Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹ከፌዴሬሽኑ ጀምሮ የእኔነት ስሜት ወደ አትሌቶች ሠርፆ እንዲገባ አልተሠራም››

‹‹ከፌዴሬሽኑ ጀምሮ የእኔነት ስሜት ወደ አትሌቶች ሠርፆ እንዲገባ አልተሠራም››

ቀን:

 ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት

በቡድን ሥራ ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ ‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሁን በታሪክ ካልሆነ በአትሌቶቹ መካከል እምብዛም አይታወቅም፡፡ ከልምምድ ጀምሮ አብሮ መሥራትና አብሮ መብላትም የማይታሰብ እንደሆነ ይወሳል፡፡ ውጤቱም በጊዜ ሒደት አለመሻሻሉም ይታያል፡፡ ለዚህም በሪዮ ዴጄኔይሮ ኦሊምፒክ የተመዘገበውን አንድ የወርቅ ሜዳሊያ እንደ ማሳያ የሚጠቅሱ አሉ፡፡ በውድድር ዓመቱ ወደ ኃላፊነት የመጣው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራር የመበታተኑ አደጋ መኖሩን አምኖ፣ ችግር ቀደም ሲል የነበረውን አብሮ የመሥራትና የመነጋገር ባህሉ ማምጣት ከተቻለ ሥጋቱን መቀነስ ይቻላል ይላል፡፡ ፌዴሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ዕቅድ ይዞ ከሚንቀሳቀስባቸው መካከል በአትሌቱ መካከል ተፈጥሮ የቆየውን ያለመተማመን ሥጋት ማጥፋት እንደሆነም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ይናገራል፡፡  ባለፈው ሳምንት በተደረገው 46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከቀደሙት በተለየ መልኩ ስም ያላቸውና አዳዲስ አትሌቶች ተካፋይ ሆነዋል፡፡ ርቀው የነበሩ አንጋፋና ታዋቂ አትሌቶችም ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጎን መቆማቸው ለአትሌቲክሱ ዕድገት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚችሉ ታምኖበታል፡፡ በአትሌቲክሱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌን ደረጀ ጠገናው አነጋግሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- 46ኛው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ተከናውኗል፡፡ ሻምፒዮናው ካለፉት ዓመታት ለየት የሚያደርገው ነገር ይኖራል?

ኃይሌ፡- ከዚህ ቀደም አገር ውስጥ በሚደረጉ ከማናቸው ውድድሮች ታላላቅና ታዋቂ ተብለው የሚጠቀሱ አትሌቶች አይሳተፉም ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ ሁሉም ታዋቂ አትሌቶች በሻምፒዮናው እንዲሳተፉ አዲሰ ደንብና መመርያ አውጥተናል፡፡ የሚገርመው ከዚህ በፊት ከሦስትና አራት የማይበልጡት አዳዲስ ክብረ ወሰኖች ዘንድሮ አሥራ አንድ ደርሰዋል፡፡ ይኼ በራሱ የሚያሳየው የሻምፒዮናውን ትልቅነት ነው፡፡ ካለፉት ዓመታት ለየት የሚያደርገውም ይኼው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በግልህ አዳዲስ ክብረወሰን ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 10,000 ብር ማበረታቻ እንደምትሰጥ ቃል ገብተህ ነበር?

ኃይሌ፡- እውነት ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ሻምፒዮናው የዚያን ያህል ጠንካራ ይሆናል የሚል እምነትም ሆነ ግምት አልነበረኝም፡፡ እኔም ቃል በገባሁት መሠረት 110,000 መክፈሌ ግድ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡- አንተም ሆንክ እነሱ ተጨካክናችሁ ገንዘቡን ተቀባበላችሁ?

ኃይሌ፡- ቃል በተገባ ጉዳይ ወደ ኋላ የለም፡፡ እኔም እከፍላለሁ፣ አትሌቶቹም ሳያቅማሙ ነው የሚቀበሉት፡፡ አትሌቲክሳችን ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ከተፈለገ ማበረታቻዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በእኔ እምነት የአገር ውስጥ ሻምፒዮናዎች በተሻለ ተወዳጅና ተዘውታሪ እንዲሆኑ አትሌቶች የላባቸውን ውጤት ሊያገኙ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው ሁኔታ አትሌቲክሱ በትክክለኛው መንገድ ላይ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል?

ኃይሌ፡- ጅምሩ ካልሆነ ገና ብዙ የሚቀር ነገር እንዳለ ነው የሚገባኝ፡፡ ምክንያቱም የሻምፒዮናው ፉክክር የሚያበረታታ ይሁን እንጂ ተመልካች አልነበረም፡፡ ተመልካች ስፖርቱ ወደ ሚፈልገው የስኬት መንገድ እንዲያመራ የሚጫወተው ሚና የጎላ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ተመልካቹ ለአትሌቲክሱ ፍላጎት ኖሮት እንዲከታተለው የማድረግ አቅም ይኖራችኋል?

ኃይሌ፡- በሒደት የምናየው መሆኑ እንደተጠበቀ በእኛ እምነት ግን ሁሉም ነገር በፌዴሬሽኑ እንቅስቃሴና ጽናት የሚወሰን ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተና ከእናንተ በፊት በነበረው ማንኛውም አትሌት አገር ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች የሚሳተፉበት ዕድል ሰፊ ነበር ከእናንተ ትውልድ ቀጥሎ በመጣው ትውልድ ግን ታዋቂ አትሌቶች በአብዛኛው በአገር ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች መሳተፍ አቆሙ፤ ምክንያቱ ይታወቃል?

ኃይሌ፡- በዋናነት ምክንያቱ ማበረታቻ የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ማበረታቻ ለውድድሮች ድምቀት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ሌላው የእኔነት ስሜት ማጣት ነው፡፡ ይህም ሲባል ከፌዴሬሽኑ ጀምሮ የእኔነት ስሜት ወደ አትሌቶች ሠርፆ እንዲገባ ሥራ አልተሠራም፡፡ በዚህ ረገድ አሁንም ገና ነው፡፡ ወደ ውድድሮች ጥራት ስንመጣ ያን ያህል አጥጋቢ አይደለም፡፡ ቀደም ካሉት ዓመታት ዘንድሮ ታላላቆቹ ስለተሳተፉበትም ሊሆን ይችላል፣ በተለይ በአምስትና አሥር ሺሕ በሁለቱም ጾታ ፉክክሩ ከባድ ነበር፡፡ ይኼ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ድሮ በእኛ ጊዜ ከልምምድ በኋላ እዚያው እንገናኝ የምንባባልበት ሁኔታ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት በውድድሩ ከእኔ ጀምሮ ሁሉም ስለሚሳተፉ ብቻ ነው፡፡ ለወደፊቱ በአጠቃላይ የተሻለ ውጤትና ተመልካች ለማግኘት ውድድሮቻችን ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ መሥራት ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ያወጣችሁት የውድድር ደንብና መመርያ ተፈጻሚነቱ ምን ያህል ነው?

ኃይሌ፡- ሕግ ካወጣን ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡ ካልሆነ ማውጣት አያስፈልግም፡፡ ሌላውና ዋናው ቁልፍ ነገር ለውድድሩ ማጣፈጫ የምንሰጠው ማበረታቻ ነው፡፡ ማንኛውንም ታዋቂም ይሁን ታዳጊ አትሌት የግድ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና መሳተፍ አለብህ የምንልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ የምናደርገው ምንድነው ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ዕድሉን የምንሰጠው የፌዴሬሽኑን ሕግና መመርያ ለሚያከብሩ ብቻ ነው፡፡ ታዳጊ ወጣቶች ሞዴል ከሚያደርጉት አትሌት ጎን መሮጥና ራሳቸውን መገምገም ይፈልጋሉ፡፡ እኛም እንፈልጋለን፡፡ ለዚህ ደግሞ የምናወጣቸው መመርያዎች ተፈጻሚ መሆን ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የእኛ ሞዴሎች እነ አበበ መኰንን ሲሆኑ፣ እኛን የተከተሉት ደግሞ እንደነ ቀነኒሳና ስለሺን የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ቅብብሎሹ በትክክል የቱ ጋ እንደተቋረጠ ይታወቃል?

ኃይሌ፡- በእነ ቀነኒሳ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባ ጊዜ ላይ ነው፡፡ የእኛ ዋናው ጥረትም የተቋረጠውን የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቀጥል ነው፡፡ እንቅስቃሴያችን ከልብ ከሆነ ከባድ እንደማይሆንም እገምታለሁ፡፡ አትሌቶቻችን ከልምምድ ጀምሮ አብረው እንዲሠሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ፌዴሬሽን እነዚህንና ሌሎችንም በክፍተትነት የተመለከትናቸው ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በአትሌቶች መካከል ሲከሰት የሚስተዋለው ችግር በዋናነት አለመተማመን እንደሆነ ይነገራል፡፡

ኃይሌ፡- በእኔ እንደዚህ የመሰሉ አለመታመኖች ሊከሰቱ የሚችሉት አብረው ስለማይሠሩ ነው፡፡ አብረው ቢሠሩ በእርግጠኝነት ነገሮች አይኖሩም፡፡ ክፍተቱ የተፈጠረው እዚህ ጋ ነው፡፡ እንደተባለው በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ቀርቶ ለዓለም ሻምፒዮናና ለኦሊምፒክ ዝግጅት ሳይቀር አብረው የማይሠሩ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በዚህ በፌዴሬሽኑ አንዱና ዋናው ሥራ ይህን መጥፎ አመለካከት መስበር እንዳለብን ነው፡፡ የግድም ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ አድርገን ልንመለከት የሚገባን አንድ ገበሬ ወይፈኑን ለመግራት ካሰበ ከቢጤው ጋር ሳይሆን ከበሬ ጋር ነው፡፡ ይኼ የሚያሳየው ታናሽ ከታላቁ የሚማረው ነገር መኖሩን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሁለት ወራት በኋላ በሐምሌ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ይጠበቅባችኋል፡፡ ለዚያስ ምን ያህል እየተዘጋጃችሁ ነው?

ኃይሌ፡- ጥያቄው ከውጤት አንፃር ከሆነ አጥጋቢ ውጤት እናመጣለን የሚል እምነት አይኖረኝም፡፡ ትልቅ ፈተና እንደሚጠብቀን እጠብቃለሁ፡፡ ምክንያቱም ዓምና በተከናወነው የሪዮ ዴጄኔሮ ውጤት በራሱ ቀደም ሲል የነበረው ነፀብራቅ እንጂ ታቅዶ አይደለም፡፡ አንድ ወርቅ ተገኝቷል፡፡ ያንን በለንደኑ የዓለም ሻምፒዮና ከተባልኩ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ በግሌ በሙሉ እምነት መናገር የምችለው ውጤት ከሁለት ዓመት በኋላ ነው፡፡ ዕቅዳችንም የሚያሳየን ይህንኑ ነው፡፡ ብዙዎቻችን በአንድና በሁለት ሦስት በምናስመዘግባቸው ሜዳሊያዎች ስንሸወድ ነው የኖርነው፡፡ የብራዚል ውጤታችን ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ከእንግዲህ ግን በአንድ ወይም በሁለት አትሌቶች ላይ መተማመን በፍፁም የምንደግፈው አይደለም፡፡ ለዚህም ነው በለንደኑ የዓለም ሻምፒዮና ውጤት አታስቡ ለማለት ያስደፈረኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ከኃላፊነት መሸሽ አይሆንም?

ኃይሌ፡- ያለውን እውነትና መሬት ላይ ያለውን መናገር እንዴት ነው ከኃላፊነት መሸሽ የሚሆነው? እኔ ራሴን ማታለል አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም ሌሎች አገሮች በሰፊ ልዩነት ርቀውናል፡፡ ይህንን ለማንበብ ደግሞ ከታች ጀምሮ መሥራት የግድ ይላል፡፡ በእርግጥ ያሉትን ጠጋግነን ተፎካካሪ ለመሆን እንሠራለን፡፡ ከትልልቆቹ አትሌቶቻችን ጀምሮ እስከታችኛው ታዳጊ ድረስ አንዱ ከሌላው ጋር አይደማመጥም፡፡ ይኼ ነው በአትሌቶቹም ሆነ ውጤቱ ላይ መስዕዋትነት እያስከፈለ ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- በለንደኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውጤት እንደማይመጣ ያረጋገጣችሁት ምን ዓይነት ጥናት አድርጋችሁ ነው?

ኃይሌ፡- እውነቱን ለመነጋገር ከሆነ ይህን ኃላፊነት በተቀበልን ማግስት በአትሌቲክሱ ዙሪያ ያለውን ጠንካራና ደካማ ጎን ተመልክተናል፡፡ ግኝታችንም በአጭር ጊዜ አጥጋቢ ውጤት ማግኘት የማይቻልባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አትሌቱ በቁጥር ደረጃ በጣም ብዙ ነው፡፡ ግን የቁጥሩ መብዛት ካልሆነ በትልልቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች እየገጠሙን ካሉት ተፎካካሪ አገሮች አንፃር የሚያስኬድ የሚያመፃድቅ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ብዙ ያልተገሩ ‹‹ወይፈኖች›› ናቸው ያሉን፡፡ እነዚህ ወይፈኖች አጣማጅ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ትክክለኛውን አጣማጅ ለማግኘት ደግሞ ጊዜ ይጠይቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ለለንደኑ የዓለም ሻምፒዮና ኔዘርላንድ ሔንግሎ በርካታ አትሌቶች ልካችሁ ሚኒማ እንዲያመጡ ለማድረግ ዕቅድ አላችሁ?

ኃይሌ፡- ኢትዮጵያውያን የሚታወቁበት በተለይ 10,000 ሜትር ውድድር ከዓለም ላይ እየጠፋ ነው፡፡ ለዚሁ የዓለም ሻምፒዮና ሚኒማ ለማምጣት እንዲረዳን አትሌቶቻችንን በጆን ሴርመንስ እገዛ ወደ ሔንግሎ እንልካለን፡፡ ከሰኔ 1 ቀን ጀምሮ አትሌቶቹ ወደ ሥፍራው ያመራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ አትሌቲክሱን መሸጥ ጀምሯል፡፡ በቅርቡ ከሶፊ ማልት ጋር የገባው በ30 ሚሊዮን ብር የአምስት ዓመት የስፖንሰርሽፕ ስምምነት ይጠቀሳል?

ኃይሌ፡- ጀምረነዋል እንቀጥልበታለን፡፡ ነገር ግን ችግሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የስፖንሰርሽፕ ስምምነት አሁንም እንደልመና ካልሆነ የጋራ ተጠቃሚነት የሚባለው ገና ነው፡፡ ከሔኒከን ጋር ለዚህ ስምምነት የበቃነው ካምፓኒው ዓለም አቀፋዊ አሠራሩን ስለሚያውቀው ነው፡፡ ይሁንና ተስፋዎች አሉ፡፡ እንገፋበታለን፡፡ በአገራችን ብዙ ተስፋ ይነገራል ወደ መሬት ለመውረድ ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ ዓለም ላይ ስፖርተኞች ከፎርሙላ ዋን ጀምሮ የማይሠሩት ማስታወቂያ የለም፤ የአገራችን ሌጀንዶች ለዚህ የታደሉ አይደሉም፡፡ ለነገሩ ራሳቸው ሌጀንዶቻችን በዚህ ረገድ ጥቅም ላይ መዋል ይችሉ ዘንድ ራሳቸውን አላስተዋወቁም፡፡ ወደ ኅብረተሰባችን ስንመጣ ደግሞ ለእነ ሜሲና ሮናልዶ ካልሆነ ቅርባችን ለሚገኙት ተገቢውን ትኩረት የመስጠት ችግር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- አትሌቲክሱን ጨምሮ ለሌሎችም ስፖርተኞች ዕድገት መቀጨጭ እስካሁን ከተነጋገርንበት ውጪ ምክንያት ነው የምትለው ይኖራል?

ኃይሌ፡- በጣም አለ፡፡ በአገራችን ሁለት ነገሮች የተምታቱብን ይመስለኛል፡፡ ምንድነው መወዳደሪያና ማዘውተሪያ የምንላቸው መሠረተ ልማቶች በውል የተረዳናቸው አይመስለኝም፡፡ ባለው ተጨባጭ እውነታ ከፈረሱ ጋሪው ዓይነት አካሄድ እየሄድን ነው፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ለመወዳደሪያ የሚሆኑ እጅግ ዘመናዊ ስታዲየሞች ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡ በማዘውተሪያ አዲስ አበባን ብንመለከት ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ የለም፡፡ ለምን? ተብሎ እየተጠየቀም አይደለም፡፡ በ1980ዎቹ አዲስ አበባ በመጣሁበት ጊዜ በየሠፈሩ ብዙ ማዘውተሪያዎች ነበሩ፡፡ አሁን ግንባታ ካልሆነ ታዳጊዎች የሚያዘወትሩባቸው ቦታዎች የሉም፡፡ በየክልሉ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የጠየቁ ስታዲየሞች እየተገነቡ ነው፡፡ ለምን ለማዘውተሪያስ? ሁላችንም ኃላፊነት ሊሰማን ይገባል፡፡ የሚገርመው ሞሮኮአዊው የቀድሞ አትሌት ኤል ጉሩሽ ባለፈው ሳምንት እዚህ አዲስ አበባ መጥቶ ሸራተን ባረፈበት ሰዓት እንቅስቃሴ ለማድረግ አስቦ ቦታውን እንዳሳየው ጠየቀኝ፡፡ እንጦጦ ካልሆነ አታገኝም ስለው ምን ያህል እንደተገረመ ታዝቤያለሁ፡፡ ስፖርትን ለገንዘብ ማግኛ ብቻ አድርገን መመልከት የለብንም፡፡ ጤናማና አምራች ዜጎችን የምናፈራበት ነው፡፡ ትውልድ የምንቀርፅበት የሙያ ዘርፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በቅርቡ ለተቋቋመው የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት በጀትና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ተሰምቷል፡፡ ምክንያቱ ይታወቃል?

ኃይሌ፡- እንደሚታወቀው እኛ እንደ አገር ለዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆነ ለዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (ዋዳ) ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠርን ነው፡፡ ውጤትም እያገኘንበት ነው፡፡ ምንም እንኳ ዋዳ አሁንም ኢትዮጵያ በጉዳዩ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ከሚያደርግባቸው አምስት የዓለም አገሮች አንዷ መሆኗ ቢታመንም ችግሮችን መቆጣጠር በሚያስችል ሁኔታ ላይ መገኘታችን ግን በዓለም አቀፍ ተቋም ጥሩ ተብሎ የተወሰደበት አግባብ ነው ያለው፡፡ ለዚያ የሚሆነውን በጀት ደግሞ መንግሥትም የድርሻውን፣ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በጋራ ተደጋግፈንና ተጋግዘን ለመሥራት መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቀደም ሲል በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ለኦሊምፒክ ዝግጅት ካልሆነ እንዲህ እንደ አሁኑ የእኔነት ስሜት አልነበረውም፡፡ አሁን ግን የመንግሥት አካሉ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርም ሆነ ሁለቱ ተቋማት ተናበው እየሠሩ ነው፡፡ በዚህም አይኤኤኤፍም ሆነ ሌሎች ከሚጠይቁን በላይ በራሳችን ተነሳሽነት ጭምር እየሠራን እንገኛለን፡፡ ብሔራዊው የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤትም በጠንካራ ባለሙያዎች የተዋቀረ በመሆኑ ተገቢውን እንቅስቃሴ እያደረገም ነው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...