Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊወደ መካከለኛ የተሸጋገሩ ማኅበራት የአዲስ አበባ አስተዳደርን አማረሩ

ወደ መካከለኛ የተሸጋገሩ ማኅበራት የአዲስ አበባ አስተዳደርን አማረሩ

ቀን:

ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ የተሸጋገሩ ማኅበራት ድጋፍ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ፣ ከሥራ ውጪ እየተገፉ መሆኑን ገለጹ፡፡ በተለይ በአራተኛውና በአምስተኛው ዙር ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት የተሸጋገሩ 147 ማኅበራት፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ብሶታቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቢያቀርቡም፣ አጥጋቢ ምላሽ አልተሰጠንም ሲሉ አማረዋል፡፡

የእነዚህ ማኅበራት ወኪሎች ግንቦት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ለከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ለካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው ያሉባቸውን ችግሮች አቅርበዋል፡፡ አቶ አሰግድ የተፈጠረው ችግር በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ቢሮ ሊፈታ የሚችል በመሆኑ እዚያ እንዲጨርሱ እንደ ገለጹላቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የማኅበራቱ ችግሮች ማጠንጠኛ በዋናነት ሁለት ሲሆኑ፣ እነሱም በኮንስትራክሽንና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያሉ ናቸው፡፡

በኮንስትራክሽን ዘርፍ ቀደም ሲል ወደ መካከለኛ ለተሸጋገሩት ማኅበራት የገበያ ትስስር ይፈጠር ነበር፡፡ የገበያ ትስስር ከተፈጠረ በኋላም፣ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ብድር ይመቻች ነበር፡፡

የማኅበራቱ ወኪል አቶ ዮሐንስ ገብሬ፣ ‹‹ወደ መካከለኛ ስንሸጋገር ደረጃ ስድስት ኮንትራክተር ተብለን ነው፡፡ ይህ ደረጃ ለግል ኩባንያዎች ሲሰጥ በርካታ መሟላት ያለባቸው መሣሪያዎች አሉ፡፡ እኛ ግን ከጥቃቅን ያደግን በመሆኑ የአቅም ውስንነት ስላለብን፣ መንግሥት እስከ 17 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ሥራ በተለያዩ መንግሥታዊ ፕሮጀክቶች ውስጥ ይሰጠናል፡፡ ሥራ ስናገኘም የተለያዩ  መሥሪያዎችን ለመግዛት ብድር ማግኘት እንችላለን፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ግን መንግሥት የሚያደርግልን ድጋፍ በመቆሙ፣ ከሥራ ውጭ ሆነናል፤›› ብለዋል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያለው ችግር ደግሞ የመሥሪያ መሬት ነው፡፡ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ዙር ወደ መካከለኛ ያደጉ ማኅበራት የመሥሪያ ቦታ ሲሰጣቸው ቆይቷል፡፡ ማኅበራቱ በአሁኑ ወቅት ቦታ እየቀረበ ባለመሆኑ ‹‹ለችግር እየተዳረግን ነው›› በማለት ላይ ናቸው፡፡

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ልዑልሰገድ ይፍሩ፣ ‹‹እነዚህ ወደ መካከለኛ የተሸጋገሩ ማኅበራትን በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሉትን ለኮንስትራክሽን ቢሮ፣ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያሉትን ለኢንዱስትሪ ቢሮ አስረክበናል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ ልዑልሰገድ፣ ‹‹ቅሬታ ሲያሰሙ ግን አያገባንም ሳንል አዳምጠናል፡፡ ከቢሮዎቹ ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት እየሞከርን ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹መታወቅ ያለበት ጉዳይ ወደ መካከለኛ ያደጉት ማኅበራት ከእኛ ጋር ለዓመታት ቆይተዋል፡፡ የተቻለንን ሁሉ አድርገናል፡፡ በማድረግ ላይም እንገኛለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ምንም ሥራ የሌላቸውን ወጣቶች ወደ ሥራ ማስገባት ደግሞ ይኖርብናል፤›› ሲሉ አቶ ልዑልሰገድ ተናግረው፣ ‹‹ለኮንስትራከሽን ማኅበራቱ በ2010 ዓ.ም. በሚጀመሩ የኮንዶሚኒየም ቤቶች የሥራ ትስስር እንዲፈጠርላቸው፣ ለማኑፋክቸሪንግም  ሥራ በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ከኢንዱስትሪ ቢሮ ጋር እየሠራን ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የማኅበራቱ ተወካዮች ግን ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ዛሬ ነገ እየተባሉ መቆየታቸውን፣ አሁን ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት ጠብቁን መባላቸውን ተቃውመዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...