በታደሰ ሻንቆ
ኢሕአዴግ ደጋግሞ የሚናገረውና የሚኩራራበት አባባል አለው፣ ‹‹የቀድሞው የአገሪቱ አንድነት የግዛት አንድነት ነበር፡፡ በአዲሲቱ ኢትዮጵያ የመሠረትነው አንድነት ግን የሕዝቦች አንድነት ነው፤” የሚል፡፡ እንዲህ የተባለለት የዛሬ የሕዝቦች ግንኙነት ግን በቅሬታዎችና በቅያሜዎች እየተቦረቦረ መጥቶ መፋጀት እንዳያስከትል እስከ ማስፈራት ደርሷል፡፡ የዚህን እውነትነት ለማሳየት ያለፈውን ቁጣ ማስታወስ ይበቃኛል፡፡
ለኢትዮጵያ ሕዝቦች መልካም ግንኙነት መቦርቦር ዋና ተጠያቂው፣ አሁንም ዋና የአደጋ ምንጭ ሆኖ የሚያስፈራው፣ ፋፍቶና ደርቶ ንቁሪያና ሽሚያን የሚያፈልቀው ጎሰኝነት/ክልልተኛነት ነው፡፡ ክልልተኛነት ብዙ ብሔረሰቦችን ባካተተ አካባቢያዊ ስሜት ሊገለጽ ይችላልና ክልልተኛነት ሁሉ ጎሰኝነት ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ጎሰኝነት ሁሉ ግን ክልልተኛነትም ነው፡፡ መልከ ብዙ እንቅስቃሴዎቹን የሚመራው አገዳ አስተሳሰብም የሁሉን ነገር መፍቻ የብሔር ብሔረሰብነት መብትና ጥቅም አድርጎ የሚመለከት ነው፡፡ የዚህ አገዳ አስተሳሰብ መሐንዲስና መሠረት ጣይ ያው እንደሚታወቀው ሕወሓት/ኢሕአዴግ ነው፡፡ ማንነት ማለት ብሔር ብሔረሰብነት ሆኖ የተበየነውም ከዚሁ አስተሳሰብ ነው፡፡ በየትም ያለህ ዜጋ ከሁሉ በላይ ብሔር/ብሔረሰብነትህን አስተውለህ የማንነትህን ሥፍራ አንሳ የሚለው አስተሳሰብ ዛሬ የዕለት ተዕለት መመርያ ሆኗል፡፡ በዚሁም መሠረት በተግባር እንደሚታየው ብሔር ብሔረሰብ/ክልል ዋና (እምዬ ሊባል የሚችል) ቤት፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የውድድር ሜዳ ሆናለች፡፡ ይህ የሽሚያ አመለካከት መግቻ እስካልተበጀለትም አገሪቱንና ሕዝቦቿን ወደ መበታተን ይዞ እንደሚነጉድ ጥርጥር የለውም፡፡ የዚህ ጽሑፍም ሙሉ ትኩረት የዚህን ችግር ሁነኛ ገጾች ማሳየት ነው፡፡
ሀ) የመዘዞች መወላለድ
“ኤፈርት” በመባል የሚታወቁት ኩንባያዎች ቅዋሜ የገጠማቸው ገና ብቅ ካሉ ጀምሮ ነበር፡፡ ይህ ችግራቸውም የመነጨው በኢሕአዴግ ገዥነት ውስጥ የበላይ ነው ተብሎ በሚታመነው ሕወሓት የተቀየሱና አመራር የሚያገኙ ከመሆናቸው በላይ ክልላዊ በሆነው ንብረትነታቸው ውስጥ በአንድ ወይ በሌላ መልክ አልፎ የሄደ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሀብት አለበት የሚል ቅሬታ ስለተፈጠረ፣ ለእንቅስቃሴያቸው፣ ለዕድገታቸውና ለመስፋፋታቸው በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ባሉ የሕወሓት ሰዎችና ሰንሰለቶቻቸው አማካይነት ቀጥተኛ/ኢቀጥተኛ ዕገዛ ይደረግላቸዋል ተብሎ ስለታመነ፣ እንዲሁም ከእናት ክልላቸው ውጪ በሆኑ አካባቢዎች የሚያደርጉት የንግድ እንቅስቃሴ በብዝበዛ በመተርጎሙ ነው፡፡
እነዚህ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን በሚገዛው ኢሕአዴግ ውስጥ ያለ የበኩር ፓርቲ በኩር ፍሬዎች እንደመሆናቸውና አመራርም የሚያገኙት ከዚያው እንደመሆኑ ይዳላላቸዋል የሚል ሐሜት ቢያርፍባቸው የሚደንቅ አይሆንም፣ የሚደንቀው እንዲያውም ባይታሙ ነበር፡፡ ምክንያቱም በኢሕአዴግ ውስጥ በኢሕአዴግነት ኅብረ ብሔራዊ ተልዕኮ እንዳለ ሁሉ በብሔር ብሔረሰብነት/ክልልነት በኩል ደግሞ አካባቢያዊ ተልዕኮዎች አሉ፡፡ እናም ለሕወሓት ዓላማ የቆሙ ሰዎች በሕወሓት ለሚመሩና ሕወሓታዊ ተልዕኮ ላላቸው ኩባንያዎች ወገንተኛ እንክብካቤ እንዲያደርጉ ተልዕኮው ራሱ ያሳስባቸዋል፡፡ አድልኦ በቁሙ የሕወሓት ድርጅታዊ አቋም ባይሆንም እንኳ፣ የብሔርተኛ ወገንተኛነት ፍልስፍና በራሱ በእኩል ዓይን ያለማየትን (የአድሏዊነትን) ፈተና ያመጣል፡፡ (የራስንና የጎረቤት ልጅን እኩል ማየት እንደሚከብድ ማለት ነው) የብሔር ወይም የክልል ወገንተኛት ለእናት አካባቢ ኩባንያዎች ከማዳላት የትና የት ተሽቀንጥሮና ግለሰቦችን በሚመለከቱ የሕግ ጉዳዮች ውስጥ ሁሉ ገብቶ ፍትሕን እያጎደፈ አይደል እንዴ! ወገንተኛ አመለካካቱ በአግባቡ አሳፋሪ እንዳለማግኘቱም እንደ ወረርሽኝ መስፋፋቱ ሎጂካዊ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ብልሽት ያደረሰውን አመለካከትና አደረጃጃት በማስተካከል ፋንታ “አድልኦ አይደረግም፣ አድሏዊነት የመንግሥት ዓላማ አይደለም!” የሚል ክርክር አይፈይድም፣ እስከዛሬ ድረስም ሰሚ አላገኘም፣ ምክንያቱም የአድልኦው ሥራ የመንግሥትን አፅዳቂነትና አይዞህ ባይነት አይሻምና፡፡ የ‹ኤፈርት› ድርጅቶች እየተቋቋሙ ክልል ዘለል እንቅስቃሴ ገና ሲጀምሩ፣ የዚያ ዓይነት የንብረት አያያዝና ክልል ዘለል እንቅስቃሴ የቅራኔ መዘዝ እንዳለው ለማሳወቅ ተሞክሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰሚ ስላልነበረ የኩርፊያ ዒላማ ሆነው ቆይተዋል፡፡ በቅርቡ በተከሰተው የቅዋሜ ግርግር ወቅትም የጥቃት በትር ጨርፏቸዋል፡፡
ከኖረው ሐሜትና ኩርፊያ፣ እንዲሁም ከቅርቡ የቅዋሜ ልምድ ትምህርት ወስዶ ከመጠመድ ነፃ የሚያወጣ መፍትሔ መፈለግ፣ የ‹ኤፈርት› ኩባንያዎች ከተጓዙበት አደገኛ መንገድ ሌሎች ወገኖችም መራቅ በተገባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የተቀየረ ነገር አላየንም፡፡ ጭራሽ በቁጣ ማግሥት ይበል የሚያሰኝ መልካም ሙያ ይመስል የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች በ‹ኤፈርት› ጎዳና ግዙፍ የንግድ ሥራ ኩባንያዎች የመፍጠር “አብዮት” ውስጥ ገብተዋል፡፡ (ለነገሩ ፊትም በመናጆነት ሞካክረዋል፣ ጎልቶ መውጣትና መደርጀት አልተሳካላቸውም እንጂ፡፡) በአማራ ክልል “ዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት” የሚባል ባለብዙ ዘርፍ ኢንዱስትሪ በአማራ ክልል መንግሥት፣ በክልሉ የልማት ድርጅቶችና ባለሀብቶች አማካይነት ተቋቁሟል (ሪፖርተር፣ መጋቢት 17 ቀን 2009 ዓ.ም.)፡፡ ከብአዴን ጋር ትስስር ያለው “ጥረት ኮርፖሬት”ም (በ1987 ዓ.ም. በብአዴንና በ25 መሥራች አባላት የተመሠረተ የተባለ) በኢትዮጵያ መንግሥት ሥር የነበሩትን የባህር ዳርንና የኮምቦልቻን ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ሊያጠቃልል መሆኑ ተወስቷል (ሪፖርተር መጋቢት 13 ቀን 2009 ዓ.ም.)፡፡ በኦሮሚያም የኦሮሚያ መንግሥትና የኦሮሞ ባለሀብቶች የጥምረት ምክር ቤት ተመሥርቶ ኦሮሞን መሠረት ያደረገ 1.6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ይኖረዋል የተባለ ‹‹ኦዳ ኢንተግሬትድ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር›› እየተደራጀ ስለመሆኑና በግማሽ ቀን ብቻ የ617 ሚሊዮን ብር አክሲዮን መሸጥ ስለመቻሉ አንብበናል (ሪፖርተር መጋቢት 13 ቀን 2009 ዓ.ም.)፡፡ ‹‹ኬኛ ቤቨሬጅ›› የሚባል ለስላሳ መጠጦች፣ የማዕድን ውኃና ጭማቂዎች የሚያመርት (ከኦሮሞ ገበሬዎች ጋር ትስስር በመፍጠር የሚሠራ) እየተደራጀም ነው፡፡ እነዚህ ወገንተኛ ኩባንያዎች ምን ይዘው ሊመጡ . . . ?
- ሕወሓት አመራር የሚሰጣቸው የ‹ኤፈርት› ዘርፈ ብዙ ኩባንያዎች ሕወሓት በሚመራው የትግራይ ክልል ውስጥ መንግሥታዊ ወገናዊነት ማግኘታቸው የማይቀር፣ ሌሎች ግላዊ የውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ከእነሱ ጋር በእኩል ተፎካካሪ መሆን እንደሚያስቸግራቸው ሁሉ፣ ይህ ዓይነቱ ችግር በአማራና በኦሮሚያም ውስጥ መደገሙ የሚጠበቅ ነው፡፡ የአማራና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥታት በየፊናቸው ባለድርሻ ለሆኑባቸው ኢንዱስትሪዎች ወገንተኛ ሳይሆኑ ሌሎች ተፎካካሪዎችን በእኩልነት ሊያስተናብሩ የሚችሉት በምን ተዓምር? የብድር፣ የጨረታና የመሬት ኪራይ ዕድሎችን፣ እንዲሁም ቀረጥና ግብር የመሳሰሉትን ነገሮች መጥቀሚያና መጉጃ አድርገው እንዳይሠሩባቸው ምን ይይዛቸዋል? እኩል ፉክክርና መስተንግዶ አገኛለሁ ብለው ሌሎች ‹‹ባይተዋር›› ኩባንያዎች እንደምን እምነት ሊኖራቸው ይችላል? ወይስ በየክልል የራስ ኩባንያዎችን ፈጥሮ በሌላው ክልል የደረሰ ባይተዋርነትን በራስ ክልል ውስጥ ማስመለስ መጪው የፍትሐዊነት ሚዛን ሊሆን?
- በእርግጥ በሌላው ክልል ውስጥ ገብቶ የተንጓለለ፣ በእምዬ ክልሉ ውስጥ መቀማጠሉና ከሌላው መብለጡ እንደሚኖር ይገመታል፡፡ ይህ ግን አሁን ባሉትና እየተፈጠሩ በመጡት ክልላዊ ኩባንያዎች ተገድቦ የሚያቆም አይደለም፡፡ እኛስ ለሌላው ሲሳይ ለምን እንሆናለን እየተባለ እስከ ትንንሽ ክልሎች ድረስ ክልላዊ ኩባንያዎች የማቋቋም ፍላጎቱና ቅናቱ መዛመቱ አይቀርም፡፡ በዚያው ልክ በየክልል ማንጓለልና መንጓለሉ ይስፋፋል፡፡ ይኼ ብቻም አይደለም፣ በሕዝብ ውስጥ ያለው የምርትና የአገልግሎት ግዢ ደንበኝነት ወደ የእናት ክልል ኩባንያዎች ይዘረዘራል፡፡ በኦሮሚያ ውስጥና ከኦሮሚያ ውጪ ያለ ኦሮሞ የኦሮሚያንና የኦሮሞን ኩባንያዎች አገልግሎቶችና ዕቃዎች ያነፈንፋል፡፡ አማራውም፣ ደቡቡም፣ ሶማሌውም፣ . . . ወዘተ እንደዚያው፡፡
- ለየእናት ክልል ኩባንያ ደንበኛ የመሆኑ ሠልፍ በልሙጡ ሲታይ እንደሚመስለው ሁሉም በየፊናው የሚደሰትበት አይሆንም፡፡ በዚህ ዓይነት ሠልፍና ውድድር አሸናፊ የሚሆኑት በካፒታል፣ በሙያና በልምድ ከመዳበር ባሻገር፣ በሕዝብ ክምችትና በክልል ዘለል ስብጥር የላቁት ይሆናሉ፡፡ በግልጽ ለመናገር አማራና ኦሮሞ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሽሚያ ለእነ ሶማሊያ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ፋይዳ የለውም፡፡ እነዚህ ክልሎች የየራሳቸውን የትራንስፖርት፣ የጭማቂ፣ የለስላሳ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ ወዘተ ድርጅቶች ቢያቋቁሙ ከክልላቸው ውጪ ለየትኛው ተወላጃቸው እያቀረቡ ሊጠቀሙ? አስተዳዳራዊ ወገናዊነት በማይኖርበት አዲስ አበባ ውስጥ ተፎካክሮ መሸጥ እንኳ ለእነሱ ትርጉም የለውም፡፡ ደንበኛ የሚሆን የሕዝብ ክምችት አዲስ አበባ ውስጥ ስለሌላቸው፡፡ ይህንን መሰሉን መዛባት ከዚህም ከዚያም ሕዝብ እየቆነጠሩ በአዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች ለማሥፈር ቢሞከር እንኳ መፍትሔ አይሆንም፡፡ በሕዝብ ብዛት አናሳዎቹ ወደየትም ቢገላበጡ ከሳሪዎች ናቸው፡፡
- በሌላ በኩል ለእናት ክልል ኩባንያ የሚደረግ ወገንተኛነት እንኳን ለአናሳዎቹ ለትልልቆቹም መሰናክል ይፈጥራል፡፡ የአማራ የሕዝብ ማመላለሻ፣ የአማራ ቢራ፣ የአማራ ጨርቅ፣ . . . ኦሮሚያ ውስጥ ገበያ (አማራ ተጠቃሚ) ማግኘት ይችላል? የኦሮሚያን ኩባንያ ጥቅም እየተሻማ ነው የሚል ስሜት በተፈጠረ ጊዜ ግን በቀረጥና በግብር መንገድ አቅራቢው ሊኮረኮም ይችላል፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ እየኖሩ የአማራ ኩባንያ ሸቀጥና አገልግሎት ደንበኛ መሆንም በራሱ የሚፈጥረው ማኅበረሰባዊ ቅራኔም አለ፡፡ በኦሮሚያ ውስጥ ያለ ከሌላ ብሔረሰብ “የተወለደ” ባለሀብት ቡና ከኦሮሞ ገበሬ ገዝቶ፣ ኦሮሞ ሠራተኞችን ቀጥሮና ቡና ቀሽሮ ወደ ውጭ የመላኩ ዕድልም የማይቻል ይሆናል፡፡ ኦሮሚያን ምሳሌ አድርገን የገለጽነው ችግር በአማራው ውስጥ መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡ ትልቁ ቀውስ የሚመጣው ግን አነስተኛና በያለበት የተከተረ ሕዝብ ካላቸው ክልሎች በኩል ነው፡፡ እንደሌላው ክልላዊ ኩባንያዎች ቢያቋቁሙም በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ለወገናዊ ደንበኛ ሸጠው ማትረፍ የሚችሉበት ዕድል ስለማይኖር፣ ሌሎች ክልላዊ ኩባንያዎችን ወደየክልሎቻቸው ማስገባት የሚፈቅዱበት ምክንያት ያጣሉ፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የፌዴራል አባል ሆኖ መቆየታቸውም ትርጉም ያጣባቸዋል፡፡ ‹‹አንቺ ነዶ አለሁ ብለሻል፣ ተበልተሽ አልቆልሻል›› እንደሚባለው የተጀመረው ጉዞ መድረሻ ጥብጣብ በመቀስ መቁረጥ ብቻ የሚቀረው መበታተን ይሆናል፡፡
- ተበታትኖም ሰላም ቢገኝ አንድ ነገር ነበር፡፡ እንደ ብትንትኖሹ ብዛት የመናቆሪያ ቅራኔዎቹም ይበረክታሉና ደሃና ትንንሽ ሆኖ በዛሬው የተጠቃለለ ዓለም ውስጥና ትርምስ በሚወደው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ መኖር እውነት የሚሆነው በቅዠት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከተበታተነች የአፍሪካ ቀንድ የማያቋርጥ የእሳት መፍለቂያ እምብርት መሆኗ አይቀርም፡፡ ከዚህ ትንታኔ ምን ያህል የተሳሳተ መንገድ እንደተያያዝን መረዳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡
ልናወላውልባቸው የማይገቡ ነጥቦችን እናስቀምጥ 1ኛ) አንድ አካባቢያዊ ፓርቲ፣ አካባቢያዊ የልማት (የንግድ) ድርጅትን በተከታታይ መምራቱ ቋሚ እውነታ ከሆነ፣ ፓርቲው በይፋ ገለጠውም አልገለጠው የንግድ ድርጅቶቹን መምራት ዓላማው አድርጎታል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ ንግድ ላይ እንዳይሰማራ ከሚከለክለው ሕግ አኳያ ስለምን ተብሎ ጥያቄ ሊነሳበት ይገባል፡፡ መሪነቱን አስፈላጊ ያደረገው የንግድ ተቋማቱ የሕዝብ ልማት ተልዕኮ ስላላቸው ነው የሚባል ቢሆን የአገርም፣ የአካባቢም ልማት ከፓርቲ ጋር ለምን ይጣበቃል? የሚያሻው ለቦታው የሚመጥን የሙያ ብቃት፣ ልምድና ተቆርቋሪነት ብቻ ነው፡፡ የአካባቢ ልማት ከ”ሀ” ወይም ከ”ለ” ፓርቲነት ተነጥሎ ሊታይ ካልቻለ የልማቱ ስኬት ከአንድ ብቸኛ ፓርቲ መሪነት ጋር ግድ ተጣብቆ ከታየ ያ ፓርቲ በምርጫ ወጪና ወራጅ ለመሆን መፍቀዱም አጠያያቂ ይሆናል፡፡ (በትምህርትና በሥልጠና መስክ ረገድም የፓርቲ ማጠንት የማይለያቸው ተቋማት መኖር የለባቸውም፡፡) እነዚህን ለመሳሰሉ እንከኖች የሕግ እርማት መሰጠት አለበት፡፡ የሕጉ እርማት ተሟልቶ ከሆነም ከሕጉ አኳያ ተግባራዊ ሥራችን መስተካከል ይኖርበታል፡፡
2ኛ) በአክሲዮን ገበያና በመዋዋጥ ሒደት የሚንሸራሸር ‹ብሔረ ብዙ›/‹አገረ ብዙ› የባለቤትነት ቅንብር ያላቸው የኩባንያዎች ቅጥልጥል የዓለም ኢኮኖሚን ተቆጣጥረው በሚዘውሩበት ዓለም ውስጥ እየኖሩ ሳሉ፣ በአንድ አገር ውስጥና በአንድ ፌዴራላዊ ባንዲራ ሥር ‹ብሔረ ብዙ› ስብስብ ያላቸውና ሁሉም የእኛ የሚላቸው (በጥበት የማይተናኮላቸው) የንግድ ሥራ ድርጅቶች ለመፍጠር አለመቻል፣ በበሬ ማረስን ሙጭጭ ብሎ ከመያዝ የማይሻል ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ደጅ ደጁን የቀንዱንም ሆነ የምሥራቅ አፍሪካን ማኅበረሰባዊ ትስስር እንፈጥራን እየተባለ የተያዘውን ሽር ጉድ ከውስጥ በሚፈነዳ ቦንብ፣ በአጭር ለማስቀረት ከመልፋት ሊቆጠር የሚችል ነው፡፡
3ኛ) የሕዝቦች የባንክ፣ የመጓጓዣ፣ የዕቃዎች፣ ወዘተ ደንበኝነት በአገልግሎትና በሸቀጥ ጥራት ላይ መመሥረቱን ትቶ የብሔር/የክልል ወገንን በመፈለግ ላይ እንዲመረኮዝ መቃኘት እጅግ ኋላቀርነት ነው፡፡ ስለዚህም ከዚህ አቅጣጫ መውጣት ተገቢና ግድ ነው፡፡
እንዴት መውጣት ይቻላል? 1ኛ/ እንኳን የክልል መንግሥት የፌዴራል መንግሥትም ኩባንያዎች የማቋቋም ሥራ ውስጥ መግባት ያለበትም ሆነ የካፒታል ድርሻ ተጋሪ መሆን ያለበት የግል ባለሀብቶች በሌሉበትና ባልቻሉበት ግን አስፈላጊ በሆነ ዒላማ ውስጥ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ቆይታውም የመላ ሕዝብ ጥቅምን ከመጠበቅ አኳያ ለረዥም ጊዜ ከሚቆዩ በጣም ጥቂት ነገሮች በቀር ጊዜያዊ መሆን አለበት፡፡
2ኛ/ በአገሪቱ ውስጥ በሰፊው መሠረጫጨት የሚሹ ኩባንያዎች መተናኮል ኩርፊያና አድማ ሳያገኛቸው ሊሠሩ የሚችሉት፣ ባልደረቀ (እንደ ፈሳሽ በሚዋልል) ብሔረ ብዙ የአክሲዮን ድርሻ ከዳር ዳር ማካለል ከቻሉ ነው፡፡ በአማራና በኦሮሚያ መንግሥታት በኩል እየተደራጁ ባሉ ኩባንያዎች ላይ ጥያቄ ሲነሳ የሌላውም ብሔር ሰው እንዲሳታፍ የተፈቀደ ነው ብሎ ማለት መናጆ ከመፈለግ የማይሻል ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ክልሎች ትልልቅ ኩባንያዎች ለማቋቋም መነሳታቸው የ‹ኤፈርት› ድርጅቶችን ለሚመለከት ትችት ጆሮ ደፍነው “የትግራይ ሕዝብ ከተጠቀመ ምን ክፋት አለው? የትግራይ ሕዝብ መጠቀም ያው የኢትዮጵያ መጠቀም አይደል!” የሚል ሙግት ለሚያቀርቡ፣ በክልል/በብሔር የታጠረ ሩጫ እንደማያዋጣ ዓይን መግለጫ ሆነው ጠቅመዋል፡፡ ከዚህ አልፈው በአገሪቱ የትኛውም ሥፍራ እንደፈለጉ በተቀባይነት ለመሥራትና ትርፍ በትርፍ እየሆኑ መራመድ ከፈለጉ፣ ካፒታል እያገናኙ አሁን ካሰቡት በላይ ማሰብና የአክሲዮን ሽያጩን በየአቅጣጫው ማስፋትና ካገጠጠ የድርሻ ተዛነፍ መውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዛሬ ያሉት ባንኮችና ኢንሹራንሶችም ከገቡበት ክልል/ብሔር ገብ የደንበኛ አጋዳይነት ተላቅቀው ለመግዘፍ መዋሀድን የጨመረ የዚህ ዓይነት ሒደት ያሻቸዋል፡፡
ለ) አዛላቂው መፍትሔ እስከምን ድረስ?
ኩባንያዎች ላይ የዳሰስነው ችግር የኩባንያዎችን ባለቤትነት ብሔረ ብዙ በማድረግ ብቻ የሚቃለል አይደለም፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ነገር መፍለቂያ የሆነው በተቃውሞ ብሔረተኛነት ውስጥም ሆነ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ብሔረተኛነት በኩል ሊስፋፋ የቻለው፣ የጎጆኛነት አስተሳሰብ እስከነገሠ ድረስ በአንድ በኩል ሊደፍኑ የሞከሩት ችግር በሌላ መልክ ብቅ ማለቱ አይገታም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የደራው ጎጆኛት ‹ባለ ባላ› ነው፡፡ የባላው አንድ መንትያ ማንነትን አኮማትሮ የብሔር/ብሔረሰብነት ተለዋጭ መጠሪያ አድርጎታል፡፡ ስለማንነት ከተወራ ስለብሔር/ብሔረሰብነት መወራቱ ሆኗል፡፡ ከዚሁ በመነሳትም ማንነትንና የማንነት አካባቢን አውቆ ለእምዬ አካባቢ ልማት መዋድቅ፣ የትም (በሩቅም በቅርብም) እየሠሩ ወደ እናት ምድር ማፍሰስ የሁሉም ጎጆኛት ብሌን ሆኗል፡፡ በባላው ሌላ ጎን ደግሞ፣ ብሔረሰቦችንና ክልሎችን እንደ ሉዓላዊ አድርጎ ማየት፣ በአስተደደር ክልል ያለ የተፈጥሮ ሀብትን (መሬትን፣ ማዕድናትና ውኃን) ሁሉ የክልል፣ ከክልልም ሌሎችን የማይጨምር የነባር ብሔር/ብሔረሰቦች የብቻ ሀብት አድርጎ ማሰብ አለ፡፡
እነዚህ ሁለት መንትያ አስተሳሰቦች በኢትዮጵያ ውስጥ የተወለዱበትንና እንጀራና ልጆች ያፈሩበትን የትኛውንም ሥፍራ አገሬ ብሎ መቁጠርን በጣጥሰዋል፡፡ በየአካባቢው ባለቤት ከሚባሉት ነባር ብሔረሰቦች ውጪ የሆኑ ማኅበረሰቦችንና ግለሰቦችን አለቤታቸው የሚኖሩ ባይተዋሮች/ሁለተኛ “ዜጎች” አድርጓል፡፡ ከዚያም አልፎ የማፈናቀልና የግጭት መነሻ ሆኗል፡፡ ከብሔረሰብ ብጤኛነትና ከአካባቢ ልጅነት የዘለለው የአገር ልጅነት፣ የቅይጥ ዝርያነት፣ በረዥም ዘመን ማኅበራዊ ባህላዊ መስተጋብር ውስጥ የተገኙ የጋራ ገጽታዎችና ትስስሮች ድንግዝግዝ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በዛሬው የተሳሰረ ዓለም ውስጥ፣ ያውም በአፍሪካ ቀንድ እምብርት ውስጥ፣ ቁርጥራጭ አገር መሆንን እንደ መብት ማየት በእሳትና በትርምስ ውስጥ መኖርን ድህነትንና ጉልበት የለሽነትን እንደ መብት መቁጠር መሆኑ ተዘንግቷል፡፡ ሉዓላዊነት (በራስ ዕጣና ጉዞ ላይ ራስ ወሳኝ የመሆን ሥልጣን)፣ እንኳን በብሔር/ብሔረሰብ ደረጃ ይቅርና እንኳን በኢትዮጵያ ደረጃ ይቅርና፣ በእነ አሜሪካም ደረጃ በዓለማዊ መጠቃለል ከጊዜ ጊዜ ተቆነጣጥሮ የተመናመነ ነገር መሆኑ፣ ትምህርት በቀመሱ ሰዎች አካባቢ እንኳ ተራ ግንዛቤ አልሆነም፡፡
በቅርቡ የተከሰተው በአሜሪካ የምርጫ ውጤት ውስጥ ከሩሲያ በኩል ኮምፒዩተር ገብ ጥቃት ተሠርቶ ይሆን የሚል ጥርጣሬ፣ በፈረንሣይም ያየነው የዚህ ዓይነት ፍርኃትና ጥቃት፣ በዛሬው የዜሯንድ (የሳይበር) ኅዋ ውስጥ መዝጊያ ሰብሮ በመዝረፍም ሆነ በማይዳሰስ ተባይ/መሣሪያ ልዩ ልዩ ዓይነት የጥፋት ሥራ በማከናወን ሊካሄድ የሚችል የውጊያ ጥበብ ያለበት ዘመን ውስጥ እየኖርን መሆናችንን ያስታወሰ ነበር፡፡ በማይዳሰስ መልክ የተከናወኑ ሥራዎች፣ የባንክ ሒሳቦች፣ መረጃዎችና ሚስጥሮች፣ ወዘተ ሁሉ ዛሬ ከርቀት ሊዘረፉ፣ ሊበረዙ፣ ሊቀየሩና ሊወድሙ የሚችሉ ናቸው፡፡ የአገሮች አለመግባባት ባለበት ሥፍራ በሐሰተኛ መልዕክት ጦርነት ሊጀመር የሚችልበት፣ ጦርነት ባለበትም በሐሰተኛ ትዕዛዝ አቅጣጫ አስቶ ለሽንፈት የመዳረግ ወይም በወገን ኃይል ላይ ጥቃት የሚያደርስ ዕርምጃ የማስወሰድ ሸፍጥ ሁሉ ሊፈጸም ይችላል፡፡ ከባዱ ነገር ደግሞ እነዚህን የመሳሰሉ ጥቃቶች በአገር ወይም በተቋም ደረጃ ብቻ ሊካሄዱ በመቻል የተገደቡ አለመሆናቸው ነው፡፡ አንድ ጥበቡን ያሟላ ጎረምሳም ያልተጠበቀ አደጋ ሊያደርስ ይችላል፡፡ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ነገር እንዲህ በተበረጋገደበት ዓለም ውስጥ ነው የእኛ አገር ጎጆኛነት አታሞ የሚመታው፡፡ የዚህ አስገራሚ ምፀት ደግሞ በገዢው ክፍል ፕሮፓጋንዳ የፌዴራል ቅንብሩ፣ የቢሻኝ/የፈቃደኝነት ጉዳይ እንደሆነና ባሰኘ ጊዜ ሕጋዊ አግባቡን ተከትሎ ውሉን ሊቀድ የፈለገ መቅደድ እንደሚችል ተደርጎ የሚሰበክ መሆኑና ይህንን የሚቃረነውን የነባራዊ ህልውና እውነት ሕዝቦች ዘንድ የሚያሰርፅ መጥፋቱ ነው፡፡
ሰላምና ተያይዞ የማደግ ዕድል ከእጃችን አፈትልኮ እንዳያመልጥ ከፈለግን ከአገር ልጅነት ትቅቅፍ ጋር የብሔር መብትንና መከባበርን ማጣጣም ግዳችን ነው፡፡ የትኛውንም የአገር ልጅ በእኩልነትና በወገንነት ማየት፣ የትም ሥፍራ ላይ አገሬ ብሎ በኩራት መኖርን፣ የየትኛውንም አካባቢ የልማት ጉዳት የእኔ ብሎ መቆርቆርን ማጎልበት አዘላለቃችንን በእጅጉ ይወስናል፡፡ ማጎልበት ሲባልም በአዳራሽና በጋዜጣ የመስበክ ጉዳይ ሳይሆን አመለካከቱን በተግባር ለመኖር የመቻል ነገር ነው፡፡ ይኼን አመለካከት የምር ለመኖር ከፈለግን ደግሞ እስካሁን ያለውን የፓርቲ አደረጃጀት ከመከለስ አናመልጥም፡፡ ብዙ ማኅበረሰቦችን ባካተተ የአካባቢ አስተዳደር ላይ አንዱን ወይም ሌላውን ብሔረሰብ መሠረት አድርጎ የተደራጀ ፓርቲ ሥልጣን መያዝ አይኖርበትም፡፡ የየራስ ጠባብ ወገንን የመጥቀም ሩጫንና ንቁሪያን ለማዳከም ከተፈለገ፣ የአካባቢ ፓርቲዎች የየአካባቢያቸውን ሕዝብ በጥቅሉ መሠረት አድርገውና የፓርቲ በራቸውን ክፍት አድርገው መደራጀታቸው ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ አገር አቀፍ (ፌዴራላዊ) ሥልጣንን በተመለከተም ብሔረተኛ ቡድኖች ግንባር በሚባል ከለላ ተወሽቀው በአንድ ጊዜ ሁለት ነገር የሁሉንም ሕዝብ የጋራ ጥቅምና ጠባብ አካባቢያዊ ተልዕኮዎችን የሚያስተናብሩበትና አንዱ ተልዕኮ ሌላውን ሊጎዳ የሚችልበት የሁለትዮሽ ሥራ መቀየር ይኖርበታል ማለትም በፌዴራል ሥልጣን ላይ የመውጣት መብት ኅብረ ብሔራዊ ስም ከመለጠፍ ጋር ሳይሆን በአግባቡ አገር አቀፍ ስብስብ ያለው ውህድ ፓርቲ ከመፍጠር ጋር መገጣጠም አለበት፡፡
ይኼ ማሻሻያ በፓርቲዎች ድርድር አማካይነት የተወሰኑ ምክር ቤታዊ ወንበሮች ለተቃዋሚዎች ከሚያቋድስ ለውጥ ጋር አብሮ መጥቶ ሕግ ቢደረግ ለውጡ የሚጠይቀው ሥራ ተገባደደ ማለት አይደለም፡፡ በአገሪቱ ችግሮች ላይ የተብላላ አገራዊ ምክክር አድርጎ ሰፊ መግባባት የመፍጠርና የሕዝቦችን ተስፋ የሚሞላ ትኩስ መሠረት የመጣል አካል ሆኖ ካልመጣ በቀር፣ እዚህም እዚያም በሚታየው ገንታራነት ላይ ከአናት ለመጫን ቢሞከር ውጤቱ የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡ ትኩስ መሠረት የመጣል ተግባር፣ ሕገ መንግሥቱን ከቋንቋ እስከ እሳቤ ድረስ የመንቀስና የማጎልበት ሥራንም ይጨምራል፡፡
- መብቶችን፣ ሥልጣንንና ባለቤትነትን ከሚመለከቱ ይዘቶች ውስጥ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፡
- አንቀጽ 8(1) የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነት ዝርዝርና ድፍን ክፍል ስለሌለው “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው” በሚል መልክ መቀመጡ ከማደናገር በቀር አይጠቅምምና የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው ተብሎ ቢቀመጥ በቂው ነው፡፡
- አንቀጽ 40(3) በአንድ ጊዜ ሁለት ነገር፣ የተፈጥሮ ሀብት (መሬትን ጨምሮ) የሕዝብና የመንግሥት ብቻ መሆኑን ይናገርና መልሶ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ሀብት ያደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ሀብት የመሆኑን ድንጋጌ ጠብቆ፣ የመንግሥት ኃላፊነት ግን በማስተዳደርና የአጠቃቀም ሥራውን በመምራት የተገደበና ተለይቶ የታወቀ እንዲሆን አድርጎ ማሻሻል የተሻለ ይሆናል፡፡
- አንቀጽ 46(4) የእሳቤ ችግር አለበት፡፡ ከአንድ አካባቢ አሰፋፈር ጋር አንድ ቋንቋ ተናጋሪነትን ያሟላና የጋራ ማንነት አለኝ ያለ ሕዝብ ክልል መሆን ስለፈለገ ብቻ ክልል አይሆንም፡፡ እንደ ክልል ለመንቀሳቀስ የሚያስችል የኢኮኖሚ፣ የአውታራትና የሰው ኃይል ልማትን አሟልቶ መገኘቱ ሚዛን ውስጥ መግባት ይገባዋል፡፡ የኢትዮጵያ ክልሎችን የመወሰን ሥራ በተሠራ ጊዜ ይህ የአቅም መመዘኛ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ነው ዛሬ እነ እከሌ አንድ ፍሪት ሆነው ክልልነት ከተሰጣቸው እኛስ ለምን ይቀርብናል የሚል እንቅስቃሴ መቁረጫ ያጣው፡፡
- በዝነኛው አንቀጽ 39 (1) ላይም የማሻሻያ ሐሳብ ለመሰንዘር ልድፈር፡፡ ባለው የአገሪቱ የአስተዳደር ውቅራት ላይ ለውጥ የሚያደርሱ ራሴን የቻልኩ ክልል ልሁን፣ ከዚህ ክልል ወጥቼ ወደ ሌላ ክልል ልግባ፣ ከናካቴው ከፌዴራል ሪፐብሊኩ አባልነት ልውጣ የሚሉ ጥያቄዎች ቢነሱ ጥያቄዎቹ በአፈናና በኃይል የሚደፈቁበት ዘመን በቁርጥ መዘጋቱን ማስቀመጥና ጥያቄዎቹ የሚፈቱት በምክክር፣ በድርድር፣ ከዚህ ሁሉ ቢያልፍ በውሳኔ ሕዝብ ብቻ መሆኑን፣ የሆነ ጥያቄ የመሣሪያ ትግልን ደርቦ ቢመጣ እንኳ የቅጣት ዕርምጃ የሚያርፈው በኃይል ተግባሩ ላይ እንጂ በጥያቄው ላይ አለመሆኑን መደንገግ፡፡ ንዑስ አንቀጹ ወደዚህ የተጠጋ ይዘት እንዲኖረው ቢደረግ 1ኛ/ መገንጠል መብት ነው የሚል ልፋፋ አይኖርም፡፡ 2ኛ/ ማኅበረሰቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ይወስናሉ/መወሰን ይችላሉ የሚል ዓይነት የግማሽ እውነት/የግማሽ ውሸት ልፈፋ ይቀራል፡፡ መቅረቱም አግባብ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ እውነቱ ከሆነ ከሪፐብሊክ መውጣት ይቅርና ከክልል አባልነት መውጣት በሁለት አቅጣጫ ዕድልን የመወሰን ውጤት አለውና፡፡ 3ኛ/ የዚህ ዓይነቱ ማስተካከያ በዚህ ንዑስ አንቀጽ ላይ ሲነሳ የነበረውን ጭቅጭቅም ያቀላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ የአንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ አራትም የቋንቋና የእሳቤ ማጥራት ማሻሻያን የሚሻ ነው፡፡ ለምሳሌ “ሐ” ላይ ለመነጠል ውሳኔ ሕዝብ የተቀመጠው የአብላጫ ድምፅ መለኪያ የሕዝብን የፍላጎት ብልጫ በአግባቡ ላያሳይ የሚችል ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ላይ ድምፅ ለመስጠት ሕግ የሚፈቅድለት ሁሉ ከሞላ ጎደል ይሳተፋል ብለን ብናስብ እንኳ፣ ድምፅ ያለመስጠት መብት በተከበረበት ድምፅ አሰጣጥ ውስጥ አብላጫ ድምፅ ከ50 በመቶ በታች ሊሆን ይችላል፡፡ 50 + 1 በመቶም ቢሆን የሚናገረው የአብዛኛውን ፍላጎት ሳይሆን የሕዝቡ ልብ ከሁለት መከፈሉን ነው፡፡
2) አገርን በሕገ መንግሥት የማደራጀት ወይም የማደስ የመጀመርያ ሥራ ላይ ሁሉ ነገር ተሟልቶ አይጠናቀቅም፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት በ1780ዎቹ በወጣበት ጊዜ ገና ባርነት አልተሻረም ነበርና ባርነት አንዱ ሁነኛ መጨቃጨቂያ ነበር፡፡ የእንደራሴ ምክር ቤት መቀመጫን በሕዝቡ ቁጥር በመደልደሉ ሥራ ውስጥ፣ ብዙ ባሪያ የነበራቸው ደቡባዊ “ስቴቶች” ብዙ ወንበር ለማግኘት ባሮች በሕዝብ ቁጥር ውስጥ እንዲካተቱ ሲሹ፣ ሰሜናዊ “ስቴቶች” ደግሞ የወንበር ሒሳብ ባሮችን ሳይጨምር እንዲታሰብ ይሹ ነበር፡፡ በዚሁ ምክንያት አምስት ባሮች የሦስት ሰው ያህል የተሠፈሩበት (አንድ ባሪያ የአንድ ሰው ክፍልፋይ የሆነበት) ተመን ሕገ መንግሥት ውስጥ ሊቀመጥ ቻለ፡፡ ለመሰረዝም የግድ የ1860ዎቹ የአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ተከናውኖ ባርነት እስኪሻር መጠበቅ ነበረበት፡፡ የኢትዮጵያ የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ብዙ አፍላ ብሔረተኛነትና የመነጠል ፍላጎት በነበረበት ሰዓት፣ የመነጠል ፍላጎት የተቀረፀ እንደመሆኑ የአገራዊና የአካባቢያዊ ፍላጎቶች መጓተት የተንፀባረቀበት ቢሆንና ከእንከኖች ባይጠራ አይደንቅም፡፡ ከእንከኖቹ ይበልጥም ገዝፎ መታየት ያለበት በብሔረተኞች በተዋጠ ፈታኝ ሰዓት ውስጥ አገሪቱንና ሕዝቦቿን አያይዞ የማስቀጠል ስኬቱ ነው፡፡
- እንጂ እስካሁን ድረስ እንከን ለማጥራት አለመሞከሩ፣ እንከን ጠፍቶ ወይስ እንከንን ለማየት የሚሻ ጠፍቶ? ብዙ ጊዜ ኢሕአዴጎች በኩራት ሲናገሩ እንደሚሰማው የ1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የመነጠል መብትን በግልጽ እስከማስቀመጥ የሄደ በመሆኑ ዲሞክራሲያዊ ትባቱ የረዥም ዘመን ዴሞክራሲና ሕገ መንግሥት ያላቸው አገሮችም “አይስተካከሉትም”፡፡ ነገር ግን በዚህ ኩራት ላይ የሚሳለቅ እንዲያውም የሕገ መንግሥቱን እየተሻሻለና እየጎለመሰ ለምዕት ዓመታት የመዝለቅ ዕድል የሚቀጭ እጅግ ኢዴሞክራሲያዊ አንቀጽ መቀመጡን ኢሕአዴጎች አያስተውሉትም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻልበትን ቀዳዳ የሚደነግገው አንቀጽ 105 በራሱ ላይና በክፍል ሦስትና በአንቀጽ 104 ላይ የቀረቀራቸው ድርብርብ ቁልፎች (የተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በእየ
ኛ ድምፅ የሕገ መንግሥቱን መሻሻል ደግፈውም ከክልል ምክር ቤቶች ውስጥ አንዱ እንኳ ቢያፈነግጥ የማሻሻሉ ጥረት ሁሉ መና የሚቀርበት ክርቸማ) ሕገ መንግሥቱን እንደ ታቦት አትንኩት አለዚያ ፈንቅላችሁ ጣሉ
ት የሚል አዋጅ ነው፡፡ የማሻሻያ ሐሳብ ለማቅረብ የተቀመጠው ክፍተትም (አንቀጽ 104) እጅግ ንፉግ ነው፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት በ200 ዓመታት ውስጥ ማሻሻያዎች የተካሄዱበት ጊዜያት ሰላሳ አይሞሉም፡፡ ከእነዚያ ውስጥ ደግሞ አሥራ ሁለቱ ማሻሻያዎች ሕገ መንግሥቱ በፀደቀ በስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተደረጉ ነበሩ፡፡ ከጊዜ ጊዜ የቀረቡት የማሻሻያ ሙከራዎች ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ ሕገ መንግሥት ብዙ ሳይነካካ ለረዥም ዘመን መቆየት የሚችለው የማሻሻያ ሙከራዎችን ዕድል በመሰነግና በድርብርብ ቁልፍ በመከርቸም ሳይሆን፣ በቅጡ አሻሽሎ በቀላሉ የማይበገር የጥራት አቅም እንዲጎናፀፍ በማድረግ መሆኑን ከዚህ መማር እንችላለን፡፡ የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ሳይሰረዝ እንዲኖር የሚሹ ሁሉ በአግባቡ ተብላልቶና የሕዝቦችን ፍላጎቶች በማቻቻል የተዋጣለት ሆኖ እንዲቃና መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
- ሳልጠቅሰው የማላልፈው ነገር ቢኖር፣ የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎቹ ነገር ነው፡፡ ዴሞክራሲን በአግባቡ የማቆናጠጥና ልማቱን የማራመድ ተግባር በአሁኑ ምዕራፍ ላይ የኢሕአዴግንና የተቃዋሚዎቹን ከሻካራ ግንኙነታቸው መውጣትንና አንዳቸው ወደ ሌላቸው በተወሰነ ደረጃ ተጠግተው የጋራ መገናኛ መፍጠራቸውን ይሻል፡፡ የአሜሪካ ሪፐብሊካንና ዴሞክራቲክ ፓርቲዎች ልዩነታቸው እጅግ ስስ ቢሆንም፣ የቅርቡ ምርጫ መንግሥታዊ የጤና ዋስትናን ካስገኘና በሰዓት እላፊም ቢሆን ለብክለት ቅነሳ ሱታፌ ከጀመረ ፕሬዚዳንትነት አውጥቶ ወደ ድንጋይ ከሰል ፊቱን ያዞረ፣ ለአቅም የለሾች ትርጉም ያለውን መንግሥታዊ የጤና መድን ለመሻር የሚተናነቅ፣ የተራቀቀ ስትራቴጂያዊ የጦር መሣሪያ እሽቅድምድምን የናፈቀና “ጠላት” ለሚላቸው የማይረሳ ቅጣት ለመስጠት የሚቅበጠበጥ ፕሬዚዳንትነትን አምጥቷል፡፡ ይህ የማዶ ልምድ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ አሸንፈው ገዢነትን ለመተካት ለሚያስቡ፣ በነባሩ ገዢነት ውስጥ የታዩ ሰባራ ጎኖችን አርሞ በመልካሙ ላይ እየጨመሩ የመራመድ ዝግጁነትን በደንብ ሊያስቡበት እንደሚገባ ያስተምራል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡