Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየኤልኒኖ ደንቃራ

የኤልኒኖ ደንቃራ

ቀን:

አፍሪካን በተለይም ከምሥራቅ እስከ ደቡባዊ አካባቢዋ የተፈጠረው ድርቅ ሚሊዮኖችን  ከችግር አዘቅት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ምግብ ዕርዳታው ርሁባኑን ለመታደግ በየቦታው እየተጣረ ነው፡፡ የኤልኒኖ ሐሩራማ ትንፋሽ ሰለባ የሆኑ የአርሶና አርብቶ አደሮች እንስሳት ቁጥር የትየለሌ ደርሷል፡፡ ይህ ፎቶ በማዕከላዊ ዚምባቡዌ፣ ማስቭንጎ የሚግጡት ሳር፣ የሚጠጡት ውኃ ካጡት ከብቶች መካከል አንዷ አቅም አንሷት በመድከሟ፣ በእግሮቿ መቆም አልቻለችም፡፡ አርሶ አደሮቹም  ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ (ፎቶ ከዶቼ ቬሌ)

          ***

የአባቱን 5 ሺሕ ፓውንድ ከጥቅም ውጭ ያደረገው ሕፃን

የአምስት ዓመት ሕፃን የደስታ የጨዋታ ጊዜ፣ የአባቱ አስፈሪ ቅዠት ሆነ በሚል ሜትሮ ያቀረበው ዘገባ ነው፡፡ በቻይና ኢንካዳ በተሰኘ ከተማ ውስጥ የሚኖረው ሚስተር ጋኦ ከሥራ ቤት ሲመለስ የአምስት ዓመት ሕፃን ልጁ ቤት ውስጥ የነበረውን 5 ሺሕ ፓውንድ በመሸረካከት አልጋና ወለል ላይ በትኖታል፡፡ አባት ንግዱን ለማስፋፋት ከብድርና ቁጠባ የተበደረው ገንዘብ እንዲያ ሆኖ ሲመለከት በከፍተኛ ድንጋጤ ተዋጠ፡፡ የተሸረካከተ የፓውንድ ቅጠሎችን በመሰብሰብ ወደ ባንክ የሄደው አባት ከባንክ ያገኘው መልስ ቅዠቱን አባባሰበት፡፡ እያንዳንዷን የተቀደደች ብር በትክክል ገጣጥሞ እስካለጠፈ ድረስ ባንኩ ምንም ሊረዳው እንደማይችል ነበር የገለጸለት፡፡ ሚስተር ጋኦም ቁጭ ብሎ ብጥቅጣቂዎቹን መገጣም ያዘ፡፡ አባት ገንዘቡን ያስቀመጠው የት እንደነበር ቢጠየቅም ለዚህ መልስ ከመስጠት ይልቅ ‹‹ልጄ ሕፃን በመሆኑ ልወቅሰው አልችልም ያደረገውን እረደዋለሁ›› ብሏል፡፡

 

የዓለም የሳክስፎን ሪከርድን የሰበረው ናይጄሪያዊው ፌሚ ኩቲ

ናይጄሪያዊው ሙዚቀኛ ፌሚ ኩቲ ለ46 ደቂቃ ከ38 ሰከንድ ያለማቋረጥ ሳክስፎን በመጫወት የዓለምን ሪከርድ ጨብጧል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረውን ሪከርድ የሰበረው ዘለግ ላለ ጊዜ አንድ የሙዚቃ ኖት በመጫወት ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት በኒው አፍሪካ ሸሪን መድረክ ለዚህ ክብር በቅቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1997 አሜሪካዊው ሳክስፎን ተጫዋች ኬኒ ጂ 45 ደቂቃ ከ37 ሴኮንድ በመጫወት ሪከርዱን ይዞ ነበር፡፡ የዝነኛው ሙዚቀኛ ፌላ ኩቲ ልጅ፣ ፌሚ ኩቲ ሪከርዱን ከሁለት ጊዜ ሙከራ በኋላ መስበር መቻሉን ቫንጋርድ ዘግቧል፡፡ ከ15 ዓመቱ ጀምሮ ሳክስፎን የሚጫወተው ሙዚቀኛ፣ ዘ ኢጂብት 80 የተባለውን የአባቱን ባንድ የተቀላቀለውም በዛው ዕድሜ ነበር፡፡ በሙዚቃው ለሰብአዊ መብት በመታገል ዝናው የናኘውን የአባቱን ባንድ ከለቀቀ በኋላ ፖዘቲቭ ፎርስ የተሰኘ የራሱን ባንድ አቋቁሞ ለዓመታት ሠርቷል፡፡ አራት ጊዜ የግራሚ ዕጩ የሆነው ፌሚ፣ እንደ አባቱ ለሰብአዊ መብት በመታገልም የሚታወቅ ሲሆን፣ ከሳክስፎን በተጨማሪ ትራምፔትና ፒያኖ ይጫወታል፡፡ በሳክስፎን ጨዋታ የዓለምን ሪከርድ በሰበረበት መድረክ የኔዘርላንድና እንግሊዝ ከፍተኛ ባለሥልጣኖችና ሌሎችም በርካታ ታዳሚዎች ተገኝተዋል፡፡ ከጊነስ ወርልድ ሪከርድ ይፋዊ ዕውቅና በቅርቡ ያገኛል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

* * *

በራፕ አልበም ከሀርቫርድ የተመረቀው ወጣት

የ20 ዓመቱ አሜሪካዊ አባሲ ሻው 10 ሙዚቃ ያለው የራፕ አልበም ሰሞንኛ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ አባሲ የሀርቫርድ ተማሪ ሲሆን፣ ለመመረቂያው እንደ አብዛኞቹ ተማሪዎች የጥናት ጽሑፍ ሳይሆን ምርመራዊ የራፕ ሙዚቃ አልበም ለትምህርት ክፍሉ አስረክቧል፡፡ ይህ ያልተለመደ አካሄዱ ተቀባይነት ማግኘቱን ቢጠራጠርም ከትምህርት ክፍሉ በሁለተኛ ደረጃ ማዕረግ ለመመረቅ በቅቷል፡፡ በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ የሙዚቃ አልበም ለመመረቂያ በማቅረብ ግንባር ቀደምነትን የያዘው አባሲ፣ ለትምህርት ክፍሉ ያስገባው፡፡ ሊሚናል ማይንድስ የተሰኘ አልበም ነበር፡፡ አልበሙ በጥቁር አሜሪካውያን ሕይወት ላይ ያተኮረና ሥነ ጽሑፍና ሙዚቃ ተጣምረውበታል፡፡ ተመራቂው በአንዳንድ መድረኮች ራፕ ሲያደርግ ያስተዋለችው እናቱ መመረቂያውን በአልበሙ እንዲያደርግ እንዳነሳሳቸው ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡ የእንግሊዝኛ ሥነ ጽሑፍ ተማሪው አባሲ የመመረቂያ አልበሙ በትምህርታዊ ይዘቱና በሙዚቃ ልቀቱም የሚወደስ መሆኑን መምህራኑ ተናግረዋል፡፡

* * *

የቴሌቪዥን ዜና ያቋረጠው ውሻ

የቴሌቪዥን ዜና አንባቢዋ ሊናርቴ እንደወትሮዋ ተመቻችታ ዜና በማንበብ ላይ ነበረች፡፡ መጀመሪያ የውሻ ጩኸት በቅርብ ይሰማት ጀመር፡፡ በዚህ በትንሹም ቢሆን እንደመረበሽ እያለች ሳለ ይብስ ብሎ ድምፁን ስትሰማው የነበረው ውሻ ስቱዲዮ ገብቶ ከጎኗ ዴስኳ ላይ ጉብ አለ፡፡ በፍርሃት እንደመሸሽ ብላ ዜና ማንበቧን ከማቋረጥ ውጭ ምንም ምርጫ እንዳልነበራት ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡ የዚህ ትዕይንት ቪዲዮ ዩቲውብ ላይ እንደተጫነ ወዲያው ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል፡፡

* * *

የንብ መንጋ የብዙዎችን የሥራ ቀን አስተጓጎለ

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ደቡብ ምሥራቅ ለንደን ውስጥ ከባድ የንብ መንጋ ወደ ሥራ ቦታቸው ለመሄድ ጥድፊያ ላይ የነበሩ መንገደኞችን ሁሉ መግታቱን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡ አንድ የዓይን እማኝ ‹‹ንቦቹ ቦታ ላይ የነበረውን ሰው ሁሉ ወርረው ነበር፤›› በማለት ሁኔታውን ገልጿል፡፡ በዚህ መልኩ በንብ መንጋ የተወረረ የተሳፋሪዎች አውቶቡስም ባለበት ለመቆም ተገድዷል፡፡ ንቦቹ መንገደኞችንና ተሽከርካሪዎችን እንዲሁም የአካባቢውን የትራፊክ መብራትም ወርረው ነበር፡፡

* * *

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...