የአገሪቱ የደን ሀብት በብዛት ከሚገኝባቸው ክልሎች መካከል ኦሮሚያ ቀዳሚውን ድርሻ እንደምትይዝ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ይኸው የደን ሀብት ለዘመናት ተጠብቆ ከቆየባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች አንዷ ደግሞ የጭልሞ መንደር ነች፡፡
ዓመቱን ሙሉ አረንጓዴነትን የተላበሰች፣ ውኃ የማይጠማት ጭልሞ፣ እንደ ስሟ ከከራራ ፀሐይ ይልቅ ደመናማ የአየር ሁኔታ የሚበዛባት ነች፡፡ ከዚህ ሁኔታዋ ተነስተው ይመስላል ቀደምት ነዋሪዎቿ ጭልሞ ብለዋታል፡፡ በደን የተሸፈነች በመሆኗ፣ ሙቀታማ አየር የማይበግራት፣ ጨለምለም ማለቱ የሚስማማት ለመሆኗ መስካሪ ስያሜ ተላብሳለች፡፡ ከባህር ጠለል በላይ በ2,600 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ በመሆኗም ቅዝቃዜ መለያዋ ነው፡፡ ደናማ በመሆኗ ግን ብዙ ታሪክ አይታለች፡፡ በርካታ ገድሎች የተፈጸሙባት ስትሆን የደን ይዞታዋ ከአፄ ምንሊክ ዘመን በፊትም የታፈረ እንደነበር ነዋሪዎቿ በኩራት ይናገራሉ፡፡
ከአዲስ አበባ 85 ኪሎ ሜትር ገደማ የምትርቀው ጭልሞ፣ ከ500 ያላነሱ አባወራዎችንና ከ3,000 ያላነሱ ነዋሪዎችን ያስጠለለች፣ የግብርና ሥራዎች እንደ ለማምነቷ ብዙም የማይሞክሯት፣ አብዛኛው ነዋሪዋ በደን ውጤቶች ገቢ የሚተዳደርባት ስትሆን፣ እንደ ጊንጪ ያሉ ከተሞችም አጎራባቿ ናቸው፡፡
ይሁንና የጭልሞ ደን ምንም እንኳ አሁን ባለበት ሁኔታ አነስተኛ ይዞታን እንደሚሸፍን ቢነገርለትም፣ የጭልሞ ነዋሪዎች ግን ከመቶ ዓመታት በፊት የነበረውን ከፍተኛ ይዞታ ማመናመን ከጀመሩት መካከል ጣልያኖች ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ይናራሉ፡፡
ደን አራቋቹ የእንጨት መሰንጠቂያ
አቶ አበራ ተፈስሁ፣ በጭልሞ ጋጂ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር የደን ኅብረት ሥራ ዩኒየን የቦርድ ሰበሳቢ ናቸው፡፡ እንደ አቶ አበራ ገለጻ በዘመነ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምንሊክ ጊዜ የጭልሞ ደን ይዞታ በመግሥት የሚጠበቅ፣ መጠኑም ከ22 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ያካልል ነበር፡፡ እስከ ኢሕአዴግ መግቢያ ድረስ በመንግሥት ጥበቃና ይዞታ ሥር የነበረው የጭልሞ ደን፣ ጣልያኖች ዳግመኛ በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ዳግመኛ ለወረራ ሲመጡ የደኑ ይዞታ ተጋላጭ ሆኗል፡፡ በ1928 ዓ.ም. ጣልያኖቹ በመጡ ጊዜ ከሰፈሩባቸው አካባቢዎች አንዷ ጭልሞ ነበረች፡፡ በዚህ ምክንያት ቀድሞ የነበረው 22 ሺሕ ሔክታር ወደ 12 ሺሕ አሽቆልቁሏል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በአካባቢው የነበሩ ጣልያኖች ጭልሞ ደን ላይ አደጋ ጣይ መሣሪያዎችን በማምጣታቸው ነው፡፡ የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽኖች፡፡ አቶ አበራ ይቀጥላሉ፡፡
ሰባት የእንጨት መሰንጠቂዎችን በጣልያን በማስመጣት ደኑን የገዘገዙት ጣልያኖች፣ ከአምስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የጭልሞን ደን በግማሽ ሊቀንሱት ችለዋል፡፡ ከጣልያኖች መውጣት በኋላ የደርግ መንግሥት በሕይወት የተፈረውን የጭልሞን ደን በዘበኛ ለማስጠበቅ ቢመክርም ከጥፋት ሊያድነው አልቻለም፡፡ የደን ሀብቱ እጅጉን እየተራቆተ የመጣው ደግሞ የመንግሥት ለውጥ በተደረገበት ወቅት ነበር፡፡ ደርግ ሥልጣን ለቆ፣ ኢሕኣዴግ በተተካበት በ1983 ዓ.ም. ሁሉም ነዋሪ በደን ጭፍጨፋ ተግባር ውስጥ እንደተሳተፈ አቶ አበራ ያስታውሳሉ፡፡ በመሆኑም ተመናምኖ አሁን ላይ የቀረው የደን ሽፋን መጠን 4,000 ሔክታር ላይ ቀርቷል፡፡ ይህንንም ያረጋገጠው ፋርም አፍሪካ የተባለ ግበረ ሰናይ ድርጅት በ1989 ዓ.ም. ባደረገው ጥናት እንደሆነ አቶ አበራ ጠቅሰዋል፡፡
አሳታፊ የደን ጥበቃ ጥቅሞች በነዋሪቹ ሲገለጽ
በመሆኑም በጭልሞ ደን ዙሪያ የሰፈረው ነዋሪ ደኑን ከነጭራሹ እንዳያጠፋው አሳታፊ በሆነ የደን ጥበቃ ሥራና ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ፣ ኅብረተሰብ አቀፍ አሳታፊ የደን አስተዳደር እንቅስቃሴ እንዲደረግ ፋርም አፍሪካ ሲጥር መቆየቱን አቶ አበራ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም 12 የደን ማኅበራት ተመሥረተው፣ ከእነዚህ ውስጥም ስምንቱ ወደ ዩኒየን አድገው ሕዝቡ ከደን ውጤቶች ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሠራር መተግበር ጀምረዋል፡፡ ድሮ ደን የመንግሥት ነው ይባል በነበረበት ወቅት ሰው እንዳሻው ይቆርጥ የነበረውን የቀነሰው አሁን በማኅበር ተደራጅቶ ደኑ የራሱም እንደሆነ በማወቁ ነው የሚሉት አቶ አበራ፣ በመሆኑም የማኅበርና የዩኒየን አባላት፣ ነባር ያልሆኑ እንደ ባህር ዛፍ፣ የፈረንጅ ጥድ ያሉ ቋሚ ያልሆኑ ዛፎችን በማልማት እየሸጠ፣ 70 በመቶውን ለራሱ፣ 30 በመቶውን ለመንግሥት እያሰረከበ እንደሚጠቀም አብራርተዋል፡፡ ይህም ቢሆን በርካታ አሰፍስፎ የሚጠብቅ የውስጥና የውጭ ጨፍጫፊ ሲያንዣብብ ውሎ የሚያድርበት የደን መንደር በመሆኑ ሁሌም በተጠንቀቅ መጠበቅ ግድ ነው፡፡
ዛሬም ድረስ በአዲስ አበባ የሚገኙ እንደ ሰባተኛ አካባቢ ያሉ የኮርኒስ እንጨት፣ የጣውላ ዓይነቶችና ልዩ ልዩ የደን ውጤቶች የሚሸጡባቸው አካባቢዎች መነሻቸው እንደ ጭልሞ ያሉ በቅርብ ርቀት የሚገኙ የደን ሀብቶች መገኛ ሥርፍራዎች መሆናቸውን የሚጠቅሱት የአካባቢ ነዋሪዎች፣ አሁንም ድረስ በእንጨት ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት የደን ይዞታውን እንደሚፈታተኑት ይገልጻሉ፡፡
የሰባት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ደጉ ወልደ ጊዮርጊስ፣ በጭልሞ አካባቢ ተወልደው ያደጉ የነበረውን የኖረውን የሚያውቁ ናቸው፡፡ እንደ አቶ አበራ ሁሉ አቶ ደጉም ሕዝብ አሳታፊ የደን አስተዳደር በመምጣቱ በደን ይዞታው ላይ የተንዣበበው አደጋ በጥቂቱም ቢሆን ጋብ እንዳለ ይናገራሉ፡፡ ደኑ በመኖሩ ምክንያት ምንጊዜም ንፁህ ውኃ እንደሚጠጡ፣ የውኃ አቅርቦትም ያለችግር እንደሚያገኙ አቶ ደጉ ይገልጻሉ፡፡ ደኑ በመኖሩ ከብቶች ያለ ችግር ዓመቱን ሙሉ ሣር ያገኛሉ፡፡ ‹‹ከብቶቻችን ምንም ባይወፍሩ እንኳ አይሞቱብንም፤›› ያሉት አቶ ደጉ፣ የደኑ ጥቅም በማኅበር በመሆን በመጠበቁ ምክንያት ሁሉም የጭልሞ ነዋሪ የሣር ቤቱን ወደ ቆርቆሮ ክዳን መለወጥ መቻሉም ከደን ተጠቃሚነቱ መገለጫዎች መካከል እንደሚመደብ ይጠቅሳሉ፡፡
ከብቶች የሚበሉት የሚጠጡት ካለማጣቸው፣ ሕዝቡም የውኃ ጥም ሳይኖርበት፣ የደርግ መንግሥት ተክሏቸው ከነበሩ የውጭ የጥድ እንዲሁም የባህር ዛፎች ሽያጭ ተጠቃሚነት፣ ሕዝቡም ችግኝ እያፈላ ከሚተክላቸውና ሲደርሱ እየቆረጠ ከሚሸጣቸው ዛፎች ባሻገር በደኑ ዙሪያ የሚገኘው የጭልሞ ነዋሪ የጓሮ አትክልቶችን እያመረተ እንደ ጊንጪ ላሉ አጎራባች ከተሞች በመሸጥ እንደሚጠቀም አቶ ደጉ አብራርተዋል፡፡ የማገዶም ችግር ጭልሞን አያውቃትም ያሉት አቶ ደጉ የደጉ ርጋፊ እንደልብ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል ብለዋል፡፡ አብዛኞቹ ነዋሪዎች ልጆቻቸውን የሚያስተምሩትም ከደኑ በሚያገኙት ጥቅም እንደሆም ጠቅሰዋል፡፡
የማኅበር አባላት ባዋጡት መጠን በየዓመቱ ስለሚያገኙት የትርፍ ድርሻ ክፍፍል አቶ አበራ ማብራሪያ አላቸው፡፡ መመዝገቢያ ከ200 እስከ 400 ብር በመክፈል ልክ እንደ አክሲዮን ማኅበር ባለ አኳኋን ድርሻ ገዝተው የሚገቡ አባላት፣ እንደ አቅማቸው የአክሲዮን ድርሻ ከመግዛት ባሻገር፣ በሚያደርጉት ተሳትፎ ማለትም በችግኝ ማፍላት፣ በደን ጥበቃ ሥራዎች፣ ማኅበራቱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በሚያደርጓቸው ተሳትፎች ሁሉ እየተመዘኑ የጥቅም ድርሻቸው ተሰልቶ ይሰጣቸዋል፡፡ ዝቅተኛው 58 ከፍተኛው እስከ 200 አባላት ያሏቸው ማኅበራት በዩኒየን የታቀፉበት የጭልሞ ጋጂ ኅብረት ሥራ፣ ካቻምና 130 አባላት ላሉት ማኅበር አንድ ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺሕ ብር መስጠቱን አቶ አበራ ያስታውሳሉ፡፡ በመሆኑም አንድ አባል በነፍስ ወከፍ በዓመት ከ12,000 እስከ 5,000 ብር የትርፍ ድርሻ የማግኘት ዕድል አለው፡፡ ከዚህም በሻገር አባላት በየጓሯቸው የፖም (አፕል) ዛፍ ተክለው ተጠቃሚ እንደሆኑም ተብራርቷል፡፡
የጭልሞ ነዋሪዎች የመሬት ባለቤትነት ይዞታ ማረጋገጫ የላቸውም የሚሉት አቶ አበራ፣ በጭልሞ ነዋሪው ደን እየጠበቀ ከላይ በነዋሪዎቹ የተብራሩትን ዓይነት ከደን የሚገኙ ተጓዳኝ ጥቅሞችን በመካፈል የሚኖር እንጂ እንደሌሎች አካባቢዎች በእርሻ ሥራ የሚተዳደር ነዋሪ እንዳልሆነም ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም ቋሚ የሰብል እርሻ ሥራ ባይካሄድም ሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎች ግን አልታጡም፡፡
ሥራ አጥነት የደን ህልውና አደጋ
አቶ አበራም ሆኑ አቶ ደጉ የደኑን ህልውና እየተፈታተኑ ይገኛሉ ካሏቸው ችግሮች መካከል የሥራ አጥነት ችግር ይጠቀሳል፡፡ ሥራ የሌላቸው ወጣቶች ከደኑ ጋር ቀን ተሌት ሲጋጩ ይውላሉ ያሉት አቶ አበራ፣ የገቢ ምንጭም ሆነ የሚተዳደሩበት የሌላቸው ወጣቶች ጥብቁ ደን ቢቆረጥ በውድ ዋጋ እንደሚሸጥ ስለሚያውቁም ጾም እያደሩ ደኑ ቆሞ ሲያዩት እንደሚፈታተናቸው መገመት ቀላል ነው ይላሉ፡፡ በመሆኑም ለወጣቶቹ ሥራ የሚያስገኙ እንቅስቃሴዎች ላይ መንግሥት ቢበረታ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
አቶ ደጉም ቢሆኑ ይኸው የወጣቶቹ ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አስታውሰው፣ መንግሥት እንደ ፋብሪካ ያለ፣ ወይም ወጣቶች ሥራ ሠርተው ራሳቸውን ችለው የሚኖሩበትና የሚለወጡበት ዕድል ካፈጠረ የጭልሞ ደን ከሥጋት ቀለበት እንደማይወጣ ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡ በዚያም ላይ ደን አላግባብ የቆረጡ ሰዎች ሲያዙ ተገቢው የሕግ ውሳኔ ስለማሳጥባቸው፣ ክትትልና ድጋፉም አነስተኛ በመሆኑ በማኅበር ተደራጅተው ደኑን እየጠበቁ በሚተዳደሩ አባላት ሞራል ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አቶ ደጉ አሳስበዋል፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ደግሞ ባለፈው ዓመት እንደተከሰቱ የፖለቲካ ተቃውሞች ሲነሱ ተጎጂ ከሚሆኑት መካከል ደንና በውስጡ የሚኖሩ እንስሳት በመሆናቸው ለደኑም ለነዋሪውም ህልውና ሲባል ሁሉ አቀፍ የመንግሥት ድጋፍ መደረግ እንዳለበትም ይመክራሉ፡፡
የጄኔራሉ ዛፍ
በጣልያን ወረራ ዘመን ባለትልቅ ስም፣ ባለብዙ ገድለኛ መሆናቸው ከሚነገርላቸው፣ ታሪክ ከሚዘክራቸው ባለሟሎች መካከል በቅርቡ ከዚህ ዓለም የተለዩት የጄኔራል ጃገማ ኬሎ ገድል ይኖራል፡፡ በጭልሞ ከባለሟሎቻቸው ጋር የሠሩት ጀብዱ እንዲሁም ጣልያንን ያንጣጡበት ታሪክ ዛሬም ድረስ እንደ አዲስ ይወራል፡፡ በጭልሞ ከ350 በላይ ባንዳዎች፣ የጣልያን ወታደሮችና አለቆቻቸው ጉድ የሆኑበት ገድል ትልቅ ሥፍራ አለው፡፡ ደራሲው ፍቅረ ማርቆስ ደስታ በጻፈው የበቃው መብረቅ በሚል ርዕሥ በጻፈው፣ የጄነራሉ የሕይወት ታሪክ ውስጥ ይኸው የጀግንነት ክራሞታቸው ተክተቧል፡፡ ይሁንና በጭልሞ ደን ውስጥ ከአናቱ በላይ የዳስ ቤት የሠሩበት ትልቁ ዋርካ አሁንም ድረስ ይገኛል፡፡ ከጥብቅ ደኑ ውስጥ ፈንጠር ብሎ የሚታየው ግዙፉና ሰልካካው ዋርካ፣ በወቅቱ አግድ የተቀሰቱበትን እንደ መሰላል መወጣጫ ያገለገሉ ፌሮ ብረቶችን እያወጣቸው ቢሆንም አሁንም ድረስ ግን ለጀግኖቹ አርበኞች ምስክር የሆነበትን አሻራ አላጣም፡፡
የጭልሞ ነዋሪዎች አንድ ትልቅ ታሪክ እየተቀባበሉ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በዕድሜ የበሰሉ አባቶች በልጅነታቸው እየወጡ ይጫወቱበት እንደነበር የሚናሩለት ዋርካ ታሪክ ከሠሩ ሰዎች ተካፋይ ስለመሆኑ ይመሰክሩለታል፡ ‹‹ጄኔራል ጃገማ ከዛፉ ላይ ሆነው አነጣጥረው በመቶክስ የጣልያን ወታደሮች መሪን ሲጥሉት፣ ተከታዮቻቸው ደግሞ እስከ አዲስ ዓለም አባረው የጣልያንን መቱት፤›› ይላሉ፡፡ የጄኔራሉ ዛፍ በአሁኑ ወቅት እስከ 280 ዓመታት የሚገመት ዕድሜ እንዳስቆጠረ በአሜካኖች የተደረገ ልኬት ይጠቀሳል፡፡ ለጄኔራል ጃገማ ኬሎ ሐውልት የማቆም እንቅስቃሴ በነዋሪው ዘንድ መጀመሩም ተሰምቷል፡፡
የዓለም ባንክ ድጋፍ
እንዲህ ያሉ ታሪከኛ ዛፎችን ለትውልድ ለማቆየት እንዲቻል፣ የአገሪቱ አብዛኛው የደን ሀብት በሚገኝባት ኦሮሚያ አዲስ የደን ጥበቃ ፕሮጀክት ይፋ ከተደረገ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ የዓለም ባንክ በኦሮሚያ ለተጀመረው የደን መልከዓ ምድር ፕሮግራም የ18 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ለግሷል፡፡ በባንኩ የተፈጥሮ ሀብቶች አስተዳደር ባለሙያ ሚስተር ስቴፈን ዳኒዮ እንዳስታወቁት፣ የዓለም ባንክ የሰጠው ድጋፍ እንደ ጭልሞ ያሉ ጥብቅ ደኖችን ከጥፋት ለመከላከል ብሎም ለመጪው ትውልድም እንዲተርፉ ለማድረግ እንዲያግዝ በማሰብ የሰጠው ገንዘብ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የዓለም ባንክን ጨምሮ፣ የኖርዌይና የአሜሪካ መንግሥት ለደን ጥበቃና ልማት ሥራዎች የሚሰጡት ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የብሔራዊ ሬድ ፕላስ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪው ዶ/ር ይተብቱ ሞገስ ናቸው፡፡ ዶ/ር ይተብቱ እንዳሉት፣ ደን ባለባቸው አካባቢዎች የሚታዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያ እንቅስቃሴዎች ደን ከማገኝባቸው ይልቅ ለነዋሪዎቹም ለአገር ኢኮኖሚም ትልቅ ድርሻ እያበረከቱ እንደሚገኙ ያብራራሉ፡፡ ደን ያለበት ሥፍራ በአብዛኛው የውኃ አካላት የሚገኙበት፣ ተፋሰሶች ለእርሻ ሥራዎችም ሆነ ለሌሎች ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ያላቸው ሚና ሚዛን አይለካውም፡፡ ይሁንና አግባብ ያለው አጠቃቀም ሊኖር እንደሚገባም ያስጠነቅቃሉ፡፡ ደን ስላለ ብቻ እንደልብ እየጨፈጨፉ ለማገዶም፣ ለቤት ሥራም ወዘተ. መፍለጡ ደኑን ከማመናመን አልፎ የመሬት መራቆትና ለምነት እያባባሰ የሚገኝ አደጋ ነው ይላሉ፡፡ የአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ አቅም በደን ሀብቷ እንደሚታገዝ የሚያምኑት ዶ/ር ይተብቱ፣ ሕዝቡ ለደን አጠቃቀም ተገቢ ግንዛቤ እንዲኖረው፣ አለአግባብ እያደገ ያለው የሕዝብ ቁጥርም መላ ሊበጅለት እንደሚገባ የሚማጸኑትም የደን ሀብት ላይ እየደረሰ ካለው ውድመት አኳያ ነው፡፡ በዚያም ላይ ‹‹የውጭ ሰዎች እንርዳችሁ ደኖቻችሁን ተንከባከቡ ሲሉን እኛም በጥበቃውና ለትውልድ በማስተላለፉ ላይ ልንጠነክር ይገባናል፤›› ብለዋል፡፡
የደን ሽፋን ሙግቶች
በአገሪቱ የተተከሉ አምስት ቢሊዮን ችግኞች እንዳሉ እነዚህንም ወደ 15 ቢሊዮን እንዲጨምሩ መንግሥት ማቀዱ ሲነገር ይደመጣል፡፡ ይሁንና ምን ያህሉ ፀደቁ? የሚለው የጠያቂው ትውልድ ሙግት የሚያረጋግጡት ግን ከሚተከሉት ውስጥ የሚጸድቁት ጥቂት መሆናቸው ነው፡፡ አንዱ ችግኝ እንደው በጥቂቱ አንድ ብር ይወጣበታል ቢባል አምስት ቢሊዮን ብር እንዲሁ ሜዳ ላይ ከስሎ ቀረ ማለት አይደለም ወይ? ይህ ገንዘብ ስንት ሥራ በሠራ ነበር የሚሉ ቆርቋሪ ጥያቄዎች ለመንግሥት አካላት ሲቀርቡም ይደመጣል፡፡
ዶ/ር ይተብቱ አበክረው እንደሚገልጹት፣ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ጠቅላላ የደን ሽፋን 15.5 በመቶ እንደሆነ በተጨባጭ ሳይሳዊ ዘዴዎች ተረጋግጧል፡፡ ይሁንና ይህ መጠን ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት ምን ያህል ነበር ብለውም ይጠይቃሉ፡፡ ሊኖር ከሚገባው ይልቅ ምን ያህል ሊቀንስ እንደቻለ ማሰቡ ይበጃል ይላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓመት 92 ሺሕ ሔክታር መሬት የደን ሽፋን እየተመነጠረ እንደሚገኝ በመግለጽ አገሪቱ የቱንም ያህል የደን ልማትና ክብካቤ ሥራዎችን ብትሠራም፣ አሳሳቢ ችግር ውስጥ እንደምትገኝ ማሳያ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ በኢትየጵያ ትርጓሜ መሠረት ደን የሚባለው ግማሽ ሔክታር የሚሸፍን፣ ቁመቱ እስከ 20 በመቶ የጥላ ሽፋን ወይም ካኖፒ ያለውና ቁመቱ ከሁለት ሜትር በላይ የሆነ ሁሉ ደን ይሰኛል፡፡ ይህ ቆላና ደጋውን የአገሪቱን ክፍሎች አካቶ ሲሰላ ሽፋኑ 15 በመቶ ነው ቢባልም በየዓመቱ ከሚታጣው 92 ሺሕ ሔክታር መሬት ውስጥ እየተተካ ያለው የደን መጠን ከ20 ሺሕ ሔክታር በላይ እንደማይሸፍን አረጋግጠዋል፡፡
በመሆኑም የደን ልማት የብልጽናችን መሠረት በመሆኑ ሁሉም በየፊናው በሚሰማራበት የሙያ መስክ፣ ሕፃናትም ከልጅነት ዕድሜ ጀምሮ ደን የህልውና ዋልታ መሆኑን እያወቁ እንዲመጡ መደረግ አለበት ያሉት ዶ/ር ይተብቱ፣ እየለማ ከሚገኘው ይልቅ እየተጨፈጨፈ ያለው የደን ሀብት ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም ጉዳዬ ሊለው እንደሚገባ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡