Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየምድር ባቡር ኮርፖሬሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ

የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ

ቀን:

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ላለፉት አሥር ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት ዶ/ር ጌታቸው በትሩ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ፡፡

 

ዶ/ር ጌታቸው ኃላፊነታቸውን የለቀቁበት ምክንያት ግልጽ ባይሆንም፣ ከግንቦት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ገበታቸው ላይ አለመገኘታቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ፣ የዶ/ር ጌታቸውን መልቀቅ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ ነገር ግን ሥልጠና ላይ በመሆናቸው ዝርዝሩን ለመግለጽ እንደሚቸገሩ አስታውቀዋል፡፡

በውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ የሚመራው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ፣ ዶ/ር ጌታቸው ያቀረቡትን መልቀቂያ እንደተቀበለና በምትካቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትን ዶ/ር ብርሃኑ በሻህ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ መሾሙ ታውቋል፡፡

መንግሥት በመላ አገሪቱ አምስት ሺሕ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባቡር አውታር ዝርጋታ ተግባራዊ ለማድረግ ከጠነሰሰ ጊዜ ጀምሮ፣ ዶ/ር ጌታቸው ዋነኛ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኅዳር 1999 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 141 ኮርፖሬሽኑን በይፋ ሲያቋቁም፣ ዶ/ር ጌታቸው መዋቅሩን ከመዘርጋት አንስቶ ፕላኑን እስከ ማውጣት ድረስ ያሉ ሥራዎችን መርተዋል፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታትም በተለይ የአዲስ አበባ (ሰበታ)-ጂቡቲ፣ የአዋሽ-መቐለና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ከመሩዋቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥ የአዲስ አበባው ፕሮጀክት ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ዶ/ር ጌታቸው ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው ነበሩ፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ-ጂቡቲ ፕሮጀክት ተጠናቆ ሙከራ ላይ እያለ ዶ/ር ጌታቸው ኃላፊነታቸውን ለቀዋል፡፡

48.9 ቢሊዮን ብር በጀት ይዞ የሚንቀሳቀሰውና ለአሥር ዓመታት በእሳቸው የተመራው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የሥራ አፈጻጸሙን የሚያደንቁት የመኖራቸውን ያህል የሚተቹትም በርካታ ናቸው፡፡

ትችት አቅራቢዎች ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከል የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የሰውም ሆነ የተሽከርካሪዎች መሸጋገሪያ በበቂ ደረጃ ሳያካትት መገንባቱ ለትራፊክ መጨናቀቅ ምክንያት ሆኗል የሚለው አንዱ ነው፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ -ጂቡቲ ባቡር መስመር ሲገነባ የደረቅ ወደብ፣ የጂቡቲ ወደብና የነዳጅ ማከማቻ መሠረተ ልማቶችን ታሳቢ አለማድረጉን ያክላሉ፡፡

የሥራ አፈጻጸሙን መልካምነት የሚገልጹ አካላት ደግሞ ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመ ገና አሥር ዓመታት ብቻ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አገሪቱ በባቡር መሠረት ልማት ግንባታ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ፕሮጀክቶችን ከዳር ማድረስ መቻሏን በበጎ ጎኑ መታየት አለበት ይላሉ፡፡

ዶ/ር ጌታቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ ጥረት ቢደረግም፣ ጥረቱ ሊሳካ አልቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...