Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሸገር ትራንስፖርት የመንግሥት ድጎማ እንዲፈቀድለት ጠየቀ

ሸገር ትራንስፖርት የመንግሥት ድጎማ እንዲፈቀድለት ጠየቀ

ቀን:

  • በ100 አውቶቡሶች የተማሪዎች ትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚጀምር አስታውቋል

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚተዳደረውና የመንግሥት የልማት ድርጅት የሆነው ሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ምንም እንኳ ራሱን ችሎ በራሱ ፋይናንስ እንዲንቀሳቀስ በመንግሥት ቢቋቋምም ከታሪፍ አነስተኛነት፣ ከሚሸፍናቸው መስመሮች የአዋጭነት ችግር፣ ከወጪ፣ እንዲሁም በዓለም ላይ ከሚታየው ተሞክሮና ከመሳሰሉት ነጥቦች አኳያ በመንግሥት ድጎማ መሥራት ሊፈቀድለት እንደሚገባ ጠየቀ፡፡

      ከአንድ ዓመት በፊት በ2.6 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት ድርጅት፣ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት በ260 አውቶቡሶች የፈጣንና መደበኛ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠም ቢሆንም፣ ድርጅቱ በራሱ ገንዘብ እንዲሠራ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነ የገለጹት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጎይትኦም ኃይሉ ናቸው፡፡ ሸገር ትራንስፖርት ሥራ የጀመረበትን አንደኛ ዓመት በማስመልከት ባካሄው ዓውደ ጥናት ወቅት ዋና ሥራ አስኪያጁ እንደጠቀሱት፣ በየትኛውም የሠለጠነ አገር ውስጥም ቢሆን የከተማ ብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት በድጎማ የሚሠራበት ዘርፍ በመሆኑ መንግሥት ይህንን መቀየር እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሸገር በራሱ ገንዘብ እንዲሠራ መደረጉ ስህተት ነው፡፡ በየትኛውም ዓለም የብዙኃን ትራንስፖርት ያለ ድጎማ አይሠራበትም፤›› ብለዋል፡፡

      በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር በለው ዳኘውም (የሸገር ትራንስፖርት የቦርድ አባል ናቸው) የሸገር ትራንስፖርት ትርፋማነትን ለማስጠበቅ ካስፈለገ በድጎማ እንዲሠራ መፍቀድ፣ ወይም ደግሞ የታሪፍ ማሻሻያ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ባቀረቡት ጽሑፍ ጠቁመዋል፡፡ ተሳታፊዎችም ይህንኑ የድጎማ ጥያቄ ትክክለኛነት አንፀባርቀዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

      ለ300 አውቶቡሶች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሙሉ ክፍያቸውን በመፈጸም መግዛቱን አቶ ጎይትኦም ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት 260 አውቶቡሶችን ተረክቦ በ11 መደበኛ መስመሮችና በ26 የሥራ ሰዓት መውጫና መግቢያ ሰዓቶች ላይ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዚህም በቀን ከ200 ሺሕ በላይ ተሳፋሪዎችን ለማጓጓዝ መብቃቱ ሲገለጽ፣ አንድ ሸገር ባስ በቀን በአማካይ 16 የደርሶ መልስ ምልልስ እንደሚያካሂድ ታውቋል፡፡ አቶ ጎይትኦም እንዳሉት፣ ቀሪዎቹን 40 አውቶቡሶች ለመረከብ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ ሜቴክ ከሳምንት እስከ ሁለት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ አሥር አውቶቡሶችን ገጣጥሞ እያስረከበው እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ አንዱ አውቶቡስ በ3.6 ሚሊዮን ብር መገዛቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

      ዶ/ር በለው ባቀረቡት ጽሑፍ መሠረት፣ በአዲስ አበባ ሰፊ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ዕጥረት ይታያል፡፡ ታክሲዎች፣ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ፣ ሸገር ባስ፣ አሊያንስ ትራንስፖርት፣ እንዲሁም ታክሲዎች የሚሰጡት አገልግሎት ተዳምሮ ከሚፈለገው የትራንስፖርት አቅርቦት ውስጥ 37 በመቶውን ይሸፍናሉ፡፡ በመሆኑም 54 በመቶ የከተማው ነዋሪ በእግሩ ለመጓዝ የሚገደድ እንደሆነና በአንፃሩ በግል ተሽከርካሪዎች አማካይት የሚገለገሉ ነዋሪዎች ቁጥር ከዘጠኝ በመቶ እንደማይበልጥ ተጠቅሷል፡፡

      የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስርፖርት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ አስማረ (የሸገር ትራንስፖርት ቦርድ አመራር) ካቻምና የተደረገ ጥናትን ጠቅሰው እንደተናገሩት፣ በከተማው ውስጥ ከ5.4 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች በየቀኑ የትራንስፖርት ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ እየቀረበ ያለው አገልግሎት ግን ሦስት ሚሊዮን በመሆኑ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የአቅርቦት ክፍተት እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳ ከመነሻው ሸገር ባስ በሚባል መጠሪያ የተየሰሙት አውቶቡሶች በ10 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ እየተዘዋወሩ ከፍተኛ ታሪፋቸው ከ3.50 ብር እንዳይበልጥ በሚል እሳቤ መካከለኛ ገቢ ላላቸው የከተማው ነዋሪዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ታስበው የነበረ ቢሆንም፣ ካለው የትራንስፖርት እጥረትና ከተጠቃሚው ፍላጎት አኳያ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን አቶ ምትኩ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከ1,100 የማይበልጡ አውቶቡሶች አግልግሎት ቢሰጡም፣ አብዛኞቹ ከመስመር ይልቅ ወደ ጋራዥ የሚያደርጉት ምልልስ እየበዛ መምጣቱንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ለከተማው አገልግሎት የሚሰጡ ተጨማሪ 850 አውቶቡሶች ግዥ እየተፈጸመ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ውስጥ 100 አውቶቡሶች ለሸገር ትራንስፖርት ድርጅት የተማሪዎች ትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ቀሪዎቹ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት የሚረከባቸው እንደሆኑም ታውቋል፡፡

ለተማሪዎች የትራንስፖርት አግልግሎት ለመስጠት የሚውሉት 100 አውቶቡሶችን በተመለከተ የከተማ አስተዳደሩ ምን ያህል ገንዘብ እንደመደበ ተጠይቀው፣ መጠኑ ገና አለመወሰኑን ሆኖም ጥያቄ ቀርቦ እንደታመነበትና አስተዳደሩ በቅርቡ ውሳኔ እንደሚሰጥበት አቶ ጎይትኦም ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የከተማው ትራንስፖርት ባለሥልጣን በሚያወጣው ድልድል መሠረት የተመረጡ ትምህርት ቤቶች በመጪው ዓመት አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ከአቶ ጎይትኦም ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር የሸገር ባስ የክፍያ ሥርዓትን ወደ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ካርድ አገልግሎት ለመቀየር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንና በመጪው ክረምት ሊጀመር እንደሚችልም አቶ ምትኩ ይፋ አድርገዋል፡፡ ‹‹ዘመናዊ›› የሚል ሥያሜ የተሰጠው የካርድ የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡

      አዋጭ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ለማቅረብ የእስያ ልማት ባንክ ባስቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት አንድ አውቶቡስ በደርሶ መልስ ምልልስ 70 ሰዎችን በማሳፈር፣ በአንድ ሊትር ነዳጅ ከአራት እስከ 4.5 ኪሎ ሜትር መጓዝ እንደሚጠበቅበት፣ ተሳፋሪዎችም እጅግ ቢበዛ ከ20 ደቂቃ በላይ በየፌርማታው እንዲጠብቁ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን፣ የጉዞ ሽፋንም እስከ 95 በመቶ መድረስ እንደሚገባው ያብራሩት ዶ/ር በለው፣ እነዚህን ደረጃዎች ለማሟላት አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚታዩ ጠቅሰዋል፡፡ የመንገድ አጠቃቀም፣ የመኪኖችና ማደሪያና ማቆሚያ ተርሚናል ችግር፣ የከተማ ትራንስፖርት ዕቅድ አወጣጥና አተገባበር ችግሮችና ሌሎችም የሚፈለገውን የብዙኃን ትራንስፖርት ችግር ለማቅረብ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ናቸው ብለዋል፡፡

      በአገሪቱ የሚመዘገበው የትራፊክ አደጋም ለእንደ ሸገር ላሉ ዘመናዊ አውቶቡሶች ትልቁ ሥጋት ተብሏል፡፡ እንደ ዶ/ር በለው ገለጻ ከሆነ፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በየዓመቱ ከ4,500 በላይ የሞት አደጋ እየተመዘገበ ነው፡፡ አንድ ሚሊዮን በማይሞሉ ተሽከርካሪዎች አማካይነት የሚደርሰው አደጋ በዓለም ከፍተኛው በመሆን ቀጥሏል፡፡ በኢትዮጵያ በ10 ሺሕ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 64 ሰዎች ይገደላሉ፡፡ በአንፃሩ 9.5 ሚሊዮን መኪኖች በሚነዱባት ደቡብ አፍሪካ በ10 ሺሕ መኪኖች የሚደርሰው የሞት አደጋ 14 ብቻ መሆኑን ዶ/ር በለው አስታውሰው፣ እንደ ሸገር ባስ ያሉ ዘመናዊ አውቶቡሶች በኢትዮጵያ በሚያደርጉት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የተለየ መስመር ስላልተዘጋጀላቸውና ከሁሉም ዓይነት ተሽከርካሪዎች ጋር ተደባልቀው መጓዛቸው የአደጋ ሥጋት ቀለበት ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

      የከተማው ትራንስፖርት ባለሥልጣን ግን ሸገር አውቶቡሶች እንደ ከተማ ባቡር ሁሉ የራሳቸው መስመር ተከልሎላቸው የሚሠሩበት የፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት ሊጀመር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡ ከጀሞ-ሜክሲኮ አደባባይ ባለው መስመር የፈጣን አውቶቡስ ትራንዚት አግልግሎት ሊጀመር መታቀዱን አስረድተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...