Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ተመረጡ

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ተመረጡ

ቀን:

ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከተማ በተካሄደው የዓለም ጤና ድርጅት ጉባዔ፣ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ተመረጡ፡፡

185 አገሮች በተሳተፉበትና ድምፅ በሰጡበት የምርጫ ሥነ ሥርዓት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴድሮስ በመጀመሪያው ዙር 95 ድምፅ፣ እንግሊዛዊው ዶ/ር ዴቪድ ናባሮ 52 ድምፅ፣ ፓኪስታናዊቷ ዶ/ር ሳኒያ ኒሽታር ደግሞ 38 ድምፅ በማግኘታቸው፣ ዶ/ር ቴድሮስና ዶ/ር ናባሮ ወደ ሁለተኛው ዙር አልፈዋል፡፡

ፓኪስታናዊቷ ሳኒያ ኒሽታር በመጀመርያው ዙር ከውድድሩ ውጪ ሲሆኑ፣ በሁለተኛው ዙር በተደረገው የድምፅ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓትም ዶ/ር ቴድሮስ 121 ድምፅ፣ እንግሊዛዊው ዶ/ር ናባሮ ደግሞ 62 ድምፅ በማግኘት ሁለት – ሦስተኛ በሚባለው የድምፅ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት መሠረት ወደ ሦስተኛ ዙር ተሸጋግረዋል፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ በሦስተኛው ዙር 133 ድምፅ በማግኘት ሲያሸንፉ፣ እንግሊዛዊው ዶ/ር ናባሮ 50 ድምፅ በማግኘት ከፉክክሩ ተሰናብተዋል፡፡

የ185 አገሮች የጤና ጥበቃ ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በ70ኛው የጄኔቯ የዓለም ጤና ድርጅት ጉባዔ ላይ በተካሄደው የዋና ዳይሬክተርነት የምረጡኝ ቅስቀሳ፣ ዶ/ር ቴድሮስ ለሰው ልጆች የጤና ችግር የሆኑትን ተላላፊ በሽታዎች ማለትም እስከ ኢቦላ ድረስ ያሉትን ለመዋጋት፣ ለመከላከልና ብሎም ለማጥፋት ቃል ገብተዋል፡፡ በሁለት ዓመታት የምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅትም በዓለም ጤና ድርጅት የተለየ ሐሳብና አተያይ በማምጣት አሁን ያለውን የዓለም ጤና ሥርዓት እንደሚለውጡት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል፡፡  

በአብዛኛው በኢትዮጵያውያን ድጋፍ ታጅበው እዚህ የደረሱት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ከምርጫ ሥነ ሥርዓቱ ቀደም ብሎ አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በጉባዔው ላይ ተገኝቶ እንዳይመረጡ ጮክ ብሎ ተናግሮ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአፍሪካ ኅብረትና በኢትዮጵያ መንግሥት አማካይነት ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ዕጩ ሆነው የቀረቡት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ግብፅን ጨምሮ የተለያዩ የእስያና የፓስፊክ አገሮችን ድጋፍ በማግኘት ለአሸናፊነት መብቃታቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ በአገሪቱ ኮሌራ መከሰቱን  ይፋ አላደረጉም በማለት በቅርቡ ኒውዮርክ ታይምስ ማስነበቡ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ዘገባው በውጤታቸው ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ውጤት አላመጣም፡፡

በስድስት ተፎካካሪ ግለሰቦች ተጀምሮ የነበረው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የምርጫ ቅስቀሳ በመጨረሻ ሦስት ተፎካካሪዎችን አስቀርቶ፣ ፍፃሜውን ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት ላይ በጄኔቭ አድርጓል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ባገለገሉበት ወቅት ደሃ አገር የጤና ኢንሹራንስ መስጠት እንደሚችል ያሳዩ መሪ በመሆናቸው፣ አሁን ለመመረጣቸው እንደ አንድ በጎ ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ዓመታዊ በጀቱ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር እንደማይበልጥ የሚነገር ሲሆን፣ ዋና የፋይናንስ ምንጩ አባል አገሮች የሚያዋጡት ገንዘብ ነው፡፡ በዋናነት የአሜሪካ መንግሥት በጀቱን እንደሚሸፍን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅትን በዋና ዳይሬክተርነት መምራት የሚጀምሩት እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ጀምሮ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ተሰናባቿ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቻይናዊቷን ማርጋሬት ቻን የሚተኩት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ከፊታቸው በርካታ ሥራዎች እንደሚጠብቋቸውና በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንደሚፈተኑ ይጠበቃል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትን በዋና ዳይሬክተርነት ለመምራት ከአፍሪካ የመጀመሪያው ቢሆኑም፣ ከዚህ ቀደም የግሎባል ፈንድን በሊቀመንበርነት ከመምራታቸውም በተጨማሪ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን በመምራት ልምዳቸው ደግሞ ይህንን ኃላፊነት በስኬት ሊወጡት እንደሚችሉም የሚናገሩ አሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...