ከስምንት ወራት በፊት መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ልዩ ቦታው አርሰዴ በሚባለው ሆራ ሐይቅ ዳርቻ በሚከበረው በዓል ላይ፣ የኦነግ ባንዲራ በማውለብለብና ከአባገዳዎች ድምፅ ማጉያ በመንጠቅ ባስተላለፉት መልዕክት በተፈጠረ ረብሻና ግርግር 55 ሰዎች እንዲሞቱ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች፣ ዓርብ ግንቦት 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ከኦነግ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም በየዓመቱ ከተለያዩ አካባቢዎች በመሰብሰብ ቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረውን በዓል ለመታደም በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተሰበሰቡበት፣ ብጥብጥና ረብሻ በማስነሳት የ55 ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ አድርገዋል የተባሉ ተከሳሾች በቅጽል ስሙ ቶሎሳ መልካ የሚባለው ቱፋ መልካ ሆርዶፋና በቅጽል ስሙ ሳባ ጄዴ የሚባለው ከድር በዳሶ ዋቆ እንደሚባሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ቱፋ መልካ የተባለው ተከሳሽ የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ቀን የዕለቱ የክብር እንግዳ አባገዳው ንግግር ለማድረግ በዝግጅት ላይ እያሉ፣ ከመድረኩ በስተጀርባ ከተደበቀበት በመውጣት የድምፅ ማጉያውን እንደነጠቃቸው ክሱ ይገልጻል፡፡ ተከሳሹ ‹‹መንግሥት ቻዎ ቻዎ›› በማለት ከተናገረ በኋላ በሕዝቡ መካከል የነበሩ የኦነግ አባላት፣ የኦነግን ባንዲራ ከፍ አድርገው ማውለብለባቸውን በክሱ ተገልጿል፡፡ ‹‹በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አይገዛንም›› በማለትም እጃቸውን አጣምረው ወደ ላይ ከፍ እያደረጉ ምልክት በማሳየት ከፍተኛ የሆነ አመፅና ሁከት እንዲቀሰቀስ ማድረጉን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡
ከድር በዳሶ የተባለው ተከሳሽም የኦነግ አመራር ለሆኑት አቶ ጀዋር መሐመድ በተለያዩ ስልኮች የቀረፃቸውን ምሥሎችና እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም ፎቶዎች በማስተላለፍ በፌስቡክና በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) በቀጥታ እንዲሠራጭ ማድረጉን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ አቶ ጀዋር በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክና በፌስቡክ ባስተላለፉት መልዕክት የመንግሥት ንብረትና የባለሥልጣናት መኖሪያ ቤትን ማውደም እንዳለባቸው መመርያ መስጠታቸውንም አክሏል፡፡ በመሆኑም በመቂ፣ ሻላ፣ ቡሌሆራ፣ ኮፈሌ፣ ቆሬኛ፣ ሲራሮ ላይ ተግባራዊ ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ኦነግ የሰጣቸውን ተልዕኮ ለማሳካት በቀጥታ ተሳታፊ በመሆን፣ አመፅን በመምራት፣ በሌሎችም አካባቢዎች አመፁ እንዲቀጥል በማድረግ በኢሬቻ በዓል ላይ 55 ሰዎች እንዲሞቱና ቁጥራቸው ያልታወቁ በርካታ ሰዎች ላይ ከፍተኛና ቀላል የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቶ ገልጿል፡፡
ተከሳሾቹ ድርጊቱን የፈጸሙት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀናለ)ን፣ አንቀጽ 35፣ 38 እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 (1እና2) ሥር የተደነገጉትን ተላልፈው መሆኑን ገልጾ፣ የሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ እንደመሠረተባቸው የክስ ቻርጁ ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ክስ የተሰጣቸው ሲሆን፣ በቀጣይ ቀጠሮ ከጠበቃ ጋር ተመካክረው ሲመጡ ግንቦት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደሚነበብላቸው ፍርድ ቤቱ አስታውቆ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡