Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የግል ትምህርት ቤቶች ታቀቡ!

ወላጆች ልጆቻችንን ከምናስተምርባቸው ትምህርት ቤቶች በሰኔ ወር መጨረሻ ለልጆቻችን ከሚቀበሉት ካርድ ጋር የሚላክልን በመጪው ዓመት የወርኃዊ ክፍያ ጭማሪ መደረጉን የሚገልጽ መልዕክት ነው፡፡ በመሆኑም በአዲሱ ዓመት ምን ያህል ዋጋ ይጨምሩቡን ይሆን? በሚል ሥጋት መወጠራችን አይቀሬ ነው፡፡ በዓመት ለትምህርት ቤቶች የምንከፍለው ክፍያ ከመስከረም እስከ ሰኔ ያለውን ጊዜ እንደሚሸፍን ቢታመንም፣ ልጆቻችን ላልተማሩባቸው የሐምሌና የነሐሴ ወራትም በተዘዋዋሪ መንገድ መክፈላችን አይቀርም፡፡ ይህ ለመሆኑ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን መመዝገቢያ የሚጠየቀው ክፍያ ገና የሐምሌ ወር ሳያልቅ መጠየቃችን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ለአዲሱ ዓመት ጭማሪ የታከለበት ወርኃዊ ክፍያ እንዲከፈል መደረጉ በየወሩ ይከፍሉት የነበረው ክፍያ ሰኔ ላይ አለማቆሙን እንገነዘባለን፡፡ ስለዚህ ልጆቻችንን ትምህርት ቤት ባልሰደድንበት ሐምሌና ነሐሴም እየከፈልን ነው፡፡

በአብዛኛው ሰኔ 30 የሚጠናቀቀው የትምህርት ዘመን ካለቀ በኋላ በተለይ የግል ትምህርት ቤቶች እንድንከፍል የሚያስገድዱን ክፍያ የቀጣዩ የትምህርት ዘመን የምዝገባና ጭማሪ የታከለበት የወርኃዊ ወይም የተርም ክፍያ ቀድማችሁ አምጡ ማለታቸውም አስረጅ ነው፡፡ ስለዚህ የተለመደ አሠራራቸው በሁለቱ ወራት ውስጥ ላልሰጡን አገልግሎት እንድንከፍል ከማስገደድ አይተናነስም፡፡ የዘንድሮው ግን ለየት ብሎብኛል፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች ተመካክረው የፈጸሙት ይመስል ለመጪው የትምህር ዘመን እስካሁን ስንከፍለው ከቆየነው ወርኃዊ የአገልግሎት ክፍያ ላይ ጭማሪ ስለማድረጋቸው ትዕዛዝ ያደረሱን ጭራሹን የሰኔ ወር ሳይገባ ከሚያዚያ መጨረሻ ጀምሮ ነው፡፡ በርካታዎቹ የግል ትምህርት ቤቶች ጭማሪ ማድረጋቸውን ያሳወቁበት መንገድ ይለያይ እንጂ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውን ሲያሳውቁ ቆይተዋል፡፡  

ፈሬኃ እግዚአብሔር ያደረባቸው ትምህርት ቤቶች ወላጆችን ጠርተው ስላደረጉት የዋጋ ጭማሪ አማክረዋል፡፡ ይህም ማለት ያሰብነው ይህንን ያህል ነው የእናንተስ ሐሳብ ምንድነው? ነው፡፡ ሌሎቹ ግን በመጪው ዓመት ወርኃዊ ክፍያ ላይ ይህንን ያህል ጭማሪ አድርገናልና እንድታውቁት የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አድርሰውናል፡፡ ልጆቼን ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ሳስተምርበት የቆየው ትምህርት ቤት የ12 በመቶ ጭማሪ ማድረጉን አሳውቆኛል፡፡  

በሳምንቱ መጀመሪያ ሰሞን ከአንድ ወዳጄ ቢሮ ተገኝቼ የታዘብኩትም አስገርሞኛል፡፡ ወጣቷ ባልንጀሬ ወላጅ እንደመሆኗ ስልክ ይደወልላታል፡፡ ከወዲያኛው አቅጣጫ የደረሳት መልዕክት የሚጎረብጥ ስለመሆኑ ከፊቷ ላይ የሚነበበው ሁኔታ ያሳብቃል፡፡ በስልክ የተነገራት መልዕክት ሥራዋን በቅጡ ለመከወን እስኪሳናት ድረስ ሲረብሻት ተመለከትኩ፡፡ ስሜቷን በአንዴ የበረዘው የስልክ ጥሪ የመጣው ልጇን ከምታስተምርበት ትምህርት ቤት ነበር፡፡ በአጭሩ የስልኩ መልዕክት በአንድ ተርም ትከፍል በነበረው ገንዘብ ላይ 600 ብር መጨመሩን የሚያረዳ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ይህንን ያህል መጨመሩ ፀጉሯን ቢያስነጫት አይገርምም፡፡ እንዲህ ያለ ጉዳይ በስልክ እንደዘበት መነገሩም ይበልጥ ያበሳጫል፡፡

ቅዳሜ ግንቦት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ስብሰባ የተጠራው ሌላኛው ወላጅ፣ ልጆቹ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ወስኖ የቆየውን በተርም የ200 ብር ጭማሪ ሰምቶ ከመመለስ በቀር አማራጭ አልነበረውም፡፡ ጭማሪው ቢያበሳጨውም አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከጨመሩት አንፃር የተሻለ መሆኑን ሲገነዘብ ዝምታውን አዳብሯል፡፡

ምን ያህል እንደሚጨመርባቸው በሥጋት እየተጠባበቁ የሚገኙ ወላጆችም አጋጥመውኛል፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች በየዓመቱ የሚጨምሩት የክፍያ መጠን ምክንያታዊነቱና ግልጽነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ ቅጥ ያጣው የግል ትምህርት ቤቶች ክፍያም ሆነ የዋጋ ተመን ሃይ ባይ ማጣቱ ሳያንስ፣ ዋጋ ሳጨምሩ አንድ ዓመት ማለፍ አለመቻላቸው እንቆቅልሽ እንደሆነብኝ ነው፡፡  

ልጆቼን ትምህርት ቤት መስደድ ከጀመርኩ ከስድስት ዓመታት ወዲህ አንድም ዓመት ጭማሪ ሳይደረግበት አላለፈም፡፡ ለመደበኛ ተማሪዎች ሁሌም እንደ አዲስ የምዝገባ ክፍያ እንጠየቃለን፡፡ በየዓመቱ የትምህርት ቤት ክፍያ እንዲህ እየጨመረ ከሄደ፣ አሁን የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተማሩ ያሉት ልጆቼ፣ ሁለተኛ ደረጃን እስኪያጠናቅቁ ድረስ በየዓመቱ እየጨመረብኝ የሚዘልቀው ክፍያ ሄዶ ሄዶ፣ ወርኃዊ ደመወዜን ጠራርጎ እንዳይወስደው እሰጋለሁ፡፡ በሌላ በኩል ደመወዝ የተጨመረልኝ ከሦስት ዓመት ቆይታ በኋላ መሆኑን ሳስብ አንድ ቦታ ብቻ ሠርቶ ቤተሰብ ማስተዳደር ለዘመኑ አባወራ ምን ያህል አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ያሳየኛል፡፡ ያስፈራኛል፡፡

ሁለትና ሦስት ልጅ ያለው የመካከለኛ ገቢ ሠራተኛ ደህና የሚባል ትምህርት ቤት ውስጥ ልጆቹን ማስተማር አይቻለውም፡፡ አገር ተረካቢ ልጆቻችንን ብቁ ለማድረግ  በጥሩ ደረጃ ማስተማሩ ግድ ነው፡፡ ባለን አቅም ልጆቻችን ጥሩ ቦታ እናስተምራለን ብለን ብንጣጣርም ለትምህርት ቤት በሚከፈለው የተጋነነ ዋጋ ሳቢያ ግን ዕዳና ሰቆቃ ውስጥ እየገባን ነው፡፡

 የአገራችን የግል ትምህርት ቤቶች ከሚያስከፍሉት ዋጋ አኳያ የሚሰጡት ካለው ትምህርት ተመጣጣኝ ነው ወይ? ብለን ከጠየቅን ብዙ ሊያነጋግረን ይችላል፡፡ በቂ የልጆች መጫወቻ ቦታ የሌላቸው፣ ለድንገተኛ ሕክምና የሚሆን ክሊኒክና ባለሙያ ከመቅጠር የሚሰስቱ፣ ከምንከፍለው ወርኃዊ ክፍያ አንፃር ለመምህራን ተመጣጣኝ ደመወዝ የማይከፈሉ መሆናቸው እየታየ ነው፡፡ እነሱ ጨምሩ ሲሉን እየተነጫነጭንም ቢሆን እንከፍላለን፡፡ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ለአንድ ተማሪ የሚጠይቁንን ትምህርት ቤቶች የመማርያ ክፍሎችና መቀመጫዎችን ስናይ ታዲያ ለምኑ ይሆን ይህን ቆልለው የሚያስከፍሉን? ማለታችን አይቀርም፡፡

የትምህርት አሰጣጣቸው በተወሰነ ደረጃ ልዩነት ሊኖረው ቢችልም፣ በነፃ ገበያ ሰበብ የተጋነነ ትርፍ የሚያጋብሱ ሆነው የመቀጠላቸው ጉዳይ መቆም አለበት፡፡ እርግጥ ነው በግል ትምህርት ቤት ማስተማር ከከበደን ወደ መንግሥት ትምህርት ቤቶች ልጆቻችንን ልከን የማስተማር ዕድል አለን፡፡ በእነዚህ ተቋማት የትምህርት አሰጣጥና ጥራት ላይ ያለው ብዥታ ብዙ በመሆኑ ወላጆች የግል ትምህር ቤቶችን ይመርጣሉ፡፡

ችግሩን ለማስተንፈስ፣ አካሄዱንም ለማስተካከል ሌሎች አማራጮች መታየት አለባቸው፡፡ አንዱ የኮሚኒቲ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት ነው፡፡ ወላጆች በጋራ ተሰባስው ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት ቢያቋቁሙ አንዱ መፍትሔ ቢባልም፣ በወላጆች የተቋቋሙ ጥቂት ትምህርት ቤቶችም ቢሆኑ የሚያስከፍሉት መጠን ከምንወቅሳቸው  የግል ትምህርቶች ብዙም ያልተለየ ሆኖ ይገኛል፡፡ ቢሆንም ጥሩ የሚሠሩ የኮሚኒቱ ትምህርት ቤቶችን መፍጠሩ አማራጭ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከፍሎ ማስተማር ባይቀርልንም ክፍያው ግን የአብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል አቅም ያገናዘበ እስካልሆነ ድረስ፣ ባለፍራንካዎች ብቻ የሚገለገሉባቸው እየሆኑ እንዲጓዙ መፍቀድ ነውና ይታይልን፡፡ ሳያተርፉ ይሥሩ አንልም፡፡ አይወጣንም፡፡ የትርፍ  ወር ጠብቀን በምናገኛት የምንተዳደር ዜጎች ላይ ጉዳቱ የከፋ ይሆናልና መንግሥት ይንቃ፣ ነጋዴም ልብ ይግዛ፡፡

ይህንን ጽሑፍ ሳሰናዳ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልሳን የሆነውን ጋዜጣ እያየሁ ነበር፡፡ በጋዜጣው ፊት ለፊት ገጽ ላይ ከተደረደሩ ዜናዎች አንዱ ‹‹በከተማው ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች አብዛኛዎቹ ስታንዳርዱን የማያሟሉ መሆናቸው ተጠቆመ፤›› ይላል፡፡ ከዜናው አንዱ ሐረግ ‹‹የመዲናዋ አብዛኞቹ የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች አገራዊ መለኪያ በተጠቀመጠላቸው ደረጃ ተመዝነው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ መረጋገጡን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፤›› ይላል፡፡ የቢሮውን ኃላፊ ጠቅሶ የሚያትተው ይኼው ዘገባ፣ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 24 በመቶዎቹ ብቻ ደረጃቸውን የሚያሟሉ ሲሆኑ፣ 76 በመቶዎቹ ግን ከደረጃ በታች ናቸው በማለት ያስረዳል፡፡ ይህ እየሆነ ነው እንግዲህ በየዓመቱ ክፍያ የሚንረው፡፡ የዋጋ ጭማሪ ወደፊት አገልግሎትና ጥራት ወደኋላ ማለት ይህ ነው፡፡   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት