የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2010 በጀት ዓመት ለሚያስጀምራቸው አዳዲስ መንገዶች ግንባታዎችና ለተያያዥ ሥራዎች 45 ቢሊዮን ብር በበጀት እንደሚያስፈልገው ታወቀ፡፡ ለመንግሥት ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ የበጀት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ከአበዳሪ ተቋማት ደግሞ አሥር ቢሊዮን ብር ይፈልጋል፡፡
ከባለሥልጣኑ በተገኘው መረጃ መሠረት፣ ለአዲሱ የበጀት ዓመት በመንግሥት እንዲፈቀድለት ያቀረበው በጀት 35 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከአበዳሪዎች ይገኛል ብሎ የያዘው ደግሞ አሥር ቢሊዮን ብር ስለሆነ፣ በጥቅሉ በ2010 በጀት ዓመት በ45 ቢሊዮን ብር በጀት ለመንቀሳቀስ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡
ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ ያስፈልገኛል ብሎ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ያቀረበው ረቂቅ በጀት፣ ባለፈው ዓመት ከተፈቀደለት በጀት ጋር ተቀራራቢ ነው ተብሏል፡፡ ከመንግሥት ከፍተኛ በጀት ከሚያዝላቸው ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ለ2010 ዓ.ም. ያስፈልገኛል ብሎ በጠየቀው በጀት በዋናነት ከ76 በላይ የአዳዲስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር እንደሚውል ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በአዲሱ በበጀት ዓመት ግንባታቸውን ለማስጀመር ከታቀዱ ትልልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከጂማ-አጋሮ-ዴዴሳ (ኦሮሚያ) ያሶ-ገላሶ-ጅባቴ (ቤንሻንጉል ጉምዝ)፣ ከጉባ-ዲማ (ጋምቤላ)፣ ከጎዴ-ቀላፎ (ኢትዮ-ሶማሌ)፣ ከድም-ሰቆጣ-አግቦ (ትግራይ) ከተርጫ-ወልደ ሃና-ወረቦ-አምናዳ (ደቡብ) ይጠቀሳሉ፡፡
በአማራ ክልል ደግሞ የተለየ ዲዛይን ተሠርቶላቸው ግንባታቸው ይጀመራሉ ተብለው ከሚጠበቁት ፕሮጀክቶች መካከል ባህር ዳር-ባይፖስ-ዓባይ ድልድይ ፕሮጀክት ይገኛል፡፡ ይህም ፕሮጀክት በባህር ዳር ዓባይ ወንዝን የሚያቋርጥ አዲስ ድልድይ ግንባታን ያጠቃለለ ነው፡፡
ከአሳይታ ተነስቶ ጂቡቲ ድንበር ድረስ የሚደርሰው መንገድ በ2010 በጀት ዓመት ይጀመራሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ የ2010 በጀት ዓመት ዕቅድ በሁሉም ክልሎች በተደጋጋሚ ጥያቄ የቀረበላቸውን የመንገድ ግንባታዎች በዋናነት ታሳቢ አድርጎ የተቀረፀ መሆኑን የባለሥልጣኑ መረጃ ይጠቁማል፡፡
ባለሥልጣኑ በ2008 በጀት ዓመት ከ25 በላይ የግንባታ ውሎችን መፈጸሙ ይታወሳል፡፡ በ2009 በጀት ዓመትም እስካሁን ድረስ ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃሉ የተባሉ 50 የአዳዲስ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን መፈራረሙን ባለፈው ዕትም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የ2009 በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት በሚቀጥሉት ሳምንታት በተከታታይ ከ20 የተጨማሪ አዳዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶች ኮንትራቶች ይፈረማሉ ተብሎ ስለሚጠበቅ፣ በ2009 በጀት ዓመት ከ70 በላይ አዳዲስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ኮንትራቶች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ይፈረማሉ ተብለው የሚጠበቁት ፕሮጀክቶች ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ አላቸው ተብሏል፡፡ በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በተከታታይ የግንባታ ውላቸው ይፈረማል ከተባሉ ፕሮጀክቶች ውስጥ፣ የፍስሐ ገነት-ሲያማ ኪሎ ሜትር 90፣ የጅማ-ጭዳ፣ የቴፒ-ሚዛን፣ የአቦምሳ-አስኮ-ባዳይ-ጨለለቃ (2 ኮንትራቶች)፣ የደብረ ብርሃን-አንኮበር፣ የኮንቾ-ካማሺ፣ የውቅሮ-ሐውዜን-ነበለት-ፈላፍል የመንገድ ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ይህም ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመት ከዕቅዱ በላይ የሆኑ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን መፈረሙን ያሳያል፡፡
በ2009 በጀት ዓመት በዕቅድ ይዞት የነበረው የአዳዲስ መንገዶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ቁጥር 69 እንደነበር ይታወሳል፡፡ ባለሥልጣኑ የአዳዲስ ኮንትራቶችን ቁጥር ከፍ ያደረገው በመንግሥት ከተያዘው በጀት ውጪ፣ በውጭ ብድር የሚገነቡ ፕሮጀክቶች በመታከላቸው ነው ተብሏል፡፡ ለዚህም የሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ለአብነት ይጠቀሳል፡፡ ባለሥልጣኑ በ2008 በጀት ዓመት 33.1 ቢሊዮን ብር በጀት የተፈቀደለት ሲሆን፣ በ2009 ዓ.ም. ደግሞ 33.2 ቢሊዮን ብር እንደተፈቀደለት ይታወሳል፡፡
ለ2010 በጀት ዓመት ለመንግሥት ያቀረበው 35 ቢሊዮን ብር የበጀት ጥያቄ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ታይቶና ማስተካከያዎች ከተደረጉለት በኋላ፣ ለፓርላማ ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡