Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሒልተን ሆቴል ሠራተኛ ማኅበር የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው አለ

የሒልተን ሆቴል ሠራተኛ ማኅበር የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው አለ

ቀን:

በሒልተን ሆቴል አስተዳደርና በሠራተኞች ማኅበር መካከል የተፈጠረው ውዝግብ አሁንም መቀጠሉንና በአባላቱ ላይ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑን የሠራተኛ ማኅበሩ አስታወቀ፡፡

ማክሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ማኅበሩ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፣ በሆቴሉ አስተዳደር ላይ ያለውን ቅሬታ በዝርዝር ገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት ከሠራተኞች የሥራ ደኅንነት፣ ዕድገት፣ እንዲሁም ጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዙ ችግሮች እንዳሉና ከጊዜ ወደ ጊዜ መፍትሔ ማግኘት እንዳልተቻለ ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

ከሳምንት በፊት የሆቴሉ አስተዳደርና የሠራተኛ ማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ከማካሄድ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሁለቱም ባለመስማማታቸው ጠቅላላ ጉባዔው ሳይከናወን ቀርቷል፡፡

ሚያዝያ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. እና ግንቦት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ አብርሃም አበበ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ እንደሚያሳየው፣ የሠራተኛ ማኅበሩ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ ፈቃድ እንዲሰጠው መጠየቁንና የሆቴሉ አስተዳደርም ጥያቄውን ተቀብሎ ፈቅዶ ነበር፡፡

ነገር ግን የሆቴሉ አስተዳዳር ግንቦት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በሆቴሉ የሰው ኃይል ዳይሬክተር ወ/ሮ አዳኑ ታፈሰ በተጻፈ ደብዳቤ፣ ግንቦት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊደረግ የነበረው ስብሰባ መሰረዙን አስታውቋል፡፡

በደብዳቤው መሠረት የስብሰባ ፈቃዱ የተሰጠው ለሆቴሉ ሠራተኞች ብቻ ነበር፡፡ ማኅበሩ ግን በስብሰባው ላይ ጋዜጠኞች፣ የመንግሥት አካላት፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የቱሪዝም፣ ሆቴሎችና ጠቅላላ አገልግሎት ኢንዱስትሪ ሠራተኛ ማኀበራት ፌዴሬሽን የጋበዘ ስለሆነ፣ ይኼንን ማስተካከል ካልተቻለ የተሰጠው የስብሰባ ፈቃድ ይሰረዛል፡፡

‹‹መጀመርያ ስብሰባው ሲፈቀድ የምናውቀው ስብሰባው ሠራተኛው ብቻ በተገኘበት እንደሚካሄድ እንጂ ሌሎች አካላት እንደሚገኙ አልነበረም፤›› ሲሉ የሆቴሉ ኃላፊ ክላውዝ ስቴነር በወቅቱ ተናግረው ነበር፡፡

‹‹ይኼ ሆን ተብሎ ሠራተኛው በነፃነት እንዳይናገርና በደሉን እንዳይገልጽ የተደረገ ዕርምጃ ነው፤›› ሲሉ የማኅበሩ ኃላፊዎች ከአሁን ቀደም ለሪፖርተር መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ማክሰኞ ዕለት ማኅበሩ በሰጠው መግለጫ ሥራ ላይ እያሉ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሠራተኞች በአግባቡ እረፍት ማግኘት እንዳልቻሉ ለአብነት ተገልጿል፡፡

በሆቴሉ ውስጥ በቤት አያያዝ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙት ወ/ሮ ፍቅርተ ገብረ ወልድ ከደረጃ ወድቀው በእጃቸውና በወገባቸው ላይ ጉዳት ቢደርስባቸውም፣ እረፍት ማግኘት ሲገባቸው ሥራ ገበታ ላይ እንዲገኙ እየተገደዱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ግንቦት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በሆቴሉ አስተዳደር ለወ/ሮ ፍቅርተ የተጻፈው ደብዳቤ፣ ‹‹ግለሰቧ ከሥራ ውጪና በሥራ ላይ እያሉ ወድቀው ጉዳት ስለደረሰባቸው ተገቢው የሕክምና ፈቃድ ቢሰጣቸውም የጤንነታቸው ሁኔታ መሻሻል ባለመቻሉ ፈቃድ እየተሰጣቸው በሥራ ላይ ከሚገኙባቸው ቀናት ይልቅ የማይገኙባቸው ስለሚያመዝን፣ በዚህ ሁኔታ ኃላፊነታቸውን ለዘለቄታው መወጣት እንደማይችሉ በግልጽ ያረጋግጣል፤›› ይላል፡፡

በዚሁ ደብዳቤ ከነሐሴ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሦስት ጊዜ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው እኚሁ ግለሰብ ተገልጾላቸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ሠራተኞችም ሥራ ላይ እያሉ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በግድ እንዲሠሩ እየተደረጉ መሆናቸውን የማኅበሩ አመራሮች ተናግረዋል፡፡

ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረውና በአሁኑ ጊዜ 630 ሠራተኞች የሚያስተዳድረው የሒልተን ሆቴል መነሻ ደመወዝ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ  600 ብር ነበረ፡፡ የመጨረሻው የደመወዝ እርከን ደግሞ 6,853 ብር ነው፡፡ ከደመወዝ እርከን ጋር በተያያዘ ሠራተኞቹ ባነሱት ጥያቄ ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ላይ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ከ15 በመቶ እስከ 25 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል፡፡

ነገር ግን ይኼ ማስተካከያ ለሠራተኞች የማይጠቅምና እነሱም እንዳልተስማሙበት የማኅበሩ አመራሮች ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ሆቴሉ ከደመወዝ ጋር በተያያዘ ወጥ የሆነ አሠራር የለውም ይላል፤›› ማኅበሩ፡፡ ‹‹መሰብሰባችንም መሠረታዊ ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ነው፤›› ሲሉም አቶ አብርሃም ከአሁን ቀደም ለሪፖርተር መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የሒልተን ሆቴል ኃላፊ ክላውዝ ስቴነር፣ እስካሁን ከሠራተኞች መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በግል የመጣላቸው ጉዳይ የለም ብለዋል፡፡

ከደመወዝ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ አስተዳደሩ በተገቢው መንገድ እየሠራ እንደሆነና እስካሁንም የተደረገው በቂ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሠራተኛ ማኅበሩ አመራሮች ግን ጥያቄያቸው በአግባቡ ምላሽ ካላገኘ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ ለአቤቱታ እንደሚሄዱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...