በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ሆቴሎች እየተገነቡ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሥሩ የሚገኘውን ብሔራዊ ሆቴል ከመስተንግዶ አገልግሎት ውጪ እንዲሆን ወሰነ፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለብሔራዊ ሆቴል አስተዳደር በቁጥር 1535/09 በጻፈው ደብዳቤ፣ ሆቴሉ ለወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ለቢሮ አገልግሎት እንዲውል የተከራየ በመሆኑ ከግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ሥራ እንዲያቆም አዟል፡፡
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትዕዛዝ መሠረት በማድረግ የብሔራዊ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ብርሃን ለሆቴሉ የሥራ ኃላፊዎች ባስተላለፉት የውስጥ ማስታወሻ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የሒሳብ ሥራ እንዲጠናቀቅ፣ በውጭ ኦዲተር እንዲመረመር፣ የንብረት ቆጠራ እንዲደረግ፣ ያልተሰበሰበ የሽያጭ ገንዘብ እንዲሰበሰብና ክፍያዎችም እንዲጠናቀቁ አሳስበዋል፡፡
ስለሚያገኙት ጥቅማ ጥቅም እርግጠኛ መሆን ያልቻሉ የብሔራዊ ሆቴል ሠራተኞች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሆቴሉ ትርፋማ ሆኖ እያለ ሥራውን አስቁሞ ለቢሮ የማከራየት ጠቀሜታው አልገባቸውም፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ገብረ እግዚአብሔር ገብረማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሆቴሉ ሥራ ትርፋማ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ የያዘውን ዓላማ ከማሳካት አንፃር ከዚህ ሥራ ውስጥ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡
‹‹ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ለመደጋገፍ አከራይተነዋል፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ገብረ እግዚአብሔር፣ ሠራተኞቹም የተሻለ ጥቅማ ጥቅም ያገኛሉ ብለዋል፡፡ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሆቴል ዲሊኦፖል አጠገብ በሚገኝ ሕንፃ ውስጥ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
በመሀል አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ከእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት የሚገኘው ብሔራዊ ሆቴል ባለ ሰባት ፎቅ ነው፡፡ ሆቴሉ 50 የመኝታ ክፍሎችና የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ክፍሎች አሉት፡፡
ሆቴሉ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በ1961 ዓ.ም. የተገነባ ሲሆን፣ በወቅቱ የተገነባበት ዓላማ ለመኖሪያ አፖርታማ እንዲውል ነበር፡፡ ነገር ግን በደርግ ዘመን በተለይ በ19ኛው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ወቅት የሆቴል ክፍሎች እጥረት በማጋጠሙ፣ አፓርትመንቱ የሆቴል አገልግሎት እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡
ከዚያ ጊዜ በኋላ የሆቴል አገልግሎት በመስጠት ላይ እያለ የቀድሞው የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ፣ ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ17.6 ሚሊዮን ብር ሽያጭ አስተላልፎታል፡፡
አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ራሱን ለመደጎም በተለይ ለአፍሪካ ውድድሮች የተመረጡ አትሌቶችን ለማሳረፍ የገዛው ብሔራዊ ሆቴል፣ የዘርፍ ለውጥ እንዲያደርግ ወስኗል፡፡
አቶ ገብረ እግዚአብሔር እንዳሉት፣ አትሌቶቹን በዚህ ሆቴል ማሳረፍ ከባድ ነው፡፡ የከተማው የአየር ብክለት እየጨመረ በመምጣቱ አትሌቶች ከከተማ ውጭ ማረፍ ይኖርባቸዋል፡፡