሚመግበውና በቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ የሚመራው የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማኅበር፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ባደረጉት ገቢ ማሰባሰቢያ 72 ሚሊዮን 500 ሺሕ ብር ቃል ተገባ፡፡

ባለፈው ሳምንት የተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ የምገባ ፕሮግራሙን ቀጣይነት ለማረጋገጥና ተጨማሪ ተማሪዎችን የምገባው ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑን በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የሕፃናት ጤናና ምገባ ባለሙያ ወ/ት ሜቲ ታምራት ተናግረዋል፡፡

የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማኅበር በአዲስ አበባ በሚገኙ 207 የመንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩና ከዝቅተኛ ቤተሰብ የመጡ 20,135 ተማሪዎችን ቁርስና ምሳ እየመገበ ሲሆን፣ ዓመታዊ ወጪውም 60 ሚሊዮን ብር ይደርሳል፡፡

የፕሮግራሙን ቀጣይነት ለማረጋገጥና ተጨማሪ ችግረኛ ተማሪዎችንም የምገባው ተጠቃሚ ለማድረግ ከተደረገው ገቢ ማሰባሰቢያ ጎን ለጎን መንግሥት በጀት እንዲይዝ እንቅስቃሴ መጀመሩን ወ/ሪት ሜቲ ተናግረዋል፡፡

የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማኅበር በመንግሥት ትምህርት ቤቶች በምገባ ፕሮግራም ካቀፋቸው ተማሪዎች በተጨማሪ፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በግለሰቦች፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በመምህራንና በትምህርት ቤት ክበባት ከ10 ሺሕ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት የምገባ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡

በአዲስ አበባ በሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በርካታ ተማሪዎች ችግር ያለባቸው ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ የጎላ ችግር ያለባቸው በትምህርት ቢሮውና በክፍለ ከተሞች ተለይተዋል፡፡ ወ/ት ሜቲ እንደሚሉትም፣ ተጨማሪ ገንዘብ ቢገኝ እነዚህን ተማሪዎች በምገባ ፕሮግራሙ ለማስገባት ታቅዷል፡፡

አንድ ተማሪ በቀን ለሚቀርብለት ቁርስና ምሳ 12 ብር ወጪ የሚደረግ ሲሆን፣ አብስሎ የማቅረቡን ሥራ ደግሞ የችግረኛ ልጆች ወላጆችን ጨምሮ 870 እናቶች ይሳተፉበታል፡፡

የምገባ ፕሮግራሙ ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በሆኑ ታዳጊ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የጤና፣ የሥነ ልቦና እንዲሁም የትምህርት አቀባበል መሻሻል መታየቱንና ይህም ለመማር ማስተማር ሒደቱ አበረታች ሁኔታ መፍጠሩን በእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማኅበር የተካሄደው የክትትልና የግምገማ ጥናት ያስረዳል፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ለምገባ ፕሮግራሙ የሚያስፈልገውን በዓመት ወደ 60 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከአገር በቀል ድርጅቶች፣ በጎ አድራጊ ግለሰቦችና የልማት አጋሮች በማሰባሰብ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጎን ለጎን፣ በጽሕፈት ቤታቸው አማካይነት የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለሆኑ ተማሪዎች ቤተሰቦች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ራሳቸውንና ልጆቻቸውን ለዘለቄታው ከተረጂነት ለማላቀቅ የሚያግዙ ፕሮጀክቶችን ነድፈው ለትግበራ ዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

እንደ ጽሕፈት ቤቱ መግለጫ፣ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራሙ በተማሪዎቹ የጤናና የትምህርት ሁኔታ ላይ ያመጣው በጎ ለውጥ የቤተሰቦቻቸው የኢኮኖሚ አቅም ተጠናክሮ ከተረጂነት እስከሚላቀቁ ይቀጥላል፡፡

ከዓመት በፊት በተደረገ ዳሰሳ በአዲስ አበባ ብቻ በመንግሥት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከሚገኙ ተማሪዎች 90 በመቶ ያህሉ የምግብ ዕርዳታ ፈላጊ ናቸው፡፡

ይህ የዳሰሳ ጥናት ከመደረጉ አስቀድሞ በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች፣ በተለያዩ ተቋማት የምግብ፣ የዩኒፎርም፣ የትምህርት መርጃና ሌሎችም ድጋፎች ሲሰጡ የነበረ ቢሆንም፣ ችግሩን በዘላቂነት መፍታትና ሁሉንም ችግረኛ ተማሪዎች ለመድረስ አልተቻለም፡፡

በመሆኑም ተማሪዎች በረሃብ ምክንያት ክፍል ገብተው ራሳቸውን ሲስቱ፣ ትምህርት መማር ሲያቅታቸው፣ ሲተኙ አልያም ከትምህርት ገበታ ሲቀሩ ማየቱ ብዙ መምህራንን ያሳቀቀ፣ ያላቸውን ምግብ እንዲያካፍሉ ያደረገ ክስተት ነበር፡፡ ሆኖም ችግሩ በመምህራኑ ብቻ የሚፈታም አልነበረም፡፡

የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ግለሰቦች መምህራን የሚያደርጉትን ዕገዛ ለመደገፍ፣ የአዲስ አበባ የትምህርትና የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮዎች በቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ የበላይ ጠባቂነት የሚንቀሳቀሰው የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማኅበር ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ የሚማሩና በጣም ችግረኛ የሆኑ ተማሪዎችን መመገብ መጀመሩ ይታወሳል፡፡   

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...