Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየብሔራዊ ፈተናው እንቅፋቶች

የብሔራዊ ፈተናው እንቅፋቶች

ቀን:

በአንድ ክፍል ውስጥ ስለ ሥራ ለመወያየት የተቀመጡ ባለሙያዎች የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎችና ተማሪዎችን ስለሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች እየተወያዩ ነው፡፡ ርዕሳቸው ኩረጃ ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ መንስዔዎቹ ምንድናቸው? የሚለው ላይም አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ አንዱ የትምህርት ጥራት መጓደል ነው ሲል፣ ሌላው ተማሪ ከትምህርቱ ይልቅ ስለ አኮራረጅ ዓይነቶች ጠንቅቆ ማወቁ ነው ይላል፡፡  የቁጥጥር ማነስና አንዳንዱ ማኅበረሰብም የዚሁ ደጋፊ እየሆነ መምጣቱም በፈተና የደንብ ጥሰት እንዲፈጸም አስተዋጽኦ አድርጓል፣ ከትምህርት ቤት ትምህርት፣ ቤት ከወረዳ ወረዳ ብሎም ከክልል ክልል ብሔራዊ ፈተናን አስመልክቶ ውድድር መግባታቸውም ፈተና ላይ ኩረጃ እንዲስፋፋ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚሉ አስተያየቶችም ይሰነዘራሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ አስተያየቶች ሲሰጡ ራሱን እየነቀነቀ ሲያዳምጡ የነበሩ የቀድሞ መምህር ግን፣ ከአምስት ዓመት በፊት የገጠማቸውን ነበር ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታወሱት፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን በውጭ ቋንቋዎች ካጠናቀቁ በኋላ ሥራን የጀመሩት በመምህርነት ነበር፡፡ የመምህርነት ሥራቸውን ባገኙበት በአንድ ክልል የወረዳ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት ውስጥ እሳቸውም ሆኑ የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ተማሪዎቻቸው ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ በግል ጥረታቸው ጭምር ተማሪዎችን ያግዙ ነበር፡፡

በትምህርት ቤቱ ውስጥ በወቅቱ 105 መምህራንና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ሲኖሩ፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የጎበዝ ተማሪዎች ማኅበርን ለማጠናከርም ብዙ ለፍተዋል፡፡ በዚህም ከተሸላሚ መምህራን አንዱ ነበሩ፡፡ የ12ኛ የመሰናዶ መልቀቂያ ፈተና ሲፈትኑ ያጋጠማቸው ግን ከመምህርነት ለቀው ሌላ ሥራ እንዲያማትሩ ተፅዕኖ ነበረው፡፡

2003 ዓ.ም. ነው፡፡ የብሔራዊ ፈተናውን ለመፈተን የተመደቡት ከሚያስተምሩበት ወረዳ ሳይሆን እዛው በዞኑ ከሚገኝ ሌላ ወረዳ ነው፡፡ ጓደኞቻቸውም እንዲሁ፡፡ ለመፈተን ከቀናት በፊት በሥፍራው ሲደርሱ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ መልካም አቀባበል ቢያደርግላቸውም፣ የአቀባበሉን ማሳረጊያ ያደረጉት ተማሪዎች እንዲኮራረጁ እንዲፈቅዱ ማስጠንቀቂያ አዘል  ትዕዛዝ በመስጠት ነበር፡፡

ፈተናው በተጀመረበት ዕለት ፈታኞች ይህንን አላደረጉም፡፡ የጠዋት ፈተና አልቆ እንደተወጣ ወላጆችና ሌሎች አካላት ተፈታኞች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እንደተደረገና መኮራረጅ እንዳልቻሉ ይሰማሉ፡፡ እኝህ መምህር ከሚያስተምሩበት ወረዳ የመጡ መምህራን ላይም ዛቻ ይሰነዘራል፡፡ ከዚህም አልፎ በዚህኛው ትምህርት ቤት ያስተምሩ የነበሩና ወደሌላኛው ወረዳ ለተመደቡ መምህራን በዚያኛው ወረዳ ለሚፈተኑ ተማሪዎች የመኮራረጅ ዕድል እንዳይሰጡ መልዕክት ይደርሳል፡፡

ለእኝህ መምህር ክስተቱ ሁሉ ያልጠበቁት ነበር፡፡ ተማሪዎች እንዲኮራረጁ የየትምህርት ቤቱ መምህራን ብቻ ሳይሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በዚህ መጠን ይሳተፋሉ ብለው አልጠበቁም፡፡ ሆኖም ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ወላጆችና አንዳንድ አካላት ጭምር ኩረጃ ላይ ያላቸው አመለካከት አዎንታዊ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

የ10ኛና የ12ኛ ክፍልን ፈተናዎች ፈትነው ከአካባቢው እስኪወጡ ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ እንደነበሩ ያስታወሱትም ‹‹የነበረውን ሁኔታ ዳግም አያምጣው፣ በሕይወት በመውጣታችን ዛሬ ገጠመኜን ለመናገር አብቅቶኛል፣ የተፈነከተ ፈታኝም ነበር፤›› በማለት ነው፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት መምህር በነበሩባቸው ጊዜያት የታዘቡትም ፈተናው  ወደ ክልሎች እንደገባ ተከፍቶ የሚታይበት፣ ለጎበዝ ተማሪዎች ቀድሞ ተሰጥቶ የሚሠራበትና በኋላ እነዚህ ጎበዝ ተማሪዎች በፈተና ጊዜ ለቀሪዎቹ ተማሪዎች የሚያስኮርጁበት አሠራር እንደነበር ነው፡፡ በወቅቱ ትክልል አለመሆኑን የሚቃወሙ ባልደረቦች ቢኖሩም፣ ሰሚ አልነበራቸውም፡፡ ‹‹የተማሪን ውድቀት፣ የአገርን ውድቀት ያየሁባቸው ወቅቶች ነበሩ፡፡ ጎበዝ ሆኖ ለሚሠራ፣ ተጠያቂነትንና ሀቀኝነትን ለሚያሰፍን ምቹ ሁኔታ አልነበረም፤›› ሲሉም የመምህርነት ጊዜያቸውን ያስታውሱታል፡፡

ብሔራዊ ፈተና በተማሪዎች፣ በወላጆችና በትምህርት ቤቶች ማኅበረሰብ የሚታየው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመግባት በኋላም ሥራ ለማግኘት እንደ አንድ የሕይወት ምዕራፍ መሸጋገሪያ ድልድይ ተደርጎ ነው፡፡ በመሆኑም አብዛኛው ትኩረት ዕውቀት በመገብየቱ ላይ ሳይሆን ፈተናውን ማለፉ ላይ እንደሆነ በአካጋን ዩኒቨርሲቲ በምዘና ላይ የተሠራ ዳሰሳ ያሳያል፡፡ ወላጆችም ሆኑ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቹ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት እንዳለባቸው ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥሩም ያክላሉ፡፡

ትምህርታዊ ጥናቶችንና መረጃዎችን በኦንላይን ቤተ መጻሕፍቱ የሚያሰራጨው ኤዱኬሽን ሪሶርስ ኢንፎርሜሽን ሴንተር (ኢአርአይሲ) ተማሪዎች በፈተናዎች ላይ ለምን አይታመኑም? ወይም ያጭበረብራሉ? በሚል ባሰፈረው ጥናት፣ እንወድቃለን ብሎ መፍራትን፣ ጥሩ ውጤት የማግኘት ምኞትን፣ የአቻ ግፊትን፣ ውድድርንና ፈተና መውደቅን የሕይወት መጨረሻ አድርጎ መቁጠርን እንደ ምክንያት አስቀምጧል፡፡

ከባህል፣ ከትምህርት ሥርዓት፣ ከትምህርት ጥራት፣ ከፈተናው ዓይነትና ከሚፈተኑበት ምክንያት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶች ተማሪዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጭምር እንዲኮርጁ ምክንያት እየሆኑ ሲሆን፣ ይህ ለኢትዮጵያም ሥጋት ነው፡፡

በኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ የሚፈጸሙ የደንብ ጥሰቶችና የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በአግባቡ ሪፖርት አለመደረጋቸው እንጂ፣ ኩረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን፣ ከሳምንታት በፊት ‹‹የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር›› በሚል አገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባዘጋጁት የውይይት መድረክ  ተወስቷል፡፡

በወቅቱ የ2009 ዓ.ም. የፈተና ቅድመ ዝግጅትና አስተዳደር በሚል የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ፣ በ2005 ዓ.ም. 828፣ በ2006 ዓ.ም. 825፣ በ2007 ዓ.ም. 603 እንዲሁም በ2008 ዓ.ም. 478 ተማሪዎች በአገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ በፈጸሙት የደንብ ጥሰት ውጤታቸው ተሰርዟል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 31 በመቶው ሞባይል በመጠቀም፣ 16.3 በመቶ ደግሞ በስማቸው ሌላ ሰው በማስፈተን ውጤታቸው የተሰረዘባቸው ናቸው፡፡

ተማሪዎች በብሔራዊ ፈተናዎች ላይ ለሚፈጽሟቸው የደንብ ጥሰቶች የተለያዩ ዘዴዎችንና ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ ከመሆናቸው ባለፈ፣ መምህራንም ተባባሪ መሆናቸው የትምህርት ሥርዓቱ በዕውቀት የታነፀ ዜጋን ለማውጣት የሚያደርገውን ጥረት እየተገዳደረው ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ወይም ወደ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲዎች መግቢያ ፈተናዎች ላይ የደንብ ጥሰቶች ወይም ኩረጃ የተራቀቀ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚፈጸም ሲሆን፣ ቻይና ይህንኑ ለመከላከል ተፈታኞችን በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) ማስጠበቅ ጀምራለች፡፡

በኢትዮጵያ የኩረጃው ዓይነት ይህንን ያህል የተራቀቀ ቴክኖሎጂን ይጠቀማል ባይባልም፣ ፈተናውን ቀድሞ በጎበዝ ተማሪ አሠርቶ ተፈታኞች በመኮራረጅ እንዲያልፉት ማድረጉ ላይ ግን ክፍተቶች አሉ፡፡

በአካጋን ዩኒቨርሲቲ የፈተናዎች ቦርድ ባለሙያ አሚን ሪሃማኒ እንደሚሉት፣ ተማሪዎችን ለኩረጃ የሚገፋፋቸው መሠረታዊ ችግር የትምህርት ጥራት መጓደል ነው፡፡  ተማሪዎች ለምን ፈተና ይኮርጃሉ? በሚል ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ተማሪዎች ትምህርቱን ጠልቀው እንዲረዱት በሚያስችል ደረጃ አለመማራቸው፣ የመረዳታቸው አቅምና ምክንያታዊነታቸው የሳሳ መሆን የተማሩትን ለረዥም ጊዜ በአዕምሯቸው እንዳይዙ ስለሚዳርግ ፈተናን ለመኮረጅ ይገፋፋሉ፡፡ የትምህርት ጥራት አስፈላጊነት ላይም አጽንኦት ይሰጣሉ፡፡

በኢትዮጵያ የትምህርት ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም፣ የትምህርት ጥራቱ ላይ ክፍተቶች ይስተዋላሉ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ባካሄዳቸው የተለያዩ መድረኮችም፣ የትምህርት ጥራት መጓደልን እንደ አንድ እንከን ነቅሶ፣ ችግሩን ለመቅረፍ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሐ ግብሮችን እየተገበረ ይገኛል፡፡

ከነዚህም የትምህርት አመራሩን የሙያ ብቃት ማሳደግ አንዱ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለ9,600 አመራሮች የሙያና የትምህርት ደረጃ ማሻሻያ ሥልጠና መሰጠቱን የትምህርት ሚኒስቴር የ2009 ዓ.ም. የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያሳያል፡፡ 63,685 የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ መምህራንም የ2008 ዓ.ም. የክረምትና የ2009 ዓ.ም. መደበኛ መርሐ ግብር ሥልጠና እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡

የትምህርት ተደራሽነትን ከማስፋፋት እኩል ጥራቱ ላይ ባለመሠራቱ ግን አገሪቱም ሆነች ተማሪዎች ዋጋ እየከፈሉ ነው፡፡

በ2008 ዓ.ም. አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ (10ኛ ክፍል) ፈተና ከወሰዱት አጠቃላይ 1,029,782 ተማሪዎች መካከል 760,761 ወይም (73.88 በመቶ) 2.0 እና ከዚህ በላይ ሲያመጡ፣ ከነዚህ የመሰናዶ ወይም 11ኛ እና 12 ክፍል ለመማር ዕድል ያገኙት 299,060 (34.4 በመቶ) ናቸው፡፡ በዚሁ ዓመት የመሰናዶ መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱት 246,452 ተማሪዎች መካከል 185,772 (ከዚህ ውስጥ 42 በመቶ ሴቶች ናቸው) ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተዋል፡፡

ዘንድሮ በብሔራዊና በክልል ፈተናዎች 2,864,913 ተማሪዎች ለመፈተን የተመዘገቡ ሲሆን፣ ለብሔራዊ ፈተና ዝግጅትና ማስፈጸሚያ የሚውል 250 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቧል፡፡

የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት፣ ፈተናውን ለመፈተን ከተመዘገቡት መካከል 1,369,488 የስምንተኛ፣ 1,206,839 የሁለተኛ ደረጃ የአጠቃላይ ትምህርት ማጠናቀቂያ እንዲሁም 288,626 የመሰናዶ ትምህርት መልቀቂያ ተፈታኞች ናቸው፡፡

በብሔራዊ ደረጃ የሚከናወኑ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከግንቦት 28 ቀን እስከ ሰኔ 1 ቀን፣ የ10ኛ ክፍል ፈተና ከግንቦት 23 ቀን እስከ ግንቦት 25 ቀን እንዲሁም የስምንተኛ ክፍል ከሰኔ 7 ቀን እስከ ሰኔ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚሰጥ ሲሆን፣ ለብሔራዊ ተፈታኞች በፕላዝማና በፊት ለፊት ስለፈተናው ገለጻ ይሰጣል፡፡

ዓምና በመሰናዶ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና ያጋጠመውን ስርቆት በመገምገም የፈተና ዝግጅቱን፣ የሥራ አመራር ቦርድ ሥርቱንና የፈተናውን ኅትመት ደኅንነት ሒደቱን በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ በማድረግ፤ የፈተናውን ነባር አስተሻሸግና አደረጃጀት በመለወጥ፣ የፈተናው ሥርጭት፣ ሥርዓት ክልሎችን የሚያሳትፍና ነባሩን ችግር ሊቀርፍ የሚችል ሥርዓት መዘርጋቱን ትምህርት ሚኒስቴር በሪፖርቱ አስቀምጧል፡፡

አቶ አርዓያ እንደሚሉት፣ በፈተና ጣቢያ ኃላፊነት፣ በተቆጣጣሪነትና በፈታኝነት የሚሰማሩ 52,000 መምህራን የተመለመሉ ሲሆን፣ በድጋፍ ሰጪነት ደግሞ 20,000 ርዕሰ መምህራንና የወረዳ ጣቢያ ኃላፊዎችና ፖሊሶች ተመርጠዋል፡፡

ከተሰናዱት 3,500 የፈተና ጣቢያዎች ውስጥ 1,000 ጣቢያዎች ለ12ኛ፣ የቀሩት 2,500 ጣቢያዎች ለ10ኛ ክፍል ተፈታኞች ናቸው፡፡

በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት የሚሰጠው ብሔራዊ ፈተና ግን ከክፍተቶች የፀዳ አይደለም፡፡ ተማሪን ዝግጁ አድርጎ ለፈተና ከማስቀመጥ፣ የትምህርት ግብዓትና ቁሳቁስ ከማሟላት፣ ለሁሉም ወጥ በሆነ መንገድ ትምህርት በመስጠቱ ለምሳሌ በፕላዝማ የሚማሩ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ባላቸው፣ የመማሪያ መርጃ መሣሪያ በተሟላላቸው እንዲሁም የተለያዩ ትምህርታዊ መርጃዎችን ከመረጃ ቋት ማግኘት በሚችሉ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ይህንን ዕድል አሟልተው ካላገኙት ጋር ተመሳሳይ ፈተና ላይ መቀመጣቸው የመማር ማስተማሩ ሒደት እንቅፋቶች ናቸው፡፡

ቢሆንም፣ ለሰዎች ስብዕናና ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት በሚጣልባቸው ትምህርት ቤቶች የተማሪውን ውጤት ማሻሻልና ውጤታማ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በ34,126 ወይም በ94 በመቶው ላይ ለሦስት ዓመታት የኢንስፔክሽን ሥራ ተከናውኗል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሪፖርት እንደሚያሳየውም፣ በአገሪቱ ካሉ አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ34,126 ትምህርት ቤቶች ማለትም 31,592 የመጀመሪያና 2,532 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በተሠራው የኢንስፔክሽን ሥራ 8,727 (25.6 በመቶ) ደረጃ አንድ በዝቅተኛ የሚፈረጁ፣ 21,865 (64.1 በመቶ) ደረጃ ሁለት በመሻሻል ላይ የሚገኙ እንዲሁም 3,510 (10.83 በመቶ) ደረጃ ሦስትና 22 (0.12 በመቶ) ደረጃ አራት ደረጃውን ያሟሉ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡

የኢንስፔክሽን ሥራው እንደሚያሳየው፣ በብሔራዊ ደረጃ ከ85 በመቶ በላይ ትምህርት ቤቶች ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እየሰጡ አይደለም፡፡ በመሆኑም ይህንን ለመለወጥ ከፍተኛ ጥረትን ይጠይቃል፡፡

የአዲስ አበባ ምክር ቤት ማኅበራዊ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮን የዘጠኝ ወራት (የ2009 ዓ.ም.) ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ሰሞኑን ግብረ መልስ በሰጠበት ወቅትም፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ አብዛኞቹ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች በተቀመጠላቸው ደረጃ መሠረት እየሠሩ አለመሆኑን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ የተቀመጠውን ደረጃ አሟልተው የሚያስተምሩ 24 በመቶ ብቻ መሆናቸውን፣ ትምህርት ቢሮው የሚያደርገው ክትትልና ድጋፍም በቂ አለመሆኑም ተመልክቷል፡፡

የትምህርት ጥራት ቁጥጥር ማነስ፣ የተማሪዎች የክፍል ጥመርታ ተመጣጣኝ አለመሆንና ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማሩ ምቹ ከማድረግና ከአዋኪ ድርጊቶች ከመከላከል አኳያም ችግሮች እንዳሉ ተነግሯል፡፡

በብሔራዊ ደረጃ በሚስተዋሉ የመማር ማስተማሩ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆነው የሚማሩ ተማሪዎች ግን ከቤተሰባቸው፣ ከትምህርት ቤታቸውና ከጓደኞቻቸው ፈተና ማለፍ እንዳለባቸው ይነገራቸዋል፡፡ ኢአርአይሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተፅዕኖዎችን አስመልክቶ እንደሚለውም፣ ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ካላመጡ፣ የሚፈልጉት ዩኒቨርሲቲ እንደማይገቡ፣ በሚፈልጉት ኮሌጅ ካልገቡ የሚፈልጉትን ሥራ እንደማያገኙ፣ የሚፈልጉትን ሥራ ካላገኙ ሕይወታቸው የተመሰቃቀለ እንደሚሆን ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲነገራቸው ያድጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሌሎች አማራጮችን የማሳጣት ተፅዕኖ ባለበት ሁኔታ፣ የትምህርት ጥራት መጓደል ተማሪዎችን ወዳልተፈለገው የፈተና ደንብ ጥሰት እንዲያመሩ ያደርጋል፡፡

ከ18 ሺሕ በላይ ተከታዮችና ወዳጆች ያሉትና ተማሪዎች ካልኮረጁ እንደማያልፉ የሚሰብከው ‹‹የኢትዮጵያ ፈተና ኮራጅና አስኮራጅ ተማሪዎች ኅብረት የፌስቡክ ገጽ›› አለ፡፡ ገጹ ላይ ትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ አገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የሚያወጧቸው መረጃዎች የሚስተናገዱ ቢሆንም፣ ይበልጡኑ ትኩረት የሚሰጠው በገጹ አቀንቃኞች የሚለጠፉ ስለኩረጃ አስፈላጊነትና ዓይነት የሚሰብኩ ጽሑፎች ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አበበ ቸርነት፣ ገጹን እንደሚያውቁት፣ ቴክኖሎጂ ሲመጣም የራሱን ተፅዕኖ ይዞ እንደሚመጣ በመግለጽ፣ ይህንን አመለካከት ግንዛቤ በመፍጠር ለመለወጥ ከወላጅ፣ ከመምህሩና ከተማሪው ጋር እንደተሠራበት ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቢሮው ብቻውን እንደማይወጣውና ኩረጃን ሙሉ ለሙሉ ማስቆም ይቻላል ብሎ መደምደም እንደማይቻል በመግለጸም፣ በቢሮ ደረጃ ስለልጁ ግድ ያልሰጠው ወላጅ ካልሆነ በስተቀር በየትምህርት ቤቱ ወላጅ ልጁን እንዲከታተል፣ መምህሩ፣ ተማሪውና ወላጅ አብሮ እንዲሠራ ዕድሉ ተመቻችቷል ብለዋል፡፡

ተማሪ ወደ መኮረጅ የሚሄደው በራሱ ላይ ያለው እምነት ሲሸረሸር በመሆኑ ፈተና ላይ ከመቀመጣቸው በፊት በራሳቸው እምነት እንዲያሳድሩ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የኩረጃ አስፀያፊነትን የተመለከቱ ማስታወቂያዎች እየተነገሩ ሲሆን፣ የዘንድሮ ብሔራዊ ፈተናዎችም እንደቀድሞ በወረቀት ሳይሆን፣ በላስቲክ እንዲታሸጉ ተደርጓል፡፡   

ለትምህርት ጥራት ወሳኝ የተባሉ መርሐ ግብሮችም እየተተገበሩ ሲሆን፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ የሚገኙ 65 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በቢሮው ከሚገኘው የመረጃ ቋት መተሳሰራቸውን፣ ተማሪዎችም የሚፈልጉትን የትምህርት መረጃ ማግኘት እንደሚችሉ የትምህርት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ገበየሁ ወርቅነህ ነግረውናል፡፡

ክልሎች ወደዚህ ሥርዓት ለመግባት እየሠሩ ቢሆንም አዲስ አበባ ተማሪዎችን የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ተጠቃሚ በማድረጉ ልቃ ትገኛለች፡፡ እንደ መላ አገሪቱ ሲታይ ሁሉም ተማሪዎች የዚህና የሌሎችም ግብዓቶች እኩል ተጠቃሚ ባይሆኑም፣ ፈተና ላይ የሚቀመጡት በአንድ ላይ ነው፡፡ ሆኖም የማለፊያ መስፈርቱ ለክልሎችና ለሴት ተማሪዎች ዝቅ ይደረጋል፡፡ ይህ ደግሞ የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አንፃር የራሱ ተፅዕኖ አለው፡፡ ተማሪዎች ግን በእነዚህ እንቅፋቶች ተሸብበው ብሔራዊ ፈተናውን እንዲወስዱ ይደረጋሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...