Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክየፌደሬሽንን ምክር ቤት ላልተሻገራቸው ፈተናዎች የሰጣቸው አስረጅ ውሳኔዎች

የፌደሬሽንን ምክር ቤት ላልተሻገራቸው ፈተናዎች የሰጣቸው አስረጅ ውሳኔዎች

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ግንቦት 13 እና 14 ቀን 2009 ዓ.ም. የፌደሬሽን ምክር ቤት አምስተኛው የፓርላማ ዘመን ሁለተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን አከናውኗል፡፡ በእነዚሁ ዕለታት በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም›› ብሎ ካቀረባቸው 52 አቤቱታዎች መካከል 49ኙን በማጽናት፤ አንዱን ለተጨማሪ ጥናት በመምራት በጥቅሉ ሦስት ጉዳዮችን የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልጋቸው ወስኗል። ምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጉም ከሰጠባቸው ጉዳዮች ውስጥ በይፋ የተነገረው በአፋር ክልል፣ በአብዓላ አካባቢ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የልዩ ወረዳ ምሥረታ ጥያቄን የሚመለከተው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ‹‹አንዱ ጉዳይ›› እየተባለ የተዘገበው ነው፡፡ መረጃው የሚሠበሰብበትም ጉዳይ ምን እንደሆን በሚዲያ አልተገለጸም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛም ምክር ቤቱ ውሳኔ የሰጠበትን ሁኔታ የሚመለከት ነው፡፡

አንዱ ጉዳይ

- Advertisement -

በሪፖርቱ እንደተመለከተው፣ ከአራቱ ጉዳዮች መካከል አንዱ ለተጨማሪ ጥናት የተመራ ሲሆን፣ ሦስቱ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልጋቸው በምክር ቤቱ ውሳኔ ተሰጥቷል። ከትግራይ ተወላጆች የልዩ ወረዳ ጥያቄ ውጭ ጉዳዮቹ ምንን እንደሚመለከቱ ምክር ቤቱ ለሕዝብ አላሳወቀም፡፡ በተለይ የሕገ መንግሥት ትርጉም የተሠጠበት አንደኛውን ጉዳይ መገናኛ ብዙኃን የዘገቡት እንዲሁ አንደኛው ጉዳይ በማለት ነው፡፡ ሚዲያዎችም የጉዳዩን ምንነት አልጠየቁም፤ ወይ እንዳይጠይቁ ተነግሯቸዋል፡፡ ለማንኛውም፣ ምክር ቤቱ አንድ ጉዳይን በተመለከተ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ውሳኔው ግን ከሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ መንግሥትን መሠረት አድርጎ የተሰጠ ፍርድ ነው፡፡

ለነገሩ ወዲያውኑ የተወሰነ ውሳኔ ቀርቶ በርካታ ዓመታት ያስቆጠሩትንም ለማወቅም ሆነ ለማግኘት እጅግ አዳጋች መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ብቻም ሳይሆን በበርካታ የሕገ መንግሥት ተመራማሪዎች ዘንድም አይታወቁም፡፡

ውሳኔዎችን ለሕዝብ ይፋ ማድረግን በተመለከተ ግን ምክር ቤቱ ለዚሁ ጉዳይ በሚወጣ መጽሔት ላይ ማሳተም እንዳለበት የፌደሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/1993 ላይ ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህንን መብት የሚጠይቀውን መጽሔት ያሳተመው የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ ነው፡፡

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔን ለማጠናከር፣ ሥልጣንና ተግባሩንም ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 798/2005 ላይ እንደተገለጸውም፣ የጉባዔው ጽሕፈት ቤት የምርምርና ጥናት አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ በየጊዜው ስለአጣሪ ጉባዔውና ሥራዎቹ መግለጫ መስጠት አለበት፡፡ መጽሔት፣ ዓመታዊ ሪፖርት እንዲሁም ሌሎች ጽሑፎችን አሳትሞ ማሰራጨት እንዳለበት ግዴታ ተጥሎበታል፡፡

ይሁን እንጂ፣ ጉባዔውም ይኼንን ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ አስተያየት ወይም ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዩች ፍፁም ተደራሽ አይደሉም፡፡ የሰበር ውሳኔዎችን እያተመ የሚሰራጨውን የፌዴራሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ሆነ ጉባዔውን የሚመሩት ሰዎች ሁልጊዜም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የአጣሪ ጉባዔውን ውሳኔዎችና ሪፖርቶች እንዲታተም ማድረግ አልቻሉም፡፡ በድረገጽም ቢሆን አልጫኗቸውም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዕለቱ የሚሠጡ ሕገ መንግሥታዊ ውሳኔዎችም ሆኑ ሕገ መንግሥታዊ አንድምታ ያላቸው ለውጦች ሲወጡ ግን በኢሜይላችን በየዕለቱ እናውቃለን፡፡ ቅረቅባችን ያሉት የእኛው ሰዎች ግን እንደራቁን ናቸው፡፡

በምክር ቤት መፍረድ

ኢትዮጵያ፣ የሕገ መንግሥት ተርጓሚ በማድረግ የመረጠችው አካሄድ ለዓለም ባይታወር ነው፡፡ ከየአገሩ የግል ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት እያንዳንዱ አገር በራሱ የተለየ እንደመሆኑ መጠን፣ የኢትዮጵያ ሞዴልም ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ለመቅረጽ የተደረገ ጥረት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(1) እንደተመለከተው፣ እንዲሁም በአንቀጽ 83(1) እንደተደነገገው ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ያለው መደበኛ ፍርድ ቤት ወይም ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች ሳይሆኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡

ይሁንና የሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ሥራ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ብቻ የሚሠራ ሳይሆን፣ በበርካታ ጉዳዮች (በተለይም የማንነትና የራስን ዕድል በራስ የመወሰንን ጉዳዮችን ሳይጨምር) ሕገ መንግሥታዊ ክርክሮችን የማጣራትና የውሳኔ ሐሳቦችን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የማቅረብ ሥልጣን የተሰጠው የሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 82(1) መሠረት ተቋቁሟል፡፡ በሁሉም ሕገ መንግሥታዊ ክርክሮች ላይ የመወሰን ሥልጣን ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢሆንም! ሕገ መንግሥታዊ ክርክሮችን በቅድሚያ የማጣራቱ ተግባር የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ነው፡፡

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አሥራ አንድ አባላት ያሉት ነው፡፡ ሰብሳቢውና ምክትል ሰብሳቢው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ በተወካዮች ምክር ቤት ተመርጠው በአገሪቱ ፕሬዚዳንት የሚሾሙ ስድስት የሕግ ባለሙያዎችና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚውጣጡ ሦስት ተጨማሪ አባላት ያሉበት ተቋም ነው፡፡ በዋናነት የሕገ መንግሥት ትርጉሙን እንዲሠሩ የተመረጡት እነዚህ ሰዎች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ይኼን አካሄድ የመረጠችበትን ምክንያት ስንፈትሽ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር ስለሆነች እነዚህ የማኅበረሰብ አካላት ያላቸውን ጥያቄ መፍታትና ፍርድ መስጠት ያለባቸው ራሳቸው እንጂ በጣት ለሚቆጠሩ ዳኞች ተላልፎ መሰጠት የለበትም ከሚል መነሻ ነው፡፡

አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ዳይሬክተር ለሆኑት ለአቶ ሙልየ ወለላው ላቀረበላቸው ጥያቄ ከሰጡት ምላሽ መገንዘብ የሚቻለው ግን ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት በብዛት እየመጡ ያሉት ጉዳዮች ቀድመው በፍርድ ቤት የታዩና በሰበርም እልባት ያገኙ ናቸው፡፡ በፍርድ ቤት የሚታይ ጉዳይ ደግሞ በአብዛኛው ይዘቱ ግለሰባዊ እንጂ ብሔር ነክ አይደለም፡፡ ዳይሬክተሩ የመለሱት እንዲህ ነው፡፡ ‹‹ጥያቄዎቹ ምን ላይ የሚያተኩሩ ናቸው ከተባለ አንዱ መሬት ላይ የሚያተኩረው ነው፡፡ መሬት አይሸጥም፣ አይለወጥም፣ የሕዝብና የመንግሥት ነው እየተባለ ሽያጭ በሚመስል መልኩ መያዣና መለወጫ ተደርጎ ይታያል፡፡ ሌሎች ጥያቄዎች ከሴቶች መብት፣ ከአሠሪና ሠራተኛ እንዲሁም ከውርስ ጋር ተያያዘው ይቀርባሉ፡፡ ከሕጻናት፣ ከአካል ጉዳተኞች፣ ከንብረት መብት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችም ይቀርባሉ፡፡ ጥቄዎቹ በአብዛኛው በእነዚህ ላይ ያጠነጠኑ ናቸው፡፡… ፍርድ ቤቶች የሰጧቸው ወደ 32 የሚሆኑ ውሳኔዎች ተሽረው በምክር ቤቱ ተወስነዋል፡፡›› በመሆኑም፣ አገሪቱ ለሕገ መንግሥት ተርጓሚነት የመረጠችው አካል በአብዛኛው እየተመለከተ ያለው ጉዳይ ብሔር ነክ አይደለም ማለት ነው፡፡ ብሔር ነክ ያልሆነ ጉዳይ የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና ሕዝቦችን መብት ይነካል የሚያሰኘው ነገር የለም ማለት ነው፡፡ በእርግጥ በጣት የሚቆጠሩ የማንነት ጥያቄዎች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡

ለምክር ቤቱ ይህ ሥልጣን የተሰጠበት ምክንያት የብሔሮችን ጉዳይ ለጥቂት የሕግ ባለሙያዎች ላለመተው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም እየተወሰነ ያለው በጣት በሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ማስረጃው የምክር ቤቱ አባላት ጉዳዩን ‹‹በአግባቡ ሳንረዳው እንዴት መወሰን እንችላለን?›› ያሉበት አንደኛው ነው፡፡ የተወሰኑ ባለሙያዎች ጥናት አድርገው ለምክር ቤቱ በማቅረብ ድምፅ እንዲሰጥበት ሲጠየቅ ምላሹም ይኼንኑ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች መወሰናቸውን በሚያረጋግጥ መልኩ ‹‹ቋሚ ኮሚቴው ጉዳዩ ውድቅ እንዲሆን ያቀረበው አስፈላጊውን ምርመራ ካደረገ በኋላ በመሆኑ ውሳኔው መጽደቅ እንዳለበት አባላቱ አንስተው ክርክር ተደርጎበት በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል።›› በማያውቁት፣ ባላጠኑት ጉዳይ ላይ እጅ በማውጣታቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እየወሰኑ ነው ማለት ግን ለሰሚውም ግራ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ እየወሰኑ ያሉት ጥቂት ሰዎች ናቸው ማለት ነው፡፡

ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥቱን  ከመተርጎሙ በፊት

የትርጉም አሰጣጥ ሒደቱን እንመለከት፡፡ ለዚህም ቢሆን አሁንም ዋቢው የዳይሬክተሩ መልስ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ጥያቄ ለምክር ቤቱ ሲቀርብ እንዴት እንደሚታይ ሲጠየቁ ‹‹የትርጉም ጥያቄዎች እያደጉ መምጣታቸውን ተከትሎ የተለያዩ መድረኮች እናዘጋጃለን፡፡ በመድረኩ የተለያዩ የፍትሕ አካላት ይሳተፋሉ፡፡ በዚህም ላይ የሚሰጧቸው አስተያየቶች በጣም ጥሩ ናቸው፡፡ እኛ ጥያቄ እናቀርብላቸዋለን፡፡ አንደኛ የምክር ቤቱን የውሳኔ አጻጻፍ እንዲተቹ ክፍት አድርገንላቸዋል፡፡ ሁለተኛ ጉዳዮችን (ኬዞችን) እንዲመዝኗቸው ክፍት አድርገንላቸዋል፡፡ ሁለተኛ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለተለያዩ ጥያቄዎች ምሁራን እየመጡ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጉዳዩን እየሰጠናቸው ሠርተናል፡፡ ስለዚህ አካሄዳችን ጥሩ እንደሆነ መረዳት ችለናል፤›› በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

ከላይ የቀረበው አስተያየትን ትንሽ በማፍታታት ለተመለከተው ግን ችግሮቹ በርካታ ናቸው፡፡ አንዱን ብቻ እንመለከት፡፡ የሕገ መንግሥት ትርጉም መስጠት ጥልቅ የሕገ መንግሥት ዕውቀትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ያለቸው አገሮችን ብንመለከት ለዳኝት የሚመለመሉት ለበርካታ ዓመታት በዩኒቨርሲቲ ሕገ መንግሥት ያስተማሩ ወይም በጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት የሠሩ ምሁራንን ነው፡፡ በተጨማሪም፣ በርካታ ረዳትና ተመራማሪዎችን በሥራቸው ይቀጥራሉ፡፡ ወጥ በሆነ መንገድ ሥራቸውና ምርምራቸው በዚሁ በሕገ መንግሥት ዙሪያ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም የሕገ መንግሥት ትርጉም ሥራ የባጣ ቆየኝ ነገር አይደለም፡፡ ውሳኔው ፍርድ ነው፡፡ ለዚያውም የሕገ መንግሥት ፍርድ ነው፡፡ ይህንን ሥራ ለማከናውን በየጊዜው የተለያየ ሰው በመጥራት መተርጎም ተገቢ አይደለም፡፡ አስተያየት መቀበልና የሙያ ማብራሪያ መጠየቅ ጥሩ ሊሆን ቢችልም የፍርድ ሥራ ለሌላ ሰው የሚተው አይደለም፡፡ የአተረጓጎም ችግርን የበለጠ ለመረዳት የትግራይ ተወላጆችን የልዩ ወረዳ ጥያቄ እንመለከት፡፡

የትግራይ ተወላጆችን የልዩ ወረዳ ጥያቄ በምሳሌነት

በአሁኑ ስብሰባው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አብዓላ ወረዳ የሚኖሩ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ያቀረቡትን የልዩ ወረዳ ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡ የምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ  ሰብሳቢ አቶ ወርቁ አዳሙ የተናገሩትና ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከሆነ፣ የማንነት መብቶች አጠባበቅን በተመለከተ በአፋር ክልል ዞን ሁለት አብዓላ ወረዳ የሚኖሩ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ‹‹የማንነት መብታችን ቢከበርም ራሳችንን በራሳችን የማስተዳደር መብታቸው  ተሸራርፏል›› በሚል ምክንያት ቅሬታ ለአፋር ክልል አቅርበው ነበር፡፡ ራሳቸውን በራሳቸው ከማስተዳደር ባለፈም ተወላጆቹ ‹‹ቋንቋችን፣ ባህላችንና ታሪካችንን የምናሳድግበት ሁኔታ አልተመቻቸልንም›› በማለት ጥያቄ እንዳቀረቡም ተገልጿል።

ክልሉም አመልካቾቹ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት የላቸውም በማለት ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ ተዘግቧል፡፡  አቤቱታ አቅራቢዎቹ በክልሉ ውሳኔ ቅር በመሰኘታቸው ጉዳያቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበዋል። ምክር ቤቱም ከቦታው ድረስ አጥኚ ቡድን በመላክ ከመረመረ በኋላ ‹‹ሁለቱም ብሔሮች በአካባቢው ተከባብረውና ተፋቅረው የሚኖሩ መሆናቸውን አረጋግጧል፤›› በማለት አቶ አዳሙ መልሰዋል፡፡ ለጥቄው መባባስ ምክንያት በወረዳው የተስተዋለው የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሆነም ተገልጿል። በመሆኑም ‹‹የቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ተቀባይነት የለውም፡፡ ነገር ግን በአካባቢው የሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታና ሕጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻች፤›› የሚል የውሳኔ ሐሳብ ከቋሚ ኮሚቴው አስተያየት ሰጥቷል፡፡

ኮሚቴው ላቀረበው የውሳኔ ሐሳብ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሓጅ ስዩም ሲመልሱ ‹‹ማንኛውም የአፋር ብሔር ተወላጅ እንደሚያገኘው ሁሉ እንዲያገኙ መብታቸው ከሚከበርላቸው በስተቀር የክልሉ የሥራ ቋንቋ አፋርኛ በመሆኑ ተወላጆቹ በአፋርኛ መማር አለባቸው፤›› ብለዋል።

ምክር ቤቱ በበኩሉ ‹‹ማንኛውም ሕጻን በአፍ መፍቻ ቋንቋው መማር አለበት›› የሚለው ሕገ መንግሥታዊ መብት ስላለው፣ የርዕሰ መስተዳደድሩን ሐሳብ ውድቅ አድርጎታል፡፡ በተጨማሪም ክልሉ ይህን ቢያደርግ የሚጎዳው ነገር እንደሌለ፣ የሚያጋጥም የበጀትና የግብዓት ችግር ካለ ግን የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል በኩል ቢያመቻች የተሻለ መሆኑን ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡

ከላይ ከቀረበው ውሳኔ ላይ ሦስት እንከኖችን ብቻ እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው ለአመልካቾች ጥያቄ መነሻ የሆነውን ‹‹መብት›› ይመለከታል፡፡ ከምክር ቤቱ ግኝት የምንረዳው የአቤቱታው መነሻ ወይም ያባባሰው የመልካም አስተዳደደር ችግር መኖሩ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደደር ችግር መኖሩ አንድ ነገር ነው፡፡ አመልካቾቹ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተደዳር መብት መኖር አለመኖር ደግሞ ሌላ ነው፡፡ የማንነት መብታቸው ከተከበረላቸው ስለምን ራሳቸውን በራሳቸው አያስተዳሩም? የስልጤ ብሔረሰብ ዕውቅና ሲሰጠው እንደተገለጸው የማንነት ጥያቄ ዞሮ ዞሮ ውጤቱ ራስን በራስ ማስተዳደር እንደሆነና ከዚህ እንደማይለይ ተገልጿል፡፡ የማንነት ጥያቄ ራስን ከማስተዳደር ጋር የተያያዘ ከሆነ የልዩ ወረዳ ምሥረታና በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር የዚህ ተከታዮች ናቸው፡፡

ሁለተኛው በራስ ጉዳይ ላይ ዳኛ ከመሆን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የአፋር ክልል ቅሬታ የቀረበበት ተከሳሽ ሆኖ ሳለ ዳኛ ሆኖ መቀመጡ በጭራሽ ምክንያታዊ አይደለም፡፡ ከተፈጥሮአዊው የፍትሕ መርሕ ያፈነገጠ ነው፡፡

ሦስተኛው የውሳኔውን ይዘት ይመለከታል፡፡ ምክር ቤቱ መጨረሻ ላይ ያስቀመጠው የአመልካቾች ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር መብት እንዳላቸው ነው፡፡ ክልሉ ይህንን ለመተግበር ከተቸገረ ግን የተለያዩ ግብዓቶችን የፌዴራል የትግራይ ክልል መንግሥታት ቢያመቻቹ የተሻለ መሆኑን በመግልጽ ነው የደመደመው፡፡ ከዚህ ውሳኔ መረዳት የሚቻለው የአመልከቾች በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማር መብታቸው ዕውቅና ማግኘቱን ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ የአፋር ክልል ይህንን ቢተገብር እንደማይጎዳ በማሰብ የተወሰነ እንጂ ግዴታ ስላለበት አይመስልም፡፡ የበጀትና ግብዓት እጥረት አጋጥሞኛል በማለትም ላይፈጽመው ይችላል፡፡ የትግራይ ክልልና የፌደራሉ መንግሥት ቢያመቻቹ የተሻለ ነው ማለትም ከምክርነት የዘለለ  አይደለም፡፡ በመሆኑም አመልካቾች ከአፋር ክልል ላይ ምን ተፈረደላቸው ቢባል መልሱ ምክረ ሐሳብ የማቅረብ ዓይነት እንጂ አስገዳጅ የሆነ ውሳኔ ነው ማለት ያዳግታል፡፡

የሕገ መንግሥት ትርጉም አስፈላጊነት

ለመሆኑ ሕገ መንግሥት ስለምን ይተረጎማል? ምን ምን ሁኔታ ሲያጋጥም የትርጉም ጉዳይ ይነሳል? ሌላው የምክር ቤቱ ተግዳሮት የሚመነጨው የሕገ መንግሥትን የትርጉም ምክንያት በአግባቡ ካለመረዳት የመነጨ ነው፡፡

ሕገ መንግሥትን ጨምሮ ማንኛውንም ሕግ መተርጎም የራሱ የሆነ የመተርጎም ሥርዓት፣ ዘዴ ወይም መርሖች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ ለማንኛውም የሕግ ድንጋጌ ትርጉም የሚያስፈልገው ግልጽ ሳይሆን ሲቀር ማለትም ድንጋጌው አሻሚ፣ ከሌሎች ሕጎች ወይም ድንጋጌዎች ጋር ግጭት ሲፈጠር ወይም መጣጣም ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡

በአንድ በኩል የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያስፈልገው በየደረጃው የሚወጡ ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር ከተቃረኑ ነው፡፡ ከመጀመሪያውኑ እነዚህን ውሳኔዎች የሚወስኑ አካላት ሕጎቹ፣ ደንቦቹ ወዘተ ከሕገ መንግሥቱ ጋር በማይቃረን መልኩ የማውጣት ግዴታ አለባቸው ፡፡

ይሁንና እነዚህ ውሳኔዎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር በተጣጣመ መልኩ እንዲወሰኑ ቢጠበቅም አንዳንድ ጊዜ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ከሕገ መንግሥቱ መንፈስና ዓላማ ጋር የተጋጩ ወይም የተቃረኑ ናቸው በሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ ስለሆነም ውሳኔው ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናል ወይስ አይቃረንም በሚል አለመግባባት ሊነሳ ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ግጭት ስለመኖሩና አለመኖሩ ለማረጋገጥ ጉዳዩን በመመርመር ሕገ መንግሥትን የመተርጐም ሥልጣን፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 84(2) መሠረት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ተሰጥቶታል፡፡ በአጠቃላይ በሕጐችና በሕገ መንግሥቱ መካከል ግጭት ስለመኖሩ የሕገ መንግሥት ጉዳይ ክርክር ሲቀርብ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 83(1) መሠረት ሕገ መንግሥትን በመተርጐም  ውሳኔ ይሰጥበታል ማለት ነው፡፡

ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ የሕገ መንግሥት አቀራረጽ በጥቅል አነጋገርና ብዙ ጉዳዮችን እንዲያካትት ተደርጎ ስለሚሆን በሕገ መንግሥት ውስጥ የተቀመጡ ቃላትን፣ ሐረጋትን፣ ዓረፍተ ነገሮችን ማብራራት፣ ግልጽ ማድረግ ወዘተ ያስፈልጋል፡፡ ከጥቅልነቱ ምክንያት ሰዎች ሕገ መንግሥቱን የሚረዱበት መንገድ ሊለያይም ይችላል፡፡ ግልፅ ያለመሆን የቃላት፣ የአገላለጽ ወይም የሕጉ መንፈስ ግልጽነትን የሚመለከት ሊሆን ይችላል፡፡

ሕገ መንግሥት ዝርዝርና ተራ ከሆኑ መርሖች ይልቅ ውስብስብና ጥቅል በሆኑ ጽንሰ ሐሳቦች የተሞላ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ቋንቋ ጥቅል ከመሆኑም ባሻገር የቃላቱ ተፈጥሮና አቀማመጥ ሕገ መንግሥትን ከሌሎች ሕጐች በእጅጉ ይለየዋል፡፡ እንዲሁም የቋንቋ ምሁራን እንደሚናገሩት፣ ቃላትም ሆኑ ቋንቋ ከጊዜ ወደ ጊዜ ያድጋሉ፣ ይሻሻላሉ፣ ይቀየራሉ፡፡ ስለሆነም እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን ግልፅ ለማድረግ ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም ይበልጥ ግልፅ ማድረግ ይገባል፡፡

ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም የሚሰጡ ቃላት፣ ሐረጋትና ዓረፍተ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም በመስጠታቸው ወይም በመረዳታቸው ጥቅሞቻቸው (መብቶቻቸው) በተረዱበት መጠን እንዲከበርላቸው ስለሚፈልጉ አለመስማማት ብሎም አለመግባባት ስለሚፈጠር የማንኛቸው ትርጓሜ ትክክል እንደሆነ የሚነግራቸው አካል ይፈልጋሉ፡፡ የተለያየ ትርጓሜ በመስጠታቸው የተፈጠረውን አለመግባባትም የሕግ ተርጓሚው አካል ትርጓሜ በመስጠት እልባት ይሰጣል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤትም አንዱ ተግባሩ ይኼው ነው፡፡

ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪም ክፍተትን ለመሙላት ይተረጎማል፡፡ የሕገ መንግሥት ሰነድ በጣም በጥቅል አቀማመጥ ከመቀመጡ የተነሳ ሕገ መንግሥት የተወሰኑ ጉዳዮችን ብቻ ሊዘረዝር ይችላል፡፡ በአብዛኛውን ጉዳዮች መርሕን ብቻ ሊያስቀምጥ ይችላል፡፡ በስልጤ ጉዳይ፣ የማንነት ጥያቄ አመላለስን በተመለከተ የተሰጠውን ትርጓሜ ማንሳት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም፣ ከእነዚህ መርሕ በመነሳት በዝርዝር ያልተቀመጡና ያልተሸፈኑትን ጉዳዮች አጠቃላይ የሰነዱን ይዘትና መንፈስ በመፈለግ የመተርጐም ሥልጣን ያለው አካል ሊተረጉም ይችላል፡፡ በእርግጥ ሕገ መንግሥት መሻሻል እንደሚችል ሁሉ በቀላሉና በማናቸውም ጊዜ የሚሻሻል ባለመሆኑ በእያንዳንዱ አገሮች ነባራዊ የዕድገት ሒደት በሕገ መንግሥት ያልተሸፈኑ ጉዳዮች ትርጉም እየተሸፈኑ ይሔዳሉ፡፡

የምክር ቤቱን የሕገ መንግሥት ትርጉም አስፈላጊነት አረዳድ ደግሞ እንመለከት፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለአቶ ሙልየ ወለላው ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም ለምን ያስፈልጋል?›› በማለት ላቀረበላቸው የሰጡት መልስ የሚከተለው ነው፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥት የሁሉም ሕጎች የበላይ ሕግ ነው፡፡ በመሆኑም የሚወጡት ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች፣ ውሳኔዎችና ልማዳዊ አሠራሮች ከሕገ መንግሥቱ ጋር መጋጨት የለባቸውም። የሚጋጭ ወይም የሚቃረን ሆኖ ከተገኘ ማረም የሚቻለው የሕገ መንግሥት ትርጉም በመስጠት ነው፡፡ አንድ ሕግ ሊሆን ይችላል፤ የሕጉ የተወሰነው ክፍል ወይም ድንጋጌ ትርጉም ያስፈልገዋል በሚል አቤቱታ የሚቀርበው የአንድ ሕግ ወይም የሕጉ የተወሰነው ክፍል ወይም ድንጋጌ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ሲጋጭ ወይም ሳይጣጣም ሲቀር ነው።››  

ከላይ በዝርዝር እንደተመለከትነው ለሕገ መንግሥት ትርጉም የመስጠት ምክንያቶች በርካታ ናቸው፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔና የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ዳይሬክተሩ ለተለያዩ የዜና አውታሮች እንደገለጹት ከሕገ መንግሥቱ ጋር ግጭት ስለተፈጠረ ብቻ አይደለም፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያስፈልገው፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ የምክር ቤቱ አፈጉባዔ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት በሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳይ ከፍተኛ የግንዛቤ ችግር በመኖሩ ‹‹ሁሉም ጉዳይ በምክር ቤቱ ይፈታል ተብሎ ስለሚታመን ትንንሽ ጉዳዮችም ጭምር ይመጣሉ›› ብለዋል። ግን የፍትሕ ጉዳይ በመጠን የሚገለጽ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ማኅበረሰቡ እንደሚለው፡-

‹‹ትንኝም ለሆዷ ዝሆንም ለሆዱ፣

ውኃ ለመጠጣት ወደ ወንዝ ወረዱ፤›› ነው ነገሩ፡፡

የፍትሕ ጉዳይ ትንሽ ነው ተብሎ አይነፈግም፡፡

ለማጠቃለል ምክር ቤቱም ሆነ አጣሪ ጉባዔው ውሳኔዎችን አለማሳወቃቸው የሕገ መንግሥቱን የሕዝብ ሰነድነት መካድ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን በሚመለከት የሚሰጡ ትርጉሞችን በተቻለ ፍጥነት ለሕዝብ ማሳወቅ ይገባል፡፡ ውሳኔ ሰጭዎቹ ሳያውቋቸው መወሰን ከታሰበለት ዓለማ ማለትም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሳያውቋቸው የመወሰን ያህል ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የምክር ቤቱ አባላት በጥልቀት ሳያጠኗቸውና ሳይወያዩባቸው በአንድ ቀን ሃምሳ ሁለት ጉዳዮችን መወሰን ዞሮ ዞሮ በጥቂት ሰዎች ለዚያውም ብዙም ተጠያቂነት በሌላቸው ሰዎች  አሳልፎ መስጠት ነው ትርፉ፡፡ የአጣሪ ጉባዔው አባላትም ይሁኑ የምክር ቤቱ አባላት ሌላ ሥራ ያላቸው መሆኑ እየታወቀ  በሌሌሎች ባለሙያዎች የሚቀርብላቸውን አስተያየት በሩጫ መወሰን ከታሰበለት ከሕገ መንግሥት የትርጓሜ መስጠት ተግባር ፍጹም የራቀ ነው፡፡ በመሆኑም ያለፈውን ጉዞ ማጤን ተገቢ ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...