Wednesday, July 24, 2024

የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የመመረጥ ፋይዳ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሽታን በመከላከል ላይ በሚያተኩረው የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ ተፈትነው ዛሬ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለመሆን አሸናፊ የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የዓለም የጤና ድርጅትን በዋና ዳይሬክተርነት ለአምስት ዓመታት ያህል ለመምራት ከ186 አባል አገሮች መካከል የ133 አገሮች ድምፅ ተችሯቸዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትን ለመምራት ከአንድ ወር ያልበለጠ ጊዜ የቀራቸው ዶ/ር ቴድሮስ፣ ‹‹በአንድነት ለጤናማ ዓለም›› በሚል መሪ ቃል የምረጡኝ ዘመቻ አካሂደው ድል ቀንቷቸዋል፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ፖሊሲን ከመላው የዓለም ሕዝብ ጋር አስተሳስረውና አዋህደው ጤናማ ዓለም ይፈጥራሉ ብለው ብዙዎቹ ተስፋ ጥለውባቸዋል፡፡ 

‹‹በዓለም ላይ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ ማን እንደሆነና ከየት እንደመጣ ልዩነት ሳይደረግበት ጤናማ ሆኖ የማየት ራዕይ አለኝ፤›› እያሉ በተደጋጋሚ ጊዜ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ሲናገሩ የነበሩት ዶ/ር ቴድሮስ፣ አሁን ጥያቄው ዕቅዳቸውን ያሳካሉ ወይስ አያሳኩም የሚለው ሆኗል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአስመራ ዩኒቨርሲቲ ያገኙት ዶ/ር ቴድሮስ፣ የማስተርስና የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን ደግሞ እንግሊዝ አገር ከሚገኙት ኖቲንግሃምና ለንደን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡

ብዙ አገሮችና ድርጅቶች የእሳቸው ደጋፊ ሆነው እንደቆዩ ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት አቅራቢነትና በአፍሪካ ኅብረት አፅዳቂነት ወደ ውድድሩ እንደገቡ የሚነገርላቸው ዶ/ር ቴድሮስ፣ የምርጫ ሥነ ሥርዓቱ ከመካሄዱ በፊት የካሪቢያንና የፓስፊክ አገሮች ድጋፋቸውን እንደሰጧቸው ተገልጿል፡፡ የእስያ፣ የአውሮፓ፣ የሰሜንና የደቡብ አሜሪካ አገሮች ከእሳቸው ጎን እንደነበሩ የተለያዩ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ከሆኑ በኋላ በአምስት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ሲገልጹ ከርመዋል፡፡ እነዚህም ጤና ለሁሉም ዜጋ እንዲደርስ መሥራት፣ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት፣ የሴቶች፣ ሕፃናትና ልጆችን ጤና መንከባከብ፣ የጤና ችግር በአካባቢና በአየር ንብረት ለውጥ ችግር እንዳያመጣ መሥራትና የዓለም ጤና ድርጅትን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር የሚሉት ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ሰው መሠረታዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ ወደ ዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ውድድር ሲገቡ፣ ዓለም አቀፍ የጤና ሽፋንን ተደራሽ ለማድረግ የአገሮቹ መሪዎች ቁርጠኝነትና ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ተባብሮ የመሥራት ዝንባሌ ሊኖራቸው ይገባል በማለት ሲናገሩ ነበር፡፡ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ትኩረት ከሰጡት ጉዳይ መካከል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ያነሱት ጉዳይ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ ዕቅዳቸውን ለማሳካት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ የየአገሮቹን የጤና ሚኒስትሮች በማወያየትና በማማከር እንደሚሠሩና በዚህም ስኬታማ እንደሚሆኑ ሲነገር ቆይቷል፡፡ 

ዶ/ር ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የአገሪቱን የሚሊኒየም የልማት ግብ በጊዜው ማሳካት ከቻሉ አገሮች ተርታ እንድትሠለፍ እንዳደረጓት የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ገልጿል፡፡ በወቅቱ የሕፃናት ሞትን በሁለት ሦስተኛ፣ በወባ የሚከሰት ሞትን በ75 በመቶ፣ በኤችአይቪ የሚሞቱትን በ70 በመቶ፣ በሳንባ ነቀርሳ የሚሞቱትንም በ64 በመቶ መቀነስ እንዳስቻሉም የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ገልጿል፡፡ በአገሪቱ 3,500 የጤና ማዕከላትና 16 ሺሕ የጤና ኬላዎች በማቋቋም የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ መቻላቸውንና የጤና ባለሙያ ማሠልጠኛ ማዕከላትን ከሦስት ወደ 33 እንዳሳደጉ ጠቁሟል፡፡ 16,500 የነበሩትን የጤና ባለሙያዎች በሰባት እጥፍ ማሳደግ መቻላቸው የጤናውን ዘርፍ የመምራት አቅማቸውን የሚያሳይ እንደሆነ አክሏል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ በተለይ በሚታወቁበት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም 38 ሺሕ ባለሙያዎችን አሠልጥነው ወደ ሥራ በማስገባት የጤና አጠባበቅ ሥርዓቱ ማኅበረሰባዊ መሠረት እንዲኖረው ማድረጋቸውንና ለጤና መድን ሽፋን መጀመር መሠረት መጣላቸውን አውስቷል፡፡

በዚህም የተነሳ በዓለም የጤና ድርጅት ጉባዔ ላይ ተገኝተው ለምን ወደዚህ ውድድር እንደገቡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹በጤናው መስክ ያካበትኩት ልምድ፣ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ላይ ጥሩ ሥራ በመሥራቴና ለሙያው ፍቅር ያለኝ በመሆኑ ነው፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የኢቦላ በሽታን ለመከላከል በተደረገው እንቅስቃሴ፣ የአፍሪካ ኅብረት አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወስድ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ የሕክምና ማኅበር ጠቁሟል፡፡ የኢቦላን በሽታ በተከሰተበት ወቅት  ባለሙያዎችን ችግሩ ወደተከሰተበት ሥፍራ በመላክ አፋጣኝ ምላሽ ከሰጡ አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንድትሆን ማድረጋቸውንም እንዲሁ፡፡  

ይህም የሚያመለክተው ሰውየው ከኢትዮጵያ አልፈው ለዓለም ሕዝብ ጤንነት መጠበቅ፣ ከዚህ በፊት ጥሩ ልምድ እንደነበራቸው አንዱ ማሳያ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሒላሪ ክሊንተን በወቅቱ፣ ‹‹ለዓለም ጤና የሚጨነቁ ታላቅ ከአፍሪካ የበቀሉ ሰው፤›› ሲሉ አሞካሽተዋቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሒላሪ ክሊንተን ዶ/ር ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የኢትዮጵያን የጤና ፖሊሲ ሲደግፉና ሲያበረታቱ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ በባለቤታቸው ስም የተሰየመውና ‹‹ክሊንተን ፋውንዴሽን›› የሚባለው ዓለም አቀፍ ተቋም ዶ/ር ቴድሮስ ወደ ዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ውድድር ሲገቡ፣ የገንዘብ ድጋፍ እንዳደሩጉላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡  

የዓለም ጤና ድርጅትን በዋና ዳይሬክተርነት ለመምራት የወራት ያህል ዕድሜ የቀራቸው ዶ/ር ቴድሮስ፣ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከበስተጀርባቸው ታላላቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንደነበሩ በተለያዩ የመረጃ መረቦች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ከታላላቅ የአሜሪካ ባለሀብቶችና ፖለቲከኞች እስከ አፍሪካዊያን ቱጃሮች በድጋፍ ታጅበው ለዚህ ድል እንደበቁ ይነገራል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ እየሠራች ባለችው አኅጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሥራ ትልቅ አመኔታ መፍጠሯን በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነገር ይደመጣል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በምሥራቅ አፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተወጣ ያለው ግዳጅ፣ የአገሪቱን ሰላም ወዳድነትና ቁርጠኝነት ማሳያ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ተነግሯል፡፡ የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት መመረጥም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ እያሳየ የመጣውን ዓመኔታና ከበሬታ የሚያሳይ እንደሆነ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዛዲግ አብርሃ ይገልጻሉ፡፡ አቶ ዛዲግ፣ ‹‹አገራችን በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ውስጥ በየጊዜው እየተሸከመች የመጣችው ኃላፊነት ማሳያ ነው፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡ ባለፈው ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተለዋጭ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆና ስትመረጥም፣ ሌላኛው የዓመኔታው ማሳያ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የኮሌራ በሽታን ይፋ አላደረጉም የሚል መረጃ ኒውዮርክ ታይምስ ይፋ ካደረገ በኋላ፣ ተቃውሞዎችና አስተያየቶች ሲሠነዘሩባቸው ነበር፡፡

የምርጫ ሒደቱ ሲቃረብ በዚህ ዜና መውጣት በርካታ አፍሪካዊያንን አሳዝኖ እንደነበር የአፍሪካ ኅብረት ገልጿል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በመግለጫው፣ እንደጠቀሰው ‹‹ለአሸናፊነት የሚገሰግስን አንድ ጥቁር አፍሪካዊ በፕሮፓጋንዳ ከውድድሩ ውጪ ለማድረግ የተቃጣ ሴራ ነው፤›› ብሏል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው መሥራታቸው ለአሁኑ ድል ይጠቀሳል፡፡ እንዲመረጡ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ በጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ጊዜ የሠሯቸው ውጤታማ ሥራዎች እንደሆኑ እየተወሳ ነው፡፡ እነዚህ ፖሊሲዎች የኢትዮጵያ ፖሊሲዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የጤና ፖሊሲ እንደሚታወቀው መከላከል ላይ የተመሠረተ የጤና ፖሊሲ ነው፡፡ ይኼ ፖሊሲ ላለፉት 26 ዓመታት ተግባራዊ ሆኖ በኅብረተሰቡ ላይ ዓይነተኛ ለውጥ እንዳመጣም ይነገራል፡፡ ስለሆነም አገሪቱ ያመጣችው ለውጥ በሌሎች አገሮችም ተግባራዊ ሆኖ ለውጥ እንዲያመጣ፣ የአገሪቱ ተሰሚነትና የፖሊሲ ትክክለኛነት ማሳያ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡  

የእሳቸው መመረጥ ፋይዳው ለአፍሪካም እንደሆነ ግልጽ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ዓለም አሁን አንድ ትልቅ ተቋም ሆናለች፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ በድርጅቱ ፖሊሲ መሠረት ባለሙያዎችን በማስተባበር የሚሠሩ ግለሰብ ናቸው፡፡ ከሀብታም ተኮር የጤና ፖሊሲ ወደ ደሃ ተኮር ሊያመጡት ይችላሉ የሚል ግምትም ይሰማል፡፡ ይህ አሠራር ደግሞ በዓለም ጤና ድርጅት መርህ ላይ ተቀምጧል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የአፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት  ድርጅት (ኢጋድ) ዋና ሰብሳቢ ሆነው መሥራታቸው ይታወቃል፡፡ የኢጋድ ዋና ሰብሳቢ ሆነው በሠሩባቸው ዘመናት የደቡብ ሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት ለመፍታት የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደነበር አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

አፍሪካዊያን ለአፍሪካ መፍትሔ በማበጀትና የቀጣናው አገሮች ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደነበር የሚናገሩ አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም አገሮች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ያሸጋገሩ እንደነበሩ፣ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በአንድ ወቅት ተናግረዋል፡፡  

እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ጀምሮ በዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ሥራቸውን ሀ ብለው የሚጀመሩት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ከዚህ በፊት በድርጅቱ ውስጥ የነበሩ የበጀትና ሌሎች ተያያዝ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር የማይበልጠው ዓመታዊ በጀቱን በእጥፍ ለማሳደግ እንደሚጥሩ ገልጸዋል፡፡

ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞ ታጅበው ለድል የበቁት ዶ/ር ቴድሮስ፣ በምርጫው ካሸነፉ በኋላ ሁሉንም የዓለም ሕዝብ በእኩልነት በማገልገል በጤናው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት እንደሚፈቱ ቃል ገብተዋል፡፡ 71 በመቶ ድምፅ በማግኘት ለማሸነፍ በቅተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክም ትልቁ ድል እየተባለ ሲሞካሽ ሰንብቷል፡፡ የእሳቸው ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት መመረጥ ወደፊት ብዙ ኢትዮጵያዊያንን በማነቃቃት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው፣ የዘርፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

ከዚህ በፊት በእንደዚህ ዓይነት ዓለም አቀፍ ኃላፊነት ራሳቸውን ዕጩ ካደረጉ ኢትዮጵያዊያን መካከል በንጉሡ ዘመነ መንግሥት ልጅ እንዳልካቸው መኮንን (ለመተድ ዋና ጸሐፊነት) እና በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ደግሞ አቶ ሱፊያን አህመድ (ለአፍሪካ ልማት ባንክ ዋና ዳይሬክተርነት) ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን በወቅቱ ድል ባይቀናቸውም፣ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የድል ባለቤት በመሆን ከሁሉም እንደሚለዩና በኢትዮጵያ ታሪክም ወደፊት ትልቅ ሥፍራ እንደሚኖራቸው ከወዲሁ እየተገለጸ ነው፡፡

የዶ/ር ቴድሮስ መመረጥ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ያስደሰተ ዜና ሆኖ ሰንብቷል፡፡ መልካም ምኞትም እየጎረፈላቸው ነው፡፡ ከተቀናቃኛቸው ዴቪድ ናባሮ (ዶ/ር) ጀምሮ እስከ አፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እስከ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እና ሌሎች የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት እንደላኩላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከድል በኋላ ቅዳሜ ግንቦት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ንጋት ላይ ከስዊዘርላንድ ጀኔቫ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ አሁን ጉዳያቸው ከኢትዮጵያ አልፎ ወደ ዓለም ማኅበረሰብ ገብቷል፡፡ የእሳቸው የውሳኔ ሰጪነት በመላው ዓለም ሕዝብ ዘንድ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ በመሆኑ በቀደመ የሥራ ብቃታቸውና ተነሳሽነታቸው እንዲሠሩ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአንድም በሌላ መልዕክት እያስተላለፈላቸው መሆኑን ተሰምቷል፡፡  

ዶ/ር ቴድሮስ ለዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት መመረጥ ለአፍሪካዊያን ያለው ፋይዳ የጎላ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አፍሪካዊያን ባለሀብቶች ዳንጎቴን ጨምሮ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የውድድሩ አሸናፊ እንዲሆኑ ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የዓለም አቀፍ የጤና ሁኔታ እጅግ ውስብስብና አስቸጋሪ በመሆኑ ዶ/ር ቴድሮስ ከፊታቸው ብዙ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ሲነገር ይደመጣል፡፡ ከዚህ በፊት በአፍሪካ ተከስቶ የነበረው የኢቦላ በሽታን ለመከላከል ለድርጅቱ እጅግ ፈታኝ ጉዳይ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከበሽታው በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ባህሪ አንፃር ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ብዙ እልህ አስጨራሽ ሥራዎችን እንደጠየቀ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በወቅቱ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 9 ቀን 2006 ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ተመርጠው እስካሁን ድረስ በኃላፊነት ላይ ያሉት ቻይናዊቷ ማርጋሬት ቻን (ዶ/ር) በድንገት በተከሰቱ የኢቦላና የዚካ ቫይረሶች አማካይነት ተፈትነው እንደነበር ዶ/ር ቴድሮስ ተናግረዋል፡፡

የዶ/ር ቴድሮስ የምርጫ ቅስቀሳ ከዚህ በፊት ድምፃቸውን ለኢትዮጵያ የማይሰጡ የነበሩ አገሮችንም ሐሳብ እንዳስቀየረ ታውቋል፡፡ ለብዙ ዓመታት ከዓባይ ወንዝ የባለቤትነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ጥያቄ የምታነሳው ግብፅ ድጋፏን ለኢትዮጵያ ሰጥታለች፡፡ ይህም አፍሪካዊያን ለአፍሪካውያን ያላቸውን ቁርኝትና አንድነት የሚያሳይ ጉዳይ እንደሆነ ዶ/ር ቴድሮስ በፌስቡክ ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ ምርጫውን ካሸነፉ በኋላ ለአባል አገሮች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የምርጫውን ግልጽነት አድንቀው ተፎካካሪያቸው የነበሩትን ዴቪድና ሳኒያ አብረዋቸው እንዲሠሩ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ በአንድ ዓመት የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜያቸው ብዙ አገሮችን እንደጎበኙና በዓለም ውበት መደነቃቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ‹‹የዓለም ውበት ተራራው፣ ወንዙና ሸለቆው ሳይሆን ሰው ነው፤›› በማለት ንግግር አድርገዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት አባል የሆኑ አገሮች የሰጧቸውን ድምፅ ተጠቅመው በቅንነትና በታማኝነት እንደሚያገለግሉ ቃል ገብተዋል፡፡ ‹‹የእናንተን ድምፅ ተቀብዬ ወደ ተግባር ለመለወጥ ቃል እገባለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ትልቁ ግዴታችን ዓለምን ማገልገል ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ከእናንተ ድጋፍ ጋር እንወጣዋለን፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ ከድል በኋላ ረቡዕ ግንቦት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በስዊዘርላንድ ጀኔቭ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፣ ሁሉም መንገዶች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጤና እንክብካቤ ክፍት መሆን አለባቸው ለአባል አገሮች ሁለንተናዊ የጤና ተደራሽነትን ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ አድርገው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ በመግለጫቸው የዓለም የጤና ድርጅት ከ70 ዓመት በኋላ ጤናን ለሁሉም የዓለም ሕዝብ በፍትሐዊነት የማዳረስ ዕቅዱ ይሳካል ብለዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -