Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጂቡቲ መንግሥት ከ590 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ያደረገበት የዶራሌህ ወደብ ግንባታ ተጠናቀቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅትን ድርሻ ለመግዛት የሚደራደረው የቻይና ኩባንያ ባለድርሻ ሆኗል

የጂቡቲ መንግሥት ከአራት ዓመት በፊት ያስጀመረው የዶራሌህ ሁለገብ ወደብ ግንባታ በ590 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ገንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ይፋ አደረገ፡፡

የዶራሌህ ሁለገብ ወደብን ጨምሮ አራት ወደቦችን የጂቡቲ መንግሥት እየገነባ ነው፡፡ ከአራቱ ወደቦች የግንባታ ሥራው የተጠናቀቀው ዶራሌህ ወደብ በጠቅላላው 690 ሔክታር መሬት የሚያካልል ሰፊ ይዞታ ያለው ነው፡፡

የጂቡቲ ወደቦች አስተዳደርና ነፃ የኢኮኖሚ ዞን ባለሥልጣን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ በጂቡቲ መንግሥት የ76.5 በመቶ ድርሻ እንዲሁም ቻይና መርቻንት ሆልዲንግስ በተባለውና ግንባታውን ባከናወነው ኩባንያ የ23.5 በመቶ ድርሻ የተገነባው የዶራሌህ ወደብ 57 ሔክታር የሚሸፍን ጠቅላላ የጭነት ቦታ ሲኖረው፣ ትልልቅ ብትን ጭነቶች የሚስተናገዱበት 20 ሔክታር የሚሸፍን ስፋት ያለው ተርሚናል፣ እንዲሁም 23 ሔክታር የሚሸፍን የኮንቴይነር ማስተናገጃ፣ 15 ሔክታር የመኪና ጭነቶች (ሮ ሮ) መጫኛና ማውረጃ ቦታን ጨምሮ 35 ሺሕ ካሬ ሜትር የማከማቻ መጋዘንና ሌሎችም አገልግሎት የሚሰጥበትን ቦታ አካቶ የተገነባ ነው፡፡ የወደቡ ግንባታ በመጠናቀቁ ረቡዕ ግንቦት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በጂቡቲ ፕሬዚንት ኦማር ጊሌይና በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በይፋ ተመርቋል፡፡

ከ90 በመቶ በላይ የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ዕቃዎች ሲያስተናግድ የቆየው የጂቡቲ ወደብ እያደገ በመጣው ከፍተኛ ጭነት ሳቢያ እየተጣበበ በመምጣቱ፣ አዳዲስ ወደቦችን ለመገንባት መነሳቱን የጁቡቲ መንግሥት ይፋ ካደረገ ከአራት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ይሁንና የሚያስፈልገውን የፋይናንስ መጠን ሊያገኝ ባለመቻሉ ምክንያት፣ በወደቦቹ ግንባታ መጓተት መከሰቱን ማስታወቁን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

የዶራሌህ ወደብን የገነባው የቻይናው መርቻንት ሆልዲንግስ ኩባንያ፣ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት ንብረት የሆነውን የንግድ መርከብ ድርጅትን የ40 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ጥያቄ አቅርቦ ድርድር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳ የጂቡቲ መንግሥት ከነባሩ የጂቡቲ ወደብ ባሻገር ግዙፉን የዶራሌህ ሁለገብ ወደብ ይፋ ቢያደርግም፣ በሰኔ ወር ሥራ የሚጀምሩትን የፖታሽ ማስተናገጃ ወደቡን የታጁራህ ወደብ እንዲሁም የጨው ምርት ማስተናጃውን የጎውበት ወደብ ለሥራ እንደሚያዘጋጅ ይፋ አድርጓል፡፡ ከሁለቱ በተጨማሪ የቁም ከብት የሚስተናገድበትን የዳመርጆግ ወደብ ግንባታ አጠናቆ ለሥራ ማዘጋጀቱም አስታውቋል፡፡

ምንም እንኳ የጂቡቲ መንግሥት ተጨማሪ አራት ወደቦችን በማዘጋጀት በአብዛኛው የኢትዮጵያን የገቢና ወጪ ዕቃዎች በቅልጥፍና ለማስተናገድ ያለውን ፍላጎት በተግባር እያሳየ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሌሎች አገሮች የሚገኙ አማራጭ ወደቦችን ማፈላለጉን አልገታም፡፡ በቅርቡ ይፋ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት፣ በሶማሌላንድ በሚገኘው የበርበራ ወደብ የ19 በመቶ ድርሻ በመግዛት በወደቡ የባለቤትነት ብቻም ሳይሆን የተጠቃሚነት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሱዳን በሚገኘው ፖርት ሱዳን ወደብም ከፍተኛ የማዳበሪያ ጭነቶችን ማስገባት ከጀመረ ሁለት ዓመታት አስቀጥሯል፡፡

ይህም ቢሆን ግን በየዓመቱ በጂቡቲ ወደብ የሚስተናገዱና ትራንዚት የሚያደርጉ መርከቦች ቁጥር በየጊዜው ጭማሪ እያሳየ መሆኑን የሚገልጸው የጂቡቲ መንግሥት ከእስያ፣ ከአውሮፓና ከአፍሪካ አገሮች የሚመላለሱ ከ30 ሺሕ በላይ መርከቦችን በማስተናገድ የ20 በመቶ ጭማሪ የሚታይበት ከ5.7 ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት በየዓመቱ በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ይሁንና በተናጠል ይህን ያህል ድርሻ ካለው ጭነት ውስጥ በአብዛኛው የኢትዮጵያ መሆኑን በስም ጠቅሶ ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡   

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች