Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ሕዝብ የሚፈልገው መሠረታዊ ለውጥ እንጂ ሽንገላ አይደለም!

  ያለፉት 26 ዓመታት የኢሕአዴግ መንግሥት አገዛዝ በበርካታ ወጀቦች ውስጥ ያለፈ መሆኑን ለማስረዳት መሞከር ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል፡፡ በተለይ አገሪቱ በፌዴራል ሥርዓት መተዳደር ከጀመረች ወዲህ በርካታ ታሪካዊ ክንውኖች ተፈጽመዋል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች ብዙ ውጣ ውረዶች ታይተዋል፡፡ ኢሕአዴግ ደርግን ያስወገደበትን 26ኛ ዓመት ሲዘክር ከመቼውም ጊዜ በላይ የተነሳበትን ተቃውሞና እንቢተኝነት ጭምር እያሰበ በመሆኑ፣ አንዳንድ ጠቃሚ ጉዳዮችን ማውሳት ተገቢ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ባለፉት 26 ዓመታት የሥልጣን ቆይታው በእጅጉ የሚኩራራው በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች ባስመዘገባቸው ስኬቶች ነው፡፡ በፖለቲካው መስክ ደግሞ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመመሥረት በተደረገው ጉዞ የብሔርና የብሔረሰቦችን መብት በማስከበር፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መደላድል በመፍጠርና የቡድን መብቶችን በማስከበርም ይኩራራል፡፡ በእርግጥ በዚህ በኩል ብዝኃነትን አክብሮ ዜጎች በማንነታቸው ኮርተው በአገር ግንባታ ተሳትፎአቸው እንዲጨምር መደረጉ ትልቅ አገራዊ ጅምር መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ አዎንታዊ ለውጦች መገኘታቸው አይስተባበልም፡፡ እነዚህ ለውጦች ግን ሙሉ መሆን አልቻሉም፡፡ ወይም ደግሞ የጋራ መግባባት አልፈጠሩም፡፡ በዚህም ሳቢያ ዜጎችን ለሞት፣ አገርን ለውድመት ያጋለጠ ብጥብጥ ተከስቶ ነበር፡፡ ከወርኃ መስከረም መጨረሻ ጀምሮ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ትገኛለች፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ደግሞ ብዙ መብቶች የሚታገዱበት ነው፡፡

  ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከዚህ ሁሉ ትርምስ በኋላ ያለፉትን 15 ዓመታት በመገምገም፣ ለሕዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ‹ጥልቅ ተሃድሶ› በስፋት ማካሄዱን አስታውቋል፡፡ በዚህ መነሻም ከላይ ሳይሆን በመካለኛና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኙ አመራሮቹና አባላቱ ላይ ዕርምጃ ወስዷል፡፡ የችግሩ ስፋትና ብዛት ከተወሰደው ዕርምጃ በላይ በመሆኑ ሕዝብ አሁንም መሠረታዊ የሚባል ለውጥ እየጠበቀ ነው፡፡ ይህ ለውጥ ጥገናዊ እንዲሆን አይሻም፡፡ ለውጡ ውጤት ሊያስገኝ የሚችለው በሕጋዊ መንገድ ሥርዓት ተከትሎ ሲሆን ነው፡፡ የለውጡ መነሻና መድረሻ በሕግ የበላይነት ሥር መሆን ያለበት፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በዚህ መንገድ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ለአመፅና ለግርግር በር የሚከፍት ሕገወጥ ተግባር ግን ደም ለማፋሰስና አገርን ለማውደም ብቻ ነው የሚያገለግለው፡፡ ሕዝብ በተለያዩ መንገዶች ጥያቄ ያነሳባቸው ጉዳዮች የሚፈቱት በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ቀና መንገድ ለመከተል ደግሞ መጀመሪያ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩ መሠረታዊ መብቶች ይከበሩ፡፡ እነዚህ መብቶች ሲከበሩ ተከትለው የሚመጡ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት ከገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቷ ፖለቲካ ውስጥ በሚሳተፉ ኃይሎች ጭምር ይሆናል፡፡ ዜጎች በመልካም አስተዳደር፣ በፍትሕ፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች፣ በፍትሐዊ ተጠቃሚነትም ሆነ በሌሎች በርካታ ጉዳዮች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተጠራቅመው አገርን ለምን ችግር ውስጥ ጣሉ ሲባል፣ መንስዔአቸውን ከሥር መሠረቱ ማየት ተገቢ ነው፡፡

  ኢሕአዴግ ብዝኃነትን በማክበርና የቡድን መብቶችን በመቀበል ረገድ የሚተጋበት መሆኑ ለዓመታት ሲናገር የቆየ ቢሆንም፣ ትልቁ ችግር የሆነው ግን የሐሳብ ብዝኃነትን ለመቀበል ዳገት ሆኖበት ዓመታት ነጉደዋል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕግ በተደነገገበት አገር መጠነኛ የሐሳብ መንሸራሸሮች ቢታዩም፣ ሙሉ ሆነው ግን በሚፈለገው ደረጃ አለመገኘታቸው አሁንም ትልቁ የአገር ራስ ምታት ነው፡፡ የመጣው ይምጣ ብለው አደባባይ ወጥተው ስሜታቸውን ከሚገልጹት ጥቂቶች በስተቀር፣ አሁንም ብዙኃኑ ሕዝብ የፍርኃት ቆፈን ውስጥ ነው ያለው፡፡ የሰብዓዊ መብት አከባበር ጉዳይ አሁንም ተከድኖ ይብሰል ነው፡፡ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ብቻ በርካታ ችግሮች የደረሱባቸው ዜጎችን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ገዥ ከሆነው አንድ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውጪ ሌላ ባለመፈለጉ ብቻ የፖለቲካ ምኅዳሩ ተዳፍኗል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያግዙ ሲቪክ ተቋማት የሉም ማለት ይቻላል፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ የነበሩ ብዙዎቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፈረካክሰዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኩርፊያ በዝቷል፡፡ የሐሳብ ብዝኃነት አለመኖር ትልቁ የአገር ችግር ማሳያ ነው፡፡

  አገሪቱ በኢኮኖሚው መስክ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር የተጨበጨለት እመርታ አሳይታለች፡፡ በመንገድ፣ በባቡር፣ በኃይል፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተሞች ልማት፣ ወዘተ. ያሳየችው ከፍተኛ መነቃቃት የሥርዓቱ ትሩፋት ነው፡፡ ነገር ግን በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ረገድ በታየው አሉታዊ ገጽታ ሳቢያ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጭምር ከፍተኛ ነቀፌታ በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሕዝብ ተንገሽግሾበታል፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚገኘው የአገሪቱ ሕዝብ የአገሪቱ መልማትና ማደግ ከማንም በላይ ይፈልገዋል፡፡ ይህ ልማት ግን ቁሳዊ ጉዳይ ላይ አተኩሮ ሰብዓዊ ፍጡርን በመርሳቱ፣ ልማቱ ባለቤት የሌለው እስኪመስል ድረስ የቅሬታ ምንጭ ሆኗል፡፡ ኢሕአዴግ ባለፉት 26 ዓመታት ቆይታው ለዘመናት የነበሩ የአገር ችግሮችን እየጠቀሰ ዴሞክራሲ በሒደት እንደሚሰፍንና ሰብዓዊ መብቶች እንደሚከበሩ ቢወተውትም፣ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አልታየም፡፡ በዚህም ምክንያት የአገርንና የሕዝብን ህልውና አደጋ ውስጥ የከተተ ችግር ነው የተከሰተው፡፡ ከችግሩ ለጊዜው የተወጣውም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አማካይነት ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ለብሔራዊ መግባባትና ለዘለቄታዊ ሰላም የሚያግዙ ዕርምጃዎች በስፋትና በጥልቀት ሲወሰዱ አልታየም፡፡ ችግሮች አሁንም በራሳቸው ዛቢያ ላይ እየተሽከረከሩ ናቸው፡፡ ሕዝብ ጥያቄዎቹ ከኑሮ ውድነት፣ ከሥራ አጥነት፣ ከመልካም አስተዳደርና ከፍትሕ ዕጦት በላይ ናቸው፡፡ የራሱንም ሆነ የአገሩን ዘለቄታዊ ህልውና የሚያስጠብቁ መሠረታዊ ለውጦች ይሻል፡፡

  አሁን ዋናው የሕዝብ ጥያቄ የአገሪቱ ሰላም አስተማማኝ ሆኖ እንዴት እንደሚቀጥል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዴሞክራሲ መስፈን አለበት፡፡ ሰብዓዊ መብቶች መከበር አለባቸው፡፡ የአመለካከት ብዝኃነት መረጋገጥ አለበት፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ዕውን መሆን ይገባዋል፡፡ ዜጎች የሚፈልጉትን መደገፍ፣ የማይፈልጉትን መንቀፍ፣ በፈለጉት ሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅት መደራጀት፣ ተሳትፎአቸው ገደብ ሳይኖርበት በአገር ጉዳይ ተዋናይ መሆን፣ ለአገራቸው በሚችሉት መንገድ ሁሉ አስተዋጽኦ ማድረግ፣ በነፃነት መምረጥና መመረጥ፣ በነፃነት መዳኘት፣ በፍትሐዊ መንገድ ተጠቃሚ መሆን፣ ለሕግ የበላይነት መገዛት፣ ወዘተ. መብታቸውም ግዴታቸውም መሆን ይኖርበታል፡፡ ለሕዝብ ቅሬታና ተቃውሞ መነሻ የሆኑ አላስፈላጊ ድርጊቶች ሲወገዱና የሕዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሲከበር ብሔራዊ መግባባት ይፈጠራል፡፡ በአገር ልማት የባለቤትነት ስሜት የሚፈጠረው ዜጎች በአገራቸው በነፃነት የመሰላቸውን አመለካከት ማንፀባረቅ ሲችሉ ነው፡፡ ዋናው ትግል መሆን ያለበትም በሰላም፣ በዴሞክራሲና በብልፅግና ውስጥ የምትገኝ አገር እየተፈጠረች መሆኑን በተግባር ማሳየት እንጂ፣ ተስፋ የሚያስቆርጡ ድርጊቶች እየፈጸሙ መሸንገል አይደለም፡፡

  አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት መርገምት ሆነው ካስቸገሯት ፈተናዎች እንድትገላገል ብሔራዊ መግባባት መፈጠር አለበት፡፡ በአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ተሳትፎአቸው ሳይገደብ አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ሲሳተፉ የፈለጉትን አመለካከት ይዘው ሲሆን፣ ይህ በተግባር ይረጋገጥ ዘንድ ደግሞ መሠረቱ ካሁኑ ሊኖር ይገባል፡፡ በኢኮኖሚው የተለያዩ ዘርፎች፣ በመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ በትምህርት፣ በጤና፣ ወዘተ. የታዩት አነቃቂ ለውጦች የበለጠ ጥራታቸውና ተደራሽነታቸው እንዲጨምር ዕውቃታቸውን፣ ልምዳቸውን፣ ገንዘባቸውንና ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ይዘው የሚመጡ ወገኖች ለዚህች አገር ያስፈልጓታል፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ እየሆነ ካለው አጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ወጣቱ ትውልድ አገሪቱን መረከብ ያለበት በጥሩ መሠረት ላይ ሆና ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን የሚሆነው በጠቅላይነትና በአምባገነንነት አስተሳሰብ ባለመሆኑ፣ ለሕግ የበላይነት አሁንም ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ፡፡ በሕግ የተደነገጉ መሠረታዊ መብቶች ተግባራዊ ሲደረጉ የሚቀረው በቅደም ተከተል ይከናወናል፡፡ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ብቻ ማስተናገድ የዚህ ዘመን ባህርይ  አይደለም፡፡ አምባገነንነት ዘመን አልፎበታል፡፡ ዘመኑ በነፃነት የሚያስብ የራሱ ትውልድ አለው፡፡ ይህ ትውልድ እንደ ትናንቱ በጠመንጃ የሚታገል ሳይሆን፣ በአስተሳሰብ የበላይነት የሚያምን ነው፡፡ ሕዝብም የሚፈልገው ይህንን ነው፡፡ ሕዝብ በዚህ መንገድ መሠረታዊ ለውጥ ሲሻ አጉል ሽንገላ ውስጥ መግባት ውጤቱ ጥሩ አይሆንም!  

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...

  ኢትዮጵያ በብድርና ዕርዳታ የምታገኘው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ፓርላማው አሳሰበ

  በብድር የተገኘ ገንዘብ በሥልጠናና ውሎ አበል መልክ እንዳይባክን ተጠየቀ የሕዝብ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...