Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉያለ ገበያ ማኅበረሰብ ትራንስፎርሜሽን ዘበት ነው

ያለ ገበያ ማኅበረሰብ ትራንስፎርሜሽን ዘበት ነው

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ሚያዝያ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹የኢንዱስትሪው ሞተር የት ነው?›› በሚል የዜና ትንታኔ የቀረበ የምሁራን ሐሳብ የያዘ ጽሑፍ ወጥቶ ነበር፡፡ በትራንስፎርሜሽን ላይ ከአቅርቦት ጎን የሚታዩ ችግሮችን ይዘረዝራል፡፡ በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በኢንዱስትሪው ዘርፍ ፈቃድ ከወሰዱ 4,387 የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ትግበራ የገቡት 79 ብቻ እንደሆኑ፣ በዕቅዱ የመጀመሪያ ዓመት ፈቃድ ከወሰዱ 993 ፕሮጀክቶች መካከል ወደ ትግበራ የተሸጋገሩት 33 ብቻ መሆናቸውን፣ በዕቅድ ዘመኑ ማብቂያ ዓመት ላይ ደግሞ ለ625 ፐሮጀክቶች ፈቃድ ቢሰጥም ወደ ትግበራ የተሸጋገሩት ሁለት ብቻ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዲን ዶ/ር ደለለ ወርቁ የሦስተኛ ዲግሪያቸውን ምርምር የሠሩት በኢንዱስትሪ ላይ እንደሆነ፣ የችግሩ ምንጭ የመረጃ ክፍተት መሆኑን፣ መመርያዎችና ደንቦች ለባለ ሀብቱ አለመድረሳቸውን፣ ደርሶስ ተገንዝበዋቸዋል ወይ? ማለታቸው ቀልብ የሚስቡ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በዚሁ በሚያዝያ ወር ውስጥ በሰንደቅ ጋዜጣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‹‹ለሕዝብ ያልተዋጠ ከሕዝብ የራቀ›› በሚል ርዕስ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ለሕዝብ በሚገባው መንገድ እንደሚነበብ አጠር ተደርጎ አልቀረበም የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ እኔም ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ትራንስፎርሜሽን የሚለው ስያሜ ትርጉም ያጣ እንደሆነ በሪፖርተር ጋዜጣ በተደጋጋሚ ጽፌአለሁ፡፡

አሁንም ሁለቱ ምሁራን ባነሱት ነጥቦች ላይ መስማማቴን ገልጬ፣ ከዚህም ጠንከር ያለ መከራከሪያ ነጥብ አነሳለሁ፡፡ የትራንስፎርሜሽንን ጽንሰ ሐሳብ ለሰው ማስረዳታቸው ቀርቶ ራሳቸው አቃጆቹ ገብቶአቸዋል ወይ? ብዬ እጠይቅና ስለትራንስፎርሜሽን የማውቀውን አካፍላለሁ፡፡

ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በታተመ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በገጽ ዘጠኝ የኢኮኖሚ  ዓምድ፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የፖለቲካ መድረክ ለሚቀርብ የዘላቂ ልማት ግቦችና የ2017 ግምገማ ሪፖርት ረቂቅ ውይይት የምክክር መድረክ ላይ ገለጻ ባደረጉ ሦስት የፕላን ኮሚሽኑ ባለሥልጣናት ለአሥር ጊዜ  ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የሚለው ሰም ተቀይሮ፣ አንደኛውና ሁለተኛው ‹የዕድገትና ሽግግር ዕቅድ› የሚል ስያሜ ተጠቅመዋል፡፡ ምነው ግለሰብ እንኳን ስሙን ለመቀየር በጋዜጣ ማሳወጅ አለበት ይባል የለም እንዴ? ላለፉት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ያላመዱትን ስያሜ እንደ ዋዛ አውጥተው ሊጥሉት ፈለጉ፡፡ የአገሪቱን መሪዎች ማኖ አስነክተው እነሱ በጓዳ ስም የሚቀይሩት ለምንድነው? ‹ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ› ይላል ያገሬ ሰው፡፡

ሽግግርና ትራንስፎርሜሽን እኩል አይደሉም፡፡ አንዱ አዝጋሚ ለውጥ ነው፣ ሌላው ፈጣን ለውጥ ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ትርጉማቸውም ሽግግር ‹ትራንዚሽን› ነው፡፡ ትራንስፎርሜሽን የሚስተካከለው አንድ የአማርኛ ቃል የለም፡፡ ከሽግግር ጠንከር ያለ ሆኖ ሰፋ  ያለ መልዕክት ያለው ነው፡፡ መሠረታዊ የይዘትና የቅርፅ ለውጥ መምጣቱን የሚያመለክት ነው፡፡ ስለሆነም ባሻ ጊዜ ተነስቶ ምክንያቱን ሳይገልጹ ሕዝብ የለመደውን የዕድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅድ ‹ዕድገትና ሽግግር› ብሎ መጥራት አይቻልም፡፡ የእንግሊዝኛውን ስያሜስ በትራንዚሽን ይቀይሩታል? ወይስ ሺሕ ጊዜ ትራንስፎርሜሽን ይል የነበረ ፈረንጅ እንዳይሳለቅ እንዳለ ይተውታል?

 

እንደወረደ ለመቅዳትና ለመገልበጥ የታለመውን የእንግሊዙን የግለ ነፃነት ወይም ሊበራሊዝም የ18ኛ ክፍለ ዘመን ታላቁ ትራንስፎርሜሽንን ከተረዳን፣ የእኛው ስያሜ ስሙና ምግባሩ የማይመሳሰሉ ከንቱ ምኞት መሆኑን ለመረዳት የአፍታ ጊዜም አይወስድብንም፡፡

የኢንዱስትሪ አብዮት መካሄድ፣ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መመሥረት፣ በአውሮፓ የብሔራዊ መንግሥታት አደረጃጀት አንድ ወጥ ፖለቲካዊ ቅርፅ መያዝ፣ የታላቁ ትራንስፎርሜሽን እንቅስቃሴ፣ በእንግሊዝና በአውሮፓ በአሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን በተመሳሳይ ወቅት የተከናወኑ ክስተቶችና አንዱ ከሌላው ጋር በጣም የተሳሰሩ ተነጣጥለው የማይታዩ ነገሮችናቸው፡፡

ካርል ፖላኒ የተባሉ የሐንጋሪ ተወላጅና አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው የፖለቲካ ኢኮኖሚስት እ.ኤ.አ. በ1944 ‹ታላቁ ትራንስፎርሜሽን› በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሐፍ፣ በኢኮኖሚክስ ሥነ ጽሑፎች ውስጥ ከፍ ያለ ሥፍራ የሚሰጠው ሆኗል፡፡

ይህ መጽሐፍ በእንግሊዝ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት በጀመረበት ወቅት የተካሄደውን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ነውጥ ያትታል፡፡ እንደ ጸሐፊው አመለካት የገበያ ኢኮኖሚና የአውሮፓ ብሔራዊ መንግሥታት ወይም አገሮች አፈጣጠር ተለያይተው የሚታዩ ነገሮች ሳይሆኑ፣ በገበያ ማኅበረሰብ (Market Society) አፈጣጠር ውስጥ የፈለቁ የተያያዙ ክስተቶች ናቸው፡፡ አዲስ የተፈጠሩት ብሔራዊ መንግሥታት በገበያ ማኅበራዊ አወቃቀሩ ላይና በሕዝቡ አመለካት ላይ ተፅዕኖ አሳድረው ለውጡን ወደ ፊት ማራመድ የቻሉ ጠንካራ ኃይሎች ነበሩ፡፡ 

በነፃ ገበያ ኢኮኖሚና በገበያ ማኅበረሰብ (Market Society) መፈጠር ምክንያት፣ የሰው ልጆች የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ተለውጧል፡፡ ቀድሞ የነበረው ልማዳዊ ማኅበረሰባዊ አደረጃጀትም ተደምስሶ በምትኩ አዲስ የገበያ ማኅበረሰባዊ አደረጃጀት ተተክቷል፡፡

ከገበያ ማኅበረሰብ በፊት መሬትና የሰው ጉልበት የመሳሰሉት የምርት ግብረ ኃይሎች ይዞታ፣ እንደዚሁም ምርት የማምረትና የመከፋፈል ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በጎሳ መሪዎች ወይም በባላባቶች የተያዙ ሲሆን፣ ምርት የማምረት ተግባር በቤተሰብ ደረጃ ሆኖ የቤተሰብ አባላት የሚያመርቱት ለቤተሰቡ የጋራ ፍጆታ ነበር፡፡ የሀብት ዝውውርም በሥጦታና በውለታ መላሽነት አግባብ የሚከናወኑ ነበሩ፡፡

በእነዚህ ዘመናት ገበያ በማኅበራዊ ኑሮ ዘዴ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ አልነበረውም፡፡ የሸቀጦች ዋጋ የሚወሰነውም በገበያ መስተጋብር አልነበረም፡፡ ሰው ራሱ ለረጅም ዘመን በኮንትራት ውል የታሰረና ከውሉ የመውጣት ነፃነት የሌለው ሆኖ፣ ኢኮኖሚው ነፃ ሊሆን አይችልም ነበር፡፡

ከነፃ ገበያ ኢኮኖሚ፣ ከኢንዱስትሪ አብዮት፣ ከብሔራዊ መንግሥታት አፈጣጠርና ከታላቁ ትራንስፎርሜሽን የገበያ ማኅበረሰብ ለውጥ በፊት የነበረው የሕዝቦች ኮንትራታዊ ውል የኑሮ ሥርዓት ሦስት የማዕዘን ድንጋዮች ነበሩት፡፡

በአለቃ የገቢ ክፍፍል ሥርዓት

ምርትና ንግድ የሚያተኩረው የጎሳ መሪ ወይም ባላባት በሆነ ማዕከላዊ አስተዳደር ነበር፡፡ ይህ ሥርዓት በኢትዮጵያ በነገሥታቱ ዘመን የነበረና ጭሰኛ ገበሬው ያረሰውን ለባላባቱ አስረክቦ ከባላባቱ ሲሶውን ተቀብሎ የሚሄድበት ዘመን ሲሆን፣ ደርግ መሬት ለአራሹን በማወጅ ቢያስቀረውም የገበያ ማኅበረሰብን አልፈጠረም፡፡ መሬትን የመንግሥት በማድረግ የባላባቱንና የጭሰኛውን ኮንትራታዊ ውል አፍርሶ፣ በምትኩ ሌላ የገበሬና የመንግሥት ኮንትራታዊ ውል መሠረተ፡፡ ገበሬው ያመረተውን ለመንግሥት ንግድ ድርጅት መንግሥት በወሰነው ዋጋ የማቅረብ ኮንትራታዊ ውል ጭኖበት ነበር፡፡

ሌላው ምሳሌ ደርግ አጠፋው እንጂ በአፄዎቹ ዘመን ሲሶ የሚሆነው የአገር ንብረት የቤተ ክህነት ነው ተብሎ አብዛኞቹ የአራት ኪሎ ሕንፃዎች በቤተ ክህነት የተያዙ ኮንትራታዊ ውሎች ነበሩ፡፡ ቤተ ክህነትም የዕለት ገቢና ምንዳ ለአባሎቿ ታከፋፍል ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን የገጠርና ከተማ መሬትን ጨምሮ መንግሥት የሚያስተዳድራቸው የሕዝብ ማምረቻ ድርጅቶችና ንብረቶች ሁሉ ከገበያ ሥርዓት ውጪ የሆኑ ኮንትራታዊ ውሎች ናቸው፡፡ ዛሬም የገበያ ማኅበረሰብ አልተፈጠረም፣ ትራንስፎርሜሽንም አልተካሄደም፡፡ መንግሥት ዘይት አስመጪና አከፋፋይ፣ ስኳር አምራችና አከፋፋይ፣ መኪና አምራችና አከፋፋይ፣ ብር ለግለሰቦች አበዳሪ ንግድ ባንክ፣ ለወጣቱ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ሲሆን፣ የመንግሥትና የሕዝብ ኮንትራታዊ ውል ጠንክሮ የነፃ ገበያን ሚና አንሷል፡፡

የውለታ መላሽነት ሥርዓት

ምርትና የምርት ልውውጥ የሚካሄደው በውለታ መላሽነት መርህ ነበር፡፡ አሁን ድረስ ገበሬው የዘር እህል እንኳ ሲያጥረው ለከርሞ ለመመለስ ከባልንጀራው ተውሶ ይዘራል እንጂ ከገበያ አይገዛም፡፡ አዛውንቶችና አቅመ ደካማ ወላጆች የሚጦሩት በልጆቻቸው ነው፡፡ የታመመ መጠየቅ፣ የሞተን መቅበር፣ ወዘተ. የውለታ ክፍያ ኮንትራታዊ ውሎች ናቸው፡፡ የሰው ድግስ በልቼ እኔ ሳላበላ እንዳልቀር አግባና ወይም አግቢና ደግሼ ላብላ ይላሉ ወላጆች፡፡ ድግስ መብላትና ደግሶ ማብላት ባህላዊ ኮንትራታዊ ውል ነው፡፡

ቤተሰባዊ የጋራነት ሥርዓት

አምራችነት በቤተሰብ ደረጃ ሆኖ ፍጆታም የጋራ የሆነበት ሥርዓት ነው፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ባል፣ ሚስት፣ የደረሰ ልጅ የእኔ የሚሉት የግል ንብረትና ምርት የላቸውም፡፡ ሁሉም ሠርተው በጋራ ነው የሚጠቀሙት፡፡ በከተማም የቤት እመቤቶች የራሳቸው ገቢ የላቸውም፡፡ የባል ከቤት ውጭ መሥራትና የሚስት በቤት ውስጥ መሥራት ቤተሰባዊ ኮንትራታዊ ውሎች ናቸው፡፡ ሚስቶች የራሳቸው የሆነ ገቢ የላቸውም፡፡ ለምግባቸው፣ ለልብሳቸውና ለሌሎችም ወጪዎቻቸው የባሎቻቸው ጥገኛ ናቸው፡፡ ባልም ደመወዙ የብቻው አይደለም፣ የቤተሰቡ የጋራ ነው፡፡

አንድ ሰው በገቢው አምስት ሰዎች ቢያስተዳድር ገቢው ባደገ ቁጥር የአምስት ሰዎች እንጀራ ፍላጎት ይጨምራል፡፡ የልብስ ፍላጎት ይጨምራል፡፡ የጫማ ፍላጎት ይጨምራል፡፡ የመዋቢያ ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ስለዚህም የአንድ ሰው ገቢ በማደጉ የአገር ሀብት የአምስት ሰው እንጀራ፣ የአምስት ሰው ልብስ፣ የአምስት ሰው ጫማና የአምስት ሰው መዋቢያ ለማምረት ይደለደላል፡፡ ይህም የነበረው የምርት ፍላጎት፣ ምርትና የምርት አደረጃጀት ሳይቀየር፣ በሌላ ሳይተካ፣ አዲስ ዓይነት ምርት ሳይመረትና ቴክኖሎጂ ሳይሻሻል ለብዙ ጊዜ እንዲቆይ ያደርጋል፡፡

በምዕራቡ ዓለም በገበያ ማኅበረሰብ መፈጠር ምክንያት ይህ ሁኔታ ተቀይሮ ሸቀጦች በነፃ ገበያና በገበያ ዋጋ የሚሸጡ ሆኑ፡፡ የማኅበራዊ ኑሮ ዘዴዎችና ተቋሞቻቸውም ተለወጡ፡፡ ሰዎችም በሚያወጡት ገንዘብ ልክ ከፍተኛ እርካታ የሚሰጣቸውን መርጠው መሸመትና ጥቅማቸውን የላቀ ለማድረግ አዋቂነት የተሞላበት የኢኮኖሚ ውሳኔ መወሰን ጀመሩ፡፡ የአንድ ሰው ገቢው የራሱ ነው፡፡ ከልጆች በቀር ማንም አይጋራውም፡፡ ለራሱ ለፈለገው ነገር የምርጫውን ጠቀሜታ በዋጋ እየለካና እያወዳደረ ያወጣል፡፡ ገቢው ሲጨምር አሮጌውን እየተወ የአዲስ ምርት ፍላጎት ያድርበታል፡፡

የካፒታሊስት ተቋማት የቀየሩት የኢኮኖሚ ሕጎችን ብቻ ሳይሆን፣ የሰዎችን የኢኮኖሚ አስተሳሰብም ነው፡፡ ለትራንስፎርሜሽን የቁስ አካላዊ ሀብት ዓይነት ብቻ ሳይሆን፣ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤና አመለካከታቸውም መቀየር አለበት፡፡

የገበያ ማኅበረሰብ ለዘመናት ፀንተው ከቆዩት ማኅበራዊ አደረጃጀቶች በሦስት ዋና መንገዶች ይለያል፡፡ አንዱ ሰው በፈለገው ቦታ የፈለገውን ሥራ ለመሥራት ነፃ ይወጣል፡፡ ሁለተኛው በሚያገኘው ገቢ ለራሱ ብቻ ወይም ለራሱና ለሕፃናት ልጆቹ ብቻ በሚሰጠው እርካታ ለክቶ የላቀ ጥቅም ለሚያገኝበት መርጦ በመክፈል ይገዛል፡፡ ሦስተኛው የምርት ዋጋ የሚወሰነው  በፍላጎትና በአቅርቦት መስተጋብር እንጂ በሌላ ዋጋ ተማኝ አካል አይደለም፡፡

ይህ ዓይነት የገበያ ማኅበረሰብ መኖር ለትራንስፎርሜሽን ቅድመ ሁኔታም ነው፡፡ በትራንስፎርሜሽን አሮጌ ሸቀጦች ከገበያ ወጥተው አዳዲስ ሸቀጦች ወደ ገበያ ይገባሉ፡፡ ይህንን በነፃነት የሚወስነውና አምራቹን የሚያዘውም ምርጫ አድራጊ ግለሰብ የገበያ ሸማች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን እስካሁን ድረስ ከልማዳዊና ባህላዊ አደረጃጀቶቹ ሙሉ በሙሉ ነፃ አልወጣችም፡፡ የውለታ መላሽነትና ቤተሰባዊ የጋራነት አዝጋሚ ለውጥ ቢያመጡም፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ኮንትራታዊ ውል የባሰ ጠንክሮ ሥር ሰዶ የገበያ ማኅበረሰብ እንዳይፈጠር አድርጓል፡፡

ሰዎች በኮንትራታዊ ውል ቀንበር ሥር ሲውሉ የሥራ ተነሳሽነትን ያጣሉ፣ የማሰብ አቅማቸው ይዳከማል፣ የፈጠራ ችሎታቸውም ይቀንሳል፡፡ ለሕዝቡ የሚበጀውን የሚያውቀው መንግሥት ከሆነ የግለሰቡ፣ የራሱና የገበያው ሥራ ድርሻ ትንሽ ነው፡፡ ከአንድ መጽሔት እንዳነበብኩት በሲንጋፖር አንድ እምነት አለ፡፡ የሚሠራን ሰው ከአገዝከው ሳይሠራ እንዲሞት ታደርገዋለህ›› ይላል፡፡ በጥቂት እኔ ላስብላችሁ ባይ ግለሰቦች የስንቱ ወጣት ወርቃማ ጭንቅላት ቦዝኖ መና ሆነ? ነፈዘ፡፡ ስንቱ ከነእውቀቱ ተቀበረ፡፡

የቱሪስት መስህቦቻችንን የምናስተዋውቅበት ቋንቋ አጣን፡፡ ስለአረንጓዴው ወርቃችን (ቡናችን) ለዓለም ሕዝብ የሚናገር ጠፍቶ የኤክስፖርት ገበያችን ሞተ፡፡ ዛሬ በድጋፍ ኃይል በዓለም አቀፍ ደረጃ ኤክስፖርተር ነን ያሉ ትናንት ማንና ምን እንደነበሩ ለራሳቸውም ሳይገርማቸው አይቀርም፡፡ ገበያና ውድድር ሞተው ከተቀበሩ ውሎ አድሯል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት አረንቋ ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ባለችበት ሁኔታ ስለትራንስፎርሜሽን ማሰብ ዘበትና ከንቱ ውዳሴ ነው፡፡ የአቃጆቹ በጓዳ ስም ቀይረን ሳይመሽ በጊዜ ከቅሌት እናምልጥም፣ ‹ገበያ ወጥቶ የሰው ዓይን ፈርቶ› እንደሚባለው ተረት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]   ማግኘት ይቻላል፡፡      

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...